የ2006 ዓ.ም የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዐተ ጉባኤ ልዩ ልዩ ውሳኔዎችን በማሳለፍ አጠናቀቀ

2021

ጉባኤው ከጥቅምት 11 ቀን 2006 ዓ.ም. ጀምሮ ላለፉት 10 ቀናት ተወያይቶ ያሳለፋቸውን ውሳኔዎች አስመልክቶ ጥቅምት21/2006 ዓ.ም ከሰዓት በኋላ የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት በተገኙበት በብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ ጋዜጣዊ መግለጫ ተሰጥቷል፡፡ የመግለጫውን ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ይቀርባል፡፡ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ የተሰጠ መግለጫ በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ፤ በዓመት ሁለት ጊዜያት እንዲሆን በፍትሕ መንፈሳዊ አንቀጽ 5 ቁጥር 164 በተደነገገው መሠረት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ የመክፈቻው ሥርዓተ ጸሎት ከተፈጸመበት ከጥቅምት 11 ቀን 2006 ዓ.ም. ጀምሮ እስከ ጥቅምት 21 ቀን 2006 ዓ.ም. ድረስ የተለመደውን ዓመታዊ መደበኛ ስብሰባን በማካሔድ፤ – ለቤተ ክርስቲያናችንና ለኅብረተሰቡ የሚጠቅመውን፤ – ለሀገርና ለዓለም ሰላም የሚበጀውን አጀንዳ በማመቻቸት በስፋትና በጥልቀት ተወያይቶ የሚከተለውን ውሳኔ አሳልፏል፤

1. የ32ኛው አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ውሳኔና የጋራ መግለጫ በምልዓተ ጉባኤ የ2006 ዓ.ም. የሥራ መመሪያ እንዲሆን ጸድቋል፤ 2. ከአጥቢያ ቤተ ክርስቲያን እስከ አዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ጽ/ቤት ድረስ በባለሙያዎች ተጠንቶ የቀረበውና በስላይድ የታየው የሥራ መዋቅር ወደታች ወርዶ በካህናት፣ በምእመናንና በሰንበት ትምህር ቤት ወጣቶች በውይይት ዳብሮ በሚገባ ተጠንቶና ተስተካክሎ ለቋሚ ሲኖዶስ እንዲቀርብና ቋሚ ሲኖዶሱም ዓይቶና ተመልክቶ በሥራ ላይ እንዲያውል ምልዓተ ጉባኤው ወስኗል፤

3. ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን በልማት ዘርፍ ዙሪያ የምታደርገው እንቅስቃሴ በማዕከልም ሆነ በየአህጉረ ስብከቱ በበለጠ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ምልዓተ ጉባኤው ተስማምቷል፤

4. – የአብነት ትምህርት ቤቶችንና የካህናት ማሠልጠኛ ማዕከላትን፤ – በጥንታዊነታቸውና በታሪክ መዘክርነታቸው ዕውቅና ያላቸውን ገዳማት፤ – ወላጅ አልባ ዕጓለማውታ ሕፃናት እየተማሩ የሚያድጉበትንና ሴቶች መነኰሳይያት በምናኔ የሚኖሩባቸውን ገዳማት በበለጠ እንዲጠናከሩ ማድረግ የታመነበት ስለሆነ፤ ለዚሁ አገልግሎት የሚውል በጀት በቤተ ክርስቲያኒቱ ማዕከላዊ አስተዳደር ተጠንቶ ይቀርብ ዘንድ ቅዱስ ሲኖዶስ ቀደም ሲል መመሪያን ሰጥቷል፤ አሁንም በድጋሜ መመሪያውን አጽንጥቷል፤

5. የዓለምን ሰላም፤ ፍቅር አንድነትን ጠብቆ መገኘት የሁሉም ዜጎች ኃላፊነት ስለሆነ ሁሉም ኅብረተሰብ አንድነትን ፈጥሮ አሁን በሀገራችን እየታየ ያለውን አክራሪነትና ጽንፈኝነትን በመቃወም ሰላምን የማስፈን ግዴታውን እንዲወጣ ቤተ ክርስቲያናችን ጥሪዋን ታስተላልፋለች፤

