ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማቲያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት የ2006 ዓ.ም.የትንሣኤ በዓልን አስመልክቶው ቃለ ምዕዳን አስተላለፉ

0908

ቃለ በረከት ዘብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት
በእንተ ትንሣኤሁ ለእግዚእነ ወአምላክነ ወመድኃኒነ ኢየሱስ ክርስቶስ
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን
•    በሀገራችን በኢትዮጵያ በገጠርና በከተማ የምትኖሩ፣
•    ከሀገር ውጭ በተለያዩ አህጉር የምኖሩ፣
•    የሀገራችንን ዳር ድንበር ለመጠበቅና ለማስከበር በየጠረፉ የቆማችሁ፣
•    በሕመም ምክንያት በየሆስፒታሉ ያላችሁ፣
•    እንዲሁም የሕግ ታራሚዎች ሆናችሁ በየማረሚያ ቤቱ የምትገኙ ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያውያት በሙሉ፤
እርሱ ሕያው ሆኖ ሕያዋን መሆናችንን በትንሣኤው ላበሠረን ለጌታችን  ለአምላካችንና ለመድኃኒታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ በዓለ ትንሣኤ እንኳን በሰላም አደረሳችሁ!!
‹‹ወርኢናሃ ለሕይወት፤ ወተዐውቀት ለነ፤
ሕይወትን አየናት፣አወቅናትም›› (1ዮሐ1÷2)
የሕይወት መገኛና ምንጭ አምላካችን እግዚአብሔር ነው፣ ከእግዚአብሔር የተገኘው ሕይወት የሰው ልጅ የዕውቀት ብርሃን ነው፤ አምላካዊ ሕይወት ካለው ሰው የሚፈልቅ ብርሃናዊ ዕውቀት ጽልመታዊውን ዓለም በብሩህነቱ ያሸንፋል እንጂ በጽልመታዊ ዓለም አይሸነፍም፡፡ (ዮሐ.1÷4-5)
    የሰው ልጅ ሕያው አምላክ በመልኩና በአምሳሉ የፈጠረው ፍጡር በመሆኑ  ሕያውና ክቡር፣ ዘላለማዊና ብርሃናዊ፣ የማሰብ፣ የማመዛዘን፣ የመምረጥና፣ የመወሰን ነጻነት ያለውና ከሌሎች ፍጥረታት ሁሉ የላቀ አእምሮ ያለው ልዑል ፍጡር ነው፤
    ሰው ከእግዚአብሔር በተሰጠው ነጻነትና አእምሮ መሠረት ነጻነቱን ተጠቅሞ የመረጠውን የማድረግ ነጻነት ያለው ፍጡር ቢሆንም በነጻ ዕውቀቱና ምርጫው ለሚፈጽመው ሁሉ እርሱ  ራሱ ኃላፊነቱን ይወስዳል፤
ይህም ማለት በምርጫው መሠረት የሚሠራው ሥራ ሁሉ በእውነተኛው ዳኛ በእግዚአብሔር ፊት መልካም ሆኖ ከተገኘ ምስጋናን፣ መልካም ሆኖ ካልተገኘ ግን ተጠያቂነትንና ፍርድን ያስከትልበታል ማለት ነው፡፡
ከዚህ አንጻር የመጀመሪያ ሰው የሆነው አዳም ማድረግ ያለበትንና ማድረግ የሌለበትን ተለይቶ ከእግዚአብሒር ቢነገረውም የተነገረውን ሕግ ወደጎን ገሸሽ በማድረግ የራሱን ነጻ ምርጫ ተጠቅሞ ‹‹አትብላ›› የተባለውን በላ፤
