የዓጋዕዝተ ዓለም ሥላሴ ዓመታዊው በዓል በድምቀት ተከበረ
በመ/ር ዘሩ ብርሃኔ
ጥር 7/2004ዓ.ም.
በየዓመቱ ከልደት ቀጥሎ ጥር 7 ቀን በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ የሚከበረው ዓመታዊው የሥላሴ በዓለ በዚህ ዓመትም በንበረ ፀባኦት ቅድሰት ሥላሴ ካቴድራል ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ፓትርያርክ ዘኢትዮጵያ የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ፕሬዚዳንት የዓለም ሃይማኖቶች ለሰላም የክብር ፕሬዚዳንትና ብፁአን ሊቃነ ጳጳሳት እንዲሁም በብዙ ሽህ የሚቆጠሩ ምዕመናን በተገኙበት እጅግ በጣም በደመቀ ሁኔታ በዓሉ ተከብሮ ውልዋል፡፡
በዓሉ መከበር የጀመረው ከዋዜማው ከጥር 6 ጀምሮ ሲሆን የካቴድራሉ ካህናትና መዘምራን ከዋዜማው ከቀኑ 6 ሰዓት ጀምሮ ለ48 ሰዓታት ሌሊትና ቀኑን ሙሉ ያለ ማቋረጥ ስብሃተ እግዚአብሔር ሲያቀርቡ ውለው አድረዋል፡፡
ይህ መንፈሳዊ አገልግሎት ማለትም ስርዓተ ማህሌተ፣ስርዓተ ቅዳሴ እንዲሁም ሰዓታትና ሰርክ ፀሎት በአጠቃለይ የስርዓተ አምልኮ አፈፃፀም በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ ልዩ በመሆኑ የእምነቱ ተከታዮች ብቻ ሳይሆን ሌሎችንም እጀግ በጣም የሚስደንቅ ነው፡፡
ቀደም ሲል የተከበረው የጌታችን የአምላካችን የመድኀኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ በዓለ ልደት ይህን በመሰለ ሁኔታ የተከበረ ሲሆን በፊታችን በታላቅ ድምቀት በየዓመቱ ጥር 10 እና 11 የሚከበረው የጌታችን የአምላካችን የመድኀኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ በዓለ ጥመቀትም በካቴድራሉ መሪነት ከ11 ታቦታት በላይ በሚያድሩበት በጃን ሜዳ እንደሚከበር የቤ/ክርስቲያኑ አስተዳደር አሳውቋል፡፡