የሚድያ አገልግሎትን እናጠናክር!!

በዘመኑ የአነጋገር ዘይቤ ሚድያ እየተባለ የሚጠራው የመረጃ ልውውጥ አገልግሎት በዓለማችን ዙሪያ የንግዱም፣ የማኅበራዊውም፣   የፖለቲካውም፣ የመንፈሳዊ ዓለሙም የሚጠቀምበትና የሚገለገልበት ቢሆንም እንኳን የዚህ ቴክኖሎጂ የመጀመሪያዋ መሥራች የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን እንደሆነች የታሪክ መዛግብት ይስማማሉ፡፡ እንደሚታወቀው ሁሉ ሚድያ በሁለት ዐበይት ነጥቦች ሊመደብ ይችላል፡፡ አንደኛው በሥነ ጽሑፍ የሚገለጥ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ በስዕልና በድምፅ የሚገለጥ ነው፡፡

ሥነ ጽሑፍ

ሥነ ጽሑፍ በተለያዩ ምሁራን የሚቀነባበር ታላቅ የአእምሮ ሥራ ሲሆን በዘመነ ነገሥት በቤተ መንግሥቱ አካባቢ የሥነ ጽሑፍ ጦማርያን እና አማካሪዎች ይኖሩ ነበር (1ዜና 27፥32) እነዚህ የመጀመሪያዎቹ የሥነ ጽሑፍ ጦማርያን ጥሩ ልብስ ለብሰው የቀለም ቀንድ በወጋባቸው ይይዙ ነበር (ሕዝ.9፥2) ከምርኮ በኋላም እንደ ዕዝራ ያሉት የሕግም ምሁራን እና ፈጣን ጦማርያን ሆኑ፡፡ (ዕዝ.7፥6) በዘመኑ አንድ ጸሐፊ (ጦማሪ) ሦስት አይነት ሥራ እንዲሠራ ይደረጋል፡፡

1) የሙሴን ሕግ በትክክል መተርጎም

2) ለሰዎች ሕግን ማስተማር

3) የዳኝነት ሥራውንም ማከናወን ነው፡፡

በሐዲስ ኪዳን መግቢያ የነበሩት ጸሐፍት ሕጉ እንዳይጣስ በማሰብ የሽማግሌ ወግ የተባለውን ልምድ በሕዝቡ ጫንቃ ላይ ጫኑት (ማቴ.15፥2) ይሁን እንጂ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለግብዝነታቸው ብዙ ጊዜ ወቀሳቸው (ማቴ.23) ምክንያቱም ለመልካም እና ሰውን ለማነፅ የሚረዳውን የሥነ ጽሑፍ ሙያ ለግል ጥቅማቸው እና ለራሳቸው ዝንባሌ ለማዋል ጥረት ያደርጉ ስለነበር ነው፡፡

ሆኖም ግን የሥነ ጽሑፍ አገልግሎት በየዘመኑ በሚፈጠሩ የሥነ ጽሑፍ ምሁራን አማካኝነት እየተጠናከረ ሊመጣ ችሏል፡፡የሥነ ጽሑፍ አገልግሎት ውጤቶች ናቸው፡፡ በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያም በመጽሔቶች በጋዜጦች እና በበራሪ ጽሑፎች ለምዕመናን ስታበረክት የቆየችው አገልግሎት እንዲህ በቀላሉ የሚገለፅ አይሆንም፡፡ በቃለዓዋዲ ሬድዎም ስብከተ ወንጌልን ስታስፋፋ እንደነበር የረጅም ጊዜ ትዝታ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል፡፡ 

