አውደ ወራዙት (ወጣትነት በቤተክርስቲያን)
“ልጆቻችሁ በጐልማሳነታቸው እንደአትክልት አደጉ ፡፡ ሴቶች ልጆቻችሁም በግንብ ሥር እንዳለ አንደተወቀረ የማዕዘን ዐምድ ይሆኑ ዘንድ” መዝ.4 ፡ 02
- 1. ወጣትነት ምንድን ነው;
ወጣትነት የሚለው ቃል ታላቅና ለጆሮ የሚያስደስት ቃል ነው፡፡ ወጣትነት በሰው ልጅ እድሜ ቀመር የእሳትነት ወቅት የሚባልው ሲሆን በቤተክርስቲያናችን አስተምህሮ ከ15 እስከ 50 ወይም ከ20 እስከ 40 ዓመት ያለውን እድሜ ክልል ያጠቃልላል፡፡ በኢትጵያ ህግ መሠረት ደግሞ ከ 18 ዓመት በላይ ከ 40 ዓመት በታች ያለው የወጣትነት ዘመን ይባላል፡፡ ወጣቶች በአትክልት ውስጥ እንደሚገኙ አበቦችና እንደ ጥዋት ፀሐይ ጮራ ናቸው፡፡ የወጣትነት ዘመን በሰው ልጆች ሕይወት ውስጥ የተሻለው ተፈላጊ ምርጥ ጊዜ ነው፡፡
በሰው ልጆች ህይወት ውስጥ የጥፋት ጨለማ ተወግዶ ብርሃን፤ እንዲሁም ቁንጅናም ሊታይ – የሚችለው በወጣትነት ነው፡፡፡ የወጣትነት ዘመን ሰው እውነተኛ ጠባዩን ፤ባሕርዩንና ተግባሩን የሚገነባበት፤ በሰዓቱ የሚጠናቀቅበትና ሳይመለስ የሚያልፈው ደቂቃው እንዳያመልጠው የሚገነዘብበት ጊዜ ነው፡፡ ወጣቶች በጊዜያቸው ቢሠሩ ያከናውናሉ፤ ቢናገሩ ያሳምራሉ፤ ቢነሡ የጀመሩትን ዳር ያደርሳሉ፤ ቢጣሩ ይሰማሉ፡፡ ወጣቶች ቤተክርስቲያንና በጠቅላላ የሰዎች ልጆች ማኀበራዊ አቋሞች የሚደገፉባቸው አዕማድ ናቸው፡፡ ወጣቶች በአባቶቻቸው ሥፍራ የሚተኩ ቤተሰብን፤ ቤተክርስቲያንንና አገርን የሚዋጉትን ክፋቶች የሚቋቋሙ ጠንካራ ኃይላት ናቸው፡፡ ወጣቶች በህይወታቸው አስተዋዮች፣ ደፋሮችና አሸናፊዎች፣ በውስጣቸው ዕውቀትን ብልሃትን ፍልስፍናን የያዙና፤ ስለ ደኀና ኑሮ በውስጣቸው የሚቃጠሉ የኅብረተሰብ ክፍሎች ናቸው፡፡
በቅዱስ መጽሐፍ ሀዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ወጣቱንና ደቀመዝሙሩን ጢሞቴዎስን እንዲህ ይለዋል “ማንም ሕፃንነትህን ወይም ወጣትነትህን አይናቀው ነገር ግን ለምእመናን ምሳሌ ሁን፡፡» ጢሞ 4 ፡02. ከዚህ እንደምንረዳው ወጣትነት ከሕጸንነት ወደ ጉልምስና ወይም እርግና መሸጋገሪያ ድልድይ ነው፡፡
ማንኛውም ሕዝብ በማንኛውም ዘመን የሚያሳየውን አካሄድና እርምጃ የሚታወቀው በወጣቶች አስተሳሰብ ነው:: ወጣቶች በሃይማኖት ክፍልም ሆነ በማህበራዊ አቋም የነገው አባቶችና የወደፊቱን ብርሃን ሰጪዎች ናቸው፡፡ በህብረተሰብ ክፍል ውስጥ ከማንኛውም በላይ በንቃት በብርታት በመሥዋዕትነት በመቆጨት ገስግሦ በመራመድ የሚሠሩ ወጣቶች ናቸው፡፡ ወጣቶች ንጹህ ወገን የሥልጣኔ የዕውቀት ምልክት ለመልካም ነገር ቀናተኞችና የኑሮ መሠረት የሕይወት ምንጮች ኃይሎች ናቸው፡፡ “የጐበዛዝቱ ጌጽ ጉልበታቸው ናት” ምሳ. 1፡19.
