የኢ.ኦ.ተ.ቤ.ክ.የ6ኛው ፓትርያርክ በዓለ ሢመት በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ተፈጸመ

                            በመ/ር ዘሩ ብርሃኔ

d

ብፁእ አቡነ ማትያስ በእስራኤል የኢትዮጵያ ገዳማት ሊቀ ጳጳስ ስድስተኛው የኢትዮጵዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስትያን ፓትሪያሪክ በመሆን የካቲት 21/2005 ዓ.ም እንደተመረጡ መዘገባችን የሚታወስ ሲሆን በዚሁ በተካሄደው የድምፅ አሰጣጥ 806 ሰዎች የተሳተፉ ሲሆን ፥ ከዚህ ውስጥ አቡነ ማትያስ 500 ድምፅ በማግኘት ነበር ስድስተኛው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ሆነው የተመረጡት፡፡

በዚሁም መሠረት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን 6ኛ ፓትርያርክ ሆነው የተመረጡት የብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ሥርዓተ ሢመት በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል የካቲት 24 ቀን 2005 ዓ.ም. እጅግ ባማረ/በደመቀ ሁኔታ ስርዓተ ሢመቱ ተከናውኗል፡፡

ከዋዜማው 2.00 ሰዓት ጀምሮ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ስብሐተ እግዚአብሔር ሲያደርሱ ያደሩ ሲሆን ከሌሊቱ 10፡00 ሰዓት ላይ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ከብፁዐን ሊቃነ ጳጳሳት ጋር በመሆን በመንበረ ጸባዖት ቅድሥት ሥላሴ ካቴድራል ሲደርሱ በክቡር መልአከ ሰላም ዳዊት ያሬድ የሰሜን አዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ስራ አስከያጅ ፤ በክቡር ሊቀ ሥልጣናት አባ ገ/ሥላሴ በላይ የመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ዋና አስተዳዳሪ እና ልብሰ ተክህኖና ጥንግ ድርብ በለበሱ የካቴድራሉ ካህናትና መዘምራን ደማቅ አቀባበል አድርገውላቸዋል ሁለቱም የካቴድራሉ ደወሎችም ለ20 ደቂቃ ያህል ተደውሏል ፡፡

በመቀጠል ኪዳን የደረሰ ሲሆን ከፀሎተ ኪዳን/ከኪዳን ጸሎት በኋላ ሥርዓተ ቅዳሴ የቀጠለ ሲሆን ፤ ከሥርዓተ ቅዳሴው ጋር በማያያዝ የቅዱስ ፓትርያርኩ ሥርዓተ ሢመት በአቃቤ መንበሩ በብፁዕ አቡነ ናትናኤል እየተመራ በማከናወን ቅዱስ ፓትርያርኩ ቤተ ክርስቲያኒቱን ለማገልገል ቃለ መሐላ ፈጽመዋል፡፡

ከሥርዓተ ሢመቱ በኋላ ከአኀት ቤተ ክርስቲያናት መካከል የሕንድ፤ የግብጽ እንዲሁም የአርመን ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያናት በየተራ ጸሎት አድርሰዋል፡፡ ሥርዓተ ቅዳሴው እንደተጠናቀቀ በአውደ ምሕረት ላይ የተለያዩ መንፈሳዊ መርሐ ግብሮች ተከናውነዋል፡፡

የአኀት አብያተ ክርስቲያናት የተወከሉ አባቶች እንዲሁም አባ ዱላ ገመዳ የህዝብ ተወካዮች ም/ቤ አፈ ጉበኤን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግስት ባለሥልጣናት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም፤ ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን 6ኛው ፓትርያርክ ሆነው በመሾማቸው መልካም ምኞታቸውን በመግለጽ ለቤተ ክርስቲያኒቱና ለአገር እድገት በጋራ እንደሚሰሩ ገልጸዋል፡፡

በመጨረሻም ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም፤ ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ባስተላለፉት መልእክት “የተሰጠኝ መንፈሳዊ ኃላፊነት አጅግ ከባድ ቢሆንም ወይኩን ፈቃድከ /እንደ ፈቃድህ ይሁን ብሎ ማገልገል ብቻ ነው የሚቻለው ምክንያቱም ሁሉም ነገር የሆነው በእግዚአብሔር ፈቃድ ብቻ ስለሆነ ነው በመሆኑም ከእግዚአብሔርና ከሕዝበ ክርስቲያኑ የተሰጠኝን አደራ ለመወጣት ከብፁዓን አባቶች፣ ካህናትና ከምእመናን ጋር አብረን ተባብረን ከሠራን ሥራው የቀለለ ይሁናል ብዬ አምናለሁ” ብለዋል፡፡

ብፁእ አቡነ ማትያስ በትግራይ ክልል በቀድሞው አጋሜ አውራጃ በሰቡሀ ወረዳ በ1934 ዓ.ም የተወለዱ ሲሆን እድሜያቸው ለትምህርት እንደደረሰም ቀሲስ ወልደገሪማ ከሚባሉ አባት ፊደልና ንባብን ተምረዋል ። የኤርትራ ሊቀ ጳጳስ ከነበሩት ብፁዕ አቡነ ማርቆስ ማእርገ ድቁና እንደተቀበሉ በቀድሞው ትግራይ ክፍለ ሀገር ተንቤን አውራጃ ጮኸ በሚባል ገዳም በ1949 ዓ. ም በመግባት ለ10 ዓመት ገዳሙን ያገለገሉ ሲሆን በ1955 ዓ ም ከገዳሙ አበምኔት ማዕርገ ምንኩስናን ተቀብለዋል ። አቡነ ማትያስ 13 ዓመታት በሊቀ ረዳኢነትና ለአንድ ዓመት የገዳሙ ቄስ ገበዝ በመሆን አገልግለዋል ። ወደ አዲስ አበባ በመምጣትም በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራልና በልዩ ልዩ መንፈሳዊ አገልግሎቶች ተመድበውም አገልግለዋል፡፡ በ 1968 ብፁእ አቡነ ተክለሃይማኖት የቤተክርስትያኒቱ ፓትሪያሪክ ሆነው ሲመረጡ አቡነ ማተያስ ምክትል ልዩ ፀሓፊ ሆነው አገልግለዋል፡፡ ብፁእነታቸው ከሀገር ውስጥ ቋንቋዎች በተጨማሪ እንግሊዘኛ ፣አረቢኛ፣እብራይስጥኛና ግሪክኛ ቋንቋዎች ይናገራሉ፡፡