ዓመታዊው የዓጋዓዝተ ዓለም ሥላሴ ክብረ በዓል በድምቀት ተከበረ

                        እንኳን ለአብርሃሙ ሥላሴ ዓመታዊ ክብረ በዓል በሰላም በጤና በሕይወት አደረሳችሁ፡፡

                          በመ/ር ዘሩ እና በመ/ር ዳዊት

5.3

‹‹እመ እግዚአብሔር ኢሐነፀ ቤተ ከንቶ ይፃምው እለ የሃንፁ›› ‹‹እግዚአብሔር ቤትን ካልሠራ ግንበኞቹ በከንቱ ይደክማሉ›› መዝ 126፡1 ይህን የታላቁን ነቢይ ቃል ለመነሻነት የተመረጠው ዛሬ በቤተ ክርስቲያናችን የሚከበረው የአጋዕዝተ ዓለም ሥላሴ በዓለ ንግሥን ምክንያት ለመግለፅ ነው፡፡ ታላቁ ነቢይ ቅዱስ ዳዊት ምንም እንኳ ይህን ኃይለ ቃል ከጊዜ በኋላ የፃፈው ቢሆንም የዚህን ጽሑፍ ሐሳብ የሚያንፀባርቀው ቀደም ሲል በዘመነ ህገ ልቡና የተፈፀመ ነበረ በዘፍ1ዐ፡32 ላይ ‹‹የኖኀ የልጆቹ ነገዶች እንደየ ትውልዳቸው በየህዝባቸው እነዚህ ናቸው፤ አህዛብም ከጥፋት ውኃ በኋላ በምድር ላይ ከነዚህ ተከፋፈሉ››፡፡ ይልና በተለይ በዘፍ 11፡1 ጀምሮ ያለውን ስንመለከት ደግሞ ‹‹ምድርም ሁሉ በአንድ ቋንቋ ንግግር ነበረች›› ብሎ የሰናኦርን ግንብ መገንባትና መፍረስን ያትታል፡፡ በአጭሩ የዚህ ኃይለ ቃል ጭብጥ ሐሳብ፡- የሰው ልጆች እግዚአብሔርን ለመቃወም ሲሉ ታላቅ ግንብ እንደገነቡና እግዚአብሔር ደግሞ ይህን ታላቅ ግንብ እንደ አፈራረሰባቸው ነው የሚያብራራው፡፡ ይህን ግንብ ለመገንባት 43 ዓመት ፈጅቶባቸዋል፡፡

ይህ ግንብ በአሁኑ ዘመን በነዱባይ ከተገነቡት ታላላቅ ሰማይ ጠቀስ ህንፃዎች እንደሚበልጥ የቤተ ክርስቲያኒቱ መምህራን ይናገራሉ፡፡ ይህንን ህንፃ ሲገነቡ የነበሩ ሰዎች ቀደም ሲል እንደተገለፀው ለትምክህትና እግዚአብሔርን ለመቃወም ስለሆነ እግዚአብሔር ደግሞ ትምክህትንና ራሱ እግዚአብሔርን የሚቃወም ሰው አይወድም ዘዳግ 5÷ 10 አስመ አነ አምላክ ቀናኢ እኔ እግዚአብሔር ቀናተኛ አምላክ ነኝ ሲል በሙሴ አፍ እንዳስተማረ የሚቃወሙትን የቃወማቸዋል ፡፡

