የአዲስ አበባ አህጉረ ስብከት ሠራተኞችና በሥራቸው የሚገኙት የገዳማትና አድባራት ሠራተኞች ከብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፖትርያርክ ጋር የትውውቅ መርሃ ግብር ተካሄደ
በመ/ር ዘሩ ብርሃኔ
የካቲት 29 ቀን 2005 ዓ.ም በጠቅላይ በተ ክህነት መሰብሰቢያ አዳራሽ በተካሄደው በዚሁ የትውውቅ መርሃ ግብር ላይ ብፁአን አባቶች ሊቃነ ጳጳሳት፤የ4ቱም አዲስ አበባ አህጉረ ስብከት ሥራ አስከያጆችና ሠራተኞች፤የገዳማትና አድባራት አስተዳዳሪዎች፤የሰበካ ጉባኤ ም/ሊቃነ መናብርት፤ፀሐፊዎች፤ቁጥጥሮች፤ሒሳብ ሹሞች፤ሰባኪያነ ወንጌሎችና የሰንበት ት/ቤት ተወካዮች በትውውቅ በፕሮግራሙ ላይ ተገኝተዋል፡፡
ስብሰባው በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፖትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት አማካኝነት በፀሎት ከተከፈተ በኋላ የዕለቱ ፕሮግራም በመጋቤ ካህናቱ አማካኝነት እንዲገለጽ ተደርጓል የዕለቱ አጀንዳዎችም፡-
1. በአዲስ አበባ አህጉረ ስብከት ሠራተኞችና በሥራቸው የሚገኙት በገዳማትና አድባራት ሠራተኞች የተዘጋውን የደስታ መግለጫ ደብዳቤ ማቅረብ
2. የ 2005ዓ.ም አቢይ ፆምን አስመልክቶ መመሪያ መስጠት
3. ስለ አክሱም ሙዝዬም ሕንፃ ግንባታ በተመለከተ እና
4. በገጠሪቱ ኢትዮጵያ ስለ ሚገኙ የተጎዱ አብያት ክርስቲያናት በተመለከተ ነበር
ወደ ዋና ፕሮግራም ከመገበቱ በፊት በ3 በፁአን አባቶች ሊቃነ ጳጳሳት ብፁዕ አቡነ ናትናኤል፤ብፁዕ አቡነ ዳንኤል የምሥራቅና የሰሜን አ/አበባ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ እና ብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤል የቅ/ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ፣ የምዕራብና የበቡብ አዲስ አበባ አህጉር ስብከት ሊቀ ጳጳስ የፋና ቤንጅ ማጂ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ አማካኘነት ስለ ነበረው የወቅቱ ሁኔታ አስመልክተው ሰፊ የሆነ ንግግር አድርገዋል፡፡
በመቀጠልም በአዲስ አበባ አህጉረ ስብከት ሠራተኞችና በሥራቸው የሚገኙት በገዳማትና አድባራት ሠራተኞች የተዘጋውን የደስታ መግለጫ ደብዳቤ በተወከሉ የገዳማትና አድባራት አስተዳዳሪዎች አማካኝነት እንዲነበብ የተደረገ ሲሆን ከዚህ በመቀጠል ቅዱስ አባታችን በ3 ዋና ዋና ጉዳዮች ላይ መመሪያ ሰጥተዋል፡-
