ትምህርተ ሃይማኖት ዘቅድስት ሥላሴ
ለክርስትና ሃይማኖት መሠረቱ ማእከሉና መደምደሚያው ምሥጢረ ሥላሴ እንደሆነ ይታወቃል ምክንያቱም ከቅድስት ሥላሴ አንዱ አካል እግዚአብሔር ወልድ ከቅድስት ድንግል ማርያም ከሥጋዋ ሥጋን ከነፍሷም ነፍስን ነሥቶ ሰው ከሆነ በኋላ የሥላሴ አንድነትና ሦስትነት የታወቀና የተረዳ ሆኖ በመገኘቱ ነው፡፡ ይህም በዚህ በልደት እና በጥምቀት ሰሞን በቂ ትምህርት ሊሰጥበት የሚገባ ነው፡፡
እግዚአብሔር ወልድ ከቅድስት ድንግል ማርያም ሰው ሆኖ በሥጋ ከመወለዱ በፊት የቅድስት ሥላሴ አንድነታውና ሦስትነታቸው በግልጥ የታወቀና የተረዳ ባለመሆኑ ሰዎች ስለ ሥላሴ አንድነትና ሦስትነት የነበራቸው እውቀት በጣም ውሱን በመሆኑ ምክንያት በብሉይ ኪዳን ውስጥ ስለአንድነታቸውና ሦስትነታቸው የተነገሩ ጥቅሶችን በአግባቡ ሊተረጉሟቸውና ምሥጢራቸውንም ሊረዱ እንዳልቻሉ መገንዘብ ይቻላል ከዘመን ሥጋዌ በኋላ ግን ምሥጢሩ ለሁሉም ግልጥ ሆኖ ታውቋል፡፡
በመሠረቱ ስለ እግዚአብሔር አንድነትና ሦስትነት የሚሰጠው ትምህርት ረቂቅ ከመሆኑ የተነሣ የፍጡር አእምሮ በቀላሉ ሊረዳው የማይችል ቢሆንም ራሱ እግዚአብሔር በቃሉ የገለጠው እውነተኛ ምሥጢር በቅዱሳት መጻሕፍት ውስጥ ተጽፎ ስለሚገኝ በዚሁ መሠረት ክርስቲያኖች እውነተኛውን ምሥጢር በመምህራን አማካይነት እየተረዱ እምነታቸውን አጽንተው መኖር ችለዋል፣ይህም ታላቅ ምሥጢር ‹‹ ምሥጢረ ሥላሴ ›› በመባል የሚታወቅ ሲሆን በክርስትና ሃይማኖት ተከታዮች ዘንድ ጸንቶ የሚኖር ነው፡፡ ምክንያቱም ከክርስትና ሃይማኖት ልዩነት ያላቸው ሃይማኖቶች ሁሉ እግዚአብሔር አንድ ገጽ አንድ አካል ብቻ እንደሆነ ሲያስተምሩ የክርስትና ሃይማትኖት ግን እግዚአብሔር በአንድነትና በሦስትነት የነበረ፣ያለና፣ የሚኖር መሆኑን የሚያስተምር በመሆኑ ነው፡፡
የአሕዛብ ሃይማኖትም ብዙ አማልእክት እንዳሉ ሲያስተምር የክርስትና ሃይማኖት ግን እግዚአብሔር በሦስትነት ቢገለጥም አንድ አምላክ እንጂ ሦስት አማልእክት አለመሆኑን የሚያስተምርና ይህንኑ የሚያረጋግጥ ስለሆነ ነው፡፡ ከዚህም ጋር ሌሎች የሃይማኖት ተከታዮች እግዚአብሔር አካላዊ ያልሆነ ዝርው ኃይል እንደሆነ ሲያስተምሩ የክርስትና ሃይማኖት ተከታታዮች ግን እግዚአብሔር ረቂቅ (መንፈስ) ቢሆንም በፈቀደ ጊዜ በፈቀደው መንገድ ለወደደው ፍጥረት መገለጥ የሚችል አካላዊ መንፈስ እንደሆነ ያምናሉ ያስተምራሉም፡፡