6. ከሀገራችን ውጭ ወደ ውጭው ዓለም ሕጋዊ ባልሆነ መንገድ የሚደረገው ፍልሰት የዜጎችን ሕይወት እየቀጠፈ በሀገርም ላይ ከፍተኛ ቀውስ እያስከተለ መሆኑ ስለሚታወቅ የችግሩን አስከፊነት ኅብረተሰቡ እንዲያውቀው በቤተ ክርስቲያናችን አስፈላጊው ትምህርት እንዲሰጥ ጉባኤው መመሪያ ሰጥቷል፤

7. የእናቶችና የዕጓለማውታ ሕፃናት፣ የአረጋውያንና የአረጋውያት፤ የሁሎችም ፍላጎት ተሟልቶ መኖር ይቻል ዘንድ ኅብረተሰቡ ትኩረት እንዲያደርግ ቅዱስ ሲኖዶስ ያሳስባል፤

8. ሀገራችን ኢትዮጵያ ከኤች አይ ቪ ኤድስ በሽታ፣ ከድንቁርና፣ ከድኅነትና ኋላ ቀርነት ተላቃ ዓለም ወደ ደረሰበት መድረስ የምትችለው ማንኛውም ወገን ተቻችሎና ተከባብሮ ለሰላምና ለልማት ሥራ ሲነሣሣ ስለሆነ፤ ይኸው ታውቆ ሁሉም የየበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ ቅዱስ ሲኖዶስ ጥሪውን ያስተላልፋል፡፡

9. የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በርካታ የሥነ ጽሑፍ፣ የሥነ ጥበብ፣ ሥነ ሥዕልና ኪነ ጥበብ ቅርሶችና ሀብቶች ባለቤት መሆንዋ የታወቀ ስለሆነ፤ የእነዚህ የቤተ ክርስቲያኒቱ የዜማ መጻሕፍት፣ የትርጓሜ መጻሕፍት፣ የሕንፃዎች፣ የቋንቋ በአጠቃላይም ብሔራዊው የአእምሮ ንብረት ባለቤትነት መብቷ በሕግ ይከበር ዘንድ በቅርስ ጥበቃና ምዝገባ በቤተ መጻሕፍት ወመዘክር መምሪያ ተከታታይነት ጉዳዩ ለሚመለከተው የፍትሕ አካል ቀርቦ ውሳኔን እንዲያገኝ፤

10. የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአኵስም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት የሲመተ ፓትርያርክነት በዐል እንደ ቀደሙት ቅዱሳን ፓትርያርኮች የተሾሙበት ዕለት በየዓመቱ የካቲት 24 ቀን እንዲከበር የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ወስኗል፤

11. ስለ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ታሪካዊነትና ቀዳሚነት ሁሉም ሰው መጻፍ ሲገባው ዕውነት ያልሆነውን በማስመሰል የሚነገረውን፣ የሚጻፈውን ዕውነታውንና ትክክለኛውን አስተካክሎ ለሕዝብ ለትውልደ ትውልድ ማስተላለፍ እንዲቻል መነሻ ይሆን ዘንድ በብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት የኮሚቴ አባልነት ተጠንቶ የቀረበውን ጽሑፍ ምልዓተ ጉባኤው በንባብ ሰምቶ ጉዳዩ ወደ ሊቃውንት ጉባኤ ቀርቦ የሊቃውንት ጉባኤውም ስለ ኢትዮጵያ ጥንታዊነትና ታሪካዊነት አብራርቶ፣ አስፍቶና አጉልቶ ለ2006 ዓ.ም. ለርክበ ካህናት ጉባኤ እንዲያቀርብ ወስኗል፤

12. የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኰሌጅ፣ የቅዱስ ፍሬምናጦስ አባ ሰላማ ከሳቴ ብርሃን መንፈሳዊ ኰሌጅ፣ የሰዋሰወ ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ መንፈሳዊ ኰሌጅ የሦስቱም የቤተ ክርስቲያኒቱ መንፈሳውያን ኰሌጆች በጀታቸው ተጠቃሎ ወደጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ገቢ እየሆነ በጀታቸውንም ጠቅላይ ቤተ ክህነቱ እየበጀተ እንዲከፍል ጉባኤው በሙሉ ድምፅ ወስኗል፤ ከዚህም ጋር በቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኰሌጅ ሥር የሚተዳደረው ከኰሌጁ ጋር ተያይዞ የሚገኘው አዲሱ ትልቁ ሕንፃ በጠቅላይ ቤተ ክህነት ቤቶችና ሕንፃዎች፤ አስተዳደርና ልማት ድርጅት ሥር ሁኖ የሕንፃዎቹ ወርኃዊ የኪራይ ገቢም በሕጋዊ መንገድ እንዲሰበሰብ ቅዱስ ሲኖዶስ ወስኗል፤

13. የቤቶችና ሕንፃዎች አስተዳደር ድርጅትን በተመለከተ በሚፈርሱ ቤቶች ምትክ ቸል ሳይባል በትጋትና በንቃት የመልሶ ማልማቱ የሕንፃ ግንባታን ለማካሔድ የሚያግዝ ገንዘብ ማግኘት እንዲቻል ለየአህጉረ ስብከት፣ ለአጥቢያ አብያተ ክርስቲያናትና በጠቅላይ ቤተ ክህነት ሥር ላሉ የልማት ድርጅቶች የአክስዮን ሽያጭ እንዲደረግ ተወስኗል፤

14. ቤተ ክርስቲያኒቱ በሥሯ ያሉ ምእመናኖቿን በትክክል ቆጥራ መመዝገብ እንድትችል በሰበካ ጉባኤ ማደራጃ መምሪያ በኩል ቅጽ ተዘጋጅቶ በየአንዳንዱ ሀገረ ስብከት ኃላፊነት ቆጠራው በየአህጉረ ስብከቱ እንዲካሔድ ተወስኗል፤

15. ስለ ሰንበት ት/ቤቶች ውስጠ ደንብ ተጠንቶ የቀረበው መመሪያ ጸድቆ በሥራ ላይ እንዲውል ተወስኗል፤

16. በጉጂ ዞን ነገሌ ቦረናና የሲዳማ ዞን አህጉረ ስብከትን በተመለከተ በሁለት ተከፍለው ያለመግባባት ችግር ፈጥረዋል በሚል የተነሣው ሁከት ዓመታትን ካስቆጠረ በኋላ ችግሩን የፈጠሩት የሁለቱም ወገኖች ጉዳዩ በዕርቅ እንዲፈጸም ጥያቄ በማቅረባቸው የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ የዕርቀ ሰላሙን ሒደት የተቀበለ በመሆኑ እቦታው ላይ ተገኝተው ዕርቀ ሰላሙን የሚያወርዱ ብፁዓን አባቶችን ሰይሟል፤ ሀ. ብፁዕ አቡነ ማትያስ የካናዳ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፤ ለ. ብፁዕ አቡነ እስጢፋኖስ በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ ረዳትና የጅማ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ሐ. ብፁዕ አቡነ ሉቃስ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊና በክልል ትግራይ የምዕራብ ሰቲት ሑመራ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በመሆን ስምምነቱንና ዕርቀ ሰላሙን አስፈጽመው የመጨረሻ የዕርቁን ሠነድ ለጉባኤው እንዲያቀርቡ ተወስኗል፤