- የ 2005 ዓ.ም አብይ ጾምን በማስመልከት ቅዱስነታቸው ባስተላለፉት መልእክት “ለእግዚአብሔር ሕግ መገዛት እስከተቻለ ድረስ ክፉውንና በጎውን ለይቶ ማወቅ ስለማያዳግት በተቻለ መጠን ከፊታችን ሰኞ መጋቢት 2 ቀን 2005 ዓ.ም. በሚጀመረው በታላቁ ጾማችን በዓብይ ጾም ወራት ጎጂ ከሆኑ ተግባራት ሁሉ መራቅ አለብን፡፡ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዓለምን የማዳን ሥራ ከመጀመሩ በፊት ዐርባ ቀንና ዐርባ ሌሊት በመጾም ድኅነተ ነፍስ እንዳስገኘልን ሁሉ እኛም ፈለጉን ተከትለን ጾም በመጾም ጥንካሬን አግኝተን ረቂቅ የሆነውን የዲያብሎስ ፈተና ማሸነፍ በሚያስችለን ቀጥተኛ መንገድ ለመጓዝ ቅድመ ዝግጅት ማድረግ ይጠበቅብናል” ብለዋል፡፡የጾም ዋና ዓላማው ለእግዚአብሔር ቃል በሙሉ ኃይል ለመታዘዝ መዘጋጀት እንደሆነ የገለጹት ቅዱስ ፓትርያርኩ በጾም ወራት ሊፈጸሙ ይገባቸዋል ያሏቸውንም ሲጠቅሱ “ተግባራችን ሁሉ በእግዚአብሔር ዘንድ የተወደደ ሊሆን የሚችለው ርኅራኄን፤ ቸርነትን፤ ምጽዋትን፤ ፍቅርን፤ ስምምነትን፤ ትሕትናን፤ መረዳዳትን፤ መተዛዘንን ገንዘብ አድርገን የጾምን እንደሆነ ነው፡፡ በጾም ወራት ልንፈጽማቸው የሚገቡን የትሩፋት ሥራዎች ብዙዎች ቢሆኑም በተለይ መሠረታዊ የሆነ የኑሮ ፍላጎት ላልተሟላላቸው ወገኖቻችን ማለትም ልብስ ለሌላቸው ልብስ በማልበስ፤ የምግብ እጥረት ላጋጠማቸው የሚቻለንን በመለገስ፤ ማረፊያ ለሌላቸው መጠለያዎችን በመቀለስ ወገኖቻችንን መርዳት ያስፈልጋል” በመሆኑም እንደ ከአሁን ከቀደም መንፈሳዊም ሆነ ማህበራዊ አገልግሎቱ ተጠናክሮ እንዲቀጥል በማለት መልእክት አስተላልፈዋል፡፡
- በአክሱም የተጀመረው ታሪካዊ የሆነው የሙዝዬም ሕንፃ ግንባታ ሥራ ተጠናክሮ እንዲቀጥል እንዲደረግ ሲሉ መመሪያ የሰጡ ሲሆን
- እንደዚሁም በገጠሪቱ ኢተዮጵያ ስለ ሚገኙ የተጎዱ አብያት ክርስቲያናት ቀደም ሲል የተጀመረው የእርዳታ ማሰባሰብ ፕሮግራም በአግባቡ ተጠናክሮ ስለ ሚቀጥልበት ሁኔታ አባታዊ መመሪያ ሰጥተዋል፡፡
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ከመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ከመደበኛ አገልጋይነት ለዚሁ ታላቅ ክብር ከበቁ ቅዱሳን ፓትርያሪኮች መካከል 4ኛ ፓትርያሪክ ናቸው
በአዲስ አበባ አህጉረ ስብከት ሠራተኞችና በሥራቸው በሚገኙት በገዳማትና አድባራት ሠራተኞች የቀረበ የደስታ መግለጫ የካቲት 29 ቀን 2005 ዓ.ም
“ ንወድሶሙ ለዕደው ክቡራን ለአበዊነ በመዋዕሊሆሙ እስከ ብዙኃ ክብረ ወሀብቦሙ እግዚአብሔር፤ “ የከበሩ አባቶቻችንን በዘመናቸው እናመሰግናቸው እግዚአብሐር ብዙ ክብርን ሰጥቷቸዋልና”
- ብፁእ ወቅዱስ አቡነ ማቲያስ ቀዳማዊ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳስ ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት
- ብፁዕ አቡነ ፊልጶስ የጠቅላይ ቤ/ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ፣ የኢሊባቦርና የጋምቤላ አህጉረ ስብከተ ሊቀ ጳጳስ
