ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ የትንሳኤ በዓልን አስመልክቶ መልዕክት አስተላለፉ

ቃለ በረከት ዘብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት በእንተ ትንሣኤሁ ለእግዚእነ ወአምላክነ ወመድኃኒነ ኢየሱስ ክርስቶስ ሎቱ ስብሐት

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን፡፡

009
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ

1. በሀገራችን በኢትዮጵያ በገጠርና በከተማ፤

2. ከሀገር ውጭ በተለያዩ አህጉር የምትኖሩ፤

3. የሀገራችንን ዳር ድንበር ለመጠበቅና ለማስከበር በየጠረፉ የቆማችኹ፤

4. በሕመም ምክንያት በየሆስፒታሉ ያላችኹ፤

5. እንዲሁም የሕግ ታራሚዎች ኾናችኁ በማረሚያ ቤት የምትገኙ ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያውያት፤

በትንሣኤው ትንሣኤያችንን ያበሠረን ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንኳ ለ፳፻፭ ዓ.ም በዓለ ትንሣኤው በሰላም አደረሳችኹ፡፡

‹‹እስመ ሐደሰ ለነ ፍኖተ ጽድቅ ወሕይወት ንቅረብ እንከ በልበ ጽድቅ›› ‹‹የሕይወትና የእውነት መንገድን አድሶልናልና ከእንግዲህ በቅን ልቡና ወደ እርሱ እንቅረብ›› (ዕብ. 10÷19) የሰው ልጅ ለማያረጅና ለማያልፍ ሕይወት የታደለ፣ በእግዚአብሔር አምሳልና አርአያ የተፈጠረ፣ እጅግ ክቡርና ታላቅ ፍጥረት እንደነበረ ቅዱሳት መጻሕፍት ይመሰክራሉ፤ በምድር በሚገኙ ፍጥረታት ሁሉ ላይ ያለው የበላይነት ሥልጣንም ይህን ያረጋግጣል፡፡

የሰው ልጅ በእግዚአብሔር ዘንድ ይህን ያህል ጸጋ ቢኖረውም የተሰጠውን ክብርና ልዕልና በአግባቡ ጠብቆ መዝለቅ አልቻለም፤ በእግዚአብሔር ፊት በፈጸመው ከባድ በደል ምክንያት የተሰጠውን ጸጋና ክብር ከማጣቱም በላይ በሕይወት ፈንታ ሞትን፣ በእውነት ፈንታ ሐሰትን፣ በዘለዓለማዊነት ፈንታ ጊዜያዊነትን፣ በማያረጀው ፈንታ የሚያረጀውን ሕይወት ተላብሶ ወደ ምድረ ፍዳ ተባረረ፤ ከእግዚአብሔር ልጅነት ተራቁቶ ከማኅበረ መላእክት ተለየ፤ ረዳት የለሽና ጎስቋላ ሕይወት ተሸክሞ መኖር ጀመረ፡፡

{flike}{plusone}

ለእርሱ ያልተፈጠሩ የሞትና የመቃብር ጎዳናዎች እስከ ስቅለተ ክርስቶስ ድረስ በሰፊው ተጓዘባቸው፡፡ ቅድመ ልደተ ክርስቶስ የነበሩ በሺሕ የሚቆጠሩ ዓመታት ለሰው ልጅ የፍዳ፣ የመርገም፣ የኵነኔ ዓመታት ነበሩ፡፡ ሲኦልና ገሃነም የሰው ዘርን በአጠቃላይ ለመዋጥ አፋቸውን የከፈቱበትና ሰውን ሁሉ በመራራ ሥቃይ የማገዱበት፣ ገነትና መንግሥተ ሰማያት አንድ ስንኳ ለእነርሱ የተገባ ፍጡር የሌለ እስኪመስሉ ድረስ ባዶአቸውን የቀሩበትና ተዘግተው የነበሩበት መራራ ጊዜ ነበር፡፡

