ካቴድራሉ ምን አጠፋ?

pp002

ቤተ ክርስቲያን ማለት ስሙ እንደሚያመለክተው የክርስቲያን ቤት የሕዝበ ክርስቲያን መሰብሰቢያ የምዕመናን አንድነት ወይም ኅብረት ማለት እንደሆነ ከአጠራሩ የምራዳው ሐቅ እንደሆነ ለማንም የተሠወረ አይደለም፡፡
ከጥንት ሲያያዝ በመጣው ተውፊት መሠረት ካህኑ በክህነቱ ቀዳሽ ምእመኑም በምእመንነቱ ለቅዳሴ ለውዳሴ አስፈላጊ የሆኑትን ንዋየ ቅድሳት እንደባለቤት ሁኖ እያሟላ ቤተ ክርስቲያን ስትገለገል ቆይታለች አሁንም እየተገለገለች ትገኛለች ለወደፊቱም እንደዚሁ፡፡
ወደ ከተማችን አ/አበባ ስንመጣም ካህኑ ራሱን የሚረዳበት የገቢ ምንጭ ስለሌለው ምእመኑ የባለቤትነት  መብቱን እንደያዘ በተቻለ መጠን አሥራት በኩራቱን እያወጣ የቤተ ክርስቲያኗ አገልዳዮች ቀጥሮ እሱ እንደባለቤት ሆኖ ቤተ ክርስቲያኑቱን እያስገለገለ ይገኛል፡፡
ታድያ ከስሙ እንደምንረዳው ቤተ ክርስቲያን የሕዝብ እንጂ ልዩ ባለይዞታ/ባለቤት/ እንደሌላት እየታወቀ አንዳንድ ጸሐፍያን ነን ባዮች በሚያሰራጩት ዌብ ሳይት የልብ ወለድ መነባንብ በዓለ ወልድ የማን ነው? ካቴድራሉስ? በማለት ሕዝብን ሲያደናግሩ ይስተዋላሉ፡፡
ይሁንና ከሙዳዩ ምጽዋት የሚገኘው ገቢ የአገልጋዩን ደመወዝ ሊሸፍን ባለመቻሉ ሌላ የገቢ ምንጭ ማፈላለግ አማራጭ የሌለው ጉዳይ ነው፡፡ ከዚህ በመነሳትም የመ/ጸ/ቅ/ሥላሴ ካቴድራል ጽ/ቤት ባለችው ከደርግ አፍ የተረፈች ይዞታ ላይ ቆርጦ ለት/ቤትና ለልዩ ልዩ አገልግሎት የሚውልና የሚከራይ ሁለገብ አዳራሽ ሠርቶ ከኪራይ በሚኘው ገቢ ከ3ዐዐ በላይ ሠራተኞችን የሚያስተዳድርና እንዲሁም ካቴድራሉ አገር አቀፍ እንደመሆኑ መጠን የሀገር መሪዎችና ታዋቁ ግለቦች በሞት ሲለዩ የሚቀበሩበት በመሆኑ እና የሕዝብ ብዛት በጨመረ ቁጥርም የቀብር ቦታ ስለሚጠብ ለሕዝቡና ለሠራተኛው ጥቅም ሲባል ረጅም ዕድሜ ያላቸውን ቀብሮች ዓጽም ወደ ሌላ ቦታ በማሰባሰብ ፉካዎችን ገንብቶ በገቢው ሠራተኞውን የሚደጉም መሆኑ ይታወቃል፡፡
ከቀብሩ የወጣው አጽምም በአዲስ መልክ ባሠራው ሙዝየም ሥር ባለው ቦታ እና ፉካ በክብር ተቀምጦ ይገኛል፡፡ ከነዚህም መካከል የቀኝ ጌታ ዮፍታሔ ዓጽም ተጠቃሽ ነበር፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በበዓለ ወልድ ቤተ ክርስቲያን ቅጥር ግቢ ውስጥ አርፈው