በኢ/ ኦ/ተ/ቤ/ ክ/የመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል
  • ቀዳሚ ገጽ
  • መ/ጸ/ቅ/ሥ/ካቴድራል
    • የአስተዳዳሪው መልእክት
    • ታሪክ
    • አስተዳደራዊ መዋቅር
    • የልማት እንቅስቃሴዎች
    • መንፈሳዊ አገልግሎቶች
    • ፎቶዎች
  • ቤተ መዘክር
    • የቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ቤተ መዘክር
    • ፎቶዎች
  • ት/ ቤት
    • መግቢያ
    • መሰናዶ እና 2ኛ ደረጃ
    • 2ኛ ደረጃ ት/ቤት ወርሐዊ ክፍያ
    • 1ኛ ድረጃ ት/ቤት ወርሐዊ ክፍያ
    • ፎቶዎች
  • ሰንበት ት/ቤት
    • መግቢያ
    • አውደ ወራዙት
    • ፎቶዎች
  • አገልግሎቶች
    • መግቢያ
    • ፎቶዎች
  • ስብከተ ወንጌል
    • መግቢያ
    • ታሪክ
    • ፎቶዎች
  • Menu Menu

ቅዱስ ሲኖዶስ የዴርሱልጣን ገዳም ጉዳይን አስመልክቶ መግለጫ ሰጠ

November 1, 2018

15

በስመአብወወልድወመንፈስቅዱስአሐዱአምላክአሜን!

የኢትዮጵያውያን ይዞታ በሆነው በዴርሱልጣን ገዳም የቅዱስ ሚካኤል ቤተመቅደስ እድሳት ላይ የግብጽ ኮፕቲክ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን አባላት ያሳዩትን ሕገወጥ ተቃውሞ አስመልክቶ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ የተሰጠ መግለጫ፤

ሁላችሁም እንደምታውቁት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን በኢየሩሳሌም ካሏት ጥንታውያንና ታሪካውያን ቅዱሳት መካናት ውስጥ አንዱና ዋናው በዴርሱልጣን የሚገኘው የመድኀኔዓለም፣ የአርባዕቱ እንስሳ እና የቅዱስ ሚካኤል ገዳማት ናቸው፡፡

ከታሪክ እንደምንረዳው ኢትዮጵያውያን በምድረ እስራኤል የነበራቸው ርስት ከሦስት ሽህ ዓመት በላይ ያስቆጠረ ነው፡፡ በብሉይ ኪዳን የአሁኗ ኢትዮጵያ መልክዓ ምድራዊ መገኛዋን ከዓባይ ምንጭ ጋር በማያያዝ ያለምንም ማሳሳት ከአርባ ጊዜ በላይ የተመዘገበች፤ በታሪክ፣ በእምነትና በማኅበራዊ ትሥሥር ከእስራኤል ጋር የጸና ግንኙነት ያላት ሀገር ናት፡፡

ከንግሥተ ሳባ የኢየሩሳሌም ጉብኝት ጀምሮ ኢትዮጵያውያን ወደ ቅድስት ሀገር ያለማቋረጥ በየዓመቱ በዓለ ፋሲካን ለማክበር፣  ዓመታዊ አምልኮተ እግዚአብሔርን ለመፈጸም፣ በርስት የተሰጣቸውን ይዞታ ለማስከበርና በንግድ ሥራዎች ይጓዙ እንደነበር በታሪክም በቅዱሳት መጻሕፍትም የተረጋገጠ እውነት ነው፡፡ 

ለዚህም በሐዲስ ኪዳን ክርስትና ወደ ኢትዮጵያ ለመግባቱ ምክንያት የሆነውና በሐዋርያት ሥራ ምዕራፍ 8 ከቁጥር 26 እስከ 40 የተጻፈው የኢትዮጵያዊው ጃንደረባ ታሪክ አንዱ ማሳያ ነው፡፡

ኢትዮጵያውያን ወደ ኢየሩሳሌም በሚያደርጉት ጉዞ፣ መንፈሳዊና ማኅበራዊ ትሥሥርን ከማጠናከር ባሻገር በዴርሱልጣን እና በብዙ መካናት ቋሚ ይዞታን በማቋቋም በርካታ ገዳማትንና አድባራትን መሥርተዋል፣ መንበረ ጵጵስናም አቋቁመዋል፡፡ ይህም ድርጊት ኢትዮጵያ በኢየሩሳሌም የሕዝቦቿ ምልክትና መመኪያ እድትሆን አድርጓታል፡፡