- ብፁዕ አቡነ ዳንኤል የምሥራቅና የሰሜን አ/አበባ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ
- ብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤል የቅ/ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ፣ የምዕራብና የበቡብ አዲስ አበባ አህጉር ስብከት ሊቀ ጳጳስ የፋና ቤንጅ ማጂ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ
- ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳስት
- የመንበረ ፖትርያርክ ጠቅላይ ቤ/ክህነት ምክትል ሥራ አስኪያጆች እና የየመምሪያው ኃላፊዎች
- የአዲስ አበባ አህጉረ ስብከት ሥራ አስኪያጆች እና የየክፍሉ ኃላፊዎች
- የጉባኤው ታዳሚዎች በሙሉ
በቅድሚያ ከሁሉ አስቀደሙን የበጐ ነገር ሁሉ መገኛ የሆነው አምላካችን እግዚአብሔር በቸርነቱ በጐ ነገርን ለማድረግ ሲፈቅድ ለዚሁ ተግባር የሚበቃ በጐ ሰው አስነስቶ ለቸርነቱ መገለጫ ያደርገዋል፡፡ በዚህም አምላካዊ ፈቃድ መሠረት ኦርቶዶክሳዊት፣ ሐዋርያዊተና ዓለምአቀፋዊት የሆነችውን የኢትዮጵያን ቤተ ክርስቲያን፣ የካህናቶቿና የሕዝቦቿ እረኛና መሪ ሆነው ያገለግሉ ዘንድ በመንፈስ ቅዱስ ተጠርተውና ተመርጠው ለዚህ ታላቅ ክብር በቅተዋለና ከማንኛውም ነገር ሁሉ በጽኑዕ ክንዱ ጠብቆ ከዚህ ያደረስዎን እግዚአብሔርን እናመሰግናለን፡፡
ቅዱስ አባታችን እንደሚታወቀው ሁሉ ሀገራችን ኢትዮጵያ ባለፉት ጥቂት ወራቶች እጅግ አሳዛኝ በሚባል የታሪክ ክስተት በሳል መሪዎቿን በሞት ያጣችበት መሪር ጊዜ እንደነበር የሚታወስ ነው፡፡ ማንም ባላሰበውና ባልገመተው ወቅት እኒህን ሁለት የልማት፣ የብልጽግና እና የሰላም ፈርጦች ሀገራችን ብቻ ሳትሆን ምድራችን ብታጣም ሀዘንና ምሬቷን በውስጧ ይዛ መሪዎቿ አኑረውላት ያለፉትን የልማት ትልም በመከተል ቤተ ክርስቲያናችንም ሆነች ሀገራችን ከታቀደላቸው የእድገት ሰገነት ላይ ይደርሱ ዘንድ በመንግስት በኩል በበሳል መሪዎቿ የተፈፀመው የሥልጣን ሽግግር ዲሞክራሲያዊና ሰላማዊ ሆኖ በመጠናቅቁ መላውን የዓለም ህብረተሰብ ያስደነቀ ሆኖ አልፏል፡፡
በሃገራችን መንግስት እንደተከናወነው የሥልጥን ሽግግር ሁሉ ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችንም የደረሰባትን ሀዘን በውስጧ አኑራ በቅዱስ ሲኖዶስ አባላት በብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት በሳል አመለካከት እንዲሁም ያለሰለሰ ጥረትና የፀሎት ውጤት አንድነቷ ሳይናጋና መሠረቷ ሳይነዋወጥ የተፈፀመው የስድስተኛ ፖትርያርክ ምርጫ እውነትም ቤተ ክርስቲያን የሰላም አውድማና መሪዎቿ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳትም የሰላምና የወንጌል ገበሬዎች መሆናቸውን ፈንትው አድርጎ ያሳየና አማኞቿንም ያኮራ ተግባር ሆኗል፡፡
