“ሆሣዕና ለዳዊት ልጅ በጌታ ስም የሚመጣ የተባረከ ነው” ማቴ. 21፤9
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን
“ሆሣዕና ለዳዊት ልጅ በጌታ ስም የሚመጣ የተባረከ ነው” ማቴ. 21፤9
ስምንተኛ እና የመጨረሻው የዐብይ ጾም ሳምንት ሆሣህና ይባላል፡፡ ሆሣዕና ከዘጠኝ አበይት የጌታ በዓል አንዱ ነው፤ መጠሪያ ስያሜውም በነቢዩ ዘካሪያስ “እነሆ ንጉሥሽ የዋህ ሆኖ በአህያ ላይና በአህያቱ ግልገል በውርንጭላይቱ ላይ ተቀምጦ ወደ አንቺ ይመጣል . . .” ተብሎ የተነገረው ትንቢት ይፈጸም ዘንድ የተነገረው ዘላለማዊ ቃል ነው፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በአህያይቷ እና በውርንጭላይቷ ላይ ተቀምጦ፤ ሕፃናቱ፡- “ሆሣዕና ለዳዊት ልጅ በጌታ ስም የሚመጣ የተባረከ ነው፣ ሆሣዕና በአርያም” እያሉ እያመሰገኑት ወደ ኢየሩሳሌም ቤተ መቅደስ ጉዞ ያደረገበት፤ ትሕትናውን የገለጠበት፤ ይህን ዓለም ከኃጢአት እስራት መፍታቱን በምሳሌ ያስረዳበት ዕለት ነው፡፡ በዚህ ሳምንት የክርስቶስን ነገረ ሕማሙን፣ ስቅለቱን፣ ሞቱን፣ ትንሣኤውን የሚናገሩ ቅዱሳት መጻሕፍት የሚነበቡበት፤ የማዳን ሥራው በሰፊው የሚታወጅት ሳምንት ነው፡፡
ስለሆነም የመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል እንኳን ለ2015 ዓ/ም የሆሣህና በዓል አደረሳችሁ እያለ ከዐቢይ ጾም መጨረሻ ሳምንት ከሆነው ከሆሣዕና በዓል ጀምሮ እስከ ትንሣኤ ድረስ ባሉት ቀናት ውስጥ የሚከበሩትን የጸሎት እና የስግደት በዓል በካቴድራላችን በአካል ተገኝታችሁ ለማክበር ላልቻላችሁ ምዕመናን በሙሉ በካቴድራሉ የዩቱዩብ
https://www.youtube.com/@holytrinitycathedrala.a
እና ፌስ ቡክ ቻናል በቀጥታ የሚያስተላልፍላችሁ ሲሆን እንድትከታተሉ ከወዲሁ እየጋበዝን በሚተላለፉት መንፈሳዊ አገልግሎት በሥጋም በነፍስም እንድትጠቀሙበት እና የካቴድራሉን ማህበራዊ ሚዲያዎችን አባል በመሆን አገልግሎቱን እንድትደግፉ በሥላሴ ስም እንጠይቃለን፡፡
የስላሴ ምህረትና ቸርነት ከሁላችን ጋር ይሁን፡፡
ክብር ለስላሴ!