ከሁሉ አስቀድሜ የሥራና የጊዜ ባለቤት የሆነው አምላካችን እግዚአብሔር ለሀገርና ለወገን የሚጠቅም መልካም ሥራ የምንሠራበትን ጊዜ በቸርነቱ ስለሰጠን ክብርና ምስጋና ሁሉ ለእርሱ ይሁን፡፡
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን በሁለንተናዊ መልኩ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ያበረከተቺው አስተዋፅዖ ታሪክ የማይረሳው ፤ይልቁንም ታሪኩ ከትውልድ ወደ ትውልድ ሳይቋረጥ ሲሻጋገር የሚኖር የታሪክ ባለቤት ናት፡፡ ቀደምት የቤተ ክርስቲያን አባቶቻችን በነበራቸው ከፍተኛ የቤተ ክርስቲያን፣የሀገርና የህዝብ ፍቅር ዘመኑ በፈቀደላቸው መጠን ለሀገርና ለወገን የሚጠቅምና የሚያኮራ ሥራ በመሥራት ቤተ ክርስቲያናችን በመላው በዓለም ላይ ሐዋርያዊት፣ታሪካዊት እና ብሔራዊት እንድትሆን አስችለዋታል፡፡
ሀገራችን ኢትዮጵያ ስሟ በቅዱስ መጽሐፍ ከ41 ጊዜ በላይ ተደጋግሞ የተፃፈው ሀገረ እግዚአብሔር በመሆኗ እና በክርስትና ሃይማኖቷ ቀዳሚ ሀገር ከመሆኗም በላይ የቀደምት የሥልጣኔ እና የሥነ–ጥበብ ባለቤት፤ እንዲሁም የሀገሪቱ ከፍተኛ የቱሪስት መስህብ ባለቤት በመሆኗ ነው፡፡
ቤተ ክርስቲያኒቱ ሀገሪቱ የራሷ የሆነ ብቸኛ ፊደል እና የቀን አቆጣር እንዲኖራት ያስቻለች ከመሆኗም ባሻገር እስከ 19ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ድርስ ብቸኛ የሀገሪቱ የትምህርት ተቅዋም/ትምህርት ሚኒስተር በመሆን ከፍተኛ የተማረ የሰው ኃይል በማፍራት ረገድ የተጨወተችው ሚና እንዲሁ በቃላት ብቻ የሚገላፅ አይደልም፡፡
የቤተ ክርስቲያን ህልውና በትምህርተ ወንጌል ላይ የተመሠረተ ስለሆነ ዘወትር መግቦቷን ሳታቋርጥ በካህናት አገልጋዮቿ ሌሊት በሰዓታት፣ በማኅሌት፣ በስብሐተ ነግህ እና በሌሎችም መንፈሳዊ ሥራዎች ሁሉ የምትሰጠው አገልግሎት በቀላል የሚገመት አይደለም፡፡
ቅድስት ሥላሴ ካቴድራልም ሀገራዊና ሃይማኖታዊ ሃላፊነቱን ለመወጣት ከመቸውም ጊዜ በተሻለ መልኩ የቤተ ክርስቲያኒቱና የህብረተሰቡን ፍላጎት ባማከለና ዘመኑ በሚጠይቀው መልኩ መንፈሳዊና ማኅበራዊ አገልግሎቶችን ለመስጠት ፈተናዎችን ሁሉ ተቋቁሞ ሌት ተቀን ጠንክሮ በመስራት ላይ ይገኛል፡፡
የመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ሰበካ ጉባዔ ከተመሠረተበት ጊዜ ጀምሮ የገቢ ዕድገት በማሳየት በልማትና መንፈሳዊ ጉዞዎች እየተጠናከረ መጥቶ አሁን ካለንበት ደረጃ ሊደርስ ችሏል፡፡ ነገር ግን አሁንም ብዙ ሥራ እንደሚቀር አያጠራጥርም ፡፡