እግዚአብሔር በባሕርይ፣በመለኮት፣በአገዛዝ፣በሥልጣን በመፍጠርና በመሳሰለው ሁሉ አንድ እንደሆነ በቅዱሳት መጻሕፍት የተመሰከረና የታወቀ እውነት ነው፡፡ ይህንንም እውነት በሚከተሉት ጥቅሶች መረዳት ይቻላል፡፡
‹‹እስራኤል ሆይ ስማ አምላካችን እግዚአብሔር አንድ እግዚአብሔር ነው አንተም አምላክህን በፍፁም ልብህ፣ በፍጹም ነፍስህ፣ በፍፁም ኃይልህ ውደድ (ዘዳ 6፣4)፡፡
‹‹ሁሉን በሁሉ የሚያደርግ እግዚአብሔር ግን አንድ ነው፡፡ (1ኛ ቆሮ 12፣6)፡፡ በእነዚህንና እነዚህን በመሳሰሉ ጥቅሶች ስለ እግዚአብሔር አንድነት ማወቅና መረዳት ይቻላል፡፡
ከላይ በተገለጠውና በተጠቀሰው መሠረት እግዚአብሔር አንድ ነው ቢባልም በስም፣በአካል፣በግብር ሦስት እንደሆነ በቅዱሳት መጻሕፍት የተመሰከረና በክርስትና ሃይማኖት ተከታዮች ዘንድ የታመነ ነው፡፡ ይህም የስም ሦስትነት አብ፣ወልድ፣መንፈስ ቅዱስ በመባል ይታወቃል፡፡ ስለሆነም አብ አብ እንጂ ወልድ ወይም መንፈስ ቅዱስ ተብሎ አይጠራም ወልድም ወልድ እንጂ አብ ወይም መንፈስ ቅዱስ አይባልም መንፈስ ቅዱስም አብ ወይም ወልድ ተብሎ አይጠራም ሦስቱም ግን እግዚአብሔር በሚለው ስም ይጠሩበታል (ዮሐ 1÷1-3፣የሐዋ ሥራ 20÷28)፡፡
አብ፣ወልድ፣መንፈስቅዱስ ለየራሳቸው ፍጹም አካል ፍጹም መልክ አላቸው ግብራቸውም በቅዱሳት መጻሕፍት መሠረትነት ሊቃውንተ ቤተክርስቲያን እንደሚያስረዱን፡- የአብ ግብሩ መውለድና ማሥረጽ ነው፡፡ የወልድም ግብሩ መወለድ ነው፣የመንፈስ ቅዱስም ግብሩ መሥረጽ ነው፡፡
ሦስትነትን በተመለከተም በሚከተሉትና በሌሎችም ጥቅሶች መረዳት ይቻላል ለምሳሌ እግዚአብሔር ራሱ ሲናገር እንዲህ ይላል፡፡
‹‹ ሰውን በመልካችን፣በምሳሌያችን እንፍጠር›› (ዘፍ 1÷26)
‹‹ ሰው ብቻውን ይኖር ዘንድ መልካም አይደለምና ረዳት እንፍጠርለት››(ዘፍ 2÷18)
‹‹ አዳም ከእኛ እንደ አንዱ ሆነ›› (ዘፍ 3÷22)፡፡
‹‹ ኑ እንውረድ አንዱ የአንዱን ነገር እንዳይሰማው ቋንቋቸውን በዚያ እንደባልቀው›› (ዘፍ11÷17)፡፡
‹‹የጌታም ድምጽ ማንን እልካለሁ ማንስ ይሄድልናል ሲል ሰማሁ፣እኔም እነሆኝ፣እኔን ላከኝ አልሁ››(ኢሳ 6÷8-9)፡፡ እንዚህ ጥቅሶች የእግዚአብሔርን የአካል