እግዚአብሔር በአምላክነቱ ቀናኢ ነው፡፡ ስለዚህ እንደነዚህ ዓይነት ሰዎች የሚሠሩት ሥራ (ህንፃ) ስኬታማ አይሆንምና ብትንትኑ ወጣ፤ ፈራረሰ፡፡ መ/ቅዱሱ እንደ ነገረን አንድ የነበረ የሰዎች ቋንቋ በሰዎቹ ቁጥር ልክ ሆነ፡፡ ይህም የኃጢአት ውጤት ነው፡፡ አዳም ከመበደሉ በፊት ሰው ከእንስሳትና አራዊት ከጠቅላላ ፍጥረታት ሁሉ በቋንቋ ይግባባ እንደ ነበረ አበው ያስተምራሉ አዳም ሐጢአት ከሠራ በኋላ ግን ከፍጥረታት ጋር መግባባት ተሳነው፡፡ አሁን ደግሞ በነዚህ ኃጢአት ምክንያት ሰውና ሰው መግባባት አቃታቸው፡፡ ሰው ኃጢአት ሲሰራ ከራሱ ከልቡናው ጋር ይጣላል፤ መግባባት ያቅተዋል፡፡ ሰዎች የሚሠሯአቸው ሥራዎች በስኬት እንዲጠናቀቁ ካስፈለገ እግዚአብሔር እንዲጨመርበት ማድረግ ነው፤ እግዚአብሔር ካልተጨመረበት ግን ነቢዩ እንደነገረን ልፋቱ ከንቱ ድካም ነው የሚሆነው፡፡ ይህ ታሪክ በዘመነ ህገ ልቡና የተፈፀመ ሲሆን ሌላ ተጨማሪም ቤተክርስቲያናችን ከዚሁ ጋር አብራ የምታከብረው ታላቁ የሐዲሱ ኪዳን የልደት በዓል ነው፡፡ ሐዋሪያው ቅዱስ ዮሐንስ በ1 ዮሐ 3÷8 ‹‹በእንተ ዝንቱ አስተርአየ ወልደ እግዚአብሔር ከመ ይሥዓር ግብሮ ለጋኔን›› ‹‹ስለዚህ የዲያብሎስን ሥራ ያፈርስ ዘንድ የእግዚአብሔር ልጅ ተገለጠ›› ብሎ እንደ ነገረን የእግዚአብሔር ልጅ ዲያብሎስ ለ55ዐዐ ዘመን የገነባው የሐጢአትን ግንብ ለማፍረስ ሰው የሆነበት ወቅት ነው፡፡ ይህ ወቅት ሠራዊተ ዲያብሎስ ያዘኑበት የተዋረዱበት ሲሆን የሰው ልጆችና መላእክት ደግሞ ያመሰገኑበትና የዘመሩበት ጊዜ (ወቅት) ነው፡፡ ታላቁ ሊቀ ቅዱስ ቄርሎስ ‹‹ዮም አሐደ መርኤተ ኮኑ መላእክት ወሰብእ ከመይሰብሕዎ ለክርስቶስ በቃለ አሚን›› ‹‹እነሆ ዛሬ መላእክትና ሰዎች በእምነት ቃል ኢየሱስ ክርስቶስን ለማመስገን አንድ መንጋ ወይም አንድ ማኀበር ሆኑ›› ሲል ይገልፀዋል ታላቁ የኢትዮጵያውያን መመኪያ የሆነ ሊቁ ቅዱስ ያሬድም በጣዕመ ዜማ ይህን ያብራራዋል፡፡

5.5

