የ2005ዓ.ም የጥምቀት በዓል በድምቀት ተከበረ

እንኳን ለጌታችን ለአምላካችን ለመድኀኒታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ በዓለ ጥመቀት በሰላም በጤና በሕይወት አደረሳችሁ፡፡

                                  በመ/ር ዘሩ ብርሃኔ

6

በየዓመቱ ጥር 10 እና 11 የሚከበረው የጌታችን የአምላካችን የመድኀኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ በዓለ ጥመቀት በገነተ ኢየሱስ ቤተክርስቲያን መሪነት ከ13 ታቦታት በላይ በሚያድሩበት በጃን ሜዳ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ዐቃቤ መንበረ ፓትርያርክና የአርሲ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ናትናኤልና ብፁአን ሊቃነ ጳጳሳት እንዲሁም በመቶ ሽህ የሚቆጠሩ ምዕመናን በተገኙበት እጅግ በጣም በደመቀ ሁኔታ በዓሉ ተከብሮ ውልዋል፡፡ የዓመቱ ተረኛ የሆነው የገነተ ኢየሱስ ቤተክርስቲያን መዘምራን ዕለቱን በማስመልከት ያሬዳዊ ዝማሬ

‹‹ ተሰሃልከ እግዚኦ ምደረከ ሃሌ ሉያ ወረደ ወልድ እም ሰማያት ውስተ ምጥማቃት በፍስሐ ወበሰላም››በማለት ያሬዳዊ ዜማ አቅርበዋል፡፡ በቤተክርስቲያናችን ሥርዓት መሠረት ዐበይት በዓላት ተብለው ከሚጠቀሱት መካከል የጥምቀት በዓል አንዱ ነው፡፡ይህም በዓል ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በእደ ዮሐንስ ፤ በማእከለ ዮርዳኖስ የተጠመቀበትን ቅድስት ቤተክርስቲያናችን በየዓመቱ ከዋዜማው ከጥር 10 ጀምሮ በደመቀ ሁኔታ በማክበር ላይ ትገኛለች፡፡ ለእኛ አብነት ይሆነን ዘንድ፤ የእዳ ደብዳቤያችንን እንደ ገል ቀጥቅጦ እንደ ሰም አቅልጦ በደላችንን ይደመስስ ዘንድ ጌታ በዮርዳኖስ ወንዝ ተጠመቀ፡፡

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ይህንን መሠረት በማረድግ በየአብያተ ክርስቲያናቱ የሚገኙ ታቦታት በብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት፣ በሊቃውንተ ቤተክርስቲያን፣ በካህናትና ዲያቆናት፤ እንዲሁም በሰንበት ት/ቤቶች መዘምራንና ምዕመናን በዝማሬ በመታጀብ በአቅራቢያቸው ወደሚገኘው ታቦት ማደሪያ በማምራት ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከገሊላ ወደ ዮርዳኖስ ወንዝ በመሔድ በዮሐንስ እጅ ለመጠመቅ ማምራቱን ያበስራሉ፡፡ ‹‹ያን ጊዜም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከገሊላ ናዝሬት መጣ ዮሐንስም በዮርዳኖሰ ወንዝ አጠመቀው›› እንዲል፡፡/ማቴ.3፡1/ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን መስራቿን መድኅነ ዓለም ክርስቶስን ለዓለም የምትሰብክበት፣ ከእርሱም ያገኘችውን፣ ይህም ዓለም እንደሚሰጠው ያልሆነውን፣ የእግዚአብሔር ልጅነት፣ ሰላም፣ ፍቅርና ትሕትና ለዓለሙ ትሰብክበታለች፡፡ እንዲሁም ለሀገራችን በጎ ገጽታን በመፍጠር ረገድ ከተለያዩ ሀገራት የሚመጡ ጎብኚዎች ተደንቀው የሚያዩትና በመስተንግዶው የሚደመሙበት በመሆኑ ሃይማኖታዊ በዓሉን በልዩ ትኩረት ታከብራለች፡፡