ቅዱስ አባታችን የቤተ ክርስቲያናችን 5ኛ ፖትርያርክ በመሆን ለሃያ ዓመታት ለዕድገትዋ ደፋ ቀና በማለት ሲጥሩላት የነበሩት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ፖትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተ/ሃይማኖት የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ምክር ቤት ፕሬዘዳንት የአለም ሃይማኖቶች ለሰላም የብብር ፕሬዘዳንት እና የሰላም አምባሳደር ይህን ቅዱስነትዎ አሁን የተረከቡትን ታላቅ መንበር ከተረከቡ ቀን አንስቶ በሚያስጨንቃቸው የቤተክርስቲያን ጉዳይ ምክንያት ለዓይን ሽፋሽፍቶቻቸው እንቅልፍን ለወገባቸውም እረፍትን ሳይሹ በጤናቸውም ሆነ በሕመማቸው ለቤተ ክርስቲያንና ለአማኞቿ ኩራት እንደሠሩ እና ቤተ ክርስቲያናችንም ከዓለም አደባባይ የላቀ ሥፍራ አግኝታ ተከብራና ታፍራ እንድትኖር ያበረከቱት አስተዋጽኦ እንዲሁ በቃል የሚነገር ታሪክ ብቻ ሳይሆን የሥራቸው ፍሬዎች በዓይን የሚታዩና በእጅ የሚዳሰሱ የተግባር ማሳያዎች በመሆናቸው እየተመለከቱ ዕፁብ ከማለት ባለፈ ሌላ መስካሪና ዘካሪ አያሻቸውም፡፡ ቅዱስነታቸው ሥራቸውን ጨርሰው ያቆሙ ሳይሆን ከዕለት ወደ ዕለት ቤተ ክርስቲያችን ካለችበት የእድገት ደረጃ ወደ ላቀ የዕድገት ጫፍ ትደርስ ዘንድ በርካታ ትልሞችን ሰንቀው እየተጉ የነበረ ቢሆንም እግዚአብሔር አምላክ ከድካመ ሥጋ ያርፉባት ዘንድ ነሐሴ 10 ቀን 2004 ዓ/ም ቆርጦ ኖሮ እርሱ ባወቀ ከእኛ በእርፍተ ሥጋ ወስዶ ወደ እርሱ እረፍተ ነፋስ አግብቷቸዋል፡፡
ታዲያ በዚህ ጊዜ እጅግ የበዛ የቤተ ክርስቲያን ሀዘን በካህናቶቿና ምዕመናኖቿ ላይ የደረሰ ቢሆንም ቅዱስ ሲኖዶስ መንፈስ ቅዱስን አጋዥ አድርጐ አስቸኳይ ውይይት በማድረግ የቤተ ክርስቲያናችን ቀጣዩ ፖትርያርክ እስኪመረጥ ድርስ ታላቁን መንበር ይጠብቁ ዘንድ አንጋፋውን አባት ብፁዕ አቡነ ናትናኤልን ዐቃቤ መንበረ ፖትርያርክ በማድረግ ከሰየመ በኋላ በብፀዕነታቸውም ሥር ሰባት የሥራ አስፈጻሚ ሊቃነ ጳጳሳትን ሰይሞ ቤትክርስቲያን የቀድሞ ፖትርየርኳ ህልመና ራዕይ ለአፍታም ሳይደናቀፍ በነበረበት ፍጥነት እንዲቀጥል እንዲሁም ሰላሟ እንዳይደፈረስና አገልግሎቷም እንዲስፋፋ በቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባዔ የደረገው አኩሪ ተግባር የቤተ ክርስቲያናችን ራስ ከሆነው ከኢየሱስ ክርስቶስ በታች ይህች ሐዋርያዊትና ዓለም አቀፋዊት ቤተክረስቲያን በርካታ የሚተጉላትና የሚሳሱላት የምሁራን አባቶች ምንጭ መሆኗን አመላክቷል፡፡
