በዓለ ሆሳዕና እና ሰሙነ ሕማማት
እንኳን ለበዓለ ሆሳዕና በሰላም አደረሳችሁ!!
የሆሳዕና በዓል ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በአህያ ጀርባ ተቀምጦ ወደ ኢየሩስአሌም ሲገባ የሚቀድሙት እና የሚከተሉት ህዝብ በተለይም አእሩግ እና ህጻናት “ሆሳዕና ለዳዊት ልጅ በጌታ ስም ሚመጣ የተባረከ ነው፤ ሆሳዕና በአርያም “ በማለት ጌታችንን መቀበላቸው የሚታወስበት በዓል ነው።
ሆሣዕና ከስምንቱ የዐቢይ ጾም እሑዶች አንዱና የመጨረሻው ሳምንት ተብሎ የሚጠራው ከትንሣኤ ቀድሞ የሚገኝ የሕማማት መግቢያ ዋዜማ ነው።
ሆሣዕና ከረቡዕ ጀምሮ የሚታሰብ ታላቅ የቤተክርስቲያን የበዓል ቀን እንደሆነ ይታወቃል። ይህ በዚሁ በዓለ ሰንበትና በዋዜማዎቹ ዕለታት የሚዘመረው ጾመ ድጓ ‘ሆሣዕና በአርያም’’ ‘ሆሣዕና ለወልደ ዳዊት’’ ‘ዕለተ ሆሣዕናሁ አርአየ… ‘ ወዘተ. በማለት ሆሣዕና የሚለውን ቃል ቅዱስ ያሬድና ሌሎችም አባቶች በየቦታው እየጠቀሱና እየተዘመረለት በአህያ ውርንጭላ ላይ ተቀምጦ ኢየሩሳሌም የገባበትን ሁኔታ እየተረከ ስለሚዘምር ይህ ሰንበት በጌትነትና በክብር በውዳሴና ቅዳሴ ሆሣዕና በአርአያም እየተባለ በሽማግሌዎችና በሕፃናት አንደበት በድንጋዮችም ልሳን ሳይቀር እየተመሰገነ ወደ ቅድስት ሀገር ኢየሩሳሌም በከብር ሲገባ ለሰጣቸው ለተቀደሰ ሰላሙና ፍቅሩ መታሰቢያ ሆኖ የተሰጠ ነው። አስቀድሞም በነቢየ እግዚአብሔር ዘካሪያስ እንደተነገረው ‘አንቺ የጽዮን ልጅ ሆይ እጅግ ደስ ይበለሽ ፣አንቺ የኢየሩሳሌም ልጅ ሆይ እልል በይ እነሆ ንጉሥሽ ጻድቅና አዳኝ ነው ትሑትም ሆኖ በአህያም በአህያያቱም ግልገል በውርንጫይቱ ላይ ተቀምጦ ወደ አንቺ ይመጣል… ሰላምን ይናገራል’’ ዘካ.9፣9። በማለት እንደሚመጣና የሠላምንም ብሥራት እንደሚያበሥር ተናገሮ ነበር። ሲመጣም ‘ሁሉም ፈጥነው ልብሳቸውን ወሰዱ በሰገነቱም መሰላል እርከን ላይ ከእግሩ በታች አነጠፉት።’’ በማለት ሊደረግለት የሚገባውን ገልጿል። 2ኛ ነገ. 9፣13 ።
የሆሣዕና በዓል በቤተክርስቲያን ጌታ ወደ ቤተመቅደስ ሲገባ ሕዝቡ ፀበርት ወይም ዘንባባ በመያዝ ‘ቡርክ ዘይመጽእ በስመ እግዚአብሔር – በእግዚአብሔር ስም የሚመጣ የተባረክ ነው።’’ መዝ.117፣26 በማለት ስለተቀበሉት ይህን በማሰብና በማድረግ ቤተክርስቲያናችን ዘንባባ ለሕዝበ ክርስቲያኑ ታድላለች። በቤተክርስቲያን በአራቱም ማዕዘናት ይህን በዓል የሚመለከቱ የቅዱስ ማቴዎስ (ማቴ. 21፣1-17)፤ የቅዱስ ማርቆስ፣(ማር.11፣1-10)፤ የቅዱስ ሉቃስና (ሉቃ.19፣29-38)፤ የቅዱስ ዮሐንስ (ዮሐ.12፣12-15) ወንጌላት ይነበባሉ ።
ታዲያ አኛ ይህን ዐቢይ በዓል የምናከብረው እንዴት ነው? በነቢያቱ ከላይ እንደተገለጠው በወንጌላቱም አንደተፈጸመው እርሱ ወደ እኛ የሚመጣበት ጊዜ መቼ ነው? ሲመጣስ ምን እናድርግ? የእግዚአብሔርን መምጫ ጊዜ ማሰብና መዘጋጀት ያለብን እንዴት ነው? ምክንያቱም
{flike}{plusone}
በዓሉ ከምንም በላይ የሚጠቅመን ለእኛ ነውና ።
ስለዚህ ይህን በዓል ስናከብር ሰላምንና ፍቅርን የእርሱን የክብር አመጣጥ እያሰብን ልንተገብረው ይገባል። ለጌታ የማያስፈልግ ፍጥረት የለም ይልቁንም የክብር ዘውድ አድርጎ በመልኩ የፈጠረው ሰው ያስፈልገዋል።ያለ እግዚአብሔር ፈቃድ የተፈጠረ ማንም የለም።እያንዳንዳችን በእግዚአብሔር ዓላማና ዕቅድ የተፈጠርን እንደመሆናችን መጠን እግዚአብሔር የሚከብርበትን ሥራ ልንሠራ ይገባል።አህያ በሰው ሰውኛ ሲታይ የንቀትና የውርደት ሲመስል ይችላል ።የአህያን ታሪክ በመጽሐፍ ቅዱስ ስንመለከት ግን
- በለዓም በሥጋዊ ገንዘብ መንፈሳዊ ዓይኑ ታውሮ እግዚአብሔር ያልረገማቸውን እስራኤላውያንን ሊራገም ሲሄድ እስራኤላውያንን እንዳይራገም ለመንገር ከእግዚአብሔር ዘንድ የተላከው መልአክ በሚሄድበት መንገድ ላይ ቆሞ ሳለ ከበለዓም ይልቅ ያየችው የበለዓም አህያ ነበረች ። አህያይቱም መልአኩን አክብራ መንገዱን እንደለቀቀችለት ቅዱስ መጽሐፍ ይነግረናል። ዘኅ.22፣23።
- በትንቢተ ኢሳያስ 1፣3 ‘ሰማይ ስሚ ምድርም አድምጪ በሬ የገዢውን አህያም የጌታውን ጋጣ አወቀ እሥራኤል ግን አላወቀም’’ እንደተባለው ጌታ በተወለደ ጊዜ ትንቢቱን ምሳሌውን የሚያውቁ እሥራኤላውያን ባላወቁ ባለተቀበሉ ሰዓት በዚያ በብርድ ወራት እናቱ የምታለብሰው ልብስ አጥታ ቅጠል አልብሳው በነበረ ጊዜ ለጌታ ሙቀት የገበሩለት እረኞቻቸውን ተከትለው የመጡ ከበቶች ላሞችና አህዮች ናቸው። ‘ወአስተማወቅዎ አድግ ወላህም’’ እንዲል አባ ሕርያቆስ በቅዳሴ ማርያም።
- በሆሣዕና ዕለት ከሌሎች እንስሳት ይለቅ ጌታን በከብር የተሸከመችው አህያ ናት። ጌታን የተሸከመችው አህያ ከዚያ በፊት ያላየችውና ያልተደረገላት ክብር ተደርጉላታል። አህያ ከዚህ በፊት ለኛ እህል ተሸክማ ስትሄድ ሂጂ እያልን በዱላ እንደበድባት ነበር፡ ነውም። ነገር ግን በሆሣዕና ዕለት እንኳን በዱላ ልትደበደብ ቀርቶ ሰዎች በእርሷ ላይ ለተቀመጠው ጌታ ሲሉ ልብሳቸውን ሁሉ እያነጠፉላት በንጣፍ ላይ ተራምዳለች ።
ስለዚህ ክርስቶስ በአህያይቱ ላይ እንዲቀመጥባት ልብስም እንደ ተጎዘጎዘላት እኛም ጌታ በፀጋውና በረድኤቱ እንዲያድርብን ልባችንን ከኃጢአትና ከተንኮል አንጽተን ፍቅርንና ትሕትና ልንጎዘጎዝ ይገባል። ጌታ በኛ ላይ በፀጋው ሲያድር በእርሱና በቅዱሳኑ ዘንድ ያለን ክብርና ፀጋ ታላቅ ነው። በነገር ሁሉ መከናወን ይሆንልናል።ክርስቶስን በመሸከሟ የአህያይቱ ታሪክ እንደተለወጠ ሁሉ በክርስቶስ ማደሪያነታችን ያለፈው መጥፎ ታሪካችን ይለወጣል።እንግዲህ በእለተ ሆሣዕና ወደ ኢየሩሳሌም ሲሄድ ሕዝቡ ሁሉ በደስታ በዝማሬ እንደ ንጉሰ እንደተቀበሉት እኛም ሀሴትን አድርገን ‘ሆሣዕና እምርት እንተ አቡነ ዳዊት…’’ በማለት እናመሰግናለን።
የሰሙነ ሕማማት ሃይማኖታዊና ቱፊታዊ ክንዋኔዎች
በዐቢይ ጾም ከሰርክ ሆሳዕና ጀምሮ እስከ ትንሳኤ ሌሊት ያሉት ዕለታት የሚገኙበት ሳምንታት ሰሙነ ሕማማት ይባላል፡፡ ዕለታቱም የዓመተ ፍዳ፣ የዓመተ ኩነኔ መታሰቢያ ናቸው፡፡ በእነዚህ ዕለታት ውስጥ የተለያዩ ትውፊታዊ እና ሃይማኖታዊ ክንዋኔዎች አሉ፡፡ ከነዚህ ክንዋኖዎች ውስጥ አለመሳሳም፣ አክፍሎት፣ ቄጤማ ማሰር፣ ጥብጠባ፣ ጉልባን እና ሕፅበተ እግር ይገኙበታል፡፡ ስለእነዚህ ክንዋኔዎች በቅድስት ቤተ ክስቲያን ስላለው ትውፊታዊ አፈፃፀም መዛግብት አገላብጠን እንደሚከተለው አቅርበናል፡፡
አለመሳሳም፡- በሰሙነ ሕማማት የኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነት ተከታዮች መስቀል እንደማይሳለሙት ሁሉ መጨባበጥ፣ መሳሳምን የትክሻ ሰላምታ መለዋወጥን አይፈጽሙም፡፡ ሰላምታ የማንለዋወጥበት ምክንያት አይሁድ ጌታን ለመስቀል ሰኞ እና ማግሰኞ መከሩ አልሰመረላቸውም፡፡ ምክረቸው የተፈጸመው ረቡዕ ነው፡፡ ስለዚህ አይሁድ እያንሾካሾኩ እንሰቀለው ፤እንግለው ብለው ይማከሩ ነበር፡፡ በዘመነ ፍዳ ወቅት ሠላምና ፍቅር አለመኖሩን የሚገልፅልን በመሆኑ ያንን ለማስታወስ ስላምታ አንለዋወጥም፡፡ መስቀልም አንሳለምም፡፡ ሳምንቱ የክፋት ምክር የተመከረበት እንጂ የፍቅርና የደስታ ሳምንት የታየበት ባለመሆኑ ይህንን በማሰብ ሰላምታ አንለዋወጥም፡፡ አይሁዳ ጌታን በጠላቶቹ ለማስያዝ እኔ የምስመው እርሱ ነው ያዙት ብሎ በሰላምታው ምልክት ሰጣቸው ይህ ሰላምታ አምሐ ቅድሳት አይደለም ተንኮል የተሞለበት እንጂ፡፡ የዲያቢሎስም ሰላምታ ተመሳሳይ ነው፡፡ ሔዋንን ስላም ለኪ ብሎ ነው ያታለላት የይሁዳም ሰላምታ ሰይጣናዊ ነው፡፡ ስለዚህ ይህንን ወቅትና ሁኔታ ለማሰብ በሰሙነ ሕማማት ሰለምታ ልውውጥ የለም፡፡ ዛሬ እየተስተዋለ ያለው ይኽው ሰላምታ ያለመለዋወጥ ሁኔታ ስርወ መሰረቱ ይህ ነው፡፡ ከጥንት ጀምሮ እዚህ ትውልድ ላይ ደርሷል፡፡ ይቀጥላልም፡፡
ሕፅበተ እግር፡- ጌታ በፍጹም ትህትና የደቀ መዛሙርቱን እግር ያጠበበት፣ ከሐዋርያት ጋር ግብር የገባበትና የክርስትና ህይወት ማሕተም የሆነውን ምስጢረ ቁርባን ያከናወነበት ዕለት ነው ጸሎተ ሐሙስ ሕፅበተ እግር ጌታችን በዚህ እለተ እናንተ ለወንድማችሁ እንዲሁ አድርጎ ለማለት የደቀ መዛሙርቱን አግር በማጠቡ ምክንያት የተሰጠ ምሳሌ ነው፡፡ ይህም የሚያሳየው እኔ ለእናንተ እንዳደረኩ እናንተ ደግሞ ታደርጉ ዘንድ ምሳሌ ሰጥቻችኋለሁና እውነት እውነት እላችኋለሁ ባሪያ ከጌታው አይበልጥም መልእክተኛም ከላከው አይበልጥም ይህን ብታውቁ ብታደርጉትም ብጹዓን ናችሁ፡፡ ዮሐ 13፡16-17 በማለት ትህትናውን አሳይቷል ጌታ በዚህ እለተ የደቀ መዛሙርቱን እግር ሲያጥብ እኔ መምህራችሁ ስሆን እግራችሁን ካጠብኳችሁ አርአዬን ሰጥቻችኋለሁ እናንተም የወንድማችሁን እግር ታጥቡ ዘንድ ይገባል፡፡ ነገር ግን ከእናንተ አንዱ ለሞት አሳልፎ ይሰጠኛል አለ ደቀ መዛሙርቱም ማንይሆን አሉ፡፡ ጌታም ህብስት ቆርሼ፣ ከወጡ አጥቅሼ የምሰጠው እርሱ ነው አላቸው፡፡ ደቀ መዛሙርቱ ደንግጠዋል ይሁዳን ማመልከቱ ነበር ለጊዜው አልገባቸውም፡፡ ጌታችን መዳኃኒታችን የሐዋርያቶቹን እግር በማጠብ ትሕትናን ካስተማረቸው በኋላ ቅዱስ ሥጋውንና ክቡር ደሙን የሰጣቸው የኦሪትን መስዋዕት የሻረው እና መስዋዕተ ሐዲስን የሠራው በዚሁ እለት ነው፡፡
አክፍሎት፡- በሰሙነ ሕማማት እለተ ዓርብ ከስግደት በኋላ ምእመናን በየቤታቸው ጥቂት ነገር ለቁመተ ሥጋ ቀምሰው እስከ እሁድ /የትንሳኤ በዓል/ ይሰነብታሉ፡፡ ይህ አክፍሎት ይባላል፡፡ ከዓርብ እስከ ቅዳሜ ሌሊት ለእሁድ አጥቢያ ማክፈል የብዙዎች ነው፡፡ አንዳንዶች ግን ከሐሙስ ጀምረው ያከፍላሉ፡፡ ይህም እመቤታቸን ያዕቆብ እና ዩሐንስ የጌታን ትንሳኤ ሳናይ እህል ውኃ አንቀምስም ብለው እስከ ትንሳኤ መቆየታቸውን ተከትሎ የመጣ ትውፊት ነው፡፡ ይህንን ትውፊት አስመልክቶ ሄሬ ኔዋስ አውሳብዩስ የተባሉ ጸሀፍተ ሐዋርያት በስሙነ ህማማት ከደረቅ ዳቦ እና ከትንሽ ውሃ በቀር እንደ ማይመገቡ እና ከሐሙስ ጀምረው እንደሚያከፍሉ ጽፈዋል፡፡ ይህም ብቻ ሳይሆን ሐዋሪያት ሌሎቹንም እንዲያከፍሉ እንዳሳሰቡና ከሐሙስ ጀምሮ ያልተቻለው ቢያንስ ከዓርብ ጀምሮ እንዲያከፍል ማዘዛቸውን ጽፈዋል፡፡ የእኛ ቤተ ክርስቲያን ትምህርትም ይኽው ነው፡፡ ቅዳሜ ይበላል ማለት ግን ቅዳሴው ሌሊት ስለሆነ በልቶ እንደ ማስቀደስ እና በልቶ እንደመቁረብ ይቆጠራል፡፡ የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ተከታዮችም ይህንኑ ትውፊት ሲከውኑ አያሌ ዘመናት ተቆጥሯል፡፡
ጉልባን እና ቄጠማ፡- ጉልባን ከባቄላ ክክ፣ ከስንዴ ወይንም ከተፈተገ ገብስ ጋር አንድ ላይ ተቀቅሎ የሚዘጋጀና የጸሎት ሐመስ እለት የሚበላ ንፍሮ ነው፡፡ የጉልባን ትውፊት እስራኤላውያን ከግብጽ ተሰደው በሚነጡበት ጊዜ በችኮላ ስለነበር አቡክተው ጋግረው መብላት ያለመቻላቸውን ሁኔታ ያመለክታል፡፡ ያን ጊዜ ያልቦካው ሊጥ እያጋገሩ ቂጣ መብላት ንፎሮም ቀቅለው ስንቅ መያዝ ተግባራቸው ነበር፡፡ ይህን ለማሰብ በሰሙነ ሕማማት ቂጣና ጉልባን በማዘጋጀት በዓል ይታሰባል፡፡ በጸሎተ ሐሙስ ይህንን መሰረት በማድረግ የሚዘጋጀው ጉልባን እንዲሁም ቂጣ ጨው በዛ ተደርጎ ይጨመርበታል፡፡ ጨው ውሃ የሚያስጠማ በመሆኑ የጌታን መጠማት ያስታውሳል፡፡ ይህ ትውፊታዊ ስርዓት በእስራኤላውያን የመጣ ሲሆን በኢትዮጵያ አብዛኛዎቹን የትውፊት ክንዋኔዎች የብሉይ ኪዳን መነሻ ስላላቸው ስርዓቱ ዛሬም ይከበራል፡፡
ጥብጠባ፡- በሰሙነ ሕማማት እለተ ዓርብ ስቅለቱ መታሰቢያ ነው፡፡ ምእመናኑ በሰሙነ ሕማማት የሰሩትን ይናዘዛሉ፡፡ ካህናቱን በወይራ ቅጠል ትከሻቸውን እየጠበጠቡ ቀን ከሰገዱት ስግደት በተጨማሪ ሌላ ስግደት ያዟቸዋል፡፡ ጥብጠባው የተግሳፅ ምሳሌ ነው፡፡ ጥብጠባው የሚደረግለት ሰው በህማማቱ ወቅት የፈጸማ በደል ወይም ኃጢአት ካለ ይህንኑ በመናገር የስግደቱ ቁጥር ከፍ እያለ እንዲል ያደርጋል፡፡ ይህ በስቅለተ ቀን የሚፈጸም ስነ ስርዓት ሲሆን ጥብጣቤ ማለት ቸብ ማድረግ ማለት ነው፡፡ ህዝብ ክርስቲያኑ በእለተ ስቅለት ሲሰግድ ሲጸልይ ሲያነብ ከዋለ በኃላ ሰርሆተ ህዝብ (የህዝብ መሰነባበቻ) ከመሆኑ በፊት በወይራ ቅጠል እያንዳንዱን ምዕመን ጀርባ ቸብ ቸብ መደረጉ የጌታን ግርፋት ያስተውሳል፡፡ ማቴ 26፡26 ማቴ 19፡1-3
ቄጠማ(ቀጤማ)፡- በቀዳም ስዑር ቀሳውቱን ዲያቆናቱ ቃጭል /ቃለ አዋዲ/ እየመቱ ገብረ ሰላመ በመስቀሉ ትንሳኤሁ አግሃደ የሚለውን ያሬዳዊ ዜማ በመዘመር ጌታ በመስቀሉ ሰላምን እንደሰጠ እና ትንሳኤውንም እንደገለጠልን በማብሰር ቄጤማውን ለምእመናን ይሰጣሉ፡፡ ምእመኑም ለቤተ ክርስቲን አገልግሎት የሚውል ገጸ በረከት ያቀርባሉ ቀጤማውንም በራሳቸው ያስራሉ፡፡ ይህም አይሁድ ጌታችንን እያሰቃዩ ሊሰቅሉት ባሉ ጊዜ የእሾህ አክሊል ጭንቅላቱ ላይ ያሰሩበትን ድርጊት የሚያስተውስ ነው፡፡ በዚህ እለት ልብስ ተክህኖ የለበሱ ካህናትና ዲቆናትን ቄጠማ ተሸክመው ቃጭል ሲቃጭሉ መታየታቸው እለተ ትንሳኤውን ለሚናፍቅ ምእመን ትልቅ ብስራት ነው፡፡
ቄጠማው የምሥራች ምልክት ተደርጐ የተወሰደው በኖህ ዘመን ከተፈጸመው ታሪክ ጋር በማቆራኘት ነው፡፡ ቅዱስ መጽሐፍ እንደሚነግረን በጻድቁ ኖኅ ዘመን የነበሩ ሕዝቦች ከሕገ እግዚአብሔር ውጪ ሆነው እጅግ የሚያሳዝን ኃጢአት በሠሩ ጊዜ በንፍር ውኃ ተጥለቅልቀዋል፡፡ በወቅቱ ጻድቁ ኖኅ ወደ መርከብ ይዞአቸው ከገባው እንስሳት መካከል የውኃውን መጉደል ለመረዳት ርግብን በመርከብ መስኮት አሾልኮ ይለቃታል፤ እርሷም ቄጠማ በአፍዋ ይዛ ትመልሳለች፡፡ ዘፍ.9-1-29፡፡ ኖኅም በዚህ ቄጠማ የውኃውን መድረቅ ተረድቶ ተደስቷል፡፡ «ቄጠማ»፣ ለጥፋት ውኃ መድረቅ የምሥራች መንገሪያ እንደሆነ አሁንም በክርስቶስ ሞት ሞተ ነፍስ ከሰው ልጆች ተወገደ ስትል ቤተ ክርስቲያን ለልጆቿ ቄጠማ ታድላለች፡፡ ምእመናንም የምሥራች ተምሳሌት የሆነውን ቄጠማ በግንባራቸው ያስሩታል፡፡ የክርስቶስ ተከታዮች ሁሉ ከጨለማ ወደ ብርሃን ከሚያቃጥለው ዋዕየ ሲኦል /የሲኦል ቃጠሎ/ ወደ ልምላሜ ገነት ጥንተ ማኅደራቸው መመለሳቸውን በዚህ አኳሃን እየገለጡ በዓለ ትንሣኤን በቅድስት ቤተ ክርስቲያን ያከብራሉ፡፡
መጽሐፈ ግብረ ሕማማት ታሪኩ ይዘቱና አገልግሎቱ
ግብረ ሕማማት የሚለው የቃሉ ፍቺ የሕማም የመከራ የስቃይ ሥራ ማለት ነው ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለአዳምና ለዘሩ ደኅነት የተቀበለውን ጸዋትወ መከራ በእለትና በሰዓት ከፍሎ የሚናገር የሚያሳስብ መጽሐፍ በመሆኑ በቤተ ክርስቲያን በሰሙነ ሕማማት የሚደርሱ የምንባብትና የጸሎታትን ዝርዝር በምን ዓይነት ሁኔታና በማን ሊከናውኑ እንዲገባ የሚበይን /የሚናገር/ በመሆኑ ‹‹ግብረ ሕማማት›› ተብሏል፡፡
ታሪኩ፡- የመጽሐፊ ግብረ ሕማማት መቅድም እንደሚገልጸው ‹‹ሐዋርያት ለስብከተ ወንጌል በሚፋጠኑበት ጊዜ ስለ እርሱ ስለጌታችን ታሪኩንና ተአምራቱን ይከታተሉ ከነበሩት መካካል የተከበሩትና የታወቁ ሊቃውንት በኢንፎስና በገማልያል እጅ ተጽፎ በቅድስት ሀገር ኢየሩሳሌም በክብር ቦታ ተቀመጦ የተገኝ ነው›› ይላል ይኸው መጽሐፈ ግብረ ሕማማት የመጽሐፉን የትመጣ ታሪክ ሲተነትን በየትኛው ገብርኤል እነደነበር አይታወቅ እንጂ ገብርኤል በሚባል የእስክንድርያ ፓትርያርክ የፕትርክና ዘመን የአባ መቃርዮስ ገዳም ሊቃውንት በነበረው ይዘቱና አገልግሎቱ ላይ የማሻሻያ /የማሟያ/ ሥራ እንደተሠራለት ያትታል፡፡/የግብረ ሕማማት መግቢያ/ መፅሐፍ ግብረ ሕማማት በወርቃማው የኢትዮጵያ የስነ ጸሑፍ ዘመን በካልዕ ሰላማ ወደ ልሳነ ግእዝ ተተርጎመ ከ 1340-1380 ግብረ ሕማማት ዘእሁድ ገጽ 466 ለዘመናት ከብራና ወደ ብራና በብዙ ድካም ሲገለበጥ የኖረው ‹‹መጽሐፈ ግብረ ሕማማት›› በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ባስልዮስ ዘመን ፕትርክና ታትሞ ተሰራጭቷል፡፡
ይዘቱ፡- የመጽሐፍ ግብረ ሕማማት ይዘት እጅግ አስደናቂ ነው፡፡ በርካታ የሀገር ውስጥና የውጪ የቤተክርስቲያን ሊቃውንት ሥራዎች መድበልም ነው የነገረ ሃይማኖት፣ የታሪክ፣ የተአምራት፣ የሥርዓትና የህገ መጽሐፍ ነው፡፡ ወይም እኒህን ሁሉ በይዘቱ አካቷል፡፡ የመጽሐፉን ይዘት የሚመረምር ሰው ብሉይንና ሐዲስን ነቢያትና ሐዋርያትን ሊቃውንትን አዋልድ መጻሕፍትን በብዛት ያገኛል፡፡ ይኸውም በዕለት እና በሰዓት ተከፍሎ በሥርዓት የተዘጋጀ የትምህርትና የጸሎት መዝገበ መጻሕፍት ነው፡፡ ለምሳሌ ወቅቱን የሚመለከቱ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎችን፣ኦሪትን፣ ነቢያትን፣ ሐዲሳትን፣ ሃይማኖተ አበውን፣ ተግሳጽን፣ ተአምረ ኢየሱስን ተአምረ ማርያምን፣ ወዘተ የያዘ መጽሐፍ ነው፡ ለመፅሐፈ ግበረ ሕማማት ይዘት የኢትዮጵያ ሊቃውንት ፈርጥ የሆኑት ቅዱስ ያሬድና አባ ጊዮርጊስም የድሻቸውን በዜማ የሚጸልዩትን አካትተውልናል፡፡
አገልግሎቱ፡- መፅሐፍ ግብረ ሕማም የስርዓት የምንባብና የጸሎት መጽሐፍ ነው፡፡ ከሆሳዕና ዋዜማ እስከ ትንሳኤ መንፈቀ ሌሊት በእለትና በሰዓት ከፍሎ፣ የቅድመ ተከተሉን መሰረት በማን ምን መባል እልዳለበት እንደ መጽሐፈ ቅዳሴ ሁሉ ይበል ካህን፣ ይበል ዲያቆን እያለ እንዴት ሊፈጸም እንደሚገባ ጽና ይያዙ፣ ጥቁር ይልበሱ፣ በዚህ በኩል ይግቡ፣ በዚህኛው ይውጡ የሚለውን ሥርዓታዊ መመሪያ ለመስጠት ለካህናትና ለምእመናን የሚገባውን ለይቶ የሚተነትን የምስጢርና የትምህርት መጽሐፍ ነው፡፡ መጽሐፈ ግብረ ሕማማት ሕማማተ እግዚእነ ከመንገር ባሻገር ለእንባና ለተመስጦ፣ ለትምህርትና ለተግሳፅ ያገለግላል የልሳነ ግእዝ አንባብያንም በስሙነ ሕማማት ሳይገድፉ በማንበብ ተግባራቸውን በጥንቃቄ የሚፈጽሙበትን የንብብ ችሎታቸውን የሚያሳዩበትም ነው፡፡ በብዙ ጥንታዉያን ገዳማትና አድባራት የብራና ቅጂ ያለው መጽሐፈ ግበረ ህማማተ በስሙነ ሕማማት ከሚሰጠው አገልግሎት በተጨማሪ ለጥናትና ምርመር ምእመናንን በብዙ መልኩ ሊጠቅም የሚችል ይዘት ያለው ነው፡፡
{flike}{plusone}