በወቅታዊ ጉዳይ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ የተሰጠ መግለጫ

266

ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ስለ ወቅታዊ ኹኔታ አስመልክቶ የተሰጠ መግለጫ

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፤ አሜን

በአገር ውስጥና በውጭ አገር የምትኖሩ፣ የተወደዳችሁና የተከበራችሁ የኢትዮጵያ ሕዝቦች ሆይ፤

ሀገራችን ኢትዮጵያ ከቅድመ ታሪክ ዘመን አንሥቶ ህልውናዋ፣ ታሪክዋ፣ ገናናነትዋ፣ ታላቅነትዋና ሥልጣኔዋ በዓለም ዘንድ የታወቀ ታላቅና አኩሪ ሀገር ናት፡፡ ለታላቅነትዋ ዓቢይ አስተዋፅኦ ካበረከቱት መካከል፥ በፈሪሀ እግዚአብሔር እና በአምልኮተ እግዚአብሔር የተገነባ፣ ስለ ሃይማኖቱና ስለ አንድነቱ ፍንክች ሳይል በአንድነትና በጽናት የቆመ ሕዝብ ያላት መኾኑ ነው፡፡

በዚህ የሃይማኖት ሥርዐት፣ የዜጎች የማይበጠስ አንድነትና ማኅበራዊ መስተጋብር ጸጋ፣ ሀገሪቱ ከውጭ ወራሪዎች የሚደርስባትን ማንኛውንም ጥቃት በሚገባ እየመከተች እስከ አኹን በኀያልነት ዘልቃለች፡፡

በዚህም የዓለም ኹሉ ጸሐፍትና ምሁራን፥ ብቸኛ የኾነ አንጸባራቂ ታሪኳን፣ ማንነትዋንና ነጻነትዋን በደማቅ ቀለም ጽፈውላታል፡፡በቀላሉ ተዝቆና ተተንትኖ የማያልቅ ሃይማኖታዊና ሀገራዊ ታሪኳ በዓለምና በአፍሪቃ ጎልቶ ሊወጣ የቻለው ሕዝቦቿ በሃይማኖት፣ በዘር፣ በቀለም፣ በመልክዐ ምድር፣ በባህልና በጥቃቅን ምክንያቶች ለሚፈጠሩ ልዩነቶች ቦታ ሳይሰጡ ዘላቂና የጋራ ጥቅማቸውን ለሚያረጋግጥ ሀገራዊ አንድነት ከማንም በፊት ቅድሚያ ሰጥተው እንደ ችቦና እንደ ነዶ አንድ ላይ በመቆማቸው እንደኾነ ታሪካችን አፍ አውጥቶ ይናገራል፡፡

በተለይም በ21ኛው መቶ ክፍለ ዘመን፣ ሀገራችን ኢትዮጵያ፥ ለምሥራቅ አፍሪቃ አልፎም ለመላው አፍሪቃና ለመላው የዓለም ጥቁር ሕዝቦች ተምሳሌት የሚኾን አንጸባራቂ የልማት፣ የአንድነትና የመልካም አስተዳደር ስኬት ታረጋግጣለች ብሎ የዓለም ሕዝብ ተስፋ በጣለበት ወቅት፣ ዜጎች ለታሪካቸው፣ ለባህላቸውና ለሃይማኖታቸው የማይመጥን ሰብእና እንደዚሁም በዓለም ሕዝብ ፊት ኃፍረትና ጸጸት የሚያስከትል ተግባር እንዳይፈጽሙ በእጅጉ መጠንቀቅ አለባቸው፡፡

