በሃይማኖት ሽፋን ቅ/ኤልያስ መጥቷል ብለው በኤልያስ ስም ሲነግዱ የነበሩ ግለሰቦች ንፁሀን ዜጎችን ሲያስደበድቡና ሁከት ሲፈጥሩ እጅ ከፍንጅ ተይዘው ታሰሩ

ቀደም ሲል በዚህ ርዕሰ ጉዳይ ላይ በተለያዩ የቤተክርስቲያኒቷ አገልጋዮች የተፃፉትን ጽሑፎች በአህጉረ ስብከታችን ዌብ ሳይት ስናስነብብ መቆየታችን አይዘነጋም፡፡

ምንም እንኳን ጉዳዩ ዘግይቶ በተለያዩ ሚዲያዎች መሰራጨት የጀመረ ቢሆንም ቀደም ሲል ከሁለት ዓመታት በፊት በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ጀርባ በተለምዶ ቆሎ ሰፈር ተብሎ በሚጠራው መንደር ቤተክርስቲያኑንና ህብረተሰቡን ሲረብሹ የቆዩ ሲሆን የካቴድራሉ ጽ/ቤት ጉዳዩን እየባሰ ሲሄድ በመስከረም ወር 2ዐዐ5 ዓ.ም ጉዳዩ በፍርድ ቤት እንዲታይ ክስ መስርቶ በፍ/ቤት ትእዛዝ ግለሰቦቹ ከተከራዩት ቤት እንዲወጡና አከራዮችም ተከራዮቹ በአስቸኳይ እንዲያስወጡ ውሳኔ ተወስኖ ነበር፡፡

ይሁንና ግን በአፈፃፀም ሂደት የሚመለከታቸው አካላት እስከ አሁን ድረስ እልባት ባለማግኘቱ ካቴድራሉንና በካቴድራሉ ጀርባ ያሉ ነዋሪዎች ከመጠን በላይ ሲቸገሩ ቆይተዋል፡፡ ግለሰቦቹ መኖሪያ ቤታቸው የት እንደሆነ በእርግጠኛነት ማወቅ ባይቻልም ሁሉም የሚገናኙት ከሥላሴ ጀርባ በተከራዩት ቤት ነው የመገናኛ ሰዓታቸውም ከቀኑ በ11 ሰዓት እስከ ሌሊቱ 6፡3ዐ ነው፡፡

የተከራዩት ቤት መጠኗ አነስተኛ ብትሆንም እስከ 4ዐዐ የሚደርሱ ሰዎች ኃይማኖትን ይሁን ፖለቲካ፣ እብደት ይሁን ስካር ባልታወቀ ሁኔታ ከበሮ እየመቱ እጣን እያጨሱና መጠጥ እየጠጡ እንደሚያመሹ የሰፈሩ ሰዎች በግልጽ ከመናገራቸውም በላይ ከቅዳሜ በስተቀር ሁልጊዜ እዛው ቦታ ላይ የሚሰበሰብ ሲሆን ከቤቱ ጎን ያሉ ነዋሪዎች ማለፍ አትችሉም፣ ጫማችሁን አውልቁ ወዘተ እያሉ በሕገ መንግስቱ የተሰጣቸውን በሰላም የመኖር መብት ሲያሳጧቸው የቆዩ ከመሆናቸውም በላይ ይባስ ብሎ በ15/ዐ8/2ዐዐ5 ዓ.ም ከምሽቱ 2፡3ዐ ላይ እንደ ሰፈሩ ሰዎች አባባል ቁጥራቸው ከ5ዐ – 1ዐዐ የሚሆኑ በሰፈሩ ሰዎች ላይ ለማድረስ ጀምረውት የነበረውን የድብደባ ጥቃት በአካባቢ ባሉት የፖሊስና የመከላከያ ኃይል አማካይነት ጉዳቱ ሊቀንስ ቢችልም በዚሁ ዕለት ጉዳዩን በዋናነት ሲመሩ የተገኙት (የነበሩት)እጅ ከፍንጅ ተይዘው 4 ኪሎ ፖሊስ ጣቢያ ታስረው ይገኛሉ፡፡ ቦታው ድረስ በአካል ሄደን ለማረጋገጥ እንደቻልነው 3 ሰዎች ተመትተው እቤታቸው ተኝተው አይተናል፡፡

የሚመለከታቸው የመንግስት አካላትም ቦታው ድረስ በመሄድ በጉዳዩ ላይ ከፍተኛ የሆነ ክትትል እያደረጉ ሲሆን የካቴድራሉ ጽ/ቤትም ከአሁን ቀደም ከቤቱ እንዲወጡ ፍ/ቤቱ የወሰነበትን ውሳኔ አያይዞ ለፖሊስ ጣቢያው ልኳል፡፡ የአካባቢው ማኀበረሰብም ፖሊስ ጣቢያው ድረስ በመሄድ ለዓመታት በዚሁ ችግር ሲኖሩ መቆየታቸውንና አሁን የደረሰባቸውን ችግር ገልፀው ክስ መስርተውባቸዋል፡፡

በመሆኑም የሚመለከታቸው የቤተክርስቲያኒቱ ባለድርሻ አካላት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመነጋገር የቤተክርስቲኒቷን ስም በማጥፋታቸው በህግ መጠየቅ ይገባቸዋል እንላለን፡፡