ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማቲያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት የ2006 ዓ.ም.የ2006 ዓ.ም. ዐብይ ጾምን አስመልክቶ ቃለ ምዕዳን አስተላለፉ
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማቲያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት የ2006 ዓ.ም. ዐቢይ ጾም አስመልክቶ እንኳን በሰላም አደረሳችሁ ባሉበት ወቅት “ጾም ለመንፈሳዊ ሕይወት መጎልበት፣ ራስን ለመግዛት፣ ከእግዚአብሔር ጋር ልዩ ግንኙነትና አንድነት ለመፍጠር እጅግ አስፈላጊ ነው” ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ቅዱስነታቸው ዐብይ ጾሙን አስመልክቶ ያስተላለፉትን ሙሉ ቃል ከዚህ በታች ይመልከቱ፡፡
መልእክት ዘእም ኀበ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአኵስም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት በእንተ በዓለ ጾም ዓቢይ ዘእግዚእነ ወአምላክነ ወመድኃኒነ ኢየሱስ ክርስቶስ ሎቱ ስብሐት፡፡
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን፡፡
በሀገር ውስጥም ኾነ በውጭ የምትኖሩ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ምእመናንና ምእመናት የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን በሙሉ፡-
እግዚአብሔር አምላክ እንኳን ለ፳፻፮ ዓ.ም. የጌታችን የአምላካችንና የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ መዋዕለ ጾም በሰላም አደረሳችኁ፡፡
‹‹ወእመሰ በምግባረ መንፈስ ቀተልክምዎ ለምግባረ ነፍስትክሙ ተሐይዉ ለዓለም፤ በመንፈሳዊ ሥራ ሥጋዊ ሥራችኹን ብትገድሉ ለዘላለሙ ትድናላችኹ፡፡›› /ሮሜ ፰÷፲፫/
ጾም ከጥንት ጀምሮ በዘመነ ብሉይም በዘመነ ሐዲስ የተወደደ፣ የፈቃደ ሥጋ መቆጣጠሪያ፣ የፈቃደ ነፍስ ማበልጸጊያ መሣርያ ነው፤ እነሙሴ፣ እነኤልያስ እና እነዳንኤል ከእግዚአብሔር ጋራ በቀጥታ ይገናኙ የነበረው ራሳቸውን በጾም ለእግዚአብሔር በማስገዛት ነው፡፡
ጌታችን አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ዓርባ መዓልትና ዓርባ ሌሊት ጾሞ፣ በሰይጣን የቀረበለትን ፈተና አሸንፎ፣ የጾምን ድል አድራጊነት በተግባርና በትምህርት አሳይቶናል፤ (ማቴ. ፬÷፩ -፲፩)
ቅዱሳን ሐዋርያትም እግዚአብሔር ሥራቸውን እንዲያቃናላቸው፣ ኃይለ መዊዕ (የአሸናፊነት ኃይል) እንዲሰጣቸው በየጊዜው ይጸልዩ ነበር፤ (ግብ. ሐዋ. ፲÷፳፫)
ሐዋርያዊት፣ ጥንታዊትና ህልውት በኵሉ የኾነች የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንም ከነቢያት፣ ከጌታችንና ከሐዋርያት በተማረችው ትምህርትና በተቀበለችው ትውፊት መሠረት ከእግዚአብሔር ጋራ ለመገናኘት፣ ኃይለ አጋንንትን ድል ለማድረግ፣ ከእግዚአብሔር በረከትንና ረድኤትን ለማግኘት ጾምን ትጾማለች፡፡
ሰው በተፈጥሮው እርስ በርስ የሚጋጩ ኹለት ፍላጎቶች በውስጡ እንዳሉ ቅዱስ መጽሐፍ ይነግረናል፤ እነዚኽ ፍላጎቶች ሥጋዊና መንፈሳዊ ተብለው የሚታወቁ ሲኾን፣ የሥጋ ፍላጎት ለነፍስ ፍላጎት፣ የነፍስ ፍላጎትም ለሥጋ ፍላጎት ተቃራኒ እንደኾነ በቅዱሳት መጻሕፍት ተብራርቶና ተገልጾ ተቀምጦአል፡፡ (ገላ. ፭÷፲፮-፲፰)
ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ይህን በተመለከተ ሲያስተምር ‹‹የሥጋ ፍላጎት ሞትን ያመጣል፤ የነፍስ ፍላጎት ግን ሰላምንና ሕይወትን ይሰጠናል፤›› ብሏል፤ (ሮሜ ፮÷፮-፰)
የጾም አስፈላጊነት የሚመነጨውም ከዚኽ መሠረታዊ ትምህርት ነው፡፡ ሥጋ ኃይልና ሙቀት ሰጪ ምግቦችን አብዝቶ በተመገበ ቁጥር ኃይል ይሰማዋል፤ በዚኽ ጊዜ ለእግዚአብሔር መታዘዝን ይዘነጋል፤ ወንድሙን ለመበደል ይፈጥናል፤ ማመዛዘን አይችልም፤ ብዙ ስሕተትንም ይፈጽማል፤ በመጨረሻም ይሞታል ማለትም ከእግዚአብሔር ጋራ አንድነትን ያጣል፤ በመንፈሳዊ እይታ ከእግዚአብሔር አንድነት መለየት እጅግ በጣም የከፋ ሞት ነው፡፡
በአንጻሩ ደግሞ ሰው ከምግብ በታቀበ ጊዜ ረጋ ብሎ ማሰብን፣ ማስተዋልን፣ ማመዛዘንን፣ ለእግዚአብሔር መታዘዝን፣ ራስን መግዛትን፣ ርኅራኄንና ቸርነትን፣ ለወንድም አዛኝነትን ገንዘብ ያደርጋል፤ በመጨረሻም ከእግዚአብሔር ጋራ አንድነቱን ያጠነክራል፤ በዚኽም የሞት አሸናፊ ኾኖ በእግዚአብሔር መንግሥት በዘላለማዊ ሕይወትና ክብር ተደስቶ ይኖራል፤
ከዚኽ አኳያ ጾም ለመንፈሳዊ ሕይወት መጎልበት፣ ራስን በመግዛት ከእግዚአብሔር ጋራ ልዩ ግንኙነትና አንድነት ለመፍጠር እጅግ አስፈላጊ ኾኖ ይገኛል፡፡
ጾማችን በእግዚአብሔር ፊት ተቀባይነት አግኝቶ ሙሉ ዋጋ ሊያሰጠን የሚችለው ከፍቅር፣ ከምጽዋት፣ ከሰላም፣ ከጸሎትና ራስን ለእግዚአብሔር ከማስገዛት ጋራ ሲኾን ነው፡፡
የተወደዳችኹ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቼ ምእመናንና ምእመናት!
በፍጹም ሓሳባችን፣ በሙሉ ኃይላችንና በፍጹም ልቡናችን ለእግዚአብሔር በምንገዛበት በዚኽ ወቅት ካለን ሀብት ከፍለን፣ በየሰፈሩ የሚገኙ ጧሪ የሌላቸው አረጋውያንን፣ አሳዳጊ የሌላቸው ሕፃናትን፣ ሠርተው ራሳቸውን መርዳት ያልቻሉ አካል ጉዳተኞችን በመርዳት ጾሙን ልንጾም ይገባል፡፡
ወርኃ ጾም በመንፈሳዊ ሕይወታችንም በሥጋዊ ኑሯችን ከምንም ጊዜ በበለጠ ግዙፍና ታላላቅ ሥራዎችን ሠርተን የምናጠናቅቅበት ጊዜ ሊኾን ይገባል፡፡
በተለይም በመንፈሳዊ ሕይወታችን ለእግዚአብሔር ያለንን ተገዥነት ለማረጋገጥ፣ በመንፈስና በጽድቅ ኾነን በየቀኑ አብዝተን የምንጾምበትና የምንሰግድበት ሊኾን ይገባል፡፡
በሥጋዊ ኑሯችንም ሥራ ከሚያስፈቱን ነገሮች ኹሉ ርቀን ቀኑን በሙሉ በሥራ ላይ የምናውልበት ሊኾን ይገባል፡፡ በመኾኑም ሕዝበ ክርስቲያኑ በአገራችን የተጀመረውን የአረንጓዴ ልማት ለማሳካት አፈርን የመገደብና መስኖን የማስፋፋት ሥራ አጠናክሮ እንዲሠራና ወርኃ ጾሙን በላቀ የሥራ ርብርብ እንዲያሳልፍ መልእክታችንን ከአደራ ጭምር እናስተላልፋለን፡፡
በመጨረሻም፡-
እግዚአብሔር አምላክ ወርኃ ጾሙን መልካም የንስሐ፣ የሰላም፣ የፍቅርና የሥራ ጊዜ አድርጎ በማስፈጸም ለጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዓለ ትንሣኤ በሰላምና በጤና እንዲያደርሰን በጾምና በጸሎት እንትጋ በማለት መልእክታችንን በድጋሚ እናስተላልፋለን፡፡
እግዚአብሔር አምላክ ኢትዮጵያንና ሕዝባችንን ይባርክ ይቀድስ አሜን!!
አባ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ
ሊቀ ጳጳስ ዘአኵስም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት
የካቲት ፲፮ ቀን ፳፻፮ ዓ.ም.
{flike}{plusone}