ሦስትነት ያመለክታሉ፡፡ ቢሆንም ከአንድ በላይ የሆነ ቁጥርን ያመለክታሉ እንጂ በሦስትነት የተወሰነ ቁጥርን አያሳዩም የሚል አስተሳሰብ ሊኖር ይችላል ይሁን እንጂ በሁለት ያልሆኑ ከሦስትም በላይ የማይሆኑ በሦስት ብቻ የተወሰኑ ጥቅሶች ከቅዱሳት መጻሕፍት ውስጥ ስለሚገኙ በእነሱ ማስረጃነት ስለቅድስት ሥላሴ ሦስትነትና አንድነት በሚገባ ልንረዳ እንችላለን፡፡ ለምሳሌም ያህል የሚከተሉት ጥቅሶች ሦስት፣ሦስት ጊዜ ተደጋግመው መነገራቸው በቂ ማስረጃዎች ናቸው
‹‹ እኔ እግዚአብሔር የአብርሃም አምላክ፣የይስሐቅ አምላክ፣የያእቆብ አምላክ ነኝ (ዘዳ 3÷6)፡፡ በትንቢተ ኢሳይያስም እንደተገለጠው መላእክት፡-
‹‹ቅዱስ፣ቅዱስ፣ቅዱስ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ምድር ሁሉ ከክብሩ ተሞልታለች—›› በማለት ሲያመሰግኑ ተሰምተዋል (ኢሳ 6÷3) በሌላም በኩል አብርሃም በድንኳኑ ደጃፍ ተቀምጦ ሳለ እግዚአብሔር በመምሬ ዛፍ በተገለጠለት ጊዜ፡- ‹‹ዓይኑንም አነሣና እነሆ ሦስት ሰዎች በፊቱ ቆመው አየ፣ ባያቸውም ጊዜ ሊቀበላቸው ከድንኳኑ ተነሥቶ ሮጠ፣ወደ ምድርም ሰገደ›› የሚለው ዓረፍተ ነገር ሦስትነቱን፣‹‹አቤቱ በፊትህ ሞገስ አግኝቼ እንደሆነ ባሪያህን አትለፈኝ ብዬ እለምንሃለሁ››የሚለው ደግሞ አንድነቱን፣‹‹ጥቂት ውኃ ይምጣላችሁ›› እግራችሁንም ታጠቡ ከዚህችም ዛፍ በታች እረፉ፣ቁራሽ እንጀራ ላምጣላችሁ ልባችሁን ደግፉ፣ ከዚያም በኋላ ትሄዳላችሁ›› የሚለው አረፍተ ነገርም እንደገና ሦስትነቱን የሚገልጥ ነው፡፡ (ዘፍ 18÷1-5)፡፡
በብሉይ ኪዳን መጻሕፍት ስለ እግዚአብሔር የስም፣የአካል እና፣የግብር ሦስትነት የተነገረው ሁሉ በሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት ግልጥና ትክክል የሆነ ትርጉም አግኝቶአል፡፡ ለምሳሌ ከሦስቱ አካላት አንዱ አካል እግዚአብሔር ወልድ ሰው ሆኖ ከድንግል ማርያም በድንግልና ከተወለደ በኋላ በ30 ዓመቱ በአጥማቂው ዮሐንስ እጅ በማየ ዮርዳኖስ በተጠመቀ ጊዜ እግዚአብሔር አብ በደመና ውስጥ የምወደው ልጄ ይህ ነው›› ሲል ተሰምቷል፡፡ እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስም በአምሳለ ርግብ በራሱ ላይ ሲያርፍ ታይቷል (ማቴ3÷15-17)፡፡
ከትንሣኤውም በኋላ‹‹እንግዲህ ሂዱና አህዛብን ሁሉ በአብ፣በወልድና፣በመንፈስ ቅዱስ ስም አጥምቋቸው››(ማቴ 28÷19)፡፡በማለት ለደቀ መዛሙርቱ የሰጠው ትእዛዝም ትልቅ ማረጃ ነው፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም ‹‹የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ፣ የእግዚአብሔር ፍቅር የመንፈስ ቅዱስም አንድነት ከሁላችን ጋር ይሁን››
