የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ዕርቀ ሰላም በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ተካሄደ

0125

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን አራተኛው ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆርዮስ ወደ ኢትዮጵያ መመለስን አስመልክቶ በመንበረ ፀባኦት ቅድስት ስላሴ ካቴድራል የአቀባበል ስነ ስርዓት ተከናውኗል። በስነ ስርዓቱ ላይ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፣ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ፣ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆርዮስ ወደ ኢትዮጵያ መመለስ ሁላችንም ተደስተናል ብለዋል። በተጨማሪም ለ26 ዓመታት ተራርቃ የቆየችውን ቤተክርስትያን አንድ በማድረጉ አምላክን እንደሚያመሰግኑም ነው የተናገሩት።

በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ቤተክርስትያን ሥረዓተ ጸሎት የተከናወነ ሲሆን፥ ካህናትመዘምራንና ወጣት የሰንበት ትምህርት ቤት ተማሪዎች ወረብ አቅርበዋል፤ ቅኔም አበርክተዋል። በአቀባበል ስነ ስርዓቱ ላይ ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆርዮስንና ብጹዓን አባቶችን ከስደት መመለስን ተከትሎ የሀገረ ስብከት መሪዎች፣ የአድባራትና የገዳም አስተዳዳሪዎች፣ የሰንበት ትምህርት ቤት ወጣቶች እንዲሁም በርካታ ምዕመናን በካቴድራሉ ተገኝተዋል። በተጨማሪም ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት፣ የተለያዩ የእምነት አባቶች እና አምባሳደሮች በስነ ስርዓቱ ላይ ታድመዋል። እንዲሁም ከጸሎት ስነስርዓት በኋላ ሁለቱም ሲኖዶሶች በዕርቅ ሂደቱ ያለፉበትን ውጣውረድ ለምዕመናኑ አንብበዋል።

ብጹዕ አቡነ አብርሃም በሀገር ውስጥና በውጭ የሚገኙት ሲኖዶሶች ሦስት ሦስት አባቶቸን በመወከል የዕርቅ ሂደቱ መጀመሩንም ገልጸዋል። በዚህም የልዑካን ቡድኑን አባላት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በጽህፈት ቤታቸው ተቀብለው የዕርቅ ሂደቱን ለመደገፍ የተቻላቸውን እንደሚያደርጉ መግለጻቸውንም አባቶች ጠቅሰዋል። ይህንንም ተከትሎ በሀገር ቤት የነበረው ሲኖዶስ ሐምሌ 11 ቀን ወደ አሜሪካ ያቀና ሲሆን፥ በዳላስ አውሮፕላን ማረፊያም በዚያ ያሉት አባቶች ባልተለመደ መልኩ ደማቅ አቀባበል ማድረጋቸውን ገልጸዋል። ሁለቱም የሲኖዶስ ተወካዮች ከተገናኙ ከጥቂት ሰዓታት በኋላ የመክፈቻ ጸሎትና የመዝጊያ ጸሎት ማድረግ እንዳለባቸው ከወሰኑ በኋላ በሁለቱም ሲኖዶሶች በኩል ስድስትና ስምንት አጀንዳዎች መቅረባቸውን ተናግረዋል። በመጨረሻም አጀንዳዎቹን ወደ ስድስት ዝቅ በማድረግ ውይይታቸውን በዝግ ስብሰባ ማድረጋቸውን ነው ያስታወቁት። በተለያየ ዓመት ለአራት ጊዜያት ያህል የእርቅና የሰላም ሂደቱ መሞከሩን ገልጸው የአሁኑ ግን በተጀመረ በሦስት ሰዓታት መጠናቀቁን አብስረዋል። ብጹዕ አቡነ አብርሃም የተስማሙባቸውን ውሳኔዎች ጠቅሰዋል በዚህም በሁለቱም ሲኖዶስ መካከል የተደረሰውን የዕርቀ ሰላም ውህደት ፍጹም ለማድረግ የሚተዳደሩበትን ቅድመ ሁኔታ ለማዘጋጀት ሁለቱም ሲኖዶሶች ተስማምተዋል። እንዲሁም በውጭ የሚገኙ ቤተክርስትያናት በስርዓተ ቤተክርስትያን ቀኖና አስተዳደር መሰረት በአንድ ቅዱስ ሲኖዶስ ብቻ እንዲመሩ መወሰኑም ነው የተገለፀው። ብጹዕ አቡነ አብርሃም ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ ከመጀመሪያ ጀምሮ ጉዳዩን በመከታተላቸው ምስጋና አቅርበዋል። እንዲሁም ጠቅላይ ሚኒስትሩ መንግስታቸውን ወክለው ዝቅ ብለው ይቅርታ ጠይቀዋል ይህንንም አስመልክቶ ሲኖዶሱ ከፍ ያለ ምስጋናውን አቅርበዋል።