እንደየ ዘመኑ አጠራርና አተገባበር ይለያይ እንጂ የሚዲያ አጠቃቀም ለቤተ ክርስቲያን አዲስ ነው ለማለት ባያስደፍርም ከቤተ ክርስቲያኒቱ ዓለም አቀፍ ሐዋርያዊ አገልግሎት አንፃር ሲታይ ሚዲያው ምን ያህል እንገለገልበታለን የሚለው ጉዳይ ግን አነጋጋሪ ነው፡፡ቤተ ክርስቲያኒቱ ቀደም ሲል በፕሪንትሚዲያ(ጋዜጣና መጽሔት…) በኋላም በተወሰነመልኩ ለስብከተ ወንጌል አገልግሎት የሚውል ኤሌክትሮኒክስ ሚዲያ(ሬድዮ) ትጠቀም እንደነበር የታሪክ መዛገብት ያስረዳሉ፡፡

ይሁን እንጂ አሁን ባለንበት ክፍለ ዘመን ኤሌክትሮኒክስ ሚዲያ /ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ(ማኅበራዊ ድረ-ገፅ፤ሳተላይት ቴሌቪዥን እና ሬድዮ) በተደራሽነቱ፤በዓለም አቀፍ ስርጭቱ፤በዋጋ ቅናሽነቱ እና ዓለምን ወደ አንድ መንደር በማምጣት በከፍተኛ ፍጥነት በማደግ ላይ ይገኛል፡፡የዚሁ ጽሁፍ ዓላማም ስለፕሪነት ሚዲያ ትርጉምና አገልግሎት ሳይሆን  ኤሌክትሮኒክስ ሚዲያን /ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂን ማእከል ያደረገ ነው፡፡ምክንያቱም አሁን ያለንበት ዘመን የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ዘመን በመሆኑ በዚሁ ቴክኖሎጂ ያልታገዘ አሠራር  አዝጋሚ እና አድካሚ ከመሆኑም በላይ የሚፈለገውን ያህል  አጥጋቢ ሥራ መስራት አይቻልም፡፡

ቤተ ክርስቲያናችን ጥንታዊት፤ሐዋርያዊት፤ታሪካዊትና ብሔራዊት እንደመሆኗ መጠን በረጅም ዘመን ጉዞዋ ለሀገራችን ኢትዮጵያ ያበረከተችው ዕሴት የአፍሪካዊያን መኩሪያና በመላው ዓለምም በታሪክ መዝገብ ከፍተኛ ሥፍራ የሚሰጣት ቤተ ክርስቲያን ናት፡፡ በሀገራችን  የሚገኙት ጥንታውያን ገዳማትና አድባራት ከመንፈሳዊ አገልግሎታቸው ባሻገር ለሀገሪቱ ማንነትና የስኬት ውጤት ዋና መሠረቶች ናቸው ፡፡

ቤተ ክርስቲያናችን በተጓዘችባቸው ጉዞዎች ሁሉ አባቶቻችን ኃላፊያትንና መፃእያትን በመገንዘብ አስቀድመው ከትውልድ ሐሳብ ቀድመውና ከትውልድ እኩል እየተጓዙ ክርስትናን አቆይተው ለእኛ አስረክበውናል፡፡ እኛም ከአባቶቻችን የተረከብነውን ሃይማኖት ለዘመኑ ትውልዱ ዘመኑ በሚፈቅደው መሣሪያ በመገልገል ሐዋርያዊ አገልግሎት ማስተላለፍ እጅግ አስፈላጊ ነው፡፡  የሰው ልጅ ሲፈጠር በቦታ የሚወሰንና የሚገደብ ሆኖ በመፈጠሩ በሌላ ሥፍራ ያለውን ነገር በራሱ ማወቅ አይችልም፡፡ይህንን ማድረግ የሚቻለው እንደ ቅዱሳኑ በሕይወቱ ሳለ በቅቶ ሲገኝ ብቻ ነው አለበለዚያ በሀገር ርቀት ምክንያት ሰዎች ከሰዎች ጋር ለመገናኘት ሌሎች መንገዶችን መጠቀም አስፈላጊ ነው ፡፡

