በኢ/ ኦ/ተ/ቤ/ ክ/የመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል
  • ቀዳሚ ገጽ
  • መ/ጸ/ቅ/ሥ/ካቴድራል
    • የአስተዳዳሪው መልእክት
    • ታሪክ
    • አስተዳደራዊ መዋቅር
    • የልማት እንቅስቃሴዎች
    • መንፈሳዊ አገልግሎቶች
    • ፎቶዎች
  • ቤተ መዘክር
    • የቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ቤተ መዘክር
    • ፎቶዎች
  • ት/ ቤት
    • መግቢያ
    • መሰናዶ እና 2ኛ ደረጃ
    • 2ኛ ደረጃ ት/ቤት ወርሐዊ ክፍያ
    • 1ኛ ድረጃ ት/ቤት ወርሐዊ ክፍያ
    • ፎቶዎች
  • ሰንበት ት/ቤት
    • መግቢያ
    • አውደ ወራዙት
    • ፎቶዎች
  • አገልግሎቶች
    • መግቢያ
    • ፎቶዎች
  • ስብከተ ወንጌል
    • መግቢያ
    • ታሪክ
    • ፎቶዎች
  • Menu Menu

ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያሪክ አቡነ ማትያስ ዐቢይ ጾምን አስመልክቶ መልእክት አስተላለፉ

March 20, 2013

                                       

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን፡፡

በሀገራችን በኢትዮጵያ በገጠርና በከተማ፤

ከሀገር ውጭ በተለያዩ አህጉር የምትኖሩ፤

የሀገራችንን ዳር ድንበር ለማስጠበቅ በየጠረፉ የቆማችኹ፤

በሕማም ምክንያት በየሆስፒታሉ ያላችኹ፤

እንዲሁም የሕግ ታራሚዎች ኾናችኁ በማረሚያ ቤት የምትገኙ ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያውያት፤

እንኳን ለጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የ2005 ዓ.ም መዋዕለ ጾም በሰላም አደረሳችኹ፡፡

‹‹እብለክሙ በመንፈስ ሑሩ ወፍትወተ ሥጋክሙ ኢትግብሩ›› ‹‹በመንፈስ ተመላለሱ እንጂ የሥጋችኹን ምኞት ከቶ አትፈጽሙ እላችኋለኹ››

የተወደዳችኹ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን!

የሰው ልጅ ከአራቱ ባሕርያተ ሥጋ ከሦስቱ ባሕርያተ ነፍስ የተገኘ ፍጡር እንደመኾኑ በሥጋዊ ፍላጎቱ ሳይሸነፍ ራሱን ለመንፈሳዊ ሕይወቱ ማስገዛት እንዳለበት መጽሐፍ ቅዱስ ያስረዳናል፡፡ ከዚህም አንጻር ‹‹በመንፈስ ተመላለሱ፤ የሥጋንም ምኞት ከቶ አትፈጽሙ፤ ሥጋ በመንፈስ ላይ መንፈስም በሥጋ ላይ ይመኛልና›› ይላል የእግዚአብሔር ቃል፡፡ ለእግዚአብሔር ሕግ መገዛት እስከተቻለ ድረስ ክፉውንና በጎውን ለይቶ ማወቅ ስለማያዳግት በተቻለ መጠን በፊታችን ሰኞ፣ መጋቢት 2 ቀን 2005 ዓ.ም. በሚጀመረው በታላቁ ጾማችን በዓቢይ ጾም ወራት ጎጂ ከኾኑ ተግባራት ሁሉ መራቅ አለብን፤ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዓለምን የማዳን ሥራ ከመጀመሩ በፊት ዐርባ ቀንና ዐርባ ሌሊት በመጾም ድኅነተ ነፍስ እንዳስገኘልን ሁሉ እኛም ፈለጉን ተከትለን ጾም በመጾም ጥንካሬን አግኝተን ረቂቅ የኾነውን የዲያብሎስ ፈተና ማሸነፍ በሚያስችለን ቀጥተኛ መንገድ ለመጓዝ ቅድመ ዝግጅት ማድረግ ይጠበቅብናል፡፡