በውጭው ሲኖዶስ በኩል የተወከሉት መላዕከ ህይወት ብርሃን የሰላምና የአንድነትና ጉባዔ ያደረገውን በአጭሩ ከመላው ዓለም ከአሜሪካ፣ አውሮፓ፣ ከናዳ ከኢትዮጵያ ተቋቁሞ ለፍጻሜ ማድረሱን ገልጸዋል። ዛሬ አንድ ለሆኑት ትላንት ሁለት በነበሩት ሲኖዶሶች መካከል ሦስተኛ አደራዳሪ ሳይገባ በራሳቸው የዕርቀ ሰላሙን መፈጸሙን አስታውቀዋል።

የአቡነ መርቆርዮስ ተወካይ የሆኑት ብጹዕ አቡነ ኤልያስ “ነገርን ሁሉ ውብ አድርጎ ሰራው ” የሚለውን የጠቢቡ ሰለሞንን መልዕክት በማንሳት ዛሬ የሆነው ነገር ሁሉ ምስጢር ነው ብለዋል። አቡነ ኤልያስ የቤተክርስትያንን ታሪክ በማንሳት ለምዕመናኑ ሰፊ ንግግር አድርገዋል። እንዲሁም መስከረም ወደ ኢትዮጵያ ለመምጣት ያሰቡ እንደነበረ ጠቅሰው ሆኖም በፈጠሪ ፍቃድ ቤተክርስትያን ዕለቱን ሰማዕቱ መርቆርዮስ እያለች በምታስብበት ቀን አቡነ መርቆርዮስ በመግባታቸው ትልቅ ምስጢር መያዙን ገልጸዋል፡፡

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ባደረጉት ንግግር “ወንድሞች በህብረት ቢኖሩ መልካም ነው” የሚለውን መልዕክት በማንሳት ዛሬ ታላቅ ደስታ ተሰምቶናል ብለዋል፡፡ እንዲሁም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያሳዩት የማቀራረብ ሂደት ባለፉት 45 ዓመታት ባልታየ ሁኔታ በሰሩት ስራ የቤተክርስቲያኒቱ ዋነኛ ታሪክ አካል መሆናቸውን ጠቅሰው በጸሎታቸውም እንደምታስባቸው ገልጸዋል። ወንድማማችነታችንና መንፈሳዊነታችንን አጸንተን ከማቆየት ምን እንከፍለዋለን ነው ያሉት። አቡነ ማትያስ ህዝበ እግዚአብሄር የሆነው ምዕመን እኛ ካልተረዳዳን ጽኑ ፈተና ያገኘዋል በዚህም ለቤተክርስትያኑ ጽናት እየተመካከርን ስራውን የበለጠ እያሻሻልን በቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ እንመራዋለን የሚል ጹኑ እምነት አለን ብለዋል፡፡