ለዚህ በዓል አከባበር ቤተክርስቲያን ቅድመ ዝግጅቶችን በማድረግ ታቦታት በሰላም ወጥተው በሰላም እንዲመለሱ ጉልህ ሚናዋን ትወጣለች፡፡ በዚህ መሠረት በየአጥቢያው የሚገኙ ወጣቶች ከክብረ በዓሉ ቀደም ብሎ ለሐላፊነት በመሰብሰብ ቅዱሳት ሥዕላትን በታቦታት ማረፊያዎች በማዘጋጀት፣ በተለያዩ ህብረ ቀለማት ያሸበረቁ ጨርቆችን /ባነሮችን/፤ የኢትዮጵያ ባንዲራን በየአብያተ ክርስቲያናቱ አደባባዮች በመስቀል፣ የቤተክርስቲያናትን ቅጥርና አስፋልት በማጽዳት ፤ለታቦት ክብርን ለመስጠት ምንጣፎችን በማንጠፍ በዓሉን ያደምቁታል፡፡

ምእመናን ከየቤታቸው ለበዓሉ በሚገባው ልብስ አሸብረቀው ወጥተዋል፡፡ እናቶቻችን ከየአጥቢያ አብያተ ክርስቲያናቱ የሚሰሙትን የሊቃውንት አባቶቻችን ወረብ ተከትልው፣ የታቦታቱን መውጣት በመጠባበቅ እልልታቸውን ያሰማሉ፡፡ የሰንበት ትምህርት ቤት ወጣቶችም ዝግጅቶቻቸውን አጠናቅዋል፣ የዝማሬ ልብሳቸውን ለብሰዋል፡፡ ምእመናኑም ከየመሥሪያ ቤታቸው በር ላይ ቆሞው የታቦታትን ማለፍ እያዩና በእልልታ እና በጭብጨባ እያጀቡ በእነርሱም መባረክን ዓይናቸው ተስፋ እያደረገች ታቦታቱ የሚመጡበትን አቅጣጫ ያማትራሉ፡፡ ከሰዓት በኋላ በነበረው መርሐ ግብር በተለይም በጃንሜዳ ከየአድባራቱ አስራ ሦስት ታቦታት በአንድነት የሚገኙበት በመሆኑ ህዝቡን ለመባረክ የተገኙት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ዐቃቤ መንበረ ፓትርያርክና የአርሲ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ናትናኤል ከብጹዓን ሊቃነ ጳጳሳት ጋር በመሆን፤ ሊቃውንተ ቤተክርስቲያን ልብሰ ተክህኖ ለብሰው ፤በመዘምራንና ምዕመናን በመታጀብ ጉዞ የተጀመረ ሲሆን አመሻሽ ላይ ጃን ሜዳ ሊደርሱ ችለዋል፡፡

5.7

የየሰንበት ት/ቤቶቹ መዘምራን ፤ የማኅበረ ቅዱሳን መዝሙር ክፍል አባላት ያሬዳዊ ዜማ እየዘመሩ ፤ምዕመናን በዕልልታና በሸብሸባ ታቦታቱን በማጀብ በዓሉን አድምቀውታል፡፡ በመቀጠልም እለቱን በማስመልከት በአቃቤ መንበረ ፓትርያርክ በብፁዕ አቡነ ናትናኤል መልካም ፈቃድ ብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤል የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ፤ የደቡብና ምዕራብ አዲስ አበባ አህጉረ ስብከትና የከፋ ሸካ ቤንች ማጂ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ እለቱን በማስመልከት ቃለ ምዕዳን ሰጥተዋል፡፡ ብፁዕነታቸው በሰጡት ቃለ ምዕዳን “የእግዚአብሔር ቸርነት ሰፊ ነው፡፡ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ልዑለ ባሕሪውን ዝቅ አድርጎ ወደ ባሕረ ዮርዳኖስ ዮሐንስ ወዳለበት ቦታ ለመጠመቅ መጥቷል፡፡

