ታሪክ
የስብከተወንጌል አጀማመር
- ወንጌልን (የምስራቹን ቃል) መስበክ የጀመረው ራሱ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ ማቴ. 4፣17
በደዌ ሥጋ የታሠሩትን በመፈወስ በደዌ ኃጢአት የተያዙትን ከኃጢአት በማንፃት የመንግሥቱን ወንጌል ሰበከ፡፡ ሐዋርያትን ሰብስቦ ካስተማራቸው በኋላ ወደ ዓለም ሁሉ እንዲሄዱና ወንጌልን እንዲሰብኩ ያዘዛቸው እሱ ነው፡፡ ማቴ. 28፣19 ማር. 16፣15
ስብከተወንጌል በሐዋርያት ዘመን
ቅዱሳን ሐዋርያት የተሰጣቸውን አምላካዊ ትዕዛዝ በደስታ ተቀብለው የሰው ዘር ባለበት ሁሉ እየሄዱ ቃለ ወንጌልን ሰበኩ፣ በስሙ አጋንንትን አወጡ፣ ድውያንን ፈወሱ፣ ሙታንን አስነሡ፣ የወንጌል ብርሃን በዓለም ሁሉ እንዲበራ አደረጉ፡፡
ስብከተወንጌል በሐዋርያውያን አበው ዘመን
በመድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተመሠረተው በሐዋርያት የተስፋፋው ስብከተ ወንጌል ከሐዋርያት ቀጥለው በተነሡ አበውም በነአግናጥዮስ፣ በነአትናቴዎስ፣ በነዮሐንስ አፈወርቅ፣ በነቅዱስ ቄርሎስ፣ ወ ዘ ተ በሕይወት መስዋዕትነት ጭምር ተሰብኳል፡፡ ይህን ለወደፊቱ በቤተክርስቲያን ታሪክ የትምህርት ዓምድ ይጠብቁን፡፡
ስብከተወንጌል በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን
- ይህን የምሥራች ቃለ ወንጌል ኢትዮጵያ አምና የተቀበለችው ገና በዚየው በኢየሩሳሌም አከባቢ እየተሰበከ በነበረበት ዘመን በ34ኛው ዓመተ ምሕረት መሆኑ በቅዱስ መጽሐፍ ላይ ስለተጻፈ ሁሉም የተረዳው ጉዳይ ነው (ግ/ሐ/8፣26-4ዐ)
በዚህ መሠረት የኢ/አ/ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ዛሬም እንደትናንቱ ወንጌለ መንግሥተ ወልደ እግዚአብሔርን በሐዋርያዊ ትጋት እየሰበከች ትገኛለች
ስብከተወንጌል አሁን ባለንበት ዘመን
አሁን እየኖርንበት ባለው በሀያ አንደኛው ምዕት ዓመት የስብከተወንጌል አገልግሎት በዓለም ዙሪያ ለመቃኘት (ለጠቅላላ ግንዛቤ) በቀጣዩ እንሄድበታለን፡፡ በኛ በኢትዮጵያችን ግን ምን ጊዜም ለኢትዮጵያውያን የዕውቀት መሠረት የሆነችው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ሕንፃ ቤተክርስቲያኑ ባለበት ቦታ ሁሉ (ከሰውና ከፋይናንስ ዕጥረት የተነሣ ከተወሰኑ አካባቢዎች በስተቀር) የስብከተወንጌል አገልግሎት ይካሄዳል፡፡