የመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል የ2008 ዓ.ም የፋሲካ በዓልን ምክንያት በማድረግ ለበርካታ ችግረኞች ታላቅ የምሳ ግብዣ አደረገላቸው!!

pp002

በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሥር የሚገኘው የመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል እሑድ ሚያዚያ 30 ቀን 2008 ዓ.ም ቁጥራቸው ከ1,000 በላይ ለሚሆኑ ነዳያን /ችግረኞች  ሰፊ የሆነ የምሳ ግብዣ ያደረገላቸው መሆኑን የዝግጅት ክፍላችን ከቦታው ድረስ በመሄድ አረጋግጧል፡፡
ይህ ታላቅ የምሳ ግብዣ የተከናወነበት ቦታ ቀደም ሲል በነገሥታቱ፣ በመሳፍንቱ፣ በመኳንንቱና በደጅአዝማቾቹ ዘመን በተመሠረተውና 107 ዓመት እድሜ ባስቆጠረው የካቴድራሉ የሰንበቴ ቤት አዳራሽ መሆኑ ታውቋል፡፡
ይህ የችግረኞች የምሳ ግብዣ በካቴድራሉ ለብዙ ዘመን ሲከናወን የቆየ ሲሆን በዘንድሮው 2008 ዓ.ም የፋሲካ በዓል የተዘጋጀው መስተንግዶ ግን ሰፋ ያለ መሆኑን የዝግጅቱ አስተባባሪዎች ገልፀውልናል፡፡
ለችግረኞቹ የምሳ ግብዣ የዋለው የገንዘብ ወጪ በሰሙነ ሕማማቱ ለጸሎት ከሚመጡ ማኅበረ ምዕመናን በስጦታ የተሰበሰበ መሆኑንና ለአንድ ጊዜ የምሳ ግብዣ ከብር 20,000 ያላነሰ ገንዘብ ወጪ መደረጉን የዝግጅት ዐቢይ ኮሚቴው ጨምሮ አብራርቷል፡፡
ወደ ምሳ ግብዣ አዳራሽ እንዲገቡ የተደረጉት ችግረኞች ማየት የተሳናቸው፣ በክራንችና በውልቸር የሚሄዱና በዕድሜ ምክንያት አቅመ ደካማ የሆኑት የመግቢያ ትኬት እየያዙ ቅድሚያ ተሰጥቷቸው ወደ ምሳ ግብዣ አዳራሹ እንዲገቡ በማድረግ የግብዣው ተሳታፊ እንዲሆኑ ተደርጓል፡፡
ከዚህም በተጨማሪ የኑሮ ውድነት አጥቅቷቸው የሚበሉትና የሚጠጡት አጥተው፣ ነገር ግን ወደ አደባባይ ወጥተው ከሕዝብ ርዳታ ለመጠየቅ ተሸማቅቀው፣ በመጠለያቸው ውስጥ ተቀምጠው የችግር ሰለባ ለሆኑት 100 ችግረኞች ኮሚቴው ከቤታቸው ድረስ በመሄድ የዱቄትና የዘይት ርዳታ ለማድረግ ቅድመ ዝግጅቱን ያጠናቀቀ መሆኑን ለዝግጅት ክፍላችን አብራርቷል፡፡
የመንበረ ጸባዖት ቅድሥት ስላሴ ካቴድራል የቅዱሳን ፓትርያርኮች በዓለ ሲመት የሚከበርበትና ልዩ ልዩ የቤተክርስቲያን የሥርዓት በዓላት የሚከበርበት፣ ከቅዱሳን ፓትርያርኮች ጀምሮ እስከ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ድረስ ያሉት በሞተ ሥጋ ከዚህ ዓለም ሲለዩ ሥጋቸው በክብር የሚያርፍበት፣ ነገሥታቱ፣ መሳፍንቱ፣ መኳንንቱ ከዚህ ዓለም በሞተ ሥጋ  ሲለዩ ሥጋቸው በክብር የሚያርፍበት፣ እንደዚሁም ታላላቅ የጥበብ ሰዎች ከዚህ ዓለም በሞተ ሥጋ ሲለዩ ሥጋቸው በክብር የሚያርፍበት ታላቅና ታሪካዊ ካቴድራል ነው፡፡ በልማቱም ዘርፍ ቢሆን ካቴድራሉ እያሳየ ያለው እንቅስቃሴ በቀላሉ የሚገመት አይደለም፡፡

