የብፁዕ ወቅዱስ ዶክተር አቡነ ጳውሎስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ አቡነ ጳውሎስ ሥርዓተ ቀብር ተፈጸመ

 

ነሐሴ 17 ቀን 2004 ..

በመ/ር ዘሩ ብርሃኔ

የብፁዕ ወቅዱስ ዶክተር አቡነ ጳውሎስ ቀዳማዊ፣ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ፣ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት፣ የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ምክር ቤት ፕሬዝደንት፣ የዓለም ሃይማኖቶች ለሰላም የክብር ፕሬዝዳንት ሥርዓተ ቀብራቸው ነሐሴ 17 ቀን 2004 . እኩለ ቀን ላይ በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት፣ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት፣ ከአኀት አብያተ ክርስቲያናትና ከሌሎችም የተወከሉ የእምነት አባቶች በሺዎች የሚቆጠሩ ምእመናን በተገኙበት በታላቅ ስነ ስርዓት ተፈጽሟል፡፡

    

የቅዱስነታቸው አስክሬን (ነሐሴ 16 ቀን 2004.) ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፣ በካህናት ፣በሰንበት ትምህርት ቤቶች ዘማሪያን ፣በፖሊስ ሠራዊት ኦርኬስትራ ማርሽ ባንድና በምእመናን ታጅቦ ከመንበረ ፓትርያርክ ቅድስተ ቅዱሳን ማርያም ገዳም ወደ መንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ከተወሰደ በኋላ በዚሁ ቤተ ክርስቲያን ጸሎተ ፍትሐትና ማኅሌት ሲደርስ አድሯል፡፡ ንጋት ላይ ጸሎተ ቅዳሴው ከተከናወነ በኋላ ከግብፅ፣ከሶርያ፣ ከሕንድና ከአርመን ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ አኀት አብያተ ክርስቲያናት የተወከሉ አባቶች በየቋንቋቸው ጸሎት አድርሰዋል፡፡

             

የግብፅ ኦርቶዶክስ ቤተክርስትያን ተወካይ በበኩላቸው ዓለማችን ብዙ አስቸጋሪ ሁኔታዎች ሲያጋጥማት ቀድመው የሚደርሱ እውነተኛ አባት ነበሩ። የእሳቸው ህልፈተ ህይወት ለኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆን ለመላው የኦርቶዶክስ ክርስትያን አማኞች በሙሉ አስደንጋጭ ዜና ነው። አቡነ ጳውሎስ ለዓለም ሰላም በጣም አስፈላጊ ሰው ነበሩ በማለት ገልጸዋቸዋል፡፡

 

በሥርዓተ ቀብሩ ላይ የኢ... ፕሬዝደንት  የተከበሩ አቶ ግርማ ወልደ ጊዮርጊስ የላኩትን የሐዘን መግለጫ በተወካያቸው አቶ አሰፋ ከሲቶ አማካኝነት የቀረበ ሲሆን፡-ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ለመላው ሰብዓዊ ፍጡር ትልቅ አክብሮት ያላቸውና በህዝቦች መካከል መልካም ጉርብትና እንዲኖር የሰሩ ብልህና መንፈሳዊ መሪ ናቸው። የአገሪቱ ህዝቦችና አፍሪካውያን ሰብዓዊ ቀውስ ሲያጋጥማቸው ፈጥነው የሚደርሱና ለህዝቦች ሰላም ሳይታክቱ የሰሩ አባት እንደነበሩ ተናግረዋል። እኚህ አባት በሰሩት ስራ ዓለም የማይረሳቸው እንደሆኑ የጠቀሱት ፕሬዚዳንቱ ለመላው የኦርቶዶክስ ክርስትያንና ቤተሰቦቻቸው መፅናናትን እንደሚመኙ መልዕክት አስተላልፈዋል ፡፡