እግዚአብሔር እውነተኛ ዳኛ እንደመኾኑ መጠን በሰው በደል ምክንያት ትክክለኛ ፍርዱን ቢያስተላልፍም ከፈራጅነቱ ጎን ለጎን መሐሪነቱን የማያርቅ ለፍጥረቱ እጅግ ሩኅሩኅ ነውና በሰው ላይ የተላለፈው የሞተ ነፍስ ፍርድ በጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መሥዋዕትነት እንዲያከትም አደረገ፤ የተዘጋው የገነት በር እንዲከፈት፣ በሲኦል የተጋዙ ነፍሳት ወደ ገነት እንዲመለሱ፣ ከዚህ ጊዜ ጀምሮ የሰው ጉዞ ወደ ሲኦል መኾኑ ቀርቶ ወደ ገነት እንዲኾን በማድረግ ሰውን በክርስቶስ ደም ታረቀው፡፡ በዚህ ታላቅ መሥዋዕትነት ያረጀውን የሲኦል መንገድ ዘግቶ አዲስ የገነት መንገድን ስለከፈተልን ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ÷ ‹‹አዲስ የእውነትና የሕይወት መንገድ ከፍቶልናልና ከእንግዲህ ወዲህ በቅን ልቡና ወደርሱ እንቅረብ›› እንዳለ በፍጹም ልባችን፣ በፍጹም ሐሳባችን፣ በፍጹም ኀይላችን ወደ እርሱ ልንቀርብ ይገባል፡፡

የተወደዳችኹ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቼ፤

ያረጀው ነገር ሁሉ በክርስቶስ ደም ተቀድሶና ነጽቶ ሐዲስ ኾኖአል፤ አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሠርቶ የሚያሠራ የመልካም ነገር ሁሉ አርኣያና መሪ እንደመኾኑ መጠን አዲሱን መንገድ ከፍቶ እንድንጓዝ ሲያደርግ እኛም በሐዲስ መንፈስ በሐዲስ ሕይወት ልንመላለስበት እንጂ እንደገና ወደአረጀውና ወደአፈጀው ሕይወት ተመልሰን ልንዘፈቅ አይደለም፡፡ አዲስ ሕይወት ማለት እግዚአብሔር ለሰው ዘር ሁሉ መድኃኒት እንዲኾን በላከው በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በማመን የዘለዓለም ድኅነትን ማግኘት ነው፤ ምንም ዐይነት አማራጭ የማይገኝለትን ይህን የእግዚአብሔር የማዳን ጸጋ የሰው ዘር ሁሉ ተቀዳሚ ሥራው አድርጎ ሊቀበለው ይገባል፤ በዚህ በኩል ካልኾነ ሌላ የምንድንበት መንገድ የምናመልጥበት ዐውድ ፈጽሞ የለምና፡፡ በቅዱሳት መጻሕፍት በግልጽ እንደተቀመጠው የክርስትና ሃይማኖት በመልካም ሥነ ምግባር ገዝፎ የሚታይ ሃይማኖት እንጂ በእምነት ብቻ ተደብቆ የሚኖርበት ሃይማኖት አይደለም፤ በርቀት ያለችው ነፍሳችን በግዙፉ ሥጋ ኾና በምትሠራው ሥራ አማካይነት በአካላችን ውስጥ እንዳለች እንደምናውቅ ሁሉ አንድ ክርስቲያንም መልካም ሥራን አብዝቶ ሲሠራ በሥራ ገላጭነት ሃይማኖቱ ገዝፎ በጉልሕ ይታያል፤ በመኾኑም በክርስትና ሕይወት ሃይማኖትና ሥነ ምግባር እንደ ነፍስና ሥጋ ተዋሕደው በአንድነት ሲኖሩ ሕይወተ ነፍስን እንደሚያጎናጽፉ ልብ ብሎ ማስተዋል ይገባል፡፡