በመሆኑም ይህ ድርጊት በእግዚአብሔር ዘንድ እጅግ ታላቅ ስሕተትና ድፍረት  ነበረና ተጠያቂነትን አስከተለ፣ በመጨረሻም ሕይወትን የሚያሳጣ የሞት ፍርድንና ቅጣትን በራሱና በልጆቹ ሁሉ ላይ አመጣ፡፡
ፍርዱ ሥራ ላይ ከዋለበት ቀን ጀምሮ ሰው ሕይወቱን አጣ ማለትም ከእግዚአብሔር አንድነት ተለየ፤ ሞትና ሲኦልም ሰውን ከእግዚአብሔር ለይተውና የራሳቸው ተገዥ አድርገው እስከ ስቅለተ ክርስቶስ ድረስ በቁጥጥራቸው ሥር አዋሉት፡፡
ሆኖም እግዚአብሔር በባህርዩ መሐሪና ፈራጅ እንደመሆኑ መጠን ለፈራጅነቱና ለመሐሪነቱ የሚስማማ መንገድ አመቻችቶ መሐሪነቱንና ፈራጅነቱን በፈጸመበት በክርስቶስ ሞት ቤዛነት የሰው ልጅን ታረቀው፤ ያጣውንም ሕይወት መለሰለት፤ በምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያን አማካኝነትም እንደገና ሕይወቱን እንዲያገኝ አደረገ (ዮሐ. 6÷56-58፤ ማር 16÷16)
    ይህን አስመልክቶ ቅዱስ ጳውሎስ ሲናገር‹‹በመጀመሪያው ሰው (አዳም) ሞት መጣ፣ በሁለተኛው ሰው (ክርስቶስ) ግን ትንሣኤ ሙታን ሆነ፤ሁሉም በአዳም እንደሚሞቱ እንደዚሁ ሁሉም በክርስቶስ  ሕያዋን ይሆናሉ›› ብሏል፤ (1ቆሮ 15÷21-22፤ሮሜ 5-12-19)
ከዚህ የምንረዳው ዓቢይ ቁም ነገር በአዳም አለመታዘዝ ምክንያት ያጣናት ሕይወት፣ በክርስቶስ መታዘዝ ያገኘናት መሆናችንን ነው፤ ጌታችንም ‹‹ትንሣኤና ሕይወት እኔ ነኝ፤ የሚያምንብኝ ቢሞት እንኳ ሕያው ይሆናል፤ ሕያው የሆነም፣ የሚያምንብኝም፣ ሁሉ ለዘላለም አይሞትም፤እኔም በመጨረሻይቱ ቀን አስነሣዋለሁ›› ብሎ ትንሣኤና ሕይወት መሆኑን እንደነገረን የሰው ልጅን ለዘላለማዊ ሕይወት እንደገና አበቃው (ዮሐ. 6÷54፤ 11÷25-26)
የዚህም እውነታ በትንሣኤው አበሰረን፣ የእርሱ ትንሣኤ የትንሣኤያችን ዋዜማ ነውና የቀደመችው ሕይወት እንደተመለሰችልን በትንሣኤው አየናት፤ አወቅናትም፤(ኤፌ.4÷5-7)
        የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቼ ምእመናንና ምእመናት
     የክርስቶስ ትንሣኤ ለሰው ልጅ የዘላለማዊ ሕይወት ማረጋገጫ ነው፤ለበርካታ ዘመናት በተስፋ ይጠበቅ የነበረው የክርስቶስ ነገረ አድኅኖ እና ነገረ ትንሣኤ በጊዜው ጊዜ እውን እንደሆነ ሁሉ፣ እንደዚያው በተስፋና በእምነት እየተጠባበቅነው ያለ የሰው ልጅ ሕይወታዊ ትንሣኤ ጊዜው ሲደርስ በክርስቶስ ዳግም ምጽአት እውን ይሆናል፤(1ቆሮ 15÷20-23፤1ተሰ 4÷13-18)
 ይሁን እንጂ ዛሬም ሕይወትን በሚሰጥ በእግዚአብሔር መንግሥት ውስጥ ያለን ስለሆን የሕይወትን ጣዕም አሁንም ማጣጣም እንችላለን፤ ሕይወት ጣዕም የሚኖረው በፍቅር ሲታጀብ ነው፣ ፍጹም ፍቅር የዘላለማዊ ሕይወት ኃይል ነው፤ ፍቅር ፍጹም የሚሆነው ሦስቱን አቅጣጫዎች ማእከል አድርጎ ሲገኝ ነው፤
