በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ለሚጦሩ አረጋወያን ለ12ኛ ጊዜ እረዳታ ተሰጠ
በመ/ር ዘሩ ብርሃኔ (Bsc)
“ለችግረኛና ለምስኪን የሚያስብ ምስጉን ነው እግዚአብሔር ከክፉ ያድነዋል፡፡” መዝ. 40÷1
“እግዚአብሔር በደስታ የሚሰጠውን ይወዳልና እያንዳንዱ በልቡ እንዳሰበ ይስጥ”2ኛ ቆሮ. 9÷7
ከዚህ በፊት በተደጋጋሚ በድህረ ገፃችን አማካኝነት ወጣት ብሩክ አስራት የክርስትና ስሙ ግርማ ጽዮን ከዛሬ 12 ወራት በፊት ጀምሮ ለካቴድራሉ አረጋውያን የሚሆን በየወሩ ለአረጋውያኑ የሚያስፈልጋቸውን የምግብ እርዳታ እያደረገላቸው መሆኑን ስንዘግብ መቆየታችን የሚታወስ ሲሆን አሁንም እንደተለመደው ለ12ኛ ጊዜ ለ1 ወር የሚሆን በእነ ወ/ሮ ማርታ ወርቄ፤በወንድሙ እና በጓደኞቹ አማካኝነት እርዳታውን ልኳል፡፡
በዚሁ ዕለት በቄሰ ገበዝ አባ ገ/ዮሐንስ ወ/ሳሙኤል አማካኝነት ለወጣት ብሩክ አስራት፤ለቤተሰዎቹና ለጓደኞቹ ጸሎትና ምስጋና እንዲሁም ቃለ ምእዳን የተሰጠ ሲሆን በወጣት ብሩክ አስራት እየተደረገ ላለው ነገር ሁሉ ምስጋናቸው እጅግ የላቀ መሆኑን ገልፀው ሌሎችም የዚሁ የተቀደሰ ዓላማ ተሳታፊ እንዲሆኑ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፡፡ በመጨረሻም መልአከ ሰላም ማሩ ለወጣት ብሩክ አስራትና ለቤተ ሰዎቹ እያደረገው ላለው ነገር ሁሉ በዓጋዕዝተ ዓለም ሥላሴ ስም ካቴድራሉን በመወከል ምስጋናቸውን አቅርበዋል ፡፡
እነዚህ አረጋውያን ከዛሬ 45 ዓመታት በፊት ከዐፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግስት ጀምሮ በንጉሱ አማካኝነት በካቴድራሉ በጎ አድራጎት /ምግባረ ሠናይ ክፍል ሥር በቃለ ዓዋዲ መሠረት የተቋቋመ ሲሆን ቀደም ሲል በብዙ መልኩ የተደራጀ እንደነበር የሚታወስ ሲሆን አሁንም በካቴድራሉ አስተዳደር አማካኝነት እንደቀድሞ ሁሉ ለማጠናከር ከፍተኛ የሆነ ጥረት እየተደረገ ነው ፡፡
በመሆኑም በዘላቂነተ የአረጋውያኑ ችግር በመጠኑ ለመቅረፍ እንደ ወጣት ብሩክ አስራት የክርስትና ስሙ ግርማ ጽዮን አቅማችሁ የፈቀደውን/የቻላችሁትን ያህል እርዳታ እንድታድርጉ እናሳስባለን፡፡
አረጋውያኑ ከሚያስፈልጓቸው መሠረታዊ ነገሮች መካከል፡- 1. ምግብ፣ 2. መጠለያ፣ 3. ልብስና 4. ሞግዚት ናቸው፡፡ ወጣት ብሩክ አስራት ለእነዚህ አረጋውያን በየወሩ ለጤፍ 980 ብር ፣ ለዘይት 500 ብር ፣ ለበርበሬ እና ሽሮ 680 ብር፣ ለጋዝ 150 ብር፣ ስኳር 140 ብር፣ ሰሙና 86 ብር እና ለሻይቅጠል 50 ብር በድምሩ 2,586 ብር በየወሩ ለአረጋውያኑ ወጪ ያደርጋል፡፡
{flike}{plusone}