የልደት በዓል በሁሉም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን በድምቅት ተከበረ
በመ/ር ዘሩ ብርሃኔ
እነሆ ዛሬ በዳዊት ከተማ መድኀኒት ተወልዶላችኋል ሉቃ.2፥11
እንኳን ለጌታችን ለመድኀኒታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ በዓለ ልደት በሰላም አደረሳችሁ፡፡
የጌታችን የአምላካችን የመድኀኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ በዓለ ልደት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ከምታከብራቸው ታላላቅ በዓላቶች መካከል አንዱ ሲሆን ሁሌ በየዓመቱ ታኅሣሥ 29 እንደሚከበር ይታወቃል፡፡ እንደ ተለመደው የዘንድሮ በዓልም መከበር የጀምረው ከዋዜማው 12.00 ሰዓት ጀምሮ ሲሆን በሁሉም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ገዳማትና አድባራት ሥራዓተ ማኅሌት፤ሰዓታት እና ሥርዓተ ቅዳሴ ሲከናወን ያድራል ፡፡ በተለይም በአገሪቱ ዋና መዲና በሆነቸው በአዲስ አበባ ከተማ በሰሜን አዲስ አበባ ሀገረ ስብከት በሚገኘው በመንበረ ጸባዖት ቅድሰት ሥላሴ ካቴድራል በዓሉ እጅግ በጣም በማቅ ሁኔታ ተከብሮ አድሯል፡፡በበዓሉ ላይ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ዐቃቤ መንበረ ፓትርያርክና የአርሲ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ናትናኤል፤ ዶ/ር ብፁዕ አቡነ ጢሞቴዎስ የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ዩኒቨርስቲ ኮሌጅ የበላይ ኃላፊ፤ብፁዕ አቡነ ሳሙኤል የልማትና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን ሊቀ ጳጳስ፤በፁዕ አቡነ አረጋዊ የመንበረ ጸባዖት ቅድሰት ሥላሴ ካቴድራል የበላይ ኃላፊ ፤ካህናት እና በብዙ ሽህ የሚቆጠሩ ምዕመናን በበዓሉ ላይ ተኝተው በዓሉን በድምቀት አክብረዋል፡፡በዐቃቤ መንበር ፓትርያርክ በብፁዕ አቡነ ናትናኤል መልካም ፈቃድ ሥርዓተ ቅዳሴውን የመሩት ብፁዕ አቡነ ሳሙኤል ሲሆኑ በ3ቱም መንበር በሥላሴ፤በማርያምና በዮሐንስ ቤተ መቅደሶች ቅዳሴው የተቀደሰ ሲሆን ሥርዓተ ቅዳሴውም በተለመደው ሰዓት ተጠናቅቋል፡፡ በበዓሉ ላይ ለተገኙ መዕመናን በዐቃቤ መንበር ፓትርያርክ በብፁዕ አቡነ ናትናኤል አማካኝነት ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ ተሰጥቶ የበዓሉ ፍፃሜ ሁኗል፡፡ ከዚሁ ጋር በተያያዘ ሁሌ በየዓመቱ የሚከበረው የቅዱስ በዓለ ወልድ በዐለ ንግሥ ታኅሣሥ 29/2005 ዓ.ም በድምቀት ተከብሮ ውሏል፡፡ቅዱስ በዓለ ወልድ በአዲስ አበባ ከሚገኙ ታላላቅ ገዳማትና አድባራት መካከል አንዱ ሲሆን የተመሠረተውም በዳግማዊ አፄ ምኒልክ ዘመን መንግስት በ1883ዓም እንደሆነ ይታወቃል፡፡
በዓመት ሁለት ጊዜ መጋቢት 29 እና ታኅሣሥ 29 ታቦተ ሕጉ ወጥቶ በዓሉ በድምቀት ይከበራል/ይነግሣል፤የዘንድሮ የ2005 ዓ.ም የጌታችን የአምላካችን የመድኀኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ በዓለ ልደትም በደማቅ ሥነ-ሥርዓት ተከብሮ የዋለ ሲሆን በበዓሉ ላይም በርካታ መእመናን ተገኝተዋል፡፡ በዓሉ መከበር የጀመረው ከዋዜማው ከታኅሣሥ 28 ጀምሮ ሲሆን የካቴድራሉ ካህናትና መዘምራን ከዋዜማው 12.00 ሰዓት ጀምሮ ለ18 ሰዓታት ያህል ሌሊትና ቀኑን ሙሉ ያለ ማቋረጥ ስብሐተ እግዚአብሔር ሲያቀርቡ ውለው አድረዋል፡፡የካቴድራሉ ሊቃውንት መዘምራን እንዲሁም ወጣት የሰንበት ት/ቤት መዘምራን ለበዓሉ የተዘጋጀውን ወረብ አቅርበዋል፡፡ ይህ መንፈሳዊ አገልግሎት ማለትም ሥርዓተ ማህሌተ፣ ሥርዓተ ቅዳሴ እንዲሁም ሰዓታትና ሰርክ ፀሎት በአጠቃለይ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን የሥርዓተ አምልኮ አፈፃፀም ልዩ በመሆኑ የእምነቱ ተከታዮች ብቻ ሳይሆን ሌሎችንም እጀግ በጣም የሚስደንቅ በዓል ነው፡፡በበዓሉ ላይ የተገኙት ክቡር ሊቀ ሥልጣናት አባ ገ/ሥላሴ በላይ የመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ዋና አስተዳዳሪ በበዓሉ ላይ ለተገኙት መዕመናን ሰፋ ያለ ትምህርተ ወንጌል ተሰጥቶ የበዓሉ ፍፃሜ ሁኗል፡፡