 ይኸውም ወደ ላይ እግዚአብሔርን በፍጹም ፍቅር መከተል ስንችል፣ ወደጎን በአርአያ እግዚአብሔር የተፈጠረውን የሰው ልጅ በአጠቃላይ መውደድ ስንችል፣ ወደ ታች ደግሞ የምንኖርባትን ምድርና በውስጧ ያሉ ፍጥረታትን ስንንከባከብ ነው፣ ይህን ካደረግን ፍጹም ፍቅር ከእኛ  አለ ማለት እንችላለን፤ እግዚአብሔር ይህንን ዓይነት ፍቅር እንዲኖረን በሃይማኖት አስተምሮናል፡፡
    በመሆኑም እኛ ክርስቲያኖች ለእግዚአብሔር ያለንን ፍቅር ለመግለጽ በመዋዕለ ጾሙ በአምልኮ፣ በጾም፣ በጸሎት፣ በምጽዋትና በስግደት ስንገልጽ እንደቆየን ሁሉ፣ በፋሲካው በዓላችን እግዚአብሔር የሰጠንን በረከት ከተቸገሩ ወንድሞቻችንና እኅቶቻችን ጋር በመካፈል ለወገኖቻችን ያለንን ፍቅር ልንገልጽ ይገባናል፤
በዚህ ዕለት በዓሉን ስናከብር የተራቡትን በማብላት፣ የተጠሙትን በማጠጣት፣ የታረዙትን በማልበስ፣ ጧሪ የሌላቸው አረጋውያን፣ አሳዳጊ የሌላቸው ሕጻናት፣ በልዩ ልዩ ምክንያት የአካልና የአእምሮ ጉዳት ደርሶባቸው የበይ ተመልካች የሆኑ ወገኖች ሁሉ ከእኛ ጋር በማዕዳችን ተሳታፊ ሆነው በዓሉን በደስታና በምስጋና እንዲያከብሩ ማድረግ ክርስቲያናዊ ግዴታችን ነው፡፡
            የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቼ ምእመናንና ምእመናት
የትንሣኤ መሠረታዊ ትርጉም ከሞት በኋላ በሕይወት መኖርና መመላለስ ነው፤ ስለሆነም የትንሣኤን በዓል ስናከብር ባለፉት ዘመናት በድህነትና በኋላ ቀርነት ከሞት አፋፍ ደርሳ የነበረችውን ሀገራችን በልማትና በዕድገት ትንሣኤዋን ለማረጋገጥ ቃል በመግባት በዓሉን ማክበር ሀገራዊ ብቻ ሳይሆን ሃይማኖታዊ ግዴታ መሆኑን መገንዘብ አለብን፤
 ምክንያቱም ጠንክረን በመሥራት ምድራችንን እንድናለማና እንድንከባከብ ከሁሉ በፊት ያዘዘ እግዚአብሔር ነውና፤ በተለይም የልማታችን የጀርባ አጥንት ሆኖ እንደ ሚያገለግል ታላቅ ተስፋ የተጣለበት ታላቁ የሕዳሴ ግድብ በተያዘው ፍጥነት ሥራው ተሠርቶና ተጠናቆ የዕድገታችን ተሸካሚ ምሶሶ ሆኖ ማየት እንድንችል ሁሉም ኢትዮጵያዊ ድጋፉን አጠናክሮ እንዲቀጥል ቤተ ክርስቲያናችን ጥሪዋን ታስተላልፋለች፤
    የሀገራችን የልማትና የዕድገት መርሐ ግብሮች ዘርፈ ብዙ እንደመሆናቸው መጠን ገበሬው በየአካባቢው እያከናወነው የሚገኝ አፈርን የመገደብና አካባቢን በአረንጓዴ ልማት የማስዋብ ሥራ ያለመቋረጥ ተጠናክሮ እንዲቀጥል በማድረግ ረገድ ቤተ ክርስቲያችን በግባር ቀደም ተሰልፋ እንደምትሠራ በዚህ አጋጣሚ ለማረጋገጥ እንወዳለን፡፡
    በአሁኑ ጊዜ በሥራ ላይ ያሉም ሆኑ ወደፊት ሊሠሩ በእቅድ የተያዙ የሀገራችን የልማትና የእድገት ሥራዎች በሕዝቡ የተባበረ ድጋፍ ሲከናወኑ የሀገራችን ብልጽግና እውን እንደሚሆን የሁላችንም እምነት ነው