በመሆኑም የሰው ልጅ ከእግዚአብሔር የተሰጠውን አዕምሮ በመጠቀም የተለያዩ የመገናኛ ዘዴዎችን ሠርቷል፡፡ከእነዚህም መካከል አሁን በዚህ ዘመን የተጀመረው ኤሌክትሮኒክስ ሚዲያ /ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ አንዱ ተጠቃሽ ሲሆን ይህ ቴክኖሎጂ ትውልዱ ሲጠቀምበት በዓለማዊ ትምህርት ብቻ ተወስኖ እንዳይቀር መንፈሳዊ ትምህርትንም ለማስታላለፍ ጥሩ አማራጭ መንገድ በመሆኑ ቤተ ክርስቲያናችንም በእውቀቱ የተካኑትን ልጆቿን በመጠቀም ዘመኑ ባስገኘው ቴክኖሎጂ ትምህርት እንዲተላለፍ መደረጉ ጠቀሜታው እጅግ የላቀ ነው፡፡

አባቶቻችን ሐዋርያት በቁጥር ጥቂቶች ሲሆኑ ወንጌልን(ቅዱስ መጽሐፍን) እስከ ምድር ዳርቻ ሄደው በልዩ ልዩ ቋንቋ የእግዚአብሔርን ቃል ለዓለም ሁሉ አዳርሰዋል፡፡በዚህ ዘመን ደግሞ  ይህንን ዓለም አቀፍና ሐዋርያዊ ተልዕኮ ለመፈጸም ቴክኖሎጂውን መጠቀም ጥሩ አማራጭ ሆኖ በመገኘቱ በተለያዩ ሀገራት የሚገኙ ሰዎችን በቀላሉ ስለ ቤተ ክርስቲያናችን ሁለንተናዊ የሥራ እንቅስቃሴም ይሁን መንፈሳዊ ትምህርት በቴክኖሎጂው  በመታገዝ ብዙ ሰዎችን በቀላሉ ማስተማር ተችሏል፡፡

ጥበብን ሁሉ የሚሰጥ እግዚአብሔር  ነው፤ እግዚአብሔር እውቀቱንና ጥበቡን ሰጥቷቸው የተሠራውን ቴክኖሎጂ ለቤተ ክርስቲያናችን ሁለንተናዊ አገልግሎት ማዋሉ ጥቅሙ እጅግ ከፍተኛ በመሆኑ ዘመኑ ያመጣውን ቴክኖሎጂ በመጠቀም በጎ ነገርን ማስተማር ከመቻሉም በላይ የቤተ ክርስቲያኒቱን ታሪካዊ ቦታዎች ማስተዋወቅን ጨምሮ ወቅታዊ የሆኑ የቤተ ክርስቲያችን ጉዳዮችንም ለዓለም ሕዝብ በተለያዩ ቋንቋዎች ማሠራጨት ይቻላል፡፡ኤሌክትሮኒክስ ሚዲያ /ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂን ተጠቅሞ ትምህርትና የተለያዩ አገልግሎቶችን መስጠት ከሚቻልባቸው ማኅበራዊ ሚዲያዎች መካከል፡- 

1.ቪዲዮ ኮንፈረንስ/video conference

2.ቻቲንግ ኮንፍረንስ/chatting conference

3.ቴሌ ኮንፈረንስ/teleconference

4.ፌስቡክ፤ ዩትዮብ/facebook and YouTube

5.ስካይአይፒ/Skype

6.ኢንስታግራም/ Instagram

7.ቲዊትር/twitter

8.ሚሴንጀር/messenger

9.ሊንክድ ኢን/linked in

10.ኢሜል እና  ወዘተ… በመጠቀም በጽሑፍ፣ በድምጽ፣ በምስልና በመሳሰሉት የቤተክርስቲያኒቱን አስተምህሮ እና ማኅበራዊ አገልግሎቶችን ለዓለም ሕዝብ ማዳረስ ይቻላል፡፡

