የመ/ጸ/ቅ/ሥላሴ ካቴድራል ስብከተ ወንጌል

መግቢያ፡- ስብከተ ወንጌል ማለት ምን ማለት ነው

ስብከተ ወንጌል ማለት የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ሰው መሆን፣ የሰውን ልጅ ወደ ቀደመ ክብሩ (ልጅነቱ) መመለስ የሚያበሥረውን ቃል ማብሠር፣ ማስተማር፣ ማሳመን….ማለት ነው፡፡ ይኸውም በደመ ወልደ እግዚአብሔር የተዋጀችው ቤተክርስቲየን ዕለት ዕለት የምትታነጽበት ቃል ወንጌል ነው፡፡

የስብከተ ወንጌል ዓላማ

ዋናው የስብከተ ወንጌል ዓላማ ሰው ሁሉ የእግዚአብሔርን መንግሥት ወራሽ እንዲሆን ማድረግ ነው፡፡ ይኸም ሲባል እግዚአብሔር ለሰው ያለውን የማይለወጥ አምላካዊ ፍቅሩን በመስቀል ላይ ቤዛ ሆኖ መግለጹን ማሳየት፡፡ ዮሐ. 3፣16
ለዘለዓለማዊ ክብርና ሕይወት ወራሽነት ማብቃት፣ የሰዎችን ልብ ከክፋት ወደ በጐነት በስብከት መለወጥ ነው፡፡ 2ኛ ቆሮ. 1ዐ፣3-6

የስብከተወንጌል ጥቅም

በፈጣሪው አርዓያ በእግዚአብሔር የተፈጠረው ሰው ፈጣሪውን አውቆ በማመንና በትእዛዙ በመሄድ ለዘለዓለም ሕያው ሆኖ የሚኖረው በወንጌል ቃል ሕይወቱ ሲገነባ ነው፡፡ ለዚህም ነው “ይህን የማይለወጥ የዘለዓለም ድኅነት ቅዱስ ወንጌል ከፀሐይ መውጫ እስከ መጥለቂያው ድረስ በሐዋርያት እጅ የላከው” ማር. 16፣8

  • ስለዚህ ስብከተ ወንጌል የቤተክርስቲያን ሕይወት ነው፡፡
  • ስብከተ ወንጌል የቤተክርስቲያን ልማት ነው፡፡
  • ስብከተ ወንጌል የቤተክርስቲያን ሁለንተናዊ እድገት ነው፡፡

የስብከተ ወንጌል ታሪክ

ስብከተወንጌል እንዲጠናከር ምን መደረግ አለበት

ስብከተወንጌል የቤተክርስቲያኗ ሕይወት ነው፣ ሁሉ ነገር ደግሞ ቅድሚያ ለሕይወት ደኅንነት ነው፡፡ ስለዚህ፡-

  • ለአገልግሎቱ በቂ ዕውቀት ያላቸው መምህራንን ዘመኑ በሚጠይቀው የአገልግሎት ደረጃ አሰልጥኖ በሁሉም ቦታ መመደብ፣
  • ማዕከሉን ያልጠበቀ (የተዘበራረቀ) የስብከተወንጌልን እንቅስቃሴ ወደ ሥርዓት ማስገባት፣
  • በመላዋ ኢትዮጵያ የሚገኙ ካህናትን ደረጃ በደረጃ የግንዛቤና የስብከተወንጌል ተልዕኮ ሥልጠና በመስጠት ሁሉም ለአገልግሎቱ መንፈሳዊ ቅናት እንዲኖራቸው ማድረግ፣ የሙያ ክህሎታቸውን ማሳደግ፣
  • ቤተክርስቲያን ካላት ገቢ ላይ ከፍተኛውን የገንዘብ ኃይል ለዚህ አገልግሎት መመደብ (በጀት መያዝ)፣
  • የምሁራኑን ሞራል መጠበቅ፣
  • በቂ ዕውቀት ሳይኖራቸው፣ ቤተክርስቲያኗ የሙያ ማረጋገጫ ሳትሰጣቸው ራሳቸውን በራሳቸው መምህራን (ሰባክያን) አድርገው ወደ መድረክ የሚወጡትን በመጀመሪያ ወደ ትምህርት ገበታ እንዲገቡ ማድረግ፣
  • እነዚህና ሌሎችም ያልተጠቀሱ ጉዳዮች በጥናትና እቅድ እየተደገፉ ቢሠሩ ስብከተወንጌሉ ከመስፋፋቱና ከመጠናከሩ ቤተክርስቲያኗም በመንፈሳዊ ሕይወቷ ከመለምለሟም ጐን በአገልግሎቱ ላይ እንደእንቅፋትና ፈተና እየሆኑ ያሉ ያለ በቂ ዕውቀት በተለይ በምሥጢረ ሥላሴና በምሥጢረ ሥጋዌ ላይ ያለእውቀት በድፍረት ሕፀፀ አእምሮ እየወለዳቸው ያሉትን ክስተቶች እንዳይከሰቱ በማድረግ የተሻለ ውጤት ይገኛል፡፡

መንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል

ለኢ/ኦ/ተ/ቤክ/ስብከተ ወንጌል መጠናከር ያደረገው አስተዋፅኦ

በካቴድራሉ ቀደም ባሉት ዓመታት እንዴት ይሰጥ እንደነበር

ከካቴድራሉ ሕንጻዊ ሥነጥበብ ጀምሮ የኢ/አ/ተ/ቤ/ከ ልዕልና መገለጫ በሆነው መ/ጸ/ቅ/ሥላሴ ካቴድራል ማዕከልነት ለመላዋ ኢትዮጵያ ይሰጥ የነበረው ስብከተ ወንጌል በወቅቱ “ብሥራተ ወንጌል” በሚል የሬድዮ ፕሮግራም በየቀኑ የሚተላለፉ ትምህርቶችን የሚያዘጋጁ ምሁራንን ያቀፈ የኢ/አ/ተ/ቤ/ክ ሐዋርያዊ ድርጅት በሚል ሥያሜ የተቋቋመው በዚሁ ካቴድራል ውስጥ ሆኖ በመሥራት አቅሙ በፈቀደው መጠን ሐዋርያዊ ተልዕኮውን ሲፈጽም ቆይቷል፡፡
በአሁኑ ጊዜ ያ እንቅስቃሴ በሚገባ ተጠናክሮ በጠቅላይ ቤተክህነት ጽ/ቤት ስብከተወንጌልና ሐዋርያዊ ተልዕኮ ዋና መምሪያ ሆኗል፡፡

አሁን በካቴድራሉ ያለው የስብከተ ወንጌል ልዩ ልዩ መርሐግብር

ከላይ እንደተገለጸው ከጥንት ጀምሮ የስብከተ ወንጌል ማዕከል የሆነው ካቴድራል የቤተክርስቲያኗን ሥርዓተ አስተምህሮ ሳይለቅ የዘመኑን ስልትና የትምህርት አቀራረብ ዘዴ በመጠቀም የስብከተ ወንጌል አገለግሎቱ ከዚህ በሚከተለው መልኩ ተጠናክሮ እና ተስፋፍቶ በመሰጠት ላይ ይገኛል፡፡

  • 1. የየዕለት መርሐግብር

ከወር እስከ ወር ከዓመት እስከ ዓመት ድረስ ለሚሰጠው ትምህርተ ወንጌል በየቀኑ መደበኛ መምህራን ተመድበው ከሌላም ቦታ የሚያስተምሩ ብቃት እና ጥራት ያላቸው መምህራን ተጋብዘው በየቀኑ ትምህርቱ ከቀኑ 11፡ዐዐ-1፡ዐዐ ሰዓት ድረስ ይሰጣል፡፡