17. የጣና ቂርቆስ ገዳም አንጡራ ሀብት የሆነው መስቀለ ያሬድ ተሠርቆ ወደ ውጭ ተወስዶ ከቆየ በኋላ ወደሀገሩ ተመልሶ በመንበረ ፓትርያርክ ቤተ መጻሕፍት ወመዘክር ስለሚገኝ ገዳሙ መስቀሉ እንዲሰጠው በጽሑፍ በመጠየቁ ምልዓተ ጉባኤው እንዲሰጥ ወስኗል፤

18. የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ልዩ ልዩ ፎቶ ግራፎች፣ መጻሕፍትና የተለያዩ ንዋያተ ቅድሳትና አልባሳት የመሳሰሉትን በተመለከተ ቋሚ ሲኖዶስ ኃላፊነት ወስዶ ኑዛዜም ካለ ሁሉንም እየመረመረና እያጣራ ለየሚመለከታቸው እንዲሰጥ ይደረግ ዘንድ ምልዓተ ጉባኤው ወስኗል፤

19. ቤተ ክርስቲያናችን ወደፊት የምታከናውነውን ማኅበራዊና መንፈሳዊ አገልግሎት በዕቅድ የሚመራ እንዲሆን ለማስቻል በግንቦቱ ርክበ ካህናት ጉባኤ 2005 ዓ.ም. ተቋቁሞ የነበረው ኮሚቴ ያዘጋጀውን ጥናት ለጉባኤው አቅርቦ ጉባኤው ማብራሪያውን ካዳመጠ በኋላ ኰሚቴው ያላለቁ ሥራዎችን እንዲቀጥል በማለት መመሪያን ሰጥቷል ፡፡

20. በጥንታዊቷ፣ በታሪካዊቷ በርዕሰ አድባራት ወገዳማት አኵስም ጽዮን ቤተ ክርስቲያን አውደ ምሕረት በመሠራት ላይ ያለው ቤተ መጻሕፍት ወመዘክሩ ግንባታን አስመልክቶ ከዓቢይ ኮሚቴው በቀረበው ሪፖርት ላይ በመነጋገር በቀጣይ የገቢ ማሰባሰቢያ ስልቶችን ያስቀመጠ ከመሆኑም በላይ ለጊዜው ለተቋራጩ ብር 5,000,000 (አምስት ሚሊዮን ብር) እንዲሰጠውና የቆመው የግንባታ ሥራ እንዲቀጥል ወስኗል፤

21. በቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ ተጠንቶ እንዲቀርብ ስለታዘዘው የማኅበረ ቅዱሳን ደንብ ደንቡን እንዲያጠና የተመደበው ኮሚቴ ጥናቱ ለጊዜው ያልደረሰለት መሆኑን ስለገለፀ ለግንቦት ርክበ ካህናት 2006 ዓ.ም. ጥናቱ ተጠናቆ ለቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ እንዲቀርብ ጉባኤው ትእዛዝ ሰጥቷል፤

22. የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኰሌጅን በተመለከተ ኰሌጁን ማጠናከር አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ ለኰሌጁ ዋና ዲን እንዲሾም ጉባኤው ውሳኔን አሳልፏል፤

23. ገዳማቱን መልሶ ማቋቋምና ማጠናከር ብሎም በነበሩበት ሁኔታ አደራጅቶ ሥራቸውን መቀጠል ይችሉ ዘንድ የሚያመለክት በመምሪያው በኩል ሰፊ ጥናት የተደረገ በመሆኑ ገዳማቱ የሚገኙትም በየአህጉረ ስብከቱ ስለሆነና ብፁዓን አበው የሌሉበት ጥናትም አጥጋቢ ውጤት ስለማይኖረው የተወሰኑ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ከመምሪያው ተጠሪ ጋር ተገናኝተው ገዳማቱ እንዴት መቋቋምና መልማት እንዳለባቸው ጥናት ይደረግበት በሚለው ጉባኤው ተስማምቶ ጠለቅ ያለ ሀሳብ ከነመፍትሔው አጥንተው ለግንቦቱ 2006 ዓ.ም. ርክበ ካህናት ዓመታዊ ጉባኤ እንዲያቀርቡ፤ 1. ብፁዕ አቡነ ኤጲፋንዮስ የምዕራብ ሸዋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስን 2. ብፁዕ አቡነ ሳሙኤል የልማትና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን ሊቀ ጳጳስና የሕንፃዎችና ቤቶች አስተዳደር ድርጅት የበላይ ኃላፊን 3. ብፁዕ አቡነ ቀሌምንጦስ የከምባታ ሐዲያና ጉራጌ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስን በመምረጥ ምልዓተ ጉባኤው በሙሉ ድምፅ ተስማምቶ ወስኖአል፡፡

24. የመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ሕንፃ ከጊዜ ብዛት የተነሣ ውሀ በማስገባቱ እድሳት የሚያስፈልገው ስለሆነ የእድሳቱም ጥናት በመቅረቡ የካቴድራሉ ሕንፃ የቅድስት ቤተ ክርስቲያናችንና የሀገር ቅርስ እንዲሁም የቱሪስቶች መዳረሻ በመሆኑ የውስጥና የውጭ ቁመናውን እንደያዘ በጥንቃቄ እድሳቱ እንዲደርግ ጉባኤው ወስኗል፤

25. በውጭ ሀገር ከሚገኙ የቤተ ክርስቲያን አባቶች ጋር ተጀምሮ የነበረው ዕርቀ ሰላም ወደፊት እንዲቀጥልና የቤተ ክርስቲያኒቱ አንድነት እንዲጠናከር ጉባኤ ተስማምቷል፤

26. በውጭው ዓለም ገለልተኛ አብያተ ክርስቲያናት ነን በሚል የሚገኙ ወገኖች ወደ እናት ቤተ ክርስቲያናቸው እንዲመለሱ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ጥሪውን አቅርቧል፤

27. የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ጥንታዊትና ታሪካዊት እንደመሆኗ ሁሉ በቀጣይም አጠቃላይ ማኅበራዊም ሆነ መንፈሳዊ ሥራዎቿን በመሪ ዕቅድ በመምራት ሙስናና የመልካም አስተዳደር እጦትም ከሥሩ መቅረፍ እንዲቻል በባለሙያዎች የተጠናውን የመሪ ዕቅድ ዘገባ በመገምገም በቀጣይ ዕቅዱ ዳብሮ በሥራ መተርጎም በሚቻልበት ሁኔታ ተዘጋጅቶ እንዲቀርብ ጉባኤው መመሪያ ሰጥቷል፤

28. አሁን ያለው ሕገ ቤተ ክርስቲያን ተሻሽሎ እንዲቀርብ በተወሰነው መሠረት የተሻሻለው ረቂቅ ሕገ ቤተ ክርስቲያን የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት እንዲመለከቱት ረቂቁ የታደለ ሲሆን እንዲሁም በሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ታይቶና ሐሳብ ተሰጥቶበት በ2006 ዓ.ም. ግንቦት ርክበ ካህናት ውይይት እንዲካሔድበት ምልዓተ ጉባኤው ተስማምቷል፤ ቅዱስ ሲኖዶስ ከላይ በተገለፁትና በሌሎችም መንፈሳውያንና ማኅበራውያን ጉዳዮች ላይ ለዐሥር ቀናት ያህል ሲወያይ ሰንብቶ አስፈላጊውን በመወሰን መደበኛ ስብሰባውን በዛሬው ዕለት በጸሎት አጠናቋል፡፡

ቸሩ እግዚአብሔር አምላካችን ለሀገራችን፣ ለሕዝባችን፣ ለዓለሙ ሁሉ ሰላሙን፣ ምሕረቱንና ፍቅር አንድነቱን ይስጥልን ፡፡

እግዚአብሔር አምላካችን ይባርከን፤ ይቀድሰን፤ አሜን ፡፡

አባ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአኵስም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ጥቅምት 21 ቀን 2006 ዓ.ም.

{flike}{plusone}