ከሚገኙት ታዋቂ ግለሰቦች መቃብር የተነሳ ቦታው በመጣበቡና በመጨናነቁ ምከንያት በበዓል ጊዜ ግቢው በሐውልትና በብረት አጥር ብዛት ስለተጨናነቀ ምዕመናን እንደልብ የአምልኮ ሥርዓታቸውን መግለፅ ከማይችሉበት ደረጃ በመድረሱ ታቦተ ሕጉ ወጥቶ በሚዞርበት እና በሚከበርበት ወቅት ሐውልቱና የብረት አጥሩ አላንቀሳቀስ በማለቱ አጽሙ እንዳለ ሆኖ የብረት አጥሩና ሐውልቱ ተነሥቶ በቀብሩ ላይ መጠለያ እንዲሠራበት እና የእያንዳንዱ ፎቶ እና ታሪክ ዓጽሙ ካለበት ፊት ለፊት እንዲጻፍ ወይም እንዲለጠፍ ተደረጎ ሕዝቡ ለጸሎትና ለማስቀደሻ እንዲገለገልበት ለማድረግ ከሕዝብ ጋር በመመካከር እና የሕዝቡን ይሁንታ በመቀበል ሥራ የተጀመረ መሆኑ ግልፅ ነው፡፡ ቢሆንም አንዳንድ ግለሰቦች ይህን ከፍተት በመጠቀም የካቴድራሉን መልካም ገጽታ ጥላሽት ለመቀባትና ለማጥቁር እንዲሁም መልካም ዝናውን ለማደፍረስና ስም ለማጥፋት በብዙ ሲደከሙ ይታያሉ፡፡ ማጠንጠኛቸውም በበዓለ ወልድ ቤተ ክርስቲያን ዙርያና አጥር ግቢ ከተነሣው እና በመነሳት ላይ ባለው በመቶዎች የሚቆጠር ቀብር እና ሐውልት መካከል እነሱ የሚያውቋቸውንና ለቢዝነሳቸው ማወፈርያ ዋጋ ያወጡልናል ያሏቸውን ግለቦች ስም እየጠሩ የካቴድራሉን አስተዳደር እና ሠሪተኛውን ሲያብጠለጥሉ ይገኛሉ፡፡
በእነርሱ እምነት እነርሱ የሚያውቋቸውን እና በየመጣጥፋቸው ሁሉ ስማቸውን የሚጠሯቸው  ብቻ እንጂ ሌላው ከቀብሩ የተነሳው ሰው ለሀገሩም ሆነ ለወገኑ ሥራ የሠራ አይመስላቸውም፡፡ ይሁንና ሐቁ ጠፍቷቸው ሳይሆን ለእነሱ ካልመሰላቸው ሥራ መሥራትም ሆነ ታሪክ መሥራት ስለማይዋጥላቸው ነው፡፡ቤተ ክርስቲያን የሕዝብ ሀብት እንደመሆኗ መጠን ካቴድራሉ የሕዝቡን ችግር አይቶና ተመልክቶ ቦታውን ለሕዝብ አገልግሎት በሚመች መልኩ ለማስተካከል ሲባል የሚመለከታቸውን የቀብሩ ቤተሰቦች ዘመኑ ባፈራቸው ሚዲያዎች ተጠርተው ስለጉዳዩ ውይይት በማድረግ ሐሳባቸውን እንዲገልፁ መደረጉና በጉዳዩ ላይ ስምምነታቸውን ከገለፁ በኋላ የአጽም ማንሳቱ መርሐ ግብር እንዲከናወን መደረጉ ጥፋቱ እና ስህተቱ የት ላይ ነው፡፡
