የሐምሌ ሥላሴ በዓለ ንግሥ በመንበረ ጸባዖት ቅድሥት ሥላሴ ካቴድራል በታላቅ ድምቀት ተከብሮ ዋለ!!

1846

በየዓመቱ ሐምሌ 7 ቀን የሚከበረው የአጋዕዝተ ዓለም ሥላሴ መለኮታዊ በዓለ ንግሥ በዘንድሮው ዓመት 2008 ዓ.ም ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት ፣ ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳትና በርካታ ምዕመናን በተገኙበት በታላቅ ድምቀት ተከብሯል፡፡

በበዓሉ ላይ ብፁዕ አቡነ እንድሪያስ የካቴድራሉ የበላይ ኃላፊ በቅዱስነታቸው መልካም ፈቃድ እለቱን አስመልክተው ሰፋ ያለ ትምህርት የሰጡ ሲሆን በመጨረሻም ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት  የአጋዕዝተ ዓለም ሥላሴ በዓልን አስመልክተው ሰፊ ትምህርት ወንጌልና ቡራኬ ሰጥተዋል::
ሐምሌ 7 ቀን እግዚአብሔር አምላክ በአብርሃም ቤት የገባበትና ሣራ ይስሐቅን እንደምትወልድ የተናገረበት ዕለት በመኾኑ በቤተ ክርስቲያን በየዓመቱ በደማቅ ሥርዓት ይከበራል፡፡ ታሪኩም በአጭሩ እንዲህ ነው፤
አባታችን አብርሃም ከተመሳቀለ ጐዳና ድንኳን ሠርቶ መንገደኞችን ኹሉ በእንግድነት እየተቀበለ ሲያስተናግድ ይኖር ነበር፡፡ ጥንተ ጠላታችን ሰይጣን ለተንኮል አያርፍምና ይህንን መልካም ግብሩን ለማሰናክል አስቦ የተጐዳ ሰው መስሎ ከጐዳና ቆሞ ወደ አብርሃም ቤት የሚሔዱ እንግዶችን አብርሃም እንግዳ መቀበል እንደ ተወ፤ እርሱም ሊበላ ሊጠጣ ከቤቱ ቢሔድ ራሱን ፈንክቶ፣ ደሙን አፍሶ፣ አጥንቱን ከስክሶ፣ ልብሱን ገፎ እንደ መለሰው አድርጎ እየተናገረ እንግዳ ወደ ቤቱ እንዳይመጣ አደረገ፡፡ አብርሃምም ማዕደ እግዚአብሔርን ያለ ምስክር (ያለ እንግዳ) አልመገብም ብሎ ሦስት ቀን ሳይመገብ ጾሙን አደረ /ቅዳሴ ማርያም አንድምታ ትርጓሜ/፡፡
በሦስተኛው ቀን እግዚአብሔር በሦስት ሰዎች ተመስሎ ከአብርሃም ቤት ገብቷል፡፡ በኦሪት ዘፍጥረት ተጽፎ እንደምናገኘው በቀትር ጊዜ አብርሃም በድንኳኑ ደጃፍ ተቀምጦ ሳለ እግዚአብሔር በመምሬ አድባር ዛፍ ለአብርሃም ተገልጦለታል፡፡ አብርሃምም ሦስት ሰዎች በፊቱ ቆመው ባየ ጊዜ ሊቀበላቸው ከድንኳኑ ደጃፍ ተነሥቶ ወደ እነርሱ ሮጠ፡፡ ወደ ምድርም ሰገደና አቤቱ በፊትህስ ሞገስ አግኝቼ እንደ ኾነ ባሪያህን አትለፈኝ ብሎ ተማጸነ፡፡ እዚህ ላይ ሦስት ሰዎች… ሊቀበላቸው… ወደ እነርሱ… የሚሉት ሐረጋት ሦስትነቱን፤ በፊትህስ ሞገስ አግኝቼ እንደ ኾነ ባሪያህን አትለፈኝ የሚለው ዐረፍተ ነገር ደግሞ አንድነቱን ያመለክታል፡፡
በመቀጠልም አብርሃም *ጥቂት ውኃ ይምጣላችሁ፤ እግራችሁን ታጠቡ፤ ከዚህችም ዛፍ በታች ዕረፉ፡፡ ቍራሽ እንጀራም ላምጣላችሁ፤ ልባችሁንም ደግፋ ከዚያም በኋላ ትሔዳላችሁ ስለዚህ ወደ ባሪያችሁ መጥታችኋልና* ሲላቸው እነርሱም እንዳልህ አድርግ ብለውታል፡፡ በዚህ ኃይለ ቃልም የእግዚአብሔርን ሦስትነት እንረዳለን፡፡ የዘፍጥረት አንድምታ ትርጓሜ እንደሚያስረዳው አብርሃም ሥላሴን ጌቶቼ ከቤት ገብታችሁ ዕረፉ ሲላቸው ደክሞናልና አዝለህ አስገባን ብለውታል፡፡ እርሱም እሺ ብሎ አንዱን አዝሎ ቢገባ ሁለቱ በግብር አምላካዊ ከቤቱ ገብተዋል፡፡