ስለሆነም ለዚህ ስኬት የኢትዮጵያውን ሁሉ ጽናት፣ አንድነት፣ ስምምነትና ፍቅር፣ ሰላምና ተቻችሎ መኖር የማይተካ ሚና እንዳላቸው ለአፍታ እንኳ መዘንጋት የለብንም፤
          የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቼ ምእመናንና ምእመናት
ልማታችን በተፈጥሮ ሀብት እንክብካቤ ብቻ ሳይሆን የተቀደሰውና የተከበረው ባህላችንና ሰብኣዊ ሥነ ምግባራችንን ጠብቆ በማስጠበቅ ጭምርም መሆን ይገባዋል
ኢትዮጵያ ሀገራችን ከጥንት ጀምሮ በቅዱሳት መጻሕፍት ሀገረ እግዚአብሔር ነች ተብሎ በተደጋጋሚ የተነገረላት ያለምክንያት አልነበረም
ኢትዮጵያውያን አባቶቻችን በማናቸውም ጊዜ ከነውረ ኃጢአትና ከርኩሰት ሁሉ ርቀው፣ ሕገ ተፈጥሮንና ሕገ እግዚአብሔርን ጠብቀው፣ እግዚአሔር የሚለውን ብቻ አዳምጠውና አክብረው የሚኖሩ ቅዱሳን በመሆናቸው እንጂ
በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ ምድር ሊፈጸም ቀርቶ ሊወራ የማይገባውን ሰዶምንና ገሞራን በእሳት ያጋየ ግብረ ኃጢአት በኢትዮጵያ ምድር መሰማቱ እግዚአብሔር ለኢትዮጵያውያን የሰጠውን የቅድስና ክብር የሚያሳጣ ከመሆኑም ሌላ በሀገራችን ላይ ልማትና ዕድገት ሳይሆን መቅሰፍትና ውድቀት እንዳያስከትልብን ሁሉም ኢትዮጵያዊ ይህንን የሰዶም ግብረ ኃጢአት በጽናት መመከት አለበት፤
ተፈጥሮን ለማልማት እየተረባረብን እንደሆነ ሁሉ ከዚህ ባልተናነሰ ሁኔታ የሰዶም ግብረ ኃጢአትን በመከላከል በቅዱስ ባህልና ሥነ ምግባር እጅግ የበለፀገና የለማ ትውልድ ማፍራት የልማታችን አካል ማድረግ አለብን፤
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ይህንን ግብረ ኃጢአት እስከ መጨረሻው ድረስ አምርራ የምትዋጋው መሆኑን በዚህ አጋጣሚ ለመላው ኢትዮጵያውያን ወገኖቻችን ማረጋገጥ እንፈልጋለን፤  ስለሆነም ሕዝባችን ለሰላምና ለአንድነት፣ ለእኩልነትና ለልማት፣ ለቅዱስ ባህልና ሥነ ምግባር ቅድሚያ ሰጥቶ በሁሉም አቅጣጫ ልማቱን እንዲያፋጥን፣ ሃይማኖቱንም እንዲጠብቅ መልክታችንን እናስተላልፋለን፡፡
መልካም የትንሣኤ በዓል ያድርግልን!!
እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝባችንን ይባርክ  ይቀድስ አሜን !!

አባ ማትያስ ቀዳማዊ
ፓትያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ
ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖ
ሚያዝያ 12 ቀን 2006 ዓ.ም
አዲስ አበባ

{flike}{plusone}