ዮሐንስን አጥምቀኝ ማለቱ ለእኛ አብነት ለመሆንና ለቤተ ክርስቲያን ሥርዓትን ለመመሥረት ሲል ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዮሐንስ እጅ ተጠመቀ፡፡ ዮሐንስ ወደ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሔዶ አጥምቆት ቢሆን ኖሮ ምእመናን ቀሳውስቱን እቤታችን ድረስ መጥታችሁ አጥመቁን እንጂ ወደ ቤተ ክርስቲያን አንሔድም ባሉ ነበር፡፡ ቤተ ክርስቲያን ሥርዓት የሌላት እንዳትሆን ሥርዓትን ለማስተማር ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዮርዳኖስ ባሕር፤ በዮሐንስ እጅ ተጠመቀ” ብለዋል፡፡ በመቀጠልም ብፁዕ አቡነ ናትናኤል የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አቃቤ መንበረ ፓትርያርክና የአርሲ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በሰጡት ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ “ጥምቀትን በየዓመቱ የምናከብረው እግዚአብሔርን ለማመስገን ነው፤ በዝናብ አብቅሎ በጸሐይ አብስሎ የሚመግብ እርሱ ስለሆነ፡፡ ሥጋውን ቆርሶ ደሙን አፍስሶ የሰጠ አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ የባህርይ አምላክ ነውና ከሦስቱ አካል አንዱ አካል መሆኑን በአደባባይ የገለጠበት ታላቅ የቤተ ክርስቲያናችን በዓል ነው” በማለት እለቱን በማስመልከት የገለጹ ሲሆን በብፁዕነታቸው ቡራኬ የበዓሉ ፍጻሜ ሆኗል፡፡ የበዓሉ ሥነ ሥርዓት ምሽቱን በመቀጠል ትምህርት በተለያዩ የቤተ ክርስቲያኒቱ ሊቃውንት የተሰጠ ሲሆን በእለቱ ተረኛ በሆነው በገነተ ኢየሱስና ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን ሊቀውንትና ሰንበት ትምህርት ቤት ተማሪዎች፤ የማኅበረ ቅዱሳን መዝሙር ክፍል አባላት ያሬዳዊ ዝማሬ አቅርበዋል፡፡

 5.8

የለሊቱ ሥርዓተ ማህሌትና ሥርዓተ ቅዳሴ በባለተረኛው በገነተ ኢየሱስ ካህናትና መዘምራን ተከናውኗል፡፡ ከለሊቱ 12፡30 ሰዓት ጀምሮ በብፁዕ አቡነ ናትናኤል የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አቃቤ መንበረ ፓትርያርክና የአርሲ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ እየተመራ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፤ የግሪክ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ አቡነ ጴጥሮስ፤ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ተወካይ ክቡር አቶ ታደሰ በንቲ፤በኢትዮጵያ የግብጽ አምባሳደር፤ጥሪ የተደረገላአቸው እንግዶች፤ አገር ጎብኚዎች፤ የየአድባራትና ገዳማት አስተዳዳሪዎችና ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን እንዲሁም ምእመናን በተገኙበት የጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጥምቀትን በማስመለከት ጸሎተ ወንጌል በማድረስ መርሐ ግብሩ ተጀመረ፡፡ ጸበሉም ተባርኮ ለምእመናን እንዲዳረስ ተደርጓል፡፡ በብፁዕ አቡነ ናትናኤል አቃቤ መንበረ ፓትርያርክ መልካም ፈቃድ ብፁዕ አቡነ ሉቃስ የሰቲት ሁመራ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ እለቱን በማስመልከት ትምህርተ ወንጌል ሰጥተዋል፡፡ ባሰተላለፉት ትምህርትም “በዓላችን የሰላማችን ፤የአንድነታችን ምልክት ነው፡፡ መሠረቱም ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዮርዳኖስ አደባባይ ተገኝቶ የእኛን ችግር ያስወገደበት ፤ ነፃነታችንን ያገኘንበት፤ የኀጢዓት ደብዳቤያችን የተቀደደበት፤ዮርዳኖስን ተሻግረን በአንድነት ድኅነት መንግስተ ሰማያትን ያየንበት እለት ነው፡፡

ዛሬ በአንድነት በዘመነ ፍዳ የተዘጋው ጆሯችን የአብ ድምጽ የሰማበት ቀን ነው፡፡” ብለዋል፡፡ በመጨረሻም በዐቃቤ መንበረ ፓትርያርክና የአርሲ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በብፁዕ አቡነ ናትናኤል ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ ተሰጥቶ ታቦታቱ ወደየ ማረፊያ ቦታቻው በክብርና በሰላም ተመልሰዋል፡፡ ወስብሐት ለእግዚአብሔር