ስለሆነም አንባብያን ስለ ካቴድራሉ ሁለገብ አግለግሎት መረዳት ይችሉ ዘንድ ስለ   ካቴድራሉ አጠር ያለ ታሪካዊና ልማታዊ ማብራሪያ እንደሚከተለው አቅርበናል፡፡
የመንበረ ጸባኦት ቅድቅት ሥላሴ ካቴድራል
የመንበረ ጸባኦት ቅድሥት ሥላሴ ካቴድራልና የበዓለ ወልድ ቤተ ክርስቲያን በአራዳና ጉለሌ ክፍለ ከተማ ሥር የሚገኝ ሲሆን በዳግማዊ አፄ ምኒልክ ዘመነ መንግሥት በ1883 ዓ.ም ተመሠረተ፡፡ አንዳንድ የታሪክ መዛግብት እንደሚናገሩት ዳግማዊ አጼ ሚኒሊክ ባዩት ራዕይ መሠረት ታቦቱን (ጽላቱን) ወረኢሉ ከሚገኘው ከማሕበረ ሥላሴ በማስመጣት በቤተ መንግሥታቸው ሰሜናዊ አቅጣጫ ላይ ባሠሩት የባለወልድ ቤ/ክ አስቀምጠዋል፡፡ የበዓለ ወልድም ቤተ ክርስቲያንም የተመሠተው በዚሁ  በ1883 ዓ.ም በዳግማዊ አፄ ምኒልክ ሲሆን በአሁኑ ዘመን አገልግሎት እየሰጠ የሚገኘው የመንበረ ጸባኦት ቅድሥት ሥላሴ ካቴድራል ሕንጻ ሥራ ግንባታ እንዲቀጥል ለማድረግ በ1924 ዓ.ም ግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት የመሠረት ድንጊያ አኖሩ፡፡ ካቴድራሉ በአሁኑ ሰዓት 163 ሠራተኞችን ያስተዳድራል፡፡ ዓመታዊ የገንዘብ ገቢው 15,289,779.00 ተገምቷል፡፡
በካቴድራሉ እየተሠሩ የሚገኙ የልማት ሥራዎች
በተለምዶ ሃያ ሁለት እየተባለ በሚጠራው አካባቢ በኩረ ምእመናን ከበደ ተካልኝ በተባሉ አንድ በጐ አድራጊ ምእመናን በነፃ በተበረከተና 1,634 ካሬ ሜትር ስፋት ባለው ቦታ ላይ ባለ 6 ፎቅ የሕንፃ ግንባታ ሥራ የተጀመረ ሲሆን ይህ ግዙፍ ሕንፃ በ1070 ካሬ ሜትር ስፋት ቦታ ላይ ያረፈ ነው፡፡ ካቴድራሉ ከአፀደ ሕጻናት ጀምሮ እስከ ሁለተኛ ደረጃ በደረሰው ት/ቤት ብዛታቸው 2255 የሚደርሱ ተማሪዎችን ያስተምራል፡፡
በትምህርት ቤቱ በመማር ማስተማር ሂደት በወር እስከ ስምንት መቶ ሺህ ብር የሚደርስ የገንዘብ ገቢ ያስገኛል፡፡ ትምህርት ቤቱ በሚአገኘው ወርሐዊ የገንዘብ ገቢ ለወርሐዊ ወጪው ራሱን የቻለ መሆኑ ተረጋግጧል፡፡ ት/ቤቱ ብዛታቸው 12 የሚደርሱ ወላጅ አልባ ሕጻናትን በነፃ ያስተምራል፡፡ የካቴድራሉን ዲያቆናት በግማሽ ክፍያ ያስተምራል፡፡ በበዓለወልድ ቤተ ክርስቲያን ዋና በር አካባቢ ከ2005 ዓ.ም ጀምሮ የሕንጻ ግንባታ ሥራው ሲካሄድ ቆይቶ 2008 ዓ.ም ጥር ወር ላይ በብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ ተባርኮ ለአገልግሎት ተዘጋጅቶ የሚገኝ ባለ 3 ፎቅ ሕንፃ ግንባታ ሲሆን ይህ ሕንጻ በ580 ካሬ ሜትር ስፋት ላይ ያረፈ ነው፡፡ ለሕንጻ ግንባታ ሥራው አጠቃላይ የወጣ የገንዘብ ወጪ 18,137,000.00 ሲሆን ሕንጻው አገልግሎት መስጠት ሲጀምር በዓመት ከብር 72,000,000.00 ያላነሰ የገንዘብ ገቢ እንደሚአስገኝ ተገምቷል፡፡
የሕንጻውን አገልግሎት በተመለከተ ከምድር ቤቱ በታች እስከ አንደኛው ፎቅ ያለው ለመካነ መቃብር አገልግሎት ይውላል፣ ሁለተኛው ወለል ደግሞ ለካህናት ማረፊያ የሚውል ሲሆን ይህም 21 ክፍሎች አሉት፡፡
የመጨረሻውና 3ኛው ፎቅ 476 ሜትር ስፋት ያለው ዘመናዊ ሁለገብ አዳራሽ ነው፡፡ በሕንጻው ሥር የሚገኙ ፉካዎች ብዛት 1396 ሲሆኑ ከእነዚህም ለአፅመ ምእመናን ማሣረፊያ አገልግሎት የሚውሉ 1205 ፉካዎች ናቸው፡፡
በካቴድራሉ ት/ቤት ሊሠሩ የታቀዱ የልማት ሠራዎች
የካቴድራሉ ሕንጻ በጊዜ ብዛት የተነሳ የመሰንጠቅ ሂደት የታየበት በሆኑ በተገቢው ሁኔታ እንዲታደስ ማድረግ፣ ቀደም ሲል የካቴድራሉ ይዞታ የሆነውንና ደርግ ወርሶት የነበረውን ቦታ ማስለቀቅ፣ የካቴድራሉ ግቢ በመቃብር የተጨናነቀ በመሆኑ ከሰባት ዓመት በላይ ዕድሜ ላላቸው አፅመ ምእመናን ማስቀመጫ ቤት መሥራትና የካቴድራሉን ግቢ ማስፋት የሚሉት ይገኝባቸዋል፡፡

ምንጭ፡-www.addisababa.eotc.org.et

{flike}{plusone}