አዲሱ የቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ዋና አስተዳዳሪ ደማቅ አቀባበል ተደረገላቸው
በመ/ር ዘሩ ብርሃኔ
በቅዱስነታቸው መልካም ፈቃድ አማካኝነት ከየካቲት 1 ቀን 2ዐዐ4 ዓ.ም. ጀምሮ የመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ዋና አስተዳዳሪ ሆነው የተሾሙት ክቡር ሊቀ ስልጣናት አባ ገ/ሥላሴ በላይ ሲሆኑ እሁድ የካቲት 4 ቀን 2ዐዐ4 ዓ.ም. የመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ሰበካ ጉባዔ፣ ካህናት፣ መዘምራን፣ የሰንበት ት/ቤት ወጣቶችና የአጥቢየው ምእመናን ደማቅ አቀባበል አድርጐላቸዋል፡፡
በክብረ በዓሉ ላይ ብፁዕ አቡነ አረጋዊ የካቴድራሉ የበላይ ጠባቂና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል፣ የቀድሞ የካቴድራሉ አስተዳዳሪ የነበሩት ሊቀሊቃውንት አባ ጥዑመልሳን ኪ/ማርያም የአሁኑ የታዕካ ነገስት ባዕታ ለማርያም ገዳም አስተዳዳሪና ሌሎች የአዲስ አበባ ገዳማትና አድባራት አስተዳዳሪዎችም ተገኝተዋል በዓሉን አስመልክቶም ከደብረ ገነት መካኒሳ ቅዱስ ሚካኤል ቤ/ክ ሊቃውነት ቅኔ ቀርቧል፡፡ ዕለቱን አስመልክተው ብፁዕ አቡነ አረጋዊ ንግግር ያደረጉ ሲሆን ቤተክርስቲያን አንዲት ናት፣ ከሐዋርያት ዘመን ጀምሮ አባቶቻችን ከቦታ ወደ ቦታ እየተዘዋወሩ ቤተክርስቲያንና ህዝበ ክርስቲያንን ይመራሉ፣ ያስተምራሉ፣ ለዚህም ነው ዛሬ ሁለቱም አባቶቻችን (ወንድሞቻችን) ከመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ወደ ባዕታና ከደብረ ገነት መካኒሳ ቅዱስ ሚካኤል ወደ መንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል አንዲቷን ቤተክርስቲያን ለማገልገልና ሐዋርያዊ ተልዕኮአቸውን ለመፈፀም የተዛወሩት ብለዋል፡፡
ምንም እንኳን የቦታው ስም ቢለያይም የቤተክርስቲያቱ አገልግሎት አንድ መሆኑን አበክረው ገልፀዋል፡፡ ከብፁዕ አቡነ አረጋዊ በመቀጠል ንግግር ያደረጉት የቀድሞ የካቴድራሉ አስተዳዳሪ የነበሩት ሊቀሊቃውንት አባ ጥዑመልሳን ኪ/ማርያም ሲሆኑ ለአዲሱ አስተዳዳሪ እንኳን ደህና መጡ በማለት ደስታቸውን ከገለፁ በኋላ የመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል መላ ማህበረካህናትና ልዩ ልዩ ሠራተኞች በነበራቸው የስድስት ዓመታት ቆይታ እጅግ በጣም አመስግነዋቸዋል፡፡ ሁሉም ሠራተኛ ሥራውን፣ መብቱንና ግዴታውን፣ አውቆ የሚሠራ ምስጉን ሠራተኛ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ አያይዘውም የተጀመሩትን መሠረተ ልማቶች በአዲሱ አስተዳዳሪ በሊቀስልጣናት አባ ገ/ሥላሴ በላይ በአጭር ጊዜ ውስጥ እንደሚጠናቀቁ ጽኑ እምነታቸው መሆኑን አክለው ገልፀዋል፡፡
በስተመጨረሻ የተደረገላቸውን አቀባበል በማስመልከት ንግግር ያደረጉት ክቡር ሊቀስልጣናት አባ ገ/ሥላሴ በላይ ሲሆኑ የተደረገላቸውን አቀባበል ካመሰገኑ በኋላ ካቴድራሉ ዓለም አቀፋዊ እንደመሆኑ መጠን በልማትና በመልካም አስተዳደር ወደተሻለ ደረጃ ላይ እንዲደርስ የሁሉም ሠራተኛና ምእመን አስተዋጽኦ ወሳኝ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ ከዚሁ ጋር አያይዘው ዘመኑ በሚፈቅደው አስተሳሰብና አሰራር ሰዎች መስራት ይኖርብናል ብለዋል፡፡ አገሮችና ሰዎች የሚያድጉት በሥራና በሥራ ብቻ መሆኑንና እግዚአብሔርም የሚወደው መልካም ሥራ መሆኑን አብራርተው ገልፀዋል፡፡
በመሆኑም ሁሉም የካቴድራሉ ሠራተኛና ምዕመናን በእውቀታቸውና በገንዘባቸው ለቤተክርስቲያን እድገትና ልማት ከጐናቸው እንዲሰለፉ ጥሪያቸውን አስተላልፏል፡፡ ከዚሁ ጋር በተያያዘ የካቴድራሉ ሰበካ ጉባዔ፣ አስተዳደር ሠራተኞች፣ ማህበረካህናትና ልዩ ልዩ ሠራተኞች በካቴድራሉ ሁለገብ አዳራሽ ትውውቅ ተደርጓል፡፡ አንዳንድ የቤተክርስቲያኑ ሠራተኞችና ምዕመናን እንደገለጹት እኚህ መንፈሳዊ አባት ለሰባት ዓመት ያህል በቆዩበት በደበረ ገነት መካኒሳ ቅዱስ ሚካኤል ቤተክርስቲያን እጅግ በጣም አስደናቂ ሥራ መሥራታቸውንና ለዚሁ ታላቅ ካቴድራል የተመረጡትን በዚሁ ልማታዊ ሥራቸው መሆኑ ተናግሯል፡፡ እንደዚሁም አንዳንድ ነባር የካቴድራሉ ሠራተኞች ሊቀሥልጣናት አባ ገ/ማርያም አጽብሐና ሌሎች ለዚሁ ካቴድራል ትልቅ ሥራ ሠርተው የሄዱት ወሳኝ የልማት አባቶች አስተዳዳሪዎችን ሊተኩ እንደሚችሉና ብሎም የላቀ ሥራ ሊሠሩ እንደሚችሉ ትልቅ ተስፋ ተጥሎባቸዋል፡፡ መልካም የሥራ ዘመን እንዲሆንላቸውም ሁሉም የካቴድራሉ ሠራተኞች ተመኝተውላቸዋል፡፡
በሌላ ዜና የቀድሞ የካቴድራሉ አስተዳዳሪ የነበሩትን ሊቀሊቃውንት አባ ጥዑመልሳን ኪ/ማርያም በካቴድራሉ ጽ/ቤት፣ ካህናትና ልዩ ልዩ ሠራተኞች አማካኝነት በዓይነቱ ልዩ የሆነ አሸኛኘት በካቴድራሉ ሁለገብ አዳራሽ የካቲት 1ዐ ቀን 2ዐዐ4 ዓ.ም. ተደርጉላቸዋል፡፡ በዚሁ ዕለት ብፁዕ አቡነ አረጋዊ፣ ሊቀሥልጣናት አባ ገ/ሥላሴ በላይ የካቴድራሉ አስተዳዳሪና ጥሪ የተደረገላቸው የአዲስ አበባ ገዳማትና አድባራት አስተዳዳሪዎች፣ የካቴድራሉ ካህናትና ልዩ ልዩ ሠራተኞች የተገኙ ሲሆን በካቴድራሉ ሠራተኞችና ጽ/ቤት አማካኝነት የተዘጋጀውን ሽልማት በብፁዕ አቡነ አረጋዊ አማካኝነት ተበርክቶላቸዋል፡፡ በማግስቱ የካቲት 11 ቀን 2ዐዐ4 ዓ.ም. ብፁዕ አቡነ አረጋዊ፣ አዲሱ የካቴድራሉ አስተዳዳሪ፣ የተለያዩ አስተዳዳሪዎች፣ ልብሰተክህነት የለበሱ የካቴድራሉ ካህናትና መዘምራን ከሌሊቱ 1ዐ፡3ዐ ላይ አባ ጥዑመልሳን ኪ/ማርያምን አጅበው ታዕካ ነገስት ባዕታ ለማርያም ገዳም የተገኙ ሲሆን የገዳሙ የቀድሞ አስተዳዳሪ የነበሩት ሊቀሊቃውንት አባ ዘርዓዳዊትና ልብሰተክህኖ የለበሱ የገዳሙ ካህናትና ዲያቆናት ደማቅ አቀባበል አድርገውላቸዋል፡፡ ሥርዓተ ቅዳቤውም በክቡር ሊቃ ሊቃውንት አባ ጥዑመልሳን ኪ/ማርያምና በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ካህናት መሪነት የተከናወነ ሲሆን ከቅዳሴ በኋላ በአሉን አስመልክቶ በአውደ ምህረቱ ላይ በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል እና በታዕካ ነገስት ባዕታ ለማርያም ገዳም ሊቃውንት ቅኔ ቀርቦ የበአሉ ፍፃሜ ሆኗል፡፡