እንደሚታወቀው ኹሉ፣ በመንፈሳዊው ዓለም ካልኾነ በቀር እኵያት ፍትወታት ባየለበት በዚህ ዓለም እንከን የለሽ ሥራና ሠሪ ይኖራል ተብሎ አይጠበቅም፡፡ በመኾኑም ስላለፈው እንከን ስናቀነቅን የወደፊቱ ዕድል እንዳያመልጠን ኹሉንም ነገር በፍቅርና በይቅርታ ማለፍ፣ አማራጭ የሌለው ጥበብ እንደኾነ ኢትዮጵያውያን ኹሉ በውል ሊገነዘቡት ይገባል፡፡ ሀገራችን ኢትዮጵያ በጥቁሮች ዓለም፣ በአፍሪቃና ይልቁንም በምሥራቅ አፍሪቃ፣ተጽዕኖ ፈጣሪ ኾና እንድትታይ ያደረጋት ምሥጢር፣ የሃይማኖቷ ጸጋና የሕዝቦቿ አንድነት እንደኾነ መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ፣ ተፎካካሪ የፖሊቲካ ፓርቲዎችና ወጣት ልጆቻችን ከልብ እንድትገነዘቡት እንመክራለን፡፡

ታላቅና ገናና የኾነች ኢትዮጵያ፣ በአንድነቷ እንደታፈረች፣ እንደተከበረችና ኀያል እንደኾነች እንደ ጥንቱ እንድትቀጥል የማይፈልግ ኢትዮጵያዊ እንደሌለ በርግጠኝነት እናውቃለን፡፡ ነገር ግን መንገዱን ስተን ወደ ገደል እንዳንገባ፣ በማስተዋልና በአርቆ አሳቢነት መጓዝ ይገባናል፡፡ በዚህ ዙሪያ የሃይማኖት መሪዎች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ ምሁራንና አርቲስቶች ያለመታከት ሌት ተቀን መሥራት ይኖርባችኋል፡፡ ወጣት ልጆቻችንም፣ በማኅበራዊ ሚዲያ ቅስቀሳ፣ በአፍራሽ የቅንብር ወሬና በስሜት ሳትሸነፉ የነገዋን ኢትዮጵያ ብሩህ ተስፋ ከወዲሁ በመመልከት ከኹሉም በላይ ለሀገር አንድነትና ለዜጎች ደኅንነት በጽናት እንድትቆሙ በሚወዳችኹና በምትወዱት በእግዚአብሔር ስም አደራ እንላለን፡፡

የተወደዳችኹና የተከበራችኹ የኢትዮጵያ ሕዝቦች፤

ለዚህች ሀገር መነሻም መገስገሻም ኾና ኹሉንም ኢትዮጵያዊ በእኩልነት እያስተናገደች የኖረችና ያለች የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን እንደኾነች ማንም ኢትዮጵያዊ አይስተውም፡፡ ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያናችን፥ለሀገሪቱ የባህል፣ የሃይማኖት፣ የቅርስ፣ የዕውቀት፣ የሥነ ጽሑፍ፣ የሥነ ጥበብ፣ የመቻቻልና የአብሮነት ጉልላት የኾነች፤ በማንም ይኹን በማን ላይ እጅዋን ጭና የማታውቅ፤ ኹሉንም በሰላምና በፍቅር እንደዚሁም በእናትነት መንፈስ የምትመለከት እናት ቤተ ክርስቲያን ናት፡፡

ይኹን እንጅ፣ በአኹኑ ጊዜ በእርሷም ላይ እየተሰነዘረ ያለው አሳፋሪ፣ ዘግናኝና አሠቃቂ ድርጊት፣ የእናት ጡት ነካሽ የሚያስብል፣ ሊደረግ ቀርቶ ሊታሰብ የማይችል፣ በእግዚአብሔር አምናለኹ የሚል ቀርቶ ሃይማኖት የለሽ ፍጡር የማይፈጽመው ድርጊት፥ በኢትዮጵያ ሶማሌ፣ በባሌ፣ በሻሸመኔ፣ በጣና በለስና በሌሎችም አካባቢዎች ተፈጽሞአል፡፡