በተያያዘ ዜና የዕርቀ ሰላም መርሃ በሚሊኒየም አዳራሽ ተካሂዷል በእርቀ ሰላም መርሃ ግብሩ ላይም የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመን ጨምሮ የተለያዩ ሀይማኖት መሪዎች እና የተለያዩ ሀገራት አምባሳደሮች ታድመውበታል። የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ በመድረኩ ላይ ባደረጉት ንግግር፥ በፍቅር እና በእርቅ ተፈትቶ አንድነት በሚከበርበት በዚህ ታላቅ በዓል ላይ በመካፈሌ በራሴ እና በኢፌዴሪ መንግስት ስም የተሰማቸውን ደስታ ገልፀዋል። የቤተ ክርስቲያን መከፋፈል ሀገር እንድትከፋፈል ያደርጋል ያሉት ፕሬዚዳንት ዶክተር ሙላቱ፥ ጠንካራ የእምነት ተቋም ሳይኖር ጠንካራ ሀገር መገንባት አይቻልም ብለዋል። በኢትዮጵያ ኦቶርዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን አባቶች መካከል የተፈጠረው እርቀ ሰላም ጠንካራ ሀገር እንዲኖረን ይረዳል ሲሉም ፕሬዚዳንት ዶክተር ሙላቱ አስታውቀዋል። የኢትዮጵያ ኦቶርዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን መጠናከር ሁላችንንም ያጠነክራል ያሉት ፕሬዚዳንት ዶክተር ሙላቱ፥ እርቀ ሰላሙ ሲመጣ የተደሰትነውም ለዚህ ነው ብለዋል። በቀጣይም የሀይማኖት አባቶች ለሀገር እንድነት የሚጠበቅባቸውን ሚና እንዲወጡም ጥሪያቸውን አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ በመርሃ ግብሩ ላይ ባስተላለፉት መልእክት፥ “ከዛሬ ጀምሮ ሰላም ይሁን” ብለዋል። በሲኖዶሶቹ መካከል እርቀ ሰላም በመፈጠሩ ደስታቸውን የገለጹት አቡነ ማትያስ፥ “ለዚህ ቀን ያበቃን እግዚአብሄር አምላክ የተመሰገነ ይሁን” ሲሉም ተናግረዋል። እግዚአብሄር ሁሉንም ነገር የሚሰራበት ጊዜ አለው ያሉት አቡነ ማትያስ፥ በአባቶች መለያየት አዝነው የነበሩ ምእመናን በዛሬው እለት በአንድነት ሆነን ሲያዩን ሀዘናቸው በደስታ እንደተቀየረ ተስፋ አለንም ብለዋል። እርቀ ሰላሙ በፍጥነት ተጠናቆ ለዚህ ላበቁት ሊቃነ ጳጳሳት እና ሌሎች አካላት ምስጋናቸውን አቅርበዋል። በተለይም በእርቀ ሰላሙ ላይ በመሳተፍ እርቀ ሰላሙ ለዚህ እንዲበቃ የበኩላቸውን አስተዋፅኦ ላበረከቱት ለጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይም ምስጋናቸውን አቅርበዋል። ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ በተወካያቸው አቡነ ቴዎፍሎስ በኩል ባስተላለፉት መልእክት፥ በተፈጠረው እርቀ ሰላም መደሰታቸውን ገልፀዋል። ለዚህ እርቀ ሰላም መሳካት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ላበረከቱ ለጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር እብይ አህመድም ምስጋናቸውን አቅርበው፥ ቤተ ክርስቲያኗ ሁሌም በፀሎት ከጎናቸው መሆኗን ገልፀዋል። እንዲሁም ለእርቀ ሰላሙ መሳካት አስተዋፅኦ ላበረከቱ በሙሉ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የጠቅላይ ቤተክህነት ዋና ስራ አስኪያጅ አቡነ ዲዮስቆሮስ፥ ሁሉን ያዘጋጀው እግዚአብሄር ነው ብለዋል። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ለሀገር በርካታ ነገሮችን አብርክታለች፤ ሆኖም ግን በተለያዩ ዘመናት በቤተ ክርስቲያኗ ላይ ግፍ የፈፀሙ ቢኖሩም፤ እነሱ ሲያልፉ ቤተ ክርስቲያኗ ግን አሁንም አለች ሲሉም ተናግረዋል። አቡነ ዲዮስቆሮስ፥ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን አስተዳደር ተፈጥሮ የነበረው ልዩነት በስራዋ ላይ እንቅፋት ሆኖ መቆየቱንም አንስተዋል። ዛሬ ላይ ግን በእግዚአብሄር ፍቃድ እርቀ ሰላም ወርዶ ለሁለት ተከፍሎ የነበረው ሲኖዶስ አንድ መሆን ችሏል ያሉት አቡነ ዲዮስቆሮስ፥ ለዚህም ብጹአን ሊቃነ ጳጳሳትን አመስግነዋል። እንዲሁም እርቁ እንዲሳካ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ላደረጉት አስተዋጽኦ ቤተ ክርስቲያኗ በእርግዚአብሄር ስም ምስጋናዋን ታቀርባለች ብለዋል። ለዚህ ተግባራቸውም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ለጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ልዩ ቦታ ሰጥታ በፀሎት ታስባቸዋለች ብለዋል። በእርቀ ሰላሙ ላይ በሽምግልና ለተካፈሉ እና በተለያየ መልኩ ድጋፍ ላደረጉ አካላትም አቡነ ዲዮስቆሮስ በቤተ ክርስቲያኗ ስም ምስጋናቸውን አቅርበዋል። በመርሃ ግብሩ ላይ በአሜሪካ ዳላስ የሚገኙ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ተወካዮች ለጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ እና ለባለቤታቸው ለቀዳማዊት እመቤት ወይዘሮ ዝናሽ ታያቸው የአልማዝ ቀለበት ስጦታ አበርክተዋል።

4ኛው ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ እና 6ኛው ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ፣ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ፣ በአንድ ቀን ማዕርገ ጵጵስና ከሦስተኛው ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ተክለ ሃይማኖት የተሾሙና ሁለቱም በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ስላሴ ካቴድራል መደበኛ አገልጋዮች የነበሩ በመሆናቸው እርቀ ሳለሙ ልዩ እና ታሪካዊ ያደርገዋል፡፡