  • 2. የዕለተ ሰንበት

በየሳምንቱ በዕለተ እሑድ ለቦታውም ጭምር ከፍተኛ ፍቅር ያላቸው እጅግ ታላላቅና እምነተ ጠንካራ ምእመናን በብዛት በጸሎተ ቅዳሴውና በትምህርቱ ላይ የሚገኙበት በመሆኑ በብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፣ በሊቀ ሥልጣናቱና በካቴድራሉ ምሁራን መደበኛ ሰባክያነ ወንጌል የምእመኑን መንፈስ በሚያረካ ሁኔታ እየተሰጠ ይገኛል፡፡ 3. በመዋዕለ ጾም በታላቁ (ዐቢይ) ጾም እና በጾመ ፍልሰታ ለማርያም ከቀኑ 5.3ዐ-6፡3ዐ ያለው ሰዓት የስብከተ ወንጌል ነው፡፡ በዚህ ጾሙ ተጀምሮ እስከ ሚፈጸም ድረስ በየቀኑ የትምህርት አርእስቶች ወጥተው ብቃቱ ያላቸው የቦታው መምህራነ ወንጌል እንዲሁም ከጠቅ ላይ ቤተክህነትና ከመንፈሳዊያን ኮሌጆች ተመድበው በብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ጭምር ትምህርቱ ይሰጣል፡፡

3. በመዋዕለ ጾም

በታላቁ (ዐቢይ) ጾም እና በጾመ ፍልሰታ ለማርያም ከቀኑ 5.3ዐ-6፡3ዐ ያለው ሰዓት የስብከተ ወንጌል ነው፡፡ በዚህ ጾሙ ተጀምሮ እስከ ሚፈጸም ድረስ በየቀኑ የትምህርት አርእስቶች ወጥተው ብቃቱ ያላቸው የቦታው መምህራነ ወንጌል እንዲሁም ከጠቅ ላይ ቤተክህነትና ከመንፈሳዊያን ኮሌጆች ተመድበው በብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ጭምር ትምህርቱ ይሰጣል፡፡

  • 4. በወርኃዊያን በዓላት

በወርኃዊያን በዓላት ሕዝበ ክርስቲያኑ በብዛት ወደ ቤተክርስቲያን የሚጐርፍበት መሆኑ ይታወቃል፡፡ የሕዝቡን ብዛትና ሃይማኖታዊ አመጣጥ በማሰብ የስብከተ ወንጌል ክፍሉ ሃይማኖቱ ለሰበሰበው ሕዝብ ምን ትምህርት መሰጠት እና እግዚአብሔርን በመዝሙር እንዴት ማመስገን እንዳለበት በሰፊው በመዘጋጀት ከቀኑ 1ዐ እስከ ምሽቱ 1፡3ዐ ሰዓት ድረስ ይሰጣል፡፡

  • 5. ዓመታዊያን እና ልዩ ልዩ ጉባዔያት

ዓመታዊ በዓለ ንግሥን አስመልክቶ እና ለትምህርተ ወንጌል ተብሎ በእቅድ ተይዘው የሚሠሩ የትምህርት ጉባዔያት ከሌላው ቀን ለየት ባለ መልኩ የሚካሄደው አስደሳች የካቴድራሉ የስብከተ ወንጌል አገልግሎት ነው፡፡ ይህ በይዘቱም ብዙ መርሐ ግብሮችን የሚያቅፍ ስለሆነ ከቀኑ 9፡3ዐ-1፡3ዐ ሰዓት የሚፈጅ መርሐ ግብር ነው የሚካሄደው፡፡
በተጨማሪም በክርስቲያኖች ሥርዓተ ጋብቻ ላይ የሚሰጠው ስብከተ ወንጌል በጸሎተ ሙታን ጊዜም ሁሉ እየተሰጠ ባለው ትምህርት ተጋቢዎች ተደስተው ኀዘንተኞች በእግዚአብሔር ተጽናንተው እግዚአብሔርን እያመሰገኑ ይገኛሉ፡፡
እንዲሁም በዚህ ድህረ ገጽ ለምትጠቀሙ የስብከተወንጌል ክፍሉ ከላይ ከተዘረዘሩት በተጨማሪ፡-

  • 1. መሠረታዊ የቤተክርስቲያኗን ትምህርት፣
  • 2. የቤተክርስቲያንን ታሪክ፣
  • 3. ወቅቱን የተመለከተ ትምህርት የምናስተላልፍ መሆኑን እንገልፃለን፡፡

ልዑል እግዚአብሔር አገልግሎታችን ይባርክልን አሜን