ከዚህ አንጻር ለሥጋዊ አካላችን ጥንካሬ ምግበ ሥጋ እንደሚያስፈልገው ሁሉ መንፈሳዊ ሕይወታችን እንዲጠነክር መንፈሳዊ ምግብ ያስፈልገዋል፡፡ ከጥንት ጀምሮ ወደ እግዚአብሔር ቅርበት የነበራቸው ቅዱሳን በተሞክሯቸው እንዳስተማሩንና ቅዱሳት መጻሕፍትም እንዳስረዱን÷ መንፈሳዊ አካላችን የሚጠነክረው የሥጋዊ አካላችን ፍላጎት በጾም ኃይል እንዲደክም ስናደርገው ነው፡፡

ሰይጣንና ክፉ ተግባሩ በሰው ላይ ኀይል የሚያገኙበት ምክንያት እኛ ወደ ምግበ ሥጋ ስናዘነብል እንደኾነ በአዳምና በሔዋን ላይ የኾነውና በጌታችን ላይ የተቃጣው በምግበ ሥጋ የመፈተን ሙከራ ማስረጃዎቻችን ናቸው፡፡ የጾም መንፈሳዊ ጥቅም በብሉይ ኪዳንም ኾነ በሐዲስ ኪዳን በማያሻማ ኹኔታ ተረጋግጧል፡፡ ጾም ማለት የቃሉ ቀጥተኛ ትርጉም መተው፣ ወይም እግዚአብሔር ከማይወደው ነገር ሁሉ መራቅ ማለት ነው፡፡ እንዲህ ከኾነ ከእንስሳትና የእንስሳት ውጤቶችን ጨምሮ ከሌሎች ፍላጎቶች ሁሉ በመራቅ ራሳችንን ተቆጣጥረን በፍጹም አእምሯችን፣ በፍጹም ልባችን፣ በፍጹም ኀይላችን እግዚአብሔር አምላካችንን ልናመልክና ለእርሱ ፍጹም ታዛዦች መኾን ይጠበቅብናል፡፡

የተወደዳችኹ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን!

እንደ ቤተ ክርስቲያናችን አስተምህሮ ሁልጊዜ ለሀገርና ለቤተ ክርስቲያናችን የሚጠቅም መልካም ሥራን ከመሥራት በቀር ጉዳት የሚያደርሱ ተግባራትን ማራመድ ፈጽሞ የተከለከለ ነው፡፡ በየአቅጣጫው የተዘረጋው የሀገሪቱ የልማት ፕሮጀክት ውጤታማ እንዲኾን እየተደረገ ያለውን ጥረት የምንመለከተው በታላቅ አድናቆት ነው፤ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የጥረቱ አካል በመኾን ጥሪውን ተቀብላ የሚጠበቅባትን ድርሻ ስታበረክት የቆየች ቢኾንም የልማት ፕሮጀክቱ እውን ኾኖ ውጤታማነቱን እስኪያረጋግጥ ድረስ ብቻ ሳይኾን ቤተ ክርስቲያኒቱ የምታደርገው የተግባር ተሳትፎ ዘወትር ይቀጥላል፡፡

ተግባራችን ሁሉ በእግዚአብሔር ዘንድ የተወደደ ሊኾን የሚችለው ርኅራኄን፣ ቸርነትን፣ ምጽዋትን፣ ትዕግሥትን፣ ፍቅርን፣ ስምምነትን፣ ትሕትናን፣ መረዳዳትን፣ መተዛዘንን ገንዘብ አድርገን የጾምን እንደኾን ነው፡፡ በጾም ወራት ልንፈጽማቸው የሚገቡ የትሩፋት ሥራዎች ብዙዎች ቢኾኑም በተለይ መሠረታዊ የኑሮ ፍላጎት ላልተሟላላቸው ወገኖቻችን ማለትም፤ ልብስ ለሌላቸው ልብስ በማልበስ፣ የምግብ እጥረት ለገጠማቸው የሚቻለንን በመለገሥ፣ ማረፊያ ለሌላቸው መጠለያዎችን በመቀለስ ወገኖቻችንን መርዳት ያስፈልጋል፡፡

በመኾኑም የጾም ዋና ዓላማው ለእግዚአብሔር ቃል በሙሉ ኀይላችን ለመታዘዝ መዘጋጀት ነውና እግዚአብሔር በቃሉ የነገረንን ሁሉ ከመፈጸም ጋራ ሃይማኖታዊና ሀገራዊ ግዴታችንን በመወጣት፣ መንፈሳዊና ማኅበራዊ መርሐ ግብራችንን በማፋጠን፣ መልካም የኾኑትን የልማት ሥራዎቻችንን ሁሉ በማከናወን ወርኃ ጾሙን ልናሳልፍ ይገባል፡፡

እግዚአብሔር አምላካችን ወርኃ ጾሙን በሰላም እንዳስጀመረን ሱባዔውን በሰላም አስፈጽሞ ለብርሃነ ትንሣኤው በሰላም እንዲያደርሰን ቅዱስ ፈቃዱ ይኹንልን፡፡

እግዚአብሔር አምላካችን ሕዝባችንን ይባርክ ይቀድስ፤ አሜን፡፡

አባ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያሪክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአኲስም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት

መጋቢት 2 ቀን 2005 ዓ.ም.

አዲስ አበባ፤

Share this entry
  • Share on Facebook
  • Share on X
  • Share on Pinterest
  • Share on LinkedIn
  • Share on Tumblr
  • Share on Vk
  • Share on Reddit
  • Share by Mail
https://eotc-htc.org/a/wp-content/uploads/logo_am2.png 0 0 tc https://eotc-htc.org/a/wp-content/uploads/logo_am2.png tc2013-03-20 13:50:122013-03-20 13:50:12ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያሪክ አቡነ ማትያስ ዐቢይ ጾምን አስመልክቶ መልእክት አስተላለፉ

መፈለጊያ

Search Search

በቅርብ የተለቀቁ

  • የአርባዕቱ እንስሳ (ኪሩቤል) የንግሥ በዓል በመካነ ሥላሴ ቅዱስ በዓለ ወልድ ቤ/ክ በድምቀት ተከበረ። 
  • ⛪️ከቅዱስ ሲኖዶስ መግለጫ የተቀነጨበ
  • የቅዱስ ሲኖዶስ መግለጫ
  • ቅዱስ ፓትርያርኩ በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል በመገኘት የካቴድራሉ እድሳት የሚገኝበት ደረጃ ጉብኝት አድርገዋል። (መስከረም 2017 ዓ.ም)
  • ከእዚህ በላይ ደስታ ምን አለ፤ እንኳን ደስ አላችሁ፤
  • “ቤተ መቅድሳችንን እናድስ ለቀጣዩም ትውልድ እናድርስ ፣ ኃላፊነታችንንም እንወጣ!” መሪ ቃል
  • ሁላችንም የኢትዮዽያ ልጆች ከከተማ እስከ ገጠር ያለን የመ/ጸ/ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ጠባቂዎች እና ደጋፊዎች ነን‼️
  • ሚያዚያ 10 ቀን 2016 ዓ.ም የመ/ጸ/ቅ/ሥላሴ ካቴድራል ህንጻ ዕድሳትን አስመልክቶ መግለጫ ተሰጠ፤
  • የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ፲፩ኛ ዓመት በዓለ ሢመተ ፕትርክና የካቲት ፳፬/፳፻፲፮ ዓ/ም በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ይከበራል።
  • የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ የጾመ ነነዌ መልዕክት

አስተያየቶች

    © Holy Trinity Cathedral | Website by atbiya.com
      Link to: በሰሜን አዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የስብከተ ወንጌል ማስፋፊያ የአንድነት ጉባኤ መርሃ ግብር ተጀመረ Link to: በሰሜን አዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የስብከተ ወንጌል ማስፋፊያ የአንድነት ጉባኤ መርሃ ግብር ተጀመረ በሰሜን አዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የስብከተ ወንጌል... Link to: በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ለሚጦሩ አረጋወያን ለ6ኛ ጊዜ እረዳታ ተሰጠ Link to: በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ለሚጦሩ አረጋወያን ለ6ኛ ጊዜ እረዳታ ተሰጠ በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ለሚጦሩ...
      Scroll to top Scroll to top Scroll to top