የቅዱስ ሲኖዶስ ዓባላትም ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት ከብፁዕ ዐቃቤ መንበረ ፖትርየርኩ ጋር በመምከር ለቤተ ክርስቲያን ይበጃል ያሉትን በርካታ ሥራዎችን ከመፈፀማቸውም ባሻገር ቀጣዩ ፖትርያርክ የሚመረጥበትን ሂደት በአትኩሮት መርምረው ብቁ የሆኑ እና በዕውቀትም ሆነ በአመለካከት የበሰሉ የአስመራጭ ኮሚቴዎችን በማቋቋምና የአስመራጭ ኮሚቴውንም የሥራ እንቅስቃሴ በቅርበት በመከታተል የበኩላቸውን ኃላፊነት የተወጡ ሲሆን የአስመራጭ ኮሚቴውም በመንፈስ ቅዱስ እየታገዘ በመሉ አቅሙና በተሟላ ነፃነት ሰፊ ጊዜ በመውሰድ ሥራውን ሲያከናውን ሰንብቶ አምስት ሊቃነ ጳጳሳትን ለእጩነት በማቅረብ ባለፈው የካቲት 21 ቀን 2005 ዓ/.ም ታሪካዊ፤ ነፃና ፍትሐዊ የምርጫ ሂደት ስድስተኛው የቤተ ክረሰቲያናችን ፖትርያርክ ማን መሆኑን ፈንትው አድረጐ አሳየቶንና ቅዱስነትዎን አስረክቦን ኮሚቴው የተጠራበትንና የተሰየመበትን ዓላማ በሚገባ ተወጥቷል፡፡
ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለሐዋርያት ሌላ አፅናኝ ጰራቅሊጦስን እስክልክላችሁ ድረስ ተግታችሁ ጠብቁ ብሎ ከተለያቸው በኋላ አዝነውና ተክዘው ለነበሩት ደቀ መዛሙርት አፅናኝ መንፈስ ቅዱስን እንደላከላቸው ሁሉ ብፁዕ ወቅድሪስ አቡነ ጳውሉስም በእረፍተ ነፍስ ሆነው ከሚገኙበት የጌታ እቅፍ በመንፈስ ሆነው እርስዎን ቅዱስነትዎን የላኩልንን ያህል ተስምቶናልና እኛ የአዲስ አበባ ገዳማትና አድባራት አስተዳዳሪዎች በቅዱስነትዎ ሢመተ ኘትርክና መደሰታችንንና መፅናናታችንን ስንገልፅልዎ ከውስጥ በመነጨ ልባዊ ሀሴት ነው፡፡
ቅዱስ አባታችን ከተፈቀደልን ውሱን ጊዜ አንፃር ብዙ ለማለተ እየፈለግን ብንቆጠብም በቅዱስነትዎ ፊት ሳናመሰግን የማናልፋቸውን አካላት በመጥቀስ (በድጋሚ) እንድናመሰግን ይፈቅዱልናል የሚል የፀና እምነት አለን፡፡
ይኸውም አንደኛ በታላቁ አባት በብፁዕ አቡነ ናትናኤል እየተመራ በርካታ ሥራዎችን በዚህ አጭር ጊዜ ላከናወነው ቅዱስ ሲኖዶስ እና በቅዱስ ሲኖዶስ ለተቋቋመው ለሰባቱ ሊቃነ ጳጳሳት የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ እጅግ የላቀ ክብርና ምስጋና ለማቅረብ እንወዳለን፡፡ ሁለተኛውም በቅዱስ ሲኖዶስ ተቋሙሞ ቅዱስነትዎን ያስገኘልንን የአስመራጭ ኮሚቴም ለከፈሉት ታላቅ መስዋዕትነት የምናመሰግን ሲሆን በሦስተኛ ደረጃ ደግሞ መላው የቤተ ክርስቲያናችን ካህናትና ምዕመናን ፈጣሪያቸውን በምሕላ፣ በጾምና በፀሎት የጠየቁበትን ረዥም የፀሎት ጊዜያት ባሰብን ቁጥር በዚህ የምርጫ ሂደት የአንበሳውን ድርሻ የሚወስዱት እነርሱ ናቸውና ለእነርሱ ያለንን ክበረና አድናቆት ልናቀርብ እንወዳለን፡፡