ወጣትነት ከሕይወታችን የተወሰነ ዘመን አይደለም:: ነገር ግን የአሰተሳሰብና የመንፈስ ርቀት ጐዳይ ነው፡፡ በእግዚአብሔር ካመንን በነፍስና በስጦታህ ከተማመንን ወጣት ነን:: ለወደፊቱም ከፍ ያለ ተስፋ አለን:: ለመጪው ጊዜ በራስ ተማምነን ካልዳንን በምንም መልክ ወጣት አይደለንም፡፡ ወጣቶች በዕድሜያቸው ሊመዘኑ አይገባም ጉዳዩ የዕድሜ ብዛት ሳይሆን የጤንነት የኃይል የንቃት ምኞት ነው፡፡
መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ወጣትነት፣ በወጣትነት ዘመን መደረግ ስለሚገባችው ነገሮች፣ ብዙ ተብሏል፡፡ ለአብነት ያህል “በወጣትነትህ ወራት ፈጣሪህን አስብ፡፡” መክ 2 ፡1
አንዳንድ ወጣቶች ከእምነት መጻሕፍት በወጣ መልኩ የእግዚአብሔር መኖር የሚያረጋግጡ ማስረጃዎችን ይጠይቃሉ፡፡ አንዳንዶቹ ደግሞ እንስሳ የለመለመ ሳርን አይቶ እንደሚበላ& እንዲሁ ማስረጃ መታየትና መዳበስ አለበት ይላሉ፡፡ ነገር ግን ሰዎች የእንስሳት ባሕርያት ብቻ ያሏቸው አይደሉም፡፡ የማሰብ ችሎታ ስላላቸው አእምሮአቸው የሚያቀርብላቸውን ማሰረጃ ሊጠቀሙበት ይችላሉ፡፡ ለምሳሌ ሰው የመዝሙርን አስደሳችነትና የቅዱሳት ሥዕላትን ቁንጅና የሚረዳውና የሚገነዘበው በአእምሮ ነው፡፡ እንስሳ ግን የሙዚቃን ድምጽ ሰምቶ ወይም ሥዕልን ተመልክቶ መመሰጥ አይችልም፡፡
ስለዚህ ወጣትነት በሚታዩ ቅዱሳት ሥዕላት፣ በሚደመጡ መዝሙራት፣ በሚነበቡ ቅዱሳት መጻሕፍት ቶሎ የሚሳብና ወደ መንፈሳዊም ሆነ ስጋዊ ለውጥ በፍጥነት የሚታይበትና ወደ ተግባር ለመለወጥ የሚቻልበት የእድሜ ክልል ነው፡፡ ባጠቃላይ “ልጆቻችሁ በጐልማሳነታቸው እንደአትክልት አደጉ ፡፡ ሴቶች ልጆቻችሁም በግንብ ሥር እንዳለ አንደተወቀረ የማዕዘን ዐምድ ይሆኑ ዘንድ” መዝ.4 ፡ 02 እንደተባለ ወጣትነት እንደአትክልት በልዩ ኩትኮታ የሚታደግበት በግንብ እንዳለና እንደተወቀረ የማዕዘን ዐምድ የሚኮንበት ወሳኝ የእድሜ ክልል ነው፡፡
- 2. በወጣትነት ዘመን ላይ የተጋረጡ እንቅፋቶች ( ይቀጥላል………..)