ይህ ዘግናኝና አሳፋሪ ድርጊት ቅዱስ ሲኖዶስን ብቻ ሳይኾን፣ መላ ኢትዮጵያውያንን ያሸማቀቀ ድርጊት ነው፡፡ በዚህ አሳዛኝና አሠቃቂ ድርጊት ለጊዜው የታወቁት ዘጠኝ አብያተ ክርስቲያን ከነሙሉ ንብረታቸውና ሀብታቸው በቃጠሎና በዝርፊያ ወድመዋል፤ የሀገረ ስብከቱ መንበረ ጵጵስና ጽ/ቤቱና መኪናው እንደዚሁም የቤተ ክርስቲያኗ ት/ቤቶች ሙሉ በሙሉ ተቃጥለዋል፤ ንብረታቸውም ተዘርፈዋል፡፡ ለጊዜው የታወቁ አምስት ካህናት በአሠቃቂ ኹኔታ ተገድለዋል፤ ሰባት ካህናትም በጽኑ ተደብድበው ሞተዋል ከተባሉ በኋላ ተርፈው በሕክምና እየተረዱ ይገኛሉ፤ ገና ቁጥራቸው ያልታወቀ ምእመናንም ተገድለዋል፤ ተደብድበዋልም፤ ንብረታቸውም ተዘርፎአል፡፡ ይህ ኢሰብአዊ የኾነ አሠቃቂ የጭካኔ ድርጊት በኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ላይ ብቻ የተፈጸመ ሳይኾን በሌሎች አብያተ ሃይማኖትም እንደተፈጸመ ለማወቅ ተችሏል፡፡

በመኾኑም፣በቤተ ክርስቲያንና በዜጎች ላይ የደረሰው ጉዳት እጅግ ከባድ ከመኾኑ አንጻር በሀገር ውስጥም ኾነ ከሀገር ውጭ ያለው ኢትዮጵያዊ ኹሉ፣ ለወገን ደራሽ ወገን ነውና የተቸገሩትን የሚላስ፣ የሚቀመስ እንዲሁም የሚለበስ ያጡትን ወገኖች ለመርዳት የበኩሉን በማድረግ እንዲረባረብ፣ የፈረሱትንና የተቃጠሉትን አብያተ ክርስቲያን እንደገና መልሶ ለመሥራት በሚደረገው ርብርብ አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያደርግ፣ ቤተ ክርስቲያናችን በእግዚአብሔር ስም ጥሪዋን ታስተላልፋለች፡፡

በመጨረሻም፤

የዜጎች ደኅንነት፣ የሀገር ሰላምና አንድነት የሚጠበቀው ገደብ የለሽ ነፃነትና መብት በመስጠት ብቻ ሳይኾን፣ የሕግን የበላይነት በማስፈንና ሥነ ሥርዐትን በማስጠበቅ እንደኾነ ጥርጥር የለውም፡፡ ይኹንና መንግሥት ለብሔራዊ መግባባት ሲል የሚከተለው ከመጠን ያለፈ ትዕግሥት፣ የሀገሪቷን አንድነትና የዜጎቿን ደኅንነት በከባድ ኹኔታ እየሸረሸረ ስለኾነ ሳይውል ሳያድር የዜጎችን የመኖር ዋስትና፣ የሃይማኖትን ልዕልና በሕጉ መሠረት በመጠበቅ ጸጥታውን እንዲያስከበር፣ ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያናችን በአጽንዖት ትማፀናለች፡፡ እንደዚሁም ተፎካካሪ የፖሊቲካ ኃይሎችና ሕዝቡም፣ ከኹሉ በፊት ለሀገር አንድነትና ለዜጎች ደኅንነት ቅድሚያ ሰጥታችኹ እንድትሠሩ፤ ወጣት ልጆቻችንም በስሜት ተገፋፍታችኹ በወገን ላይ መጨከንን ከዛሬ ጀምሮ እርም ብላችሁ እንድታቆሙ፤ መንግሥት፣ የሃይማኖት አባቶችና የሀገር ሽምግሌዎች፣ የሚሏችሁን ብቻ እየሰማችሁ ሀገር የምታድግበትን፣ አንድነቷ የሚጠበቅበትንና ሰላሟ የሚጠናከርበትን ሥራ ብቻ ለመሥራት በማስተዋል እንድትተጉ አባታዊ መልእክታችንን በድጋሚ በእግዚአብሔር ስም እናስተላልፋለን፡፡

እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይባርክ

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፤ አሜን፡፡

አባ ማትያስ ቀዳማዊ

ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ

ሊቀ ጳጳስ ዘአኵስም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት

ነሐሴ ፲፩ ቀን ፳፻፲ ዓ.ም.

አዲስ አበባ