በመጨረሻም ብርሃኑ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ ወደ ቆሮንቶስ በላከው 2ኛ መልዕክት ም.13 ቁ11 ላይ “ተፈሥሑ እንከሰ አኃዊነ አጥብዑ ወተዓገሡ ወተሰናአው ወአምላክ ሰላም ወፍቅር የሃሉ ምስሌክሙ፤ በቀረውስ ወንድሞች ሆይ በአንድ ልብ ሁኑ በሰላም ኑሩ የፍቅርና የሰላም አምላክ ከእናንተ ጋር ይሆናል” ብሎ እንደተናገረው እኛም የአዲስ አበባ ገዳማትና አድባራት አስተዳዳሪዎች ቅዱስነትዎ ያልዎትን ዓለም አቀፍ እና ጥልቅ እውቀት በጠቀም ቤተክረስቲያን ዛሬ ከምትገኝበት ታላቅ ደረጃ ከፍ ለማድረግ በሚተጉበት ማንኛውም ሥራና በየአህጉሩ በመዘዋወር እንደየሰው ቋንቋ (ልሳን) በመናገር ለሚከውኑት ታላቅ የቤተ ክረስቲያን ሥራ ከእግርዎ ሥር በመሆን ልንታዘዝዎትና ልናገለግልዎት በቁርጠኝነት መቆማችን ስንገልፅልዎ እጅግ ጥልቅ በሆነ ደስታና ስሜት ሲሆን ልዑል እግዚአብሔርን አጋዥ አድርገው የላቀ ሥራም እንደሚፈፅሙ እምነታችን የፀና ነው፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
የቅዳስነትዎ ቡራኬ ይድረሰን የአዲስ አበባ ገዳማትና አድባራት አስተዳዳሪዎች
በሌላ ዜና የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን በሀገሪቱ የሰላም፣የልማትና የዕድገት ጉዞ እያደረገች ያለችውን እንቅስቃሴ አጠናክራ እንደምትቀጥል ብፁእ ወቅዱስ አቡነ ማቲያስ ቀዳማዊ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳስ ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ገልፀዋል፡፡
ቅዱስነታቸው ከኢትዮጵያ ፌድራላዊ ሪፐብሊክ መንግስት ፕሬዚዳንት ከክቡር አቶ ግርማ ወ/ጊዮርጊስና ከኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ከአቶ ኃይለማርያም ጋር ባደረጉት ውውይት ቤተክርስትያኗ በሀገሪቱ የልማት ጉዞ በመሳተፍ ለሰላምና ለዕድገት የምታበረክተውን አስተዋፅኦ አጠናክራ ትቀጥላለች ብለዋል፡፡
ምዕመናኑም ከመላው የኢትዮጵያ ህዝብ ጋር በመሆንና በመከባበር በሀገሪቱ የልማት ተግባራት ላይ ተሳትፎውን እንዲቀጥል ጠይቀዋል፡፡
የኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ በበኩላቸው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን በልማታዊ እንቅስቃሴዎች ላይ ያላትን አስተዋፅኦ እንደምትቀጥል እምነታቸው መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ወጣቱን በልማት ስራው በማሳተፍ እንዲሁም ከሀገር ወጥተው ወደ ዓረብ ሀገራት የሚሰደዱ ዜጎችን በማስተማር በኩል ትኩረት መሰጠት አለበትም ብለዋል፡፡ መንግስት ከቤተክርስትያኗ ጎን መሆኑንም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለፓትሪያሪኩ ገልፀውላቸዋል፡፡