ይህ የሚያመለክተው ሰዎች ለ55ዐዐ ዘመን በዲያብሎስ ሥር ተገዝተው(በዲያብሎስ ግዛት )ስለነበሩ በዚሁ በጌታ ልደት ከዚህ አስቀያሚ ከሆነው የዲያብሎስ ግዛት ነፃ መውጣታቸውን ያረጋገጡበት ቀን ስለሆነ ለአምላካቸው፣ ለመድኃኒታቸው ታላቅ ምስጋናን አቅርበዋል፡፡ መላእክትም ደግሞ በሰው ሞት አዝነውና ተክዘው ነበር አሁን ግን ሰው ድህነተ፤ ሥጋ ድህነተ ነፍስን ስላገኘ ደስ ብሏቸው አመስግነዋል ዘምረዋል፡፡ መላእክት ሰዎች በሥጋቸውም ይሁን በነፍሳቸው እንዳይጎዱ ወደ ፈጣሪ የሚለምኑ፣ የሚማፀኑ ናቸው፡፡ በዘካ 1፡12 ‹‹የእግዚአብሔርም መልአክ መልሶ አቤቱ የሠራዊት ጌታ ሆይ እነዚህን ሰባ ዓመት የተቆጣሃቸው ኢየሩሳሌምንና የይሁዳን ከተሞች የማትምራቸው እስከ መቼ ነው›› አለ ይላል ይህ የመላእክትን ምልጃ የሚያመላክት ነው፡፡ ስለዚህ መላእክት ለሰው ድህንነት በየጊዜው ይፀልያሉ፤ ይማልዳሉ፡፡ ሰው ሲድን ደግሞ ደስ ብሏቸው ይዘምራሉ ያመሰግናሉ ይህን ቅዱስ ሉቃስ በወንጌሉ በሉቃ2÷12 ድንገትም የሰማይ ሠራዊት ከመልአኩ ጋራ ነበሩ እግዚአብሔርንም እያመሰገኑ ክብር ለእግዚአብሔር በአርያም ይሁን ፤ሰላምም በምድር ለስውም በጎ ፈቃድ ወይም እርቅ ተጀመረ አሉ ሲል የመዘገበልን ፡፡ አሁን ታላቁ ኢትዮጵያዊ ሊቁ ቅዱስ ያሬድ በዝማሬው ‹‹ዮም መላእክት ይየብቡ ወሊቃነ መላእክት ይዜምሩ ኃይላት ይየብቡ እስመ መድኀን መጽአ ውስተ ዓለም ለቢሶ ሥጋነ›› ‹እነሆ መላእክት ሊቃነ መላእክት ለአምላካቸው ለፈጣሪያቸው፣ ምስጋናን ያቀርባሉ ምክንያቱም ኢየሱስ ክርስቶስ መድኃኒት ለመሆን የሰውን ሥጋ ለብሶ ወደ ዓለም መጥቷልና በተጨማሪም ለኛ ስለ ተወለደልን ሥልጣን ያላቸው መላእክት ይቀድሱታል፤ ሱራፌልም እግዚአብሔርን ይባርካሉ፤ ኪሩቤልም ውዳሴን ያቀርባሉ፤ ዛሬ ከኛ የጥንቱ መርገም ተወግዷል፤ ዛሬ ሐጢአታችን ተተወልን ወዘተ….. በማለት ያመሰገኑትን ምስጋና ይቀጥላል፡፡ በነዚህ ሁለቱ ታሪኮች ተመሳሳይ የሆኑ ድርጊቶችን እግዚአብሔር አከናውኗል፡፡