አብርሃምም ወደ ሣራ ዘንድ ፈጥኖ ገባና *ሦስት መሥፈሪያ ዱቄት ፈጥነሽ አዘጋጂ፤ ለውሺውም፤ እንጎቻም አድርጊ አላት፡፡ እርሷም እንዳዘዛት አደረገች፡፡ ሦስት መሥፈሪያ የሦስትነት፤ ዳቦው አንድ መኾኑ የአንድነት ምሳሌ ነው፡፡ አብርሃምም ወደ ላሞቹ ሔዶ ወይፈን አምጥቶ አርዶ አወራርዶ አዘገጅቶላቸው ተመግበዋል፡፡ ነገር ግን ሥላሴ በሰው አምሳል ስለ ተገለጡና ለአብርሃም የበሉ መስለው ስለ ታዩት ተመግበዋል ተባለ እንጂ ለሥላሴ መብል መጠጥ የሚስማማቸው ኾኖ አይደለም፡፡ መምህራነ ቤተ ክርስቲያን እንዳስተማሩን ሥላሴ ምግብ በሉ ማለት ቅቤ ከእሳት ገብቶ አልቀለጠም እንደ ማለት ነው፡፡
ከዚያ በኋላ እግዚአብሔር አብርሃምን ጠርቶ ሚስትህ ሣራ ወዴት ናት አለው፡፡ አብርሃምም ከድንኳኑ ውስጥ እንዳለች ነገረው፡፡ አዚህ ላይ እግዚአብሔር ሣራ ወዴት ናት ሲል መጠየቁ ያለችበት ጠፍቶት ሳይኾን የሚነግራት ታላቅ የምሥራች እንዳለ ያጠይቃል፡፡ ይኸውም አዳም ወዴት ነህ ከሚለው ጥያቄ ጋር ተመሳሳይነት አለው /ዘፍ.3፥9/፡፡ እግዚአብሔር አዳምን ወዴት ነህ ሲል የጠየቀው ያለበትን ዐላውቅ ብሎ ሳይኾን ቃል በቃል ሊያነጋግረውና ከልጅህ ተወልጄ አድንሃለሁ የሚለውን ቃል ኪዳን ሊገባለት ነበር፡፡ እንደ አዳም ኹሉ ለሣራም ለጊዜው ይስሐቅን እንደምትወልድ፤ ለፍጻሜው ግን እግዚአብሔር ከአብርሃም ወገን ከምትኾን ከቅድስት ድንግል ማርያም ሥጋ ለብሶ እንደሚገለጥና ዓለምን እንደሚያድን ለመንገር አብርሃምን ሚስትህ ሣራ ወዴት ናት ሲል ጠይቆታል፡፡
እግዚአብሔርም *የዛሬ ዓመት እንደ ዛሬው ጊዜ ወደ አንተ በእውነት እመለሳለሁ፤ ሚስትህ ሣራም ልጅን ታገኛለች* ብሎ ለአብርሃም ነገረው፡፡ ሣራ ይህንን ቃል በሰማች ጊዜ ባለቤቷም አርጅቶ፤ እርሷም የሴቶች ግዳጅ ትቷት ነበርና */ሲያረጁ አምባር ይዋጁ/ እንዲሉ እስከ ዛሬ ድረስ ቆንጆ ነኝን? ጌታዬ አብርሃምስ ገና ጐረምሳ ነውን? ብላ በመጠራጠሯ ሳቀች፡፡ እግዚአብሔርም አብርሃምን ሣራ ለምን ትስቃለች? በውኑ ለእግዚአብሔር የሚሳነው ነገር አለን?* አለው፡፡ ይህንን ኃይለ ቃል ቅዱስ ገብርኤል እመቤታችንን በድንግልና ፀንሳ በድንግልና እንደምትወልድ ሲያበሥራት *ወንድ ሳላውቅ ይህ እንዴት ሊኾን ይችላል?* ብላ በጠየቀችው ጊዜ መልአኩ ተናግሮታል /ሉቃ.፩፥፴፯/፡፡
ሣራም ስለፈራች አልሳቅሁም አለች፡፡ እግዚአብሔርም መሳቋን እንዳወቀባት ከነገራት በኋላ በድጋሜ በዓመቱ ወደ አብርሃም ቤት እንደሚመጣና ሣራ እንደምትወልድ በአጽንዖት ነገሯቸዋል፡፡ ይህም ከዓመት በኋላ ይስሐቅ እንደሚወለድ ሲያበሥራቸው ነው፡፡ አንድም አምስት ሺሕ ከአምስት መቶ ዓመት ሲፈጸም ከልጅ ልጅህ ተወልጄ ሥጋ ለብሼ በመጣሁ ጊዜ ሣራ ወንጌል ምእመናንን ታስገኛለች ማለትም ሐዲስ ኪዳን ተመሥርታ ክርስቲያኖችን ታፈራለች ሲለው ነው፡፡