 ይሁን እንጂ ቤተ ክርስቲያናችን በቴክኖሎጂው የማይከናወኑ እና የግድ በአካል በቤተክርስቲያን በመገኘት የሚከናወኑ ሥርዓቶችም አሏት፡፡ እነሱም፡-ሰባቱ ምሥጢራተ ቤተክርስቲያን ማለትም ምሥጢረ ጥምቀት፣ ሜሮን፣ ቁርባን፣ ክህነት፣ ንሥሐ፣ ተክሊል እና ቀንዲል ሲሆኑ ከእነዚህም በተጨማሪ አጠቃላይ ስብሐተ ነግህ፤ የሠርክ ጸሎት፤ ሰዓታት፤ማኅሌት፤ፀሎተ ፍትሐት እና የመሳሰሉት በዚህ ቴክኖሎጂ አይፈፀሙም፡፡ ነገር ግን በድምጽም ሆነ በምስል ተቀርፆ የቤተ ክርስቲያን ትምህርት ማስተላለፍ ይቻላል፡፡ 

በአሁኑ ሰዓት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን በማእከል ደረጃ ዘመኑ ያስገኘው አንድ ዘመናዊ ሳተላይት ቴሌቪዥን ከፍታ ሐዋርያዊ አገልግሎቷን በመስጥት ላይ ትገኛለች፡፡ ይህ ጥሩ ጅምር ቢሆንም ይህ ብቻ ግን በቂ ነው ማለት አይቻልም ተጨማሪ የኤሌክትሮኒክስ ሚዲያዎች ያስፈልጋሉ፡፡ ከእነዚህ ውስጥ ኤሌክትሮኒክስ ሚዲያ /ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ አንዱ ነው፡፡

ካቴድራሉም ዘመኑ ያስገኘውን ቴክኖሎጂ በመጠቀም አገልግሎቱን የበለጠ ለማሳደግና በመላው ለዓለም ስርጭቱን ተደራሽ እንዲሆን ታስቦ  እጅግ ዘመናዊ የሆነ  ይፋዊ(ኦፊሻል) ድረ-ገፅ አዘጋጅቶ ሥራ ላይ እንዲውል አድርጓል፡፡

የዚሁ አገልግሎትም ዘመኑ ባስገኘው  ቴክኖሎጂ በመጠቀም ስብከተ ወንጌልን ፤ የቤተ ክርስቲያናችንን አስተምህሮ እና የቤተ ክርስቲያኒቱን ማኅበራዊ አገልግሎቶች ለዓለም ሕዝብ በማዳረስ ዓይነተኛ መሣሪያ ሆኖ አገልግሎት መስጠት ሲሆን በተጨማሪም ድረ ገጹን  በመጠቀም የቤተ ክርስቲያናችንን አኩሪ ታሪክ ቅርስና ታሪካዊ ቦታዎችን  ከማስተዋወቅ ባሻገር ወቅታዊ የሆኑ መረጃዎችን ፤እቅዶችን እና  የሥራ አፈጻጸም ሪፖርቶችን ለኢትዮጵያ ኦርቶዶከስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን እምነት ተከታዮች በቀላሉ እንዲዳረስ በማድረግ በኩል ከፍተኛ የሆነ የግልፅነትና የተአማኒነት ሚና እንዲጫወት ማድረግ ነው ፡፡ 

የካቴድራሉ ማኅበረሰብ የሚዲያን ጥቅም ቀድሞ ያወቀና የተረዳ ቢሆንም እስከ አሁን ባለው ሁኔታ በሥነ ጽሁፍ ተሳትዎ እንደሚጠበው አለመሆኑ ብዙዎችን አስገርሟል በተለይም የወጣት ሰንበት ተማሪዎች ተሳትፎ የለም ቢባል ይቀላል፡፡ከዚሁ አንጻር ሁሉም የካቴድራሉ ማኅበረ ሰብ ለማህባረዊ ሚዲያው የበኩሉን አስተዋፅኦ ሊያደርግ ይገባል፡፡