የሐምሌ ሥላሴ በዓለ ንግሥ በመንበረ ጸባዖት ቅድሥት ሥላሴ ካቴድራል ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ በተገኙበት በታላቅ ድምቀት ተከብሮ ዋለ!!
በየዓመቱ ሐምሌ 7 ቀን የሚከበረው የአጋዕዝተ ዓለም ሥላሴ መለኮታዊ በዓለ ንግሥ በዘንድሮው ዓመት 2007 ዓ.ም ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት ፣ ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳትና በርካታ ምዕመናን በተገኙበት በታላቅ ድምቀት የተከበረ ሲሆን ሥርዓተ ቅዳሴው በብፁዕ አቡነ ሄኖክ የምሥራቅ ወለጋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ተመርቶአል፡፡
በሥርዓተ ቅዳሴው አጋማሽ ላይ “የእግዚአብሔር ቸርነት ምድርን ሞላች ፣ በእግዚአብሔር ቃል ሰማዮች ፅኑ ፣ ሠራዊታቸው ሁሉ በአፉ እስትንፋስ” መዝ 33፤6 የሚለው የዳዊት መዝሙር በዜማ ተሰምቶአል፡፡ በመቀጠልም “ዮሐ 8፤51 ላይ እውነት እውነት እላችኋለሁ ቃሌን የሚጠበቅ ቢኖር ለዘለዓለም ሞትን አያይም የሚለው የወንጌል ቃል ተነቧል፡፡
እንደ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ የበዓሉ መሠረታዊ የት መጣ በኦሪት ዘፍጥረት ምዕ 20 እና 22 ላይ የተመሠረተው የአባታችን የአብርሃም ታሪክ የተፈጸመበት ጥንተ ታሪክ ነው፡፡ አብርሃም የጣኦት አምልኮ ከተስፋፋበት ከካራን በመውጣት ወደ ተቀደሰችው ምድረ ርስት ወደ ከነአን የገባበት ታሪክ ሲሆን ከካራን ከወጣ በኋላ እግዚአብሔር አብርሃምን ለመፈተን እና የእምነቱን ፅናት ለማረጋገጥ አብርሃምን ልጅህ ይስሐቅን ሰዋልኝ ባለው ጊዜ አብርሃም ሳያመነታ ፣ ልጁን ይስሐቅን አስከትሎ ፣ እንጨት፣ ቢላዋና እሳት ይዞ ወደ መሰዊያ ቦታ ወደ ተራራ ወጣ፡፡
አብርሃም ልጁ ይስሐቅን ለእግዚአብሔር መስዋዕት አድርጎ ለማቅረብ ዝግጁ ቢሆንም እግዚአብሔር ግን ለይስሐቅ ተለዋጭ የሆነ ቀንዶቹ ብዕፀ ሳቤቅ የታሠሩ ነጭ በግ በማቅረቡ ከሰማይ የተላከው ነጭ በግ የይስሐቅ ተለዋጭ በመሆን የተሰዋ መሆኑን ሊቁ ቅዱስ ያሬድ በድርሰቱ ሲአብራራ “አብርሃም ወሰዶ ለይስሐቅ ወልዱ ከመይሱኦ አውረደ ሎቱ ቤዛሁ በግአ” በማለት አብራርቶአል፡፡ ከሰማይ የወረደው የይስሐቅ ተለዋጭ የሆነው ያ በግ የጌታችንና የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ምሳሌ መሆኑን የአዲስ ኪዳን መጻሕፍት ይገልፃሉ፡፡
በዚሁ እለት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት ታለቁንና መለኮታዊ የሆነውን የአጋዕዝተ ዓለም ሥላሴን በዓል አስመልክተው ያስተላለፉትን ትምህርትና ቃለ በርከት እንደሚከተለው አቅርበነዋል፡፡
ዘአቀበ ቃልየ ኢይጥእሞ ለሞት ዮሐ 8፤5
በዚህ መንፈሳዊ ጉባኤ ላይ የተሰበሰብን የሥላሴ ፍጡሮች ነን፡፡ ሥላሴ ሰማዩን፣ ምድሩን፣ ሰውን እና እንስሳውን የፈጠሩ ናቸው፡፡ ጸሎታችንን ተቀብለው የለመናቸውን ይሰጡናል፤ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቃሌን የጠበቀ ሞትን አያይም ብሏል፡፡ አይሁድ ግን አባታችን አብርሃም ሞቷል አንተ ከማን ትበልጣለህ አሉት፡፡ አይሁድ ሳይገባቸው ጌታን ነቀፉት ፤ ሰው የጽድቅን ሥራ ከሠራ ዘለዓለማዊ ሕይወት ያገኛል፡፡ ስለዚህ ክርስቲያን የእግዚአብሔር ስጦታ ይጠብቀዋል፡፡ ሁሉም መንገደኛ ነው ፤ በዚህ ዓለም ላይ ሆነን ድሆችን በመርዳት የታመሙትን በመጠየቅ የተጨነቁትን በማጽናናት መልካም ሥራ መሥራት አለብን፡፡
ሥላሴ በመካከላችን አሉ ፤ ቃሉን ጠብቀን ከኖርን የመንግሥተ ሰማያት ዜጎች እንሆናለን፡፡ ቃሉን የጠበቀ ሞተ ነፍስን አይቀምስም ሥለሴ በአብርሃም ቤት ተስተናገዱ በሚለው መሠረትነት ነው በዓላችንን ያከበርነው ፤ ሥላሴ በረከታቸውን ያሳድሩብን በማለት ቅዱስነታቸው ሰፋ ያለ መልእክት ካስተላለፉ በኋላ የበዓሉ ፍጻሜ ሆኗል፡፡
{flike}{plusone}