ይሁን እንጅ ነባሩን ታሪካዊ እውነት ለመሻርና በማይገባ ሁኔታ ግብፃውያን በሌላቸው መብትና ሕጋዊ ባልሆነ የፈጠራ መረጃ ኢትዮጵያን ከኢየሩሳሌም የዴርሱልጣን ገዳም ባለቤትነቷን ለማሳጣት ብዙ ጥረቶች ሲደረጉ ቢቆዩም ኢትዮጵያውያን ሕይወታቸውን ሳይቀር መስዋዕት በማድረግ ሃይማኖታቸውንና ጥንታዊ ገዳማቸውን ጠብቀው እስከ አሁን ቆይተዋል፡፡ 

የኢትዮጵያውያን የኢየሩሳሌም ይዞታ ከቅዱሳት መጻሕፍት ማስረጃነት በተጨማሪ ኢየሩሳሌምን ይገዙ በነበሩ መሪዎች የግብርና የመንግሥት አዋጅ መዛግብት፣ ኢየሩሳሌም ድረስ ተጉዘው ታሪክ በጻፉ ምሁራን፣ በኢየሩሳሌም ተሳላሚዎች የግል ማስታወሻ እና በዓለም አቀፍ መዛግብት ሳይቀር የተመዘገበ ሐቅ ነው፡፡ 

ለምሳሌ ያህልም እንደነ አባ ጀሮም ያሉ የላቲን ታሪክ ጸሐፊዎች፣ እንደነ ከሊፋ ዑመርና ሳላሐዲን ባሉ ገዥዎች፣ በኢየሩሳሌም ተመሳሳይ ይዞታ ባላቸው በአርመንና በሶርያ ኦሬንታል ኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት፣ በግሪክና በራሽያ የምሥራቅ ኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት እንዲሁም በካቶሊክ ቤተክርስቲያን ልዩ ልዩ ገዳማት መዛግብት የተመሰከረ ነው፡፡ 

ይሁን እንጅ ግብፃውያን በሚፈጥሩት ግፍና ኢሰብዓዊ ድርጊት በይዞታችን ያለውን ገዳም ከጉዳት ለመጠበቅና ለማደስ አንኳ ሳንችል በመቅረታችን እየፈራረሰ ይገኛል፡፡ 

በመሆኑም ቤተክርስቲያኒቱ ስታሰማ በነበረው ተደጋጋሚ አቤቱታና የኢትዮጵያ መንግሥት ባቀረበው ሕጋዊ የመብት ጥያቄ መሠረት የእስራኤል መንግሥት ገዳሙን ለማደስ ቃል በመግባቱ እና በዚሁ መሠረት መንግሥት ቃሉን በመጠበቅ በቅርቡ ጉዳት ከደረሰበት ከቅዱስ ሚካኤል ቤተመቅደስ እድሳቱ በመጀመሩ የተሰማንን ከፍተኛ ደስታ በቅድስት ቤተክርስቲያን እና በመላው ኢትዮጵያውያን ስም በመግለጽ ልባዊ ምስጋናችንን እናቀርባለን፡፡

የተጀመረው እድሳት በዴርሱልጣን የሚገኙ እና እጅግ በአስከፊ ጉዳት ላይ ያሉ ሁሉንም የኢትዮጵያ ይዞታዎች በማዳረስ ገዳሙ ጥንታዊ ይዞታውን ጠብቆ ለትውልድ እንዲተላለፍ እንደሚደረግልን እናምናለን፡፡

አሁን እየተደረገ ያለውን ጥገና አስመልክቶ የኢትዮጵያ መንግሥትም ሆነ በመላው ዓለም የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ለእስራኤል መንግሥት ምስጋናችሁን እንድታቀርቡልን የግብጽ ቤተክርስቲያንን መሠረት የለሽ ክስና ሁከት በመቃወም ገዳማችሁን በመጠበቅ የበኩላችሁን እንድትወጡ፣ ወደ ፊትም ከግብጽ ያልተመለሱ ይዞታዎቻችንን ለማስመለስ ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ እንድታደርጉ ጥሪ እናደርጋለን፡፡

በዚሁ አጋጣሚየ ግብጽ ኮፕቲክ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን አባላት በይዞታችን ላይ አግባብነት የሌለው ሥራን የማደናቀፍና በታሪክም ሆነ በማንኛውም የሰነድ ማስረጃ መሠረት የሌለው የባለቤትንት ጥያቄ በማንሣት እየፈጠሩት ያለውን አላስፈላጊ ሁከትና ብጥብጥ እንዲያቆሙ፣ 

