የመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል በቅጥረ ግቢው መካነ መቃብር ዙሪያ በሶሻል ሚዲያ ላይ ለተሰራጨው መሠረተ ቢስ ዘገባ ማብራሪያ ሰጠ
በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል እና በበዓለ ወልድ ቤተ ክርስቲያን መካነ መቃብራት የሚገኙ ዐፅሞች እንዲፈልሱ የተወሰነው፣ በቦታው ሕንፃ ለመሥራት ተፈልጎ ሳይሆን፤ የመቃብር ቦታው በመሙላቱና በመጨናነቁ እንደሆነ የካቴድራሉ አስተዳደር አስታወቀ፡፡
ሊቀ ሥልጣናት አባ ገብረ ሥላሴ በላይ፣ የቅድስት ሥላሴ ካቴድራል እና የበዓለ ወልድ ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ፣ ስለ ጉዳዩ ከሰንደቅ ጋዜጣ ተጠይቀው በሰጡት ምላሽ፥ መካነ መቃብራቱን ከማልማት፣ ከማስዋብና ከመከባከብ ውጭ ሕንፃ የመገንባት ዕቅድ አስተዳደሩ ፈጽሞ እንደሌለው አረጋግጠዋል፡፡
ካቴድራሉ በቅጥር ግቢው ከሚገኙ መካነ መቃብራት ውስጥ፣ በበዓለ ወልድ ቤተ ክርስቲያን ደቡባዊ ክፍልና በካቴድራሉ መካከል የሚገኘውን የመካነ መቃብር ሥፍራ ለማልማት እንዲቻል፥ በጋዜጦች፣ በራዲዮና በቴሌቭዥን ቤተሰቦች ተገኝተው ዐፅሞችን እንዲያነሡ ጥሪ መተላለፉን ሊቀ ሥልጣናቱ ጠቅሰው፤ በጥሪው መሠረት የተገኙ ቤተሰቦች ባደረጉት ትብብርና ስምምነት መሠረት ዐፅሞቹ በክብር እንዲነሡ መደረጉን ተናግረዋል፡፡
የማፍለስ ሒደቱም በሁለት ዓይነት መልኩ እንደተከናወነ፣ ሊቀ ሥልጣናት አባ ገብረ ሥላሴ ያስረዳሉ፡፡ ይኸውም፣ በመካነ መቃብሩ ላይ የሚገኙ ሐውልቶች ብቻ ተነሥተው አዕፅምቱ ሳይነሡ፣ ስማቸውና ታሪካቸው በግድግዳ ላይ እንዲጻፍ መደረጉን፤ በሌላ በኩል ደግሞ፣ ሙሉ በሙሉ ከመካነ መቃብራቱ ተነሥተው በተዘጋጀላቸው ሥፍራ እንዲያርፉ የተደረጉ አዕፅምት መኖራቸውን አስረድተዋል፡፡ በዚህ ሁኔታ እንዲነሡ ከተደረጉት ከ290 ያላነሱ አፅሞች መካከል፦ የቀኝ ጌታ ዮፍታሔ ንጉሤ፣ የመልአከ ብርሃን አድማሱ ጀንበሬ እና የፕሮፌሰር ዐሥራት ወልደየስ እንደሚገኙበት ዘርዝረዋል፡፡
የቀኝ ጌታ ዮፍታሔ ንጉሤ ቤተሰቦች በወቅቱ ባለመምጣታቸው፣ ዐፅማቸው ከመካነ መቃብሩ ተነሥቶ በክብር በተዘጋጀለት የካቴድራሉ ቦታ ያረፈው የዛሬ ስምንት ዓመት መሆኑን ያዘከሩት ሊቀ ሥልጣናቱ፥ በቅርቡ ግን፣ ቤተሰቦቻቸው መጥተው ወደ ትውልድ ሥፍራቸው ወስደው ማሳረፍ እንደሚፈልጉ በመግለጻቸው፣ በሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን መሠረት ተገቢው ጸሎት ተደርሶ በክብር እንደ ተሸኘ አስረድተዋል፡፡ ይህን አስመልክቶ በተለይ በማኅበራዊ ድረ ገጾች የተዛቡና እውነት ያልሆኑ መረጃዎች መሰራጨታቸው ካቴድራሉን እንዳሳዘነም ጠቁመዋል፡፡የመልአከ ብርሃን አድማሱ ጀንበሬን ዐፅም ወደ ካቴድራሉ መካነ መቃብር ለማፍለስ፣ ወንድማቸው መጥተው የነበረ ቢሆንም፣ በዐቅም ማነስ ምክንያት ወደ ካቴድራሉ ማሳረፊያ ማንሣት እንደማይችሉ ተናግረዋል፡፡ በዚህም ምክንያት፣ “የካቴድራሉ አስተዳደር ሐውልቱን በማንሣት ዐፅማቸው ባለበት እንዲቆይና ስምና ታሪካቸው በግድግዳ ላይ እንዲጻፍ ወስኖ ነበር፤” ብለዋል ሊቀ ሥልጣናቱ፡፡ ሆኖም በአሁኑ ወቅት፣ የልጃቸው ባለቤት የሆኑ ግለሰብ ቀርበው በማመልከታቸው፣ ካቴድራሉ፥ የመልአከ ብርሃን አድማሱን ዐፅም ሌላ ቦታ ሰጥቶ ለማፍለስና ለማሳረፍ እየተዘጋጀ እንዳለ አስተዳዳሪው አስታውቀዋል፡፡
የበዓለ ወልድ ቤተ ክርስቲያን በያዛቸው ሐውልት/ቀብር/ ቤት እና የመቃብር አጥር ብዛት ቅጽረ ግቢው ለማስቀደሻ እየጠበበ መሆኑን የሚጠቅሰው የካቴድራሉ “የቀብር የሐውልት ማሥነሻ ቅጽ”፣ ዐፅሙ ባለበት እንዲሆንና ቦታው ተስተካክሎ ለምእመናን ማስቀደሻ – መጠለያ እንደሚሠራበት ያመለክታል፤ ለዚህም ተግባር የሟች ቤተሰብ ያለምንም ቅሬታ ተስማምቶ ለሥራው ተባባሪና የሚፈለገውን ድጋፍ ለማድረግም ፈቃደኛ እንደሆነ በፊርማው ማረጋገጡን ይገልጻል፡፡
የበዓለ ወልድ ቤተ ክርስቲያን – በዐፄ ምኒሊክ ዘመነ መንግሥት፤ የመንበረ ጸባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ደግሞ፣ በቀዳማዊ ዐፄ ኃይለ ሥላሴ መተከላቸውን፤ የቀብር አገልግሎቱ የተጀመረውም፦ ንጉሠ ነገሥቱ ከነቤተሰቦቻቸው የቀብር ቦታ ካዘጋጁና ለሀገራቸው የተዋደቁ ጀግኖች እንዲቀበሩበትና በሌላም ቦታ የተቀበሩት ዐፅማቸው እንዲያርፍበት ከፈቀዱ በኋላ መሆኑን ሊቀ ሥልጣናቱ ጨምረው አስታውሰዋል፡፡ የመቃብር ቦታው፣ ከ60 ዓመታት ላላነሰ ጊዜ እንዳገለገለም በካቴድራሉ የሚገኙ ሰነዶች ያረጋግጣሉ፡፡
ሊቀ ሥልጣናቱ አያይዘውም፥ ቤተሰቦች ከቀብር በኋላ የመቃብር ሥፍራዎችን የመጠበቅ፣ የመከባከብና የማስዋብ ሥራ እንደማይሠሩ ተችተዋል፡፡ በዚህም ምክንያት፣ በተለይ ከ127 ዓመታት በላይ የዕድሜ ባለጸጋ የሆነው የባለወልድ ቤተ ክርስቲያን የመቃብር ስፍራ፣ ወደ ቆሻሻ መጣያነት ተቀይሮ መቆየቱ አሳዛኝ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ ካቴድራሉ፥ ከመዲናዪቱ የቱሪስት መስሕቦች አንዱ እንደመሆኑ መጠን፣ የመካነ መቃብሩ አያያዝ የሀገር ገጽታንም የሚያበላሽ እንደነበር አስገንዝበዋል፡፡
ምንጭ፡-ሰንደቅ ጋዜጣ፤ ረቡዕ፣ ሐምሌ 5 ቀን 2009 ዓ.ም.
{flike}{plusone}