ጉዳዩ ወዲህ ነው ሕዝብና ሕዝብ ሲጋጭና ሲተራመስ አጃቸው የሚሞላላቸው የሕዝብ እና የቤተ ክርስቲያን ተቆርቋሪ ነን ባዮች ምእመናኑ በካቴድራሉ ልማት እና ለቤተ ክርስቲያኑ የሚደረገውን እንቅስቃሴ አይቶና ተገንዝቦ የአጽም ማንሳቱን ሥራ ደግፎ መርሐ ግብሩ በሰላም እንዲከናወን ፈቃደኛ ከመሆኑም ባሻገር ለሚደረገው የካቴድራሉ ልማተና የማስፋፊያ መርሐ ግብር ልዩ ልዩ አስተዋጽኦ በማድረጉ ውስጣቸው ስላቃጠላቸውና ስለከነከናቸው በሕልምም ሆነ በገሀድ የሚመኙትና የማፈልጉት የሕዝብ ትርምስ ባለመከሰቱ አዛኝ እና ተቆርቋሪ በመምሰል ለቢዝነሳቸው ማሳኪያ እና ማበልፀጊያ ሲሉ የሙታኑ ቤተሰቦች እንዲቀርቡ/መጡ አዋጅ መነገር አልተሰራበትም እያሉ የግብረ ዲቁና ሙያ እንኳ ሳይኖራቸው የቤተ ክርስቲያን ቀኖና አዋቂ ለመምሰል ሌት ተቀን ሲያላዘኑ ይሰማሉ፡፡
የበዓለ ወልድ ቤተ ክርስቲያን ጥንታዊና ዕድሜ ጠገብ እንደመሆኑ መጠን ጫካ ስለዋጠውና ማንኛውም የበዓለ ወልድ ተስፈኛ የኔቢጤ ሁሉ እንደመጸዳጃ ቤት ሲጠቀምባቸው ከነበሩት ዕድሜ ጠገብ መቃብራት መካከል አንዱ የቀኝ ጌታ ዮፍታሔ መቃብር ሲሆን ከዛሬ 8 ዓመት በፊት ዓጽሙን በክብር አንስቶ አዲስ ባሠራው ሙዝየም ውስጥ በክብር አሳርፎት የነበረ ሲሆን ያኔ ቀብሩ እንደመጸዳጃ ቤት ሁኖ የቆሻሻ መጣያ በነበረበት ወቅት አንድ ቀን ብቅ ብሎ ያየ ሰው ሳይኖር አሁን ቤተ ሰቦቻቸው ከ8 ዓመታት ቆይታ በኋላ በክብር ከተቀመጡበት ሙዝየም አንስተው ሲወስዱ የካቴድራሉን ካህናትና አስተዳደር እያነሱ ማራገብና የስም ማጥፋት ዘመቻ መክፈት ለፖለቲካ ፍጆታ የሚያገለግል መስሏቸው ካልሆነ በቀር እነቆርጦ ቀጥል የሚጽፉት       መነባንብ የታሪክም ሆነ የእምነት መሠረት ያለው አይደለም፡፡
ሲጀመር የቀኝ ጌታ ዮፍታሔ ዓጽም ከነበረበት አልባሌ ቦታ በክብር ተነሥቶ ለ8 ዓመታት ያህል ሙዝየም ቤት ሥር በክብር ተቀምጦ ነበር እንጂ እነራስ ገዝ እንደ ሚሉት አልባሌ ቦታ ላይ አልነበረም፣አልተቀመጠም፡፡የካቴድራሉ ካህናትም አባቶቻቸውንና የሀገር ባለውለታዎችን ጠንቆቀው የሚያውቁና የሚያከበሩ በመሆናቸው ዓጽማቸውን ከነበረበት ዝቅተኛ ደረጃ አንስተው ለ8 ዓመታት ያህል በክብር በሙዝየም ውስጥ እንዲቀመጥ ያደረጉ ስለሆነ ሊያስመሰግናቸው እንጂ ሊያስወቅሳቸው አይገባም ነበር፡፡
በመሆኑ ካ/ሉ የአባቶችንና የሀገር ባለውለታዎችን ክብር አሳምሮ የሚገነዘብ ስለሆነ መምህር ሳይኖራቸውና ከመምህራን ሥር ቁጭ ብለው ሳይማሩ መምሀር ነን ከሚሉ የደጀ ሰላም ቀበኞች የሚወሰደው ግንዛቤ እና ትምህርት አይኖርም፡፡
