የመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ሰበካ ጉባኤ ጽ/ቤት በተለምዶ 22 ማዞሪያ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ የሕንፃ ግናባታው ተጀምሮ ቆሞ የነበረውን ሕንፃ ግንባታ ለማስጀመር የውል ሰነድ ተፈራረመ

                                                                                                                                              በመ/ር አምሃ ኃብቴ(BA)

01369

የመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ሰበካ ጉባኤና ልማት ኮሚቴ ቀደም ሲል ከበጎ አድራጊው ክቡር በኵረ ምዕመናን ከበደ ተካልኝ 1634 ካሬ ሜትር ቦታ በስጦታ አግኝቶ በ1070 ካሬ ሜትሩ ላይ የሕንፃ ግንባታው ከተጀመረ በኋላ በተለያዩ ምክንያቶች ለተወሰኑ ዓመታት ቆሞ የቆየ ቢሆንም የዲዛይን ክለሳ ተደርጎለት በአሁኑ ሰዓት  ሕንፃውን ለማስጀመር ተገቢውን ሕጋዊ የጨረታ ሂደት ካከናወነ እና ከፈጸመ በኋላ ጥቅምት 20 ቀን 2008 ዓ.ም ጨረታውን ካሸነፈው ከባማኮን ኢንጂነሪንግ ኃ.የተ.የግ.ማኅበር ጋር የውል ስምምነት ፈጸመ፡፡ የካቴድራሉ ሰበካ ጉባኤ ጽ/ቤት ከላይ ከተጠቀሰው ድርጅት ጋር የውል ስምምነቱን ሲፈጽም የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ተወካይ ልዑካን፣ የኤም ጂ ኤም ኮንሰልት ኃ.የተ.የግ.ማኅበር ተወካይ፣ የካቴድራሉ ሰበካ ጉባኤ፣ ልማት ኮሚቴ አባላትና የአስተዳደር ሠራተኞች በተገኙበት የፊርማ ስነ ሥርዓቱ ተከናውኗል፡፡
የሕንፃው አጠቃላይ ወጪ ብር ቫትን ጨምሮ 72‚280‚478.00 (ሰባ ሁለት ሚሊዮን አራት መቶ ሰባ ስምንት ብር ብቻ) ሲሆን ነገር ግን የግንባታ ሥራው በሁለት ምዕራፍ እንዲሠራ ከተቋራጭ ድርጅቱ ጋር ስምምነት ላይ በመደረሱ ለመጀመሪያው ምዕራፍ ሥራ ውል ተፈጽሟል፡፡የመጀመሪያው ምዕራፍ ሥራው የሚያካትተው፡-
1.የኮንክሪት ሥራ ሙሉ ለሙሉ
2.የጣሪያ ሥራው ሙሉ በሙሉ
3.የግድግዳ ሥራ ማለትም ብሎኬትና ጡብ ሥራ በአጠቃላይ
4.የብረት ውቅር ሥራና ተያያዥ ሥራዎች በሙሉ
5.የልስንና ተያያዥ ሥራዎች በሙሉ
6.የመብራት መስመር ዝርጋታ 1-10.3 ድረስ
7.የንፁህ ውሃ አቅርቦትና የፍሳሽ ማስወገጃ መስመር ዝርጋታ ሥራዎች ከተራ ቁጥር 4-5 ድረስ ያካትታል፡፡ ይህንን ሥራ ለመሥራት አጠቃላይ ወጪው ከቫት በፊት ብር 27‚681‚604.80 (ሃያ ሰባት ሚሊዮን ስድስት መቶ ሰማንያ አንድ ሺህ ስድስት መቶ አራት ብር ከሰማንያ ሳንቲም) ሲሆን ሥራውን ለማጠናቀቅ 365 ቀናት የሚያስፈልጉት መሆኑንም ስምምነት በተደረገበት ቀን ተገልጿል፡፡ በዚህ አጋጣሚ የተቋራጭ ድርጅቱ ባለቤት ክቡር ኢንጂነር ግርማ ገላው  ከዚሁ ገንዘብ ላይ የ4% (የአራት በመቶ) ቅናሽ ያደረጉልን በመሆኑ ስለአደረጉልን ቅናሽ የካቴድራሉ አስተዳዳሪ ክቡር ሊቀ ሥልጣናት አባ ገብረ ሥላሴ በላይ በካቴድራሉ ሰበካ ጉባኤ ጽ/ቤት ስም አመስግነው አጠር ያለ ትምህርት ከሰጡ በኋላ የፕሮግራሙ ፍጻሜ ሆኗል፡፡
የሕንፃው አጠቃላይ ይዘት ሕንፃው በ1070 ካሬ ሥፋት ቦታ ላይ ያረፈ ሲሆን ቤዝመንት፣ ምድር ቤት፣ መዳረሻ፣ አምስት ወለል (ፎቅ) እና  መዳረሻ (B+G+M+5+M)  ያለው ዘመናዊ ሕንፃ ነው፡፡
ሕንፃው የሚሰጠው አገልግሎት ሕንፃው ሁለገብ አገልግሎት የሚሰጥ ሲሆን ቤዝመንቱ ለመኪና ማቆሚያ (parking lot) ፣ ምድር ቤቱ ለባንከ፣ ለኢንሹራንስና ሌሎች ተያያዥ አገልግሎት ለሚሰጡ ሥራዎች የሚሆን ሲሆን አምስቱ ወለሎች ደግሞ ለቢሮ፣ለሱቅ፣ አዳራሾችና ተያያዥ አገልግሎት የሚሰጡ ክፍሎች ያሉት ነው፡፡

{flike}{plusone}