የቅድስት ሥላሴ ክብረ በዓል በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል በድምቀት ተከብሮ ዋለ።
++++++++++++++++++++++++++++++++++
ጥር 7 ቀን 2014 ዓ/ም
(አዲስ አበባ: ኢትዮጵያ)
የቅድስት ሥላሴ ክብረ በዓል ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት፥ ሊቃውንተ ቤተ ክስርስቲያንና በርካታ ምእመናን በተገኙበት በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል በድምቀት ተከብሮ ውሏል።
በዓውደ ምሕረት መርሐ ግብሩ “ዮም መላእክት ይዬብቡ ወሊቃነ መላእክት ይዜምሩ፤ እስመ መድኅን መጽአ ውስተ ዓለም ለቢሶ ሥጋነ”የሚል ያሬዳዊ ወረብ በሊቃውንት ሲቀርብ፤ በካቴድራሉ ሰንበት ትምህርት ቤት መዘምራን ወይቤላ አብ ለማርያም አምጣንየ አምጣነኪ አዝማንየ አዝማነኪ ማርያም ድንግል ፥ ማርያም ሐቀፍኪዮ ወአመ ወለድኪ ” የሚል ያሬዳዊ ዝማሬ ተዘምሯል።
በመቀጠልም ያካቴድራሉ አስተዳዳሪ ሊቀ ሥልጣናት ቆሞስ አባ ሲራክ አድማሱ ስለ ካትድራሉ ሪፖርት አቅርበዋል። ካቴድራሉ በአጼ ኃይለ ሥላሴ አማካኝነት በ1924 ዓ/ም ተመሥርቶ ግንባታው በ1936 ዓ/ም ተጀምሮ በ1939 ዓ/ም ተጠናቅቆ እስካሁን አገልግሎት ሲሰጥ መቆየቱን ገልጻል።
አሁን ግን ካቴድራሉ የማርጀትና የመሰንጠቅ አደጋ ስላጋጠመው ኮሚቴ ተዋቅሮ በባለሙያ ጥናት መሠረት ዕድሳት እንደሚያስፈልገው ውሳኔ ላይ መድረሳቸውን አብራርተዋል።
በጥናቱ መሠረት የካቴድራሉ ሕንጻና መላ ግቢው ለማደስ ከ80 እስከ 100 ሚልዮን ብር እንደሚያስፈልግ በመግለጽ በውስጥም በውጭም የሚገኙ ምእመናን ለዕድሳቱ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።
ከዚህ በመነሣት በዕለቱ የገቢ ማሰባሰብ መርሐ ግብር ተካሂዶ በርካታ ምእመናን በቀጥታ በመስጠትና ቃል በመግባት ተሳትፎ አድርገዋል፡፡
የካቴድራሉ ዋና ጸሐፊ ላእከ ሰላም ሽታው ብርሃኑ የካቴድራሉ ካህናት አገልጋዮችና የካቴድራሉ ልዩ ልዩ ሠራተኞች ለዕድሳቱ የሚውል የወር ደመወዛቸው መስጠታቸውን ገልጸዋል።
በመጨረሻም ብፁዕ አቡነ ኤልያስ “ሠለስቱ ስም አሐዱ እግዚአብሔር” በሚል መነሻነት ቅድስት ሥላሴን በተመለከተ ሰፉ ያለ ትምህርት በመስጠት ቃለ ምዕዳንና አባታዊ መልአክታቸውን አስተላልፈዋል።
ታቦተ ሕጉም የካቴድራሉ ሕንጻ እስኪጠናቀቅ ድረስ ወደ ቅዱስ በዓለ ወልድ ቤተ ክርስቲያን ገብቷል።
በበዓሉ ሊቃነ ጳጳሳት፥ በርካታ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያንና አንደሰማይ ከዋክብት ደምቀውና አምረው የሚታዩ እጅግ በርካታ የተዋሕዶ ልጆች ምእመናንና ምእመናት ተገኝተዋል።።
ለካቴድራሉ ዕድሳት አስተዋጽኦ ማድረግ ለምትፈልጉ ሁሉ ከታች ባሉ የሒሳብ ቁጥር ማስገባት እንደምትችሉ ልንገልጽላችሁ እንወዳለን፦
1. 10000037786334 የኢ/ያ ንግድ ባንክ።
2. 53431186 አቢሲንያ ባንክ።
3. 7000022335516 ንብ ባንክ።
4. 01320414050300 አዋሽ ባንክ።