(2ኛ ቆሮ 13÷14)፡፡ ሲል ያስተማረው ይህንኑ መሠረት በማድረግ ስለሆነ በእነዚህና እነዚህን በመሳሰሉ ጥቅሶች እየተረዳን ስለ እግዚአብሔር አንድነትና ሦሰትነት ያለንን ዕውቀት የበለጠ በማዳበር እምነታችንን ልናፀና ይገባል፡፡
አባቶቻችን ሊቃውንትም የብሉያትንና የሐዲስ ኪዳናትን ትምህርት መሠረት በማድረግ የእግዚአብሔር አንድነትና ሦስትነት በትምህርት ብቻ ሳይወሰን በዘወትር ጸሎትም ውስጥ እነዲገባና ሰው ሁሉ በዚሁ እምነት ውስጥ ሆኖ እንዲጸልይ አድርገዋል፡፡ በዚህም መሠረት የዘወትር ጸሎታችን መጀመሪያው፡- ‹‹ በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ ›› የሚል ሲሆን ይህም ከላይ የተገለጠውን በማቴዎስ ወንጌል ምዕ 28÷19-20 ያለውን መሠረት ያደረገ ነው፡፡ ቀጥሎም ሦስት መቶ አሥራ ስምንቱ ሊቃውንተ ቤተክርስቲያን በወሰኑት ጸሎተ ሃይማኖት‹‹ሁሉን በያዘ ሰማይና ምድርን፣የሚታየውንና የማይታየውን በፈጠረ በአንድ አምላክ በእግዚአብሔር አብ እናምናለን፣ዓለም ሳይፈጠር ከእርሱ ጋር በነበረ የአብ አንድ ልጅ በሚሆን በኢየሱስ ክርስቶስም እናምናለን ጌታ ማሕያዊ በሚሆን ከአብ በሠረጸ በመንፈስ ቅዱስ እናምናለን›› የሚሉት አነቀፆች በጸሎታችን ውስጥ እንዲገቡ አድርገዋል ፡፡ እነዚህም አንቀፆች አንድነትና ሦስትነትን መግለጥ ብቻ ሳይሆን የአብን፣የወልድን፣የመንፈስ ቅዱስን ግብራቸውን ጭምር የሚያሳውቁ ናቸው፡፡
እንደገናም ‹‹እንዘ አሐዱ ሠለስቱ ወእዘ ሠለስቱ አሐዱ፣ይሤለሱ በአካላት ወይትዋሐዱ በመለኮት›› ማለት አንድ ሲሆን ሦስት፣ሦስት፣ሲሆኑ አንድ ናቸው፣ በአካል ሦስት ይሆናሉ፡፡ በመለኮትም አንድ ይሆናሉ፡፡ የሚለው ሐረግ ቅዱሳት መጻሕፍትን መሠረት ያደረገና ስለ ሥላሴ አንድነትና ሦስትነት ያለንን ግንዛቤ የበለጠ የሚያጠናክር ስለሆነ ጸሎት በጸለይን ቁጥር ልናጤነውና ልብ ልንለው ይገባል፡፡ ከዚህምጋር የሥላሴ ሦስትነታቸው በአንድነታቸው የማይጠቃለል፣አንድነታቸው፣ በሦስትነታቸው፣የማይከፋፈል፣ሆኖ፣በስም፣በአካል፣በግብር፣ሦስት፣በመለኮት፣በሥልጣንና በፈቃድ አንድ አምላክ እንደሆኑ በጥልቀት ልናውቅና ልንረዳ ያስፈልጋል፡፡
{flike}{plusone}