1. ሰው የገነባው ግንብን ማፍረስ ነው፡፡ እግዚአብሔር ለሰው ልጆች አእምሮን የሰጣቸው መልካም ነገርን እንዲሰሩበትና መልካም ነገርን እንዲያስቡበት እንጂ ለመጥፎ አልነበረም እነሱ ግን ይህንን አእምሮ ለመጥፎ ነገር ያውሉታል ሰዎች በአእምሮአቸው መጥፎ ሥራ ቢሰሩ የሚጎዱ ራሳቸው ፤ጥሩ ሥራ ቢሠሩ የሚጠቀሙ ራሳቸው ነቸው፡፡

2. ዲያብሎስ ለ55ዐዐ ዘመን የገነባውን የኃጢአት ግንብን ማፍረስ ነው፡፡ ከነዚህ ከሁለቱ ታሪኮች የምንማረው ፡-

1. የሰው ልጅ ያለ እግዚአብሔር ፈቃድ ምንም፣ ምንም ነገር መሥራት እንደማይችል ነው ሰው ግንብን ቢገነባ፣ መኪና ቢገዛ፣ ቢነግድ ያለ እግዚአብሔር ፈቃድ ሊሆን እንደማይችል መገንዘብ አስፈላጊ ነው፡፡

2. አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዲያብሎስ ለ55ዐዐ ዘመን በብዙ ውጣውረድ የገነባውን የኃጢአት ግንብ በልደቱ (ሰው ሆኖ) ንዶታል፡፡ ነገር ግን ይህ የተናደውን ግንብ እንደገና ኃጢአትን በመስራት እንዳንገነባው ወይም እንዳንጠግነው ጥንቃቄ ያስፈልጋል፡፡ ዲያብሎስ ይህንን የፈረሰውን የኃጢአት ግንብ ለማስጠገን እየወጣና እየወረደ ነው ያለው ሊቀ ሐዋርያት ቅዱስ ጴጥሮስ በ1ኛ መልእክቱ 5÷8 በመጠን ነሩ ነቁም ባላጋራችሁ ዲያብሎስ የሚውጠውን ፈልጎ እንደሚያገሣ አንበሳ ይዞራልና ሲል የሚገልፀው፡፡ ስለዚህ በጥንቃቄ እንድንኖር እጅግ አስፈላጊ ነው ይህንንም እንድናደርግ አምላካችን እግዚአብሔር ይርዳን፡፡ይትባረክ እግዚአብሔር አምላከ እስራኤል ዘተሰሃለነ ወገብረ መድኃኒተ ለሕዝበ ዚአሁ፡፡ ስለዚህ በዓለ ቅድስት ሥላሴ ጥር 7 ቀን ምን ተደረገ? ከጥፋት ውሃ በኋላ የኖኅ ልጆች ወልደው ተዋልደው ብዙዎች ሆኑ ባቢሎን የነበሩት በሰናዖር ምድር ሰፊ ሜዳ አግኝተው ሳንሞት ስም ማስጠሪያ ግንብ እንገንባ ብለው መክረው ታላቅ ግንብ ገነቡ፡፡ አለቃቸውም ናምሩድ ይባላል፡፡ ሞትን የሚያመጡብን ሥላሴ ናቸው እነርሱን ወግተን ሞትን እናርቅ አላቸው፡፡ እነርሱም ከግንቡ ላይ ሆነው ጦር እየሰበቁ ይወረውሩ ጀመር፡፡ ሰይጣን በደመና በምትሀት ጦሩን ደም እየቀባ ይልክላቸዋል እነርሱም ደሙን እያዩ አሁን አብን ወጋነው አሁን ወልድን ወጋነው ይሉ ጀመር፡፡ ሥላሴ ምንም እንኳን ምህረታቸው የበዛ ቢሆንም ባቢሎናዊያን ዲያቢሎስ ስለሰለጠነባቸው ቋንቋቸውን ለያዩባቸው ከዚያም ውሃ ሲለው ጭቃ፣ ጭቃ ሲለው ደንጊያ የሚያቀብለው ሆነ፡፡ እንዲህ የማይግባቡ ቢሆኑ ተበታትነዋል፡፡ ባለማስተዋል የሰሩትም ሕንፃ ነፋስ ጠራርጎ አጥፍቶታል፡፡ ዘፍ.11 1-9 በዘመነ አብርሃምም የሰዶምና የገሞራ ሰዎች ወንድ ለወንድ እስከ መጋባት ድረስ ኃጢአት ሰሩ እግዚአብሔርንም በደሉ፡፡ የአብርሃም የወንድም ልጅ ሎጥ በዚያ ይኖር ነበር፡፡ ሊያድኑት ቢሹ ሁለቱን መላእክት ልከው እግዚአብሔር ሰዶምና ገሞራን አጠፋለሁ ብሏልና ሚስትህንና ልጆችህን ይዘህ ወደ ዞዓር ሂድ ስትሄድም ወደ ኋላ ዞረህ አትመልከት አሉት፡፡ ሎጥም ማልዶ ተነስቶ ሚስቱንና ልጆቹን ይዞ ከከተማ ወጣ፡፡ ሰዶምና ገሞራም ባህረ እሳት ሆኑ፡፡ የሎጥም ሚስት ወይኔ ሀገሬ ብላ መለስ ብትል የጨው ሀውልት ሆና ቀርታለች፡፡ ዘፍ.19 1-29 ይህ የተደረገው በወርኀ የካቲት እንደሆነ አባቶች ይናገራሉ፡፡ፍሬ ነገሩ ግን ይህን ያደረጉት ቅድስት ሥላሴ እንደመሆናቸው በዚህ ዕለት ይዘከራል ሁል ጊዜ በየዓመቱ በድምቀት ይከበራል ፡፡በመሆኑም የዘንድሮው ዓመትም እንደተለመደው በሰሜን አዲስ አበባ ሀገረ ስብከት በታላቁ ካቴደራል በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል በድምቀት ተከብሯል፡፡በበዓሉ ላይ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ዐቃቤ መንበረ ፓትርያርክና የአርሲ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ናትናኤል፤በፁዕ አቡነ አረጋዊ የመንበረ ጸባዖት ቅድሰት ሥላሴ ካቴድራል የበላይ ኃላፊ ፤በፁዕ አቡነ ማቲያስ የካናዳ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፤በፁዕ አቡነ ኤልሳዕ የሰሜን ጎንደር ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፤በፁዕ አቡነ ዮናስ የአፋር ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፤በፁዕ አቡነ ስምኦን የምዕራብ ወለጋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፤የካቴድራሉ ዋና አስተዳዳሪ ክቡር ቆሞስ አባ ገ/ሥላሴ በላይ፤የካትድራሉ ሰበካጉባኤ አባላትና መላው ማህበረ ካህናት እንዲሁም በብዙ ሺህ የሚቆጠር ሕዝበ ክርስቲያን በበዓሉ ላይ ተገኝተው በዓሉን በድምቀት አክብረዋል፡፡