ቅዱስ ፓትርያርኩ በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል በመገኘት የካቴድራሉ እድሳት የሚገኝበት ደረጃ ጉብኝት አድርገዋል። (መስከረም 2017 ዓ.ም)

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት እና ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት በዛሬው ዕለት በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል በመገኘት የካቴድራሉ እድሳት የሚገኝበትን ደረጃ ጉብኝት አድርገዋል።

በንጉሠ ነገሥት ዐፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት የተገነባው የመንበረ ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ለበርካታ ዓመታት አገልግሎት ሲሰጥ ከቆየ በኋላ በእድሜ ብዛት የካቴድራሉ አንዳንድ ክፍሎች ላይ ጉዳት በመድረሱ ጥር 7/2014 ዓ.ም ታቦተ ሕጉ ወደ መካነ ሥላሴ ቅዱስ በዓለ ወልድ ቤ/ክ በማዘዋወር የካቴድራሉ እድሳት የተጀመረ ሲሆን አሁን ላይም እድሳቱ በመጠናቀቅ ላይ ይገኛል።

የመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴደራል የፓትርያርኮች እና የጳጳሳት በዓለ ሲመት የሚከናወንበት፣ በዕረፍታቸውም ጊዜ የማረፊያ ቦታ የሚገኝበት እንዲሁም ለሀገር ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደረጉ ግለሰቦችና መሪዎች መካነ መቃብር የሚገኝበት ሲሆን በውስጡም ዘመናትን ያስቆጠሩ ቅርሶች ይገኙበታል።