የኢ/ኦ/ተ/ቤተ ክርስቲያን ልዕልና መገለጫ የሆነው ካቴድራሉ ቀደም ባሉ ጊዜያት ለመላዋ ኢትዮጵያ በአጭርና በመካከለኛ ሞገድ ብሥራተ ወንጌል በሚል ይታወቅ በነበረው ሬድዮ ጣቢያ በየቀኑ የሚተላለፉ ትምህርቶችን የሚያዘጋጁ ምሁራንን ያቀፈ የኢ/ኦ/ተ/ቤተ ክርስቲያን ሐዋርያዊ ድርጅት በሚል ስያሜ ተቋቁሞ በዚሁ ካቴድራል እንደነበርና የስርጭት ሽፋኑም በመላዋ ኢትዮጵያና አፍሪካ በሙሉ እንዲሁም በእስያ አህጉራት የሚዘልቅ እንደነበር የታሪክ ማኅደራት ምስክሮች ናቸው፡፡
የሰው ልጅ ሲፈጠር በቦታ የሚወሰንና የሚገደብ ሆኖ በመፈጠሩ በሌላ ሥፍራ ያለውን ነገር ሁሉ በራሱ ማወቅ አይችልም፡፡ሆኖም የሰው ልጅ ከእግዚአብሔር የተሰጠውን አዕምሮ በመጠቀም የተለያዩ የመገናኛ ዘዴዎችን ሠርቷል፡፡
ከእነዚህም መካከል አሁን በዚህ ዘመን የተጀመረው የመረጃ መረብ ቴክኖሎጂ አንዱ ተጠቃሻ ሲሆን ይህ ቴክኖሎጂ ትውልዱ ሲጠቀምበት በዓለማዊ ትምህርት ብቻ ተወስኖ እንዳይቀር መንፈሳዊ ትምህርትንም ለማስታላለፍ ጥሩ አማራጭ መንገድ በመሆኑ ቤተ ክርስቲያናችንም በእውቀቱ የተካኑትን ልጆቿን በመጠቀም ዘመኑ ባስገኘው ቴክኖሎጂ ትምህርት እንዲተላለፍ መደረጉ ጠቀሜታው እጅግ የላቀ ነው፡፡
የመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራልም ዘመኑ ያስገኘውን ቴክኖሎጂ በመጠቀም ታሪካዊውንና ዓለም አቀፋዊ ይዘት ያለውን ካቴድራል አገልግሎቱን የበለጠ ለማሳደግና በመላው ለዓለም ለማስተዋወቅ እንዲረዳ ታስቦ ከ2003 ዓ.ም ጀምሮ አገልግሎት ላይ ነበረውን ድረ-ገፅ በአዲስ መልክ ከጥር 7/2011 ዓ.ም ጀምሮ ደረጃውን የጠበቀ ዘመናዊ ኦፊሻል ድረ-ገፅ ተዘጋጅቶ ሥራ ላይ እንዲውል አድርገናል፡፡
የዚሁ አገልግሎትም ዘመኑ ባስገኘው ቴክኖሎጂ በመጠቀም ስብከተ ወንጌልን እና የቤተ ክርስቲያናችንን አስተምህሮ ለዓለም ሕዝብ በማዳረስ ዓይነተኛ መሣሪያ ሆኖ አገልግሎት መስጠት ሲሆን በተጨማሪም ድረ ገጹን በመጠቀም የቤተ ክርስቲያናችንን አኩሪ ታሪክ ፤ቅርስና ታሪካዊ ቦታዎችን ከማስተዋወቅ ባሻገር ወቅታዊ የሆኑ መንፈሳዊና ማኅበራዊ መረጃዎችን ለኢትዮጵያ ኦርቶዶከስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን እምነት ተከታዮች በቀላሉ እንዲዳረስ በማድረግ ነው ፡፡
በአሁኑ ሰዓት የካቴድራሉ ድረ- ገጽ ለሕዝበ ክርስቲያኑ ጠቃሚ የሆነ መረጃ ከመስጠቱም በላይ ለሀገር ውስጥና ለውጭ ሀገር ጎብኚዎች መረጃን በመስጠት ረገድ እጅግ በጣም አመርቂ የሆነ ሥራ በመሥራት ላይ ይገኛል፡፡
እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይባርክ
ሊቀሥልጣናት ቆሞስ አባ ገ/ዋህድ ገ/ኪዳን
የመ/ጸ/ቅ/ሥላሴ ካቴድሪል አስተዳዳሪ