ዴርሱልጣን የኢትዮጵያ ገዳም ምንጊዜም ቢሆን የኢትዮጵያ የነበረና ወደፊትም የኢትዮጵያ ሆኖ የሚቆይ ታሪካዊና ሃይማኖታዊ ቅርሳችን፣ የኢትዮጵያውያን በኢየሩሳሌም ቅድስት ሀገር በሁሉም ዘመን በቋሚነት ለመገኝታቸው ምስክር ስለሆነ ከዚህ የተሳሳተ ትንኮሳና ሁከት እንዲታቀቡ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን፡፡

በመጨረሻም የተጀመረው የእድሳት ሥራ ተጠናክሮ በመቀጠል ሁሉንም የኢትዮጵያ የዴርሱልጣን ይዞታዎች በአግባቡ እንዲጠገኑልን፣ 

በኢትዮጵያ መንግሥትም ሆነ የሰው ልጅ ቅርስ ጥበቃ ለሚያሳስባቸው በጎ አድራጊዎች ሁሉ ጥሪያችንን እያስተላለፍን እድሳቱ ያለምንም እንቅፋትና ሁከት ከፍጻሜ እንዲደርስ ጸሎታችንና ምኞታችን መሆኑን እናስታውቃለን፡፡

እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይባርክ

ወስብሐት ለእግዚብሔር አሜን!

አባ ማትያስ ቀዳማዊ

ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነጳጳሳት ዘኢትዮጵያ

ሊቀጳጳስ ዘአኵስም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት

ጥቅምት 21 ቀን 2011 ዓ.ም.

አዲስ አበባ፡ ኢትዮጵያ

Share this entry
  • Share on Facebook
  • Share on X
  • Share on Pinterest
  • Share on LinkedIn
  • Share on Tumblr
  • Share on Vk
  • Share on Reddit
  • Share by Mail
https://eotc-htc.org/a/wp-content/uploads/holytrinity/15.jpg 402 500 tc https://eotc-htc.org/a/wp-content/uploads/logo_am2.png tc2018-11-01 04:59:532018-11-01 04:59:53ቅዱስ ሲኖዶስ የዴርሱልጣን ገዳም ጉዳይን አስመልክቶ መግለጫ ሰጠ

መፈለጊያ

Search Search

በቅርብ የተለቀቁ

  • የአርባዕቱ እንስሳ (ኪሩቤል) የንግሥ በዓል በመካነ ሥላሴ ቅዱስ በዓለ ወልድ ቤ/ክ በድምቀት ተከበረ። 
  • ⛪️ከቅዱስ ሲኖዶስ መግለጫ የተቀነጨበ
  • የቅዱስ ሲኖዶስ መግለጫ
  • ቅዱስ ፓትርያርኩ በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል በመገኘት የካቴድራሉ እድሳት የሚገኝበት ደረጃ ጉብኝት አድርገዋል። (መስከረም 2017 ዓ.ም)
  • ከእዚህ በላይ ደስታ ምን አለ፤ እንኳን ደስ አላችሁ፤
  • “ቤተ መቅድሳችንን እናድስ ለቀጣዩም ትውልድ እናድርስ ፣ ኃላፊነታችንንም እንወጣ!” መሪ ቃል
  • ሁላችንም የኢትዮዽያ ልጆች ከከተማ እስከ ገጠር ያለን የመ/ጸ/ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ጠባቂዎች እና ደጋፊዎች ነን‼️
  • ሚያዚያ 10 ቀን 2016 ዓ.ም የመ/ጸ/ቅ/ሥላሴ ካቴድራል ህንጻ ዕድሳትን አስመልክቶ መግለጫ ተሰጠ፤
  • የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ፲፩ኛ ዓመት በዓለ ሢመተ ፕትርክና የካቲት ፳፬/፳፻፲፮ ዓ/ም በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ይከበራል።
  • የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ የጾመ ነነዌ መልዕክት

አስተያየቶች

    © Holy Trinity Cathedral | Website by atbiya.com
      Link to: የጥቅምት 2011 ዓ.ም ቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ባለ 15 ነጥቦች መግለጫ በማወጣት ተጠናቀቀ Link to: የጥቅምት 2011 ዓ.ም ቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ባለ 15 ነጥቦች መግለጫ በማወጣት ተጠናቀቀ የጥቅምት 2011 ዓ.ም ቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ባለ... Link to: የካቴድራሉ ፎቶዎች Link to: የካቴድራሉ ፎቶዎች የካቴድራሉ ፎቶዎች
      Scroll to top Scroll to top Scroll to top