የገብረ ሰላም በዓል በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል በድምቀት ተከበረ!!!
በየዓመቱ በትንሣኤ ዋዜማ ሲከበር የቆየው የገብረ ሰላመ በዓል በዘንድሮው ዓመት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ፣ ፖትርያርክ ርእሰ ሊቃ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ፣ ሊቀ ጳጳስ ዘአኲስም፣ ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት፣ ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት፣ የጠቅላይ ቤተክህነት የየመምሪያ ኃላፊዎች፣ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ መ/ር ጎይቶኦም ያይኑ እና የሀገረ ስብከቱ የዋና ክፍል ኃላፊዎች፣ የአዲስ አበባ ገዳማት እና አድባራት የሥራ ኃላፊዎችና ሠራተኞች በተገኙበት ዛሬ ቅዳሜ ሚያዝያ 7 ቀን 2009 ዓ.ም በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል በታላቅ ድምቀት ተከብሯል፡፡ በተረኛው ደብር በደብረ ጽጌ ቅዱስ ዑራኤል ደብር ካህናት ጸሎተ ወንጌል ተደርሷል፡፡
“አሜሃ መልአ ፍስሐ ዓፉነ፤ ወተኀሥየ ልሳንነ፤ አሜሃ ይቤሉ አሕዛብ፡፡” በዚያን ጊዜ አፋችን ደስታን ሞላ፤ አንደበታችንም ሐሴትን ሞላ፤ በዚያን ጊዜ በአሕዛብ ዘንድ፡፡ መዝ. 125÷2 የሚለው የዳዊት መዝሙር በዲያቆዩ በዜማ ተዚሟል፡፡
ከዚያም በዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ 19 ላይ የተጻፈው የወንጌል ቃል በብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ በንባብ ተሰምቷል፤ በወንጌሉ እንደተጻፈው ጌታችን እና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በተሰቀለበት ወቅት እናቱ ቅድስት ድንግል ማርያም እና ቅዱስ ዮሐንስ ወንጌላዊ በመስቀሉ ሥር ቆመው እንደበርና ኢየሱስ ክርስቶስም ከኀዘናቸው እንዳጽናናቸው ያብራራል፡፡
በመቀጠልም ወለመልአከ ሕይወትሰ ሰቀልዎ ለዘተንሥአ እሙታን ገብረ ሰላመ በመስቀሉ ትንሣኤሁ አግሃደ የሚል ያሬዳዊ መዝሙር በተረኛው በደብረ ጽጌ ቅዱስ ዑራኤል ደብር ሊቃውንት ቀርቧል፤ ከዚያም አንሰ እረክብ ሰላመ በእንቲአሁ ለብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ወልድ እሁየ ሊተ ወአነ ሎቱ አፈቅሮ እስከ አመ ፈቀደ የሚል ያሬዳዊ ወረብ በቅዱስ ዑራኤል ደብር ወጣቶች ቀርቧል፡፡ ከዚያም በማያያዝ ሁለት የቅኔ ሊቃውንት በዓሉን የተመለከተ ቅኔያት አቅርበዋል፡፡
በመቀጠልም በብፁዕ አቡነ እንድርያስ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የሊቃውንት ጉባኤ የበላይ ኃላፊ ትምህርተ ወንጌል ተሰጥቷል፡፡ ብፁዕነታቸው በሰጡት ትምህርት በኢየሱስ ክርስቶስ ስቅለት ስደት እና ባርነት ተወግዷል፤ በነፍስ በሥጋ ተቆራኝተው የነበሩ አጋንንት ተበትነዋል፤ የ5500 ዓመት መከራ አልቋል፤ ምድርና ሰማያት ተቀድሰዋል፤ በፈጣሪ ደም ዓለም ተቀድሷል፤ ለሰው ልጆች ካሳ ተፈጽሟል፤ ልጅነት ተሰጥቷል፤ ይህች ዕለት በእግዚአብሔር ዘንድ የድኅነት እቅድ ተይዞባት የነበረች እለት ናት፤ ስብከተ ወንጌል በአራቱም ማዕዘን ተሰራጭቷል፤ መርገመ ሥጋ እና መርገመ ነፍስ ጠፍቷል፤ ይሁዳ ዘነፍስ በዓልህን አድርግ ተብሏል፤ የማናይ ታምራት አይቶ ስላመነ ከአባቱ ከአዳም ቀድሞ ገነት ገብቷል፤ በጨካኙ ጠላት ተይዘው የነበሩት ነፃነት ተሰብኮላቸዋል በማለት ብፁዕነታቸው ሰፋ ያለ ትምህርተ ወንጌል ሰጥተዋል፡፡
በመጨረሻም ብፁዕ ወቅዱስ ፖትርያርኩ ባስተላለፉት አባታዊ ትምህርት እና ቃለ ምዕዳን ዛሬ በዚህ ካቴድራል የተገኘነው የገብረ ሰላመን በዓል ለማክበር ነው፤ ጌታችን እና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሙስና መቃብርን ያሸነፈበት በዓል ስለሆነ በዓሉ የሰላም በዓል ነው፤ የሰው ልጆች ከዘለዓለማዊ የሲዖል እሥራት የተፈቱበት በዓል ስለሆነ በዓሉ ትልቅ በዓል ነውና እንኳን ለዚህ ትልቅ በዓል በሰላም አደረሳችሁ! በማለት አባታዊ ቡራኬ እና ቃለ ምዕዳን ካስተላለፉ በኋላ የሰላምና የነፃነት ምልክት የሆነውን ቄጤማ ከብፁዓን ሊቃ ጳጳሳት ጀምሮ በካቴድራሉ ለተገኙት ሊቃውንት እና ምእመናን በመስጠት የበዓሉን ምሥራች አብሥረዋል፡፡
ምንጭ፡-www.addisababa.eotc.org.et
{flike}{plusone}