የመልአከ ብርሃን አድማሱ ዓጽም በተመለከተም እነቆርጦ ቀጥል እንደሚሉት ወደ የመን ወይም ወደሮም እንዲሄዱ ሳይሆን በዓጽማቸው ላይ ተጭኖ  የነበረውን የድንጋይ ክምር እና የብረት አጥር ብቻ ተነሥቶ ዓጽሙ ያለበት ቦታ ለሕዝበ ክርስቲያኑ መጸለያ እና ማስቀደሻ እንዲሆን ከማመቻቸት በቀር አስከሬኑ አልተነሳም ከቦታውም አልወጣም ዓጽሙም በነበረበት ቦታ ላይ እንደ ተቀመጠ ይገኛል፡፡
የሚገርመው ደግሞ ክህነቱስ ይቅርና የክርስትና እምነቱ ሳይኖር እርስ በሳቸው ዲ/ን እገሌ ቄስ እገሌ፣ መምሀር እገሌ፣ ወዘተ—የሚል ስያሜ እየተሰጣጡ የቤተ ክርስቲያን ሰዎች ለመምሰል ሲዳዳቸው የቤተ ክርስቲያን ሰዎች የተወላጅነት አሠራር እየተዋሐደን ስለመጣ ቅዱሳንን ከጎጥና ከቤተሰብ ውጭ ልናያቸው አልቻልም በማለት ራስን ካህን አስመስሎ የመግለፁ ጉዳይ ነው፡፡
 ከዚህ ጽሑፍ ላይ ጎልቶ የሚታየው ነጥብ አጥንትንና ጉልጥምትን በተመለተ እና እንዲሁም የጎጥና የተራራዎች ጉዳይ የሚመለከት ነው፡፡ ይህም የሚያሳየው ካጥንታቸውና ከጉልጥምታቸው ውስጥ የተዋሐደው ጠባብ አመለካከት የሚያንፀባርቅ እንጂ የካ/ሉን ስህተት አያመለክትም፡፡ ምከንያቱም ካ/ሉ እነርሱ እንደሚሉት የቀብሩን ምንነት በመለየት ሳይሆን በበዓለ ወልድ ውስጥ ቦታውን አጣቦ የሚገኘውን ቀብር ሁሉ ዓፅሙን/አስከሬኑን/ ሳይነካ እንዳለ ከመሬት በመተው ከቅጥር ግቢ ውስጥ ከሚገኙ መቃብራት ላይ የነበረውን የብረት አጥር እና የዕብነ በረድ ክምር ብቻ እንዲነሳ ሲያደረግ ከ6ዐ በላይ ቁጥር ያለው ቀብር ሲሆን የሰው እኩልነትና አንድነት የማይዋጥላቸው በሕዝብ ስም የሚነግዱ የቢዝነስ እና የእምነት ኮንትሮባንዲስቶች ከግቢው ከተነሱት አያሌ የሀገርና የቤተ ክርስቲያኗ ባለውለታዎች መካከል ስለአንድና ሁለት ሰዎች ቀብር ብቻ ሲያላዝኑ ስለሚደመጡ ነው፡፡
ይህም ከምን የተነሳ እንደሆነ የሕዝበ ክርስቲያኑ አስተዋይ አእምሮና ትክክለኛ ሚዛን የሚስተው አይሆንም፡፡ በእውነት ስለ ታሪክ እና ስለ ሕዝብ የሚቆረቆሩ ቢሆን ኖሮ ለምን ስለነ ቀኛዝማች መንገሻ —–  እና ሌሎች ታዋቂ የሀገር ባለውለታዎች አይጽፉም ነበር፡፡ ዳሩ ግን የእነሱ ተልዕኮ አንድና አንድ ብቻ በመሆኑ የሞኝ ልቅሶ ሆነና ስለ ሀገር፣ስለ ሥነ ጥበብ፣ ስለ ታሪክ ወዘተ —የተቆረቆሩ እና የተጨነቁ በመምሰል ቢዝነሳቸውን በምን መልኩ እንደሚያካብቱ በማሰብና በማሰላሰል ብቻ የሕዝቡን ቀልብ ለመሳብ የሚያደርጉት የብልጣብልጥነት ዘዴና ስልት ለመጠቀም ታስቦ የሚቀርብ ልብ ወለድ ነው፡፡