እግዚአብሔር አምላክ ለአብርሃም በሦስትነቱ ተገልጦ የይስሐቅን መወለድና በሥጋ ማርያም መገለጡን ነግሮት ሔዷል፡፡ *ሔዷል* ስንልም ሥላሴ ከአብርሃም ቤት ሲወጡ መታየታቸውን ለማመልከት እንጂ እግዚአብሔር መሔድ መምጣት የሚነገርለት ኾኖ አይደለም፡፡ እርሱ በዓለሙ ኹሉ ሰፍኖ የሚኖር አምላክ ነውና፡፡ ነገር ግን በልዩ ልዩ ምሳሌ እየተገለጠ ጸጋውን፣ በረከቱን ማሳደሩን ለመግለጽ መጣ፤ ሔደ፤ ወረደ፤ ዐረገ እየተባለ ይነገርለታል፡፡
ሐምሌ 7 ቀን እግዚአብሔር በአብርሃም ቤት ከመገኘቱና የይስሐቅን መወለድ፤ ሰው ኾኖ እንደሚገለጥ ለአብርሃም ከመናገሩ በተጨማሪ አብርሃምን ዘሩን እንደሚያበዛለት እንደዚሁም አሕዛብ ኹሉ በአብርሃም እንደሚከብሩ ማለትም ከአብርሃም ዘር በተገኘው በኢየሱስ ክርስቶስ አሕዛብ እንደሚቀደሱና ይህንን ምሥጢርም እግዚአብሔር ከወዳጁ ከአብርሃም እንደማይሠውር ቃል የገባለት ቀን ነው፡፡ በተጨማሪም እግዚአብሔር በኀጢአታቸው የተነሣ ሰዶምንና ገሞራን ያጠፋው አብርሃምም በአማላጅነት በፊቱ የቆመው በዛሬው ዕለት ነው፡፡ /ምንጭ፡- የኦሪት ዘፍጥረት አንድምታ ትርጓሜ፣ ዘፍ.፲፰፥፩-፳፱/፡፡ከዚህ ከአብርሃምና ከሣራ ቤት ታሪክ ብዙ የምንማራቸው ቁም ነገሮች አሉ፤ ከእነዚህ መካከልም እግዚአብሔር እንደ አብርሃም ልቡናቸው ቅን በኾነና በለጋሾች ማለትም ምጽዋትንና እንግዳ መቀበልን የዘወትር ልማዳቸው አድርገው በሚኖሩ ሰዎች ቤት እንደሚገኝ፤ እግዚአብሔር በረድኤቱ ወደ ቤት ሲገባም የተዘጋ ማሕፀን እንደሚከፈትና ቤቱ በበረከት እንደሚሞላ እንደዚሁም የተሠወረ ምሥጢር እንደሚገለጽ እግዚአብሔር በአብርሃም ቤት ገብቶ ያደረገው ኹሉ ትልቅ ማስረጃ ነው፡፡ ከዚሁ ኹሉ ጋርም እግዚአብሔር አምላክ በአንድነቱም በሦስትነቱም እየተገለጠ አምላክነቱን እንደሚገልጥና የቸርነቱን ሥራ እንደሚሠራም ከዚህ ታሪክ እንረዳለን፡፡
ይህ የእግዚአብሔር በአብርሃም ቤት መገለጥ በአንድ ወቅት ተፈጽሞ ነበር እየተባለ የሚነገር ሳይኾን ለዘለዓለሙ ሲነገርና ሲፈጸም የሚኖር ሕያው ትምህርት ነው፡፡ ይህንንም እግዚአብሔር ለቅዱሳኑ በልዩ ልዩ መንገድ እየተገለጠ በሚያደርገው ድንቅና ተአምር መገንዘብ እንችላለን፡፡ ዛሬም ሀብት ንብረት ያለን በትሩፋት ሥራ በመሠማራት ማለትም እንግዶችን በመቀበል፣ ለተራቡ በማብላት፣ በመመጽወት ተግባር ከኖርን፤ በቂ ንብረት የሌለን ደግሞ ልቡናችንን ንጹሕ ከማድረግና ከኀጢአት ከመራቅ በተጨማሪ ቤት ላጡና ለተቸገሩ በመራራት ቀና አስተሳሰብን ገንዘብ ካደረግን እግዚአብሔር በሕይወታችን ውስጥ መንፈሱን እያሳደረ የምንሻውን ኹሉ ያደርግልናል፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር አሜን፡፡
{flike}{plusone}