የካቴድረሉ ዋና አስተዳዳሪ ሆነው የተሾሙት ክቡር ሊቀ ስልጣናት አባ ገ/ሥላሴ በላይ ደማቅ አቀባበል ተደረገላቸው

0022

በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት መልካም ፈቃድ ከነሐሴ 1 ቀን 2ዐዐ6 ዓ.ም. ጀምሮ  የመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ዋና አስተዳዳሪ ሆነው የተሾሙት ክቡር ሊቀ ስልጣናት አባ ገ/ሥላሴ በላይ ሲሆኑ ሐሙስ ነሐሴ 1 ቀን 2ዐዐ6 ዓ.ም. የመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ሰበካ ጉባዔ አባላት፣መላው ማህበረ ካህናት፣ መዘምራን፣ የሰንበት ት/ቤት ወጣቶችና የአጥቢየው ምእመናን  ደማቅ አቀባበል አድርጐላቸዋል፡፡

ክቡር ሊቀ ስልጣናት አባ ገ/ሥላሴ በላይ በካቴድራሉ ሲሾሙ አሁን ለ2ኛ ጊዜ ሲሆን ቀደም ሲል ከ2004 እስከ 2005 ዓ.ም ካቴድረሉን ባስተዳደሩበት ጊዜ ብዙ ሥራ እና መልካም አስተዳደር ከማስፈናቸውም በላይ ለካቴድራሉ መንፈሳዊ እና ለሁለንተናዊ አገለግሎት የሚሆን ብዙ ገንዘብና ጥሬ እቃ ካሰባሰቡ በኋላ በደብረ ገነት መካኒሳ ቅዱስ ሚካኤል ካቴድራል ማህበረ ካህናትና ማህበረ ምእመናን ጥያቄ አማካኝነት ለ1 ዓመት ያህል ወደ መካኒሳ ቅዱስ ሚካኤል ካቴድራል ሄደው ዘርፈ ብዙ ልማት ካለሙ  በኋላ ልክ በ1 አመታቸው በካቴድራሉ ማህበረ ካህናት እና ልይ ልዩ ሠራተኞች ጥያቄና በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት መልካም ለ2ኛ ጊዜ የካቴድራሉ ዋና አስተዳዳሪ ሆነው ተሹመው መጥተዋል፡፡ክቡር ሊቀ ስልጣናት አባ ገ/ሥላሴ በላይ ወደ ካቴድራሉ በድጋሚ እንዲመጡ የተመረጡበት መክንያት መንፈሳዊና የልማት አባት በመሆናቸው ሲሆን ከአሁን በፊት የሠሯቸው ሥራዎች ትላልቅ ማረጋገጫዎች ናቸው፡፡

በክብረ በዓሉ ላይ ብፁዕ አቡነ አረጋዊ የካቴድራሉ የበላይ ጠባቂና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል ፤የአዲስ አበባ ገዳማትና አድባራት አስተዳዳሪዎች  ፤የደብረ ገነት መካኒሳ ቅዱስ ሚካኤል ካቴድራል ካህናት፤የካቴድራሉ ማህበረ ካህናትና ልይ ልዩ ሠራተኞች በክብረ በዓሉ ላይ ተገኝተዋል፡፡ በዓሉን አስመልክቶም የተለያዩ ቅኔዎችና ዝማሬዎች በካቴድራሉ ሊቃውነት  አማካኝነት ቀርቧል፡፡
በስተመጨረሻ የተደረገላቸውን አቀባበል በማስመልከት ንግግር ያደረጉት ክቡር ሊቀስልጣናት አባ ገ/ሥላሴ በላይ ሲሆኑ የተደረገላቸውን አቀባበል ካመሰገኑ በኋላ ካቴድራሉ ዓለም አቀፋዊ እንደመሆኑ መጠን በልማትና በመልካም አስተዳደር ወደተሻለ ደረጃ ላይ እንዲደርስ የሁሉም ሠራተኛ እና ምእመናን አስተዋጽኦ ወሳኝ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ ከዚሁ ጋር አያይዘውም ዘመኑ በሚፈቅደው አስተሳሰብና አሰራር ሰዎች መሥራት ይኖርብናል ብለዋል፡፡ ሥርዓተ ቅዳሴው በክቡር ሊቀ ስልጣናት አባ ገ/ሥላሴ በላይ መሪነት ከተከናወነ በኋላ የበዓሉ ፍፃሜ ሆኗል፡፡
መልካም የሥራ ዘመን እንዲሆንላቸውም ሁሉም የካቴድራሉ ሠራተኞች ተመኝተውላቸዋል፡፡

{flike}{plusone}