አሁን በተያዘው ጉዳይ ርዕሳችን አይደለም እንጂ የእኛው የ4 ኪሎ ሐራዎች ሊቅ የጸጋ ዘአብና የእግዚእ ኃረያ ልጅ ስለሆኑት አቡነ ተክለ ሃይማኖት የልደት ቦታም ሊያስተምሩን እየዳዳቸው ነው፡፡ ይሁን እና የሕዝበ ክርስቲያኑ ተስፋ ስለ ጻድቁ ጸሎትና ምልጃ በተመለከተ እንጂ ስለሀገራቸው የሚገደው ነገር ስለሌለ ይህ ጉዳይ አያከራክረንም፡፡ የሚያስገርመው ግን እያስመሰሉ መናገር የአዋቂነት ምልክት የሚመስላቸው ቆርጦ ቀጥሎች ምንም እንኳ የቤተ ክህነት ተወካዮች በፍለጋው የተሳተፉ ቢሆኑም የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ አጽም ከተቀበረበት ሲወጣ ፈላጊና አፈላላጊ የነበሩት የሥጋ ዘመዶቻቸው ጭምር መሆናቸው እየታወቀ እንዳልነበሩ ተደርጎ የተፃፈው የማጣቀሻ ጽሑፍ ምናልባት የየዋሆችን እና ከ2ሺ ዓ/ም ወዲህ ለተወለዱ ሕፃት ማታለያ ካልሆነ በቀር በወቅቱ ለነበርነው እና ሁኔታውን በቅርብ ሁነው ሲከታተሉ ለነበሩ ግን ከትዝብት በቀር የሚያተርፈው ቁም ነገር አይኖርም፡፡
ሲጠቃለልም ቤተ ክርስቲያን የሕዝቡ የሥርዓተ አምልኮ መፈጸሚ እንደ መሆኗ መጠን ለሕዝቡ አገልግሎት ምቹ ለማድረግ እንጂ የግሉን ቤት የሠራበት አካል የለም፡፡ በመሆኑም በዓለ ወልድ የማን ነው?የሚያሰኝ ተግባር አልተፈጸመበትም መልሱም የሕዝቡ ሊሆን ይገባል፡፡ ሊቀ ሥልጣናቱም ቢሆኑ ቀብሩ እንዲነሳ ሲሉ ሕዝቡን ያነጋገሩት ለሕዝብ አገልግሎት የሚውል የሕዝብ መጠለያ ለማሠራት እንጂ ተልባ ሊዘሩበት አልነበረም፡፡
አስተያየት ጸሐፊዎችም ቢሆኑ ስለ ቤተ ክርስቲያኗ ሥርዓት እና ታሪክ ተቆርቁረው ሳይሆን ሕዝቡ ከካቴድራሉ አስተዳደር ጋር ለምን ተስማምቶ ዓጽሙ እንዲነሳ ፈቀደ ለምንስ ትርምስ አልተፈጠረም በማለት የባሕር ማዶ ተስፈኞች የሚዘምሩትን መዝሙር ለማድመቅ እንጂ ስለ መልአከ ብርሃን አድማሱ ቀብር በመቆርቆር የሚቀርብ ተቃውሞ አይደለም፡፡ ስለሆነም እንኳን ክህነት እምነት ሳይኖራቸው በመምሰል በቤተ ክርስቲያን አባቶች እና በቤተ ክህነት ሠራተኞች ላይ ዓይናቸውን ተክለው ባለማቋረጥ አተኩረው የሚመለቱ የብፁዓን አባቶች ቀንደኛ ጠላቶች እስከመቼ ድረስ የዘለፋ ብዕራቸውን