በተመሳሳይ በስርዓተ ቀብሩ ላይ የተገኙት የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፖብሊክ ጊዜያዊ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ እንደተናገሩት ቅዱስነታቸው ባለፉት 20 ዓመታት መንግሥት የጀመረውን የልማት ጉዞ ለማሳካት ያለሰለሰ ጥረት ያደረጉ ታላቅ አባት ነበሩ።  በተለይ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን አገሪቱ በነደፈችው የልማት ስራ ላይ ተሳትፎ እንዲኖራት ከፍተኛ ጥረት በማድረግ ለልማቱ ያላቸውን ቁርጠኝነት ያሳዩ አባት ነበሩ ብለዋል። በሌላ በኩል በውጭ የሚገኙ የአገሪቱ ቅርሶች ወደ አገራቸው እንዲመለሱ በማድረግ ረገድና በአገር ውስጥ ያሉ ቅርሶችም በአዓለም ቅርስነት እንዲመዘገቡ ሰዎችን በማስተባበር ከፍተኛ ስራ መስራታቸውን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል። ተተኪ የቤተክርስትያን አባቶችም የእሳቸውን ፈለግ በመከተል በመንግሥት የልማት ስራዎች ላይ በመሳተፍ አገሪቱን ከድህነት ለማውጣት በሚደረገው የልማት ጥረት የበኩላቸውን እንዲወጡ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

እንዲሁም የአዲስ አበባ ከንቲባ ኩማ ደመቅሳ በበኩላቸው ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ በአገሪቱ የኃይማኖት መቻቻል እንዲጎለብት ትልቅ ጥረት ያደሩጉ ታላቅ መንፈሳዊ መሪ እንደነበሩ አመልክተው በሞታቸው የተሰማቸውን ጥልቅ ኀዘን በከተማዋ ነዋሪዎች ስም ገልጸዋል። በተለይ የአክራሪነትን ጎጂ ባህል በማስተማርና የትምህርት ዕድል በአገሪቱ እንዲስፋፍ የበኩላቸውን የተወጡ ትልቅ አባት እንደነበሩ ጠቁመዋል፡፡ በአገሪቱ ጧሪና ቀባሪ ያጡትን በመደገፍና በጤናው መሰክ ኤች.አይ../ኤድስ በመከላከል ረገድ ያሳዩት ተግባር በተምሳሌት የሚጠቀስ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በቀብር ስነ ስርዓቱ ላይ የዓለም አብያተ ክርስትያናት ተወካይ ባስተላለፉት መልዕክት እኚህ አባት በአገራት መካከል የሚከሰቱ አለመግባባቶችን በማብረድና ሰብዓዊ ቀውስ ያጋጠማቸውን ሀገራት በመደገፍና በማፅናናት ከፍተኛ ስራ የሰሩ ናቸው። በተለይ ሱዳን ውስጥ የነበረውን ችግር ለመፍታት ከባለ ድርሻ አካላት ጋር በመተባበር ይሰጡት የነበረው ጠቃሚ አስተያየት ዓለም የሚረሳው አለመሆኑን ገልፀዋል።

ብፁዕ ወቅዱስ ዶክተር አቡነ ጳውሎስ ቀዳማዊ የኢትዮጵያ ፓትርያርክ ጥቅምት 25 ቀን 1928 .. በቀድሞው አጠራር በትግራይ ክፍለ ሀገር በአድዋ አውራጃ በእንዳ አባ ገሪማ ገዳም አካባቢ ከአባታቸው ከአፈ መምህር ገብረ ዮሐንስ ወልደ ሥላሴና ከእናታቸው ከወይዘሮ አራደች ተድላ ተወለዱ ሲሆን፡፡ ከስድስት ዓመታት ዕድሜ ጀምሮ እስከ ዕውቀት ድረስ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መንፈሳዊ ትምህርትን ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያንንና የአበው መነኮሳትን ሥርዓት የተከተለ ገዳማዊ ኑሮን በአባ ገሪማ ገዳም እያጠኑ አባቶችን እያገለገሉ እንዳደጉ የህይወት ታሪካቸው ያስረዳል፡፡

ሥርዓተ ቀብሩን በመምራት ያስፈጸሙት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አቃቤ መንበርና የአርሲ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ናትናኤል   ቃለ ምእዳንና ጸሎተ ቡራኬ ሰጥተዋል ብፁዕነታቸው በዚሁ መልእክታቸው የቅዱስ ፓትርያርኩን ቅድስና አውስተው ለመላው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ምእመናንና ምእመናት መጽናናትን ተመኝተዋል፡፡