የተወደዳችኹ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቼ፤

ከክርስትና ሃይማኖት አስተምህሮ በሚመነጨው መርሕ መሠረት በሥራ በመትጋትና በፍጹም ፍቅር በመኖር ሕይወታችንን ይበልጥ ልናሳድገው ይገባል፤ ከሁሉ በፊት ሰው የተፈጠረው ለሥራና ለክብር እንደኾነ ከቶ ልንዘነጋው አይገባም፤ ይህም ከኾነ ሰው ለአንዲት ደቂቃ ያህል እንኳ እጅ እግርን አጣጥፎ ያለሥራ ሊቀመጥ እግዚአብሔር አልፈቀደም፤ አይፈቅድምም፡፡ በሐፈ ገጽከ ብላዕ ኅብስተከ፤ ወደወጣኽበት መሬት እስክትመለስ ድረስ ጥረኽ ግረኽ ላብኽን አንጠፍጥፈኽ ብላ ነውና የሚለው (ዘፍጥ.3÷19)፡፡ በዙሪያችንም ኾነ በሌላው አካባቢ የተሻለ ኑሮና ክብር ያላቸው ኾነው የሚታዩ ሁሉ የመክበራቸው ምስጢር ጠንክረው መሥራታቸው እንደኾነ በውል ልናጤነው ይገባል፤ እኛ ኢትዮጵያውያንም በታላቁ የሕዳሴ ግድባችን እንደሚታየው ኻያ አራት ሰዓት ሙሉ በትጋት ከሠራን በአጭር ጊዜ ሌሎች የበለጸጉ አገሮች ከደረሱበት የዕድገት ደረጃ የማንደርስበት ምክንያት አይኖርም፤ ዋናው ቁም ነገር ሁላችንም ኢትዮጵያውያን በኅብረት፣ በአንድነት፣ በስምምነት፣ በመተማመን፣ በመቻቻል ለሥራና ለሥራ ብቻ መነሣቱ ላይ ነው፡፡

ይህ ኹኔታ ደግሞ በአሁኑ ጊዜ በአገራችን በጥሩ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ የምናየው ስለኾነ ለምንጣደፍለት የዕድገት ሽግግር ትልቅ መሣርያችን መኾኑን ዐውቀን እንደ ዐይን ብሌን ልንጠብቀው ይገባል፤ ይህ የኾነ እንደኾነ የሕዳሴውን ግድብ ጨምሮ በአገራችን የተጀመሩትን ታላላቅ ሥራዎች ኹሉ ያለጥርጥር ማሳካት እንችላለን፡፡ ‹‹የእውነትና የሕይወት መንገድ አድሶልናልና፤›› የሚለውን የፋሲካ ትምህርተ ሃይማኖት የሕዳሴውን ልማት በማፋጠንና በማሳካት ልንገልጸው ይገባል፡፡ በሌላ በኩል ታላቁን የፋሲካ በዓላችንን ስናከብር ለእኛ ብሎ፣ በእኛ ፈንታ መሥዋዕት ኾኖ የዘለዓለም ሕይወትን ካጎናጸፈን ጌታ ጋራ ማክበር አለብን፤ ፋሲካን ከመድኃኒታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋራ ማክበር የምንችለው የተራቡትን በመመገብ፣ የተጠሙትን በማጠጣት፣ የታረዙትን በማልበስ፣ የታመሙትንና የታሰሩትን በመጠየቅ፣ እንግዶችን ተቀብሎ በማስተናገድ ነው፡፡ ስለኾነም ሕዝበ ክርስቲያኑ ከሃይማኖቱ፣ ከተቀደሰ ሥነ ምግባሩና ባህሉ በወረሰው ሥርዐት መሠረት እንደተለመደው በዓሉን በሰላም፣ በፍቅር፣ በስምምነትና በመረዳዳት፣ ድኾችን ይዞ በመመገብ በመንፈሳዊ ደስታ እንዲያከብር መንፈሳዊ መልእክታችንንና ጥሪያችንን እናስተላልፋለን፡፡

የተቀደሰና የተባረከ የፋሲካ በዓል ያድርግልን፤ እግዚአብሔር አገራችንንና ሕዝባችንን ይባርክ፤ አሜን፡፡

አባ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያሪክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት

ሚያዝያ 27 ቀን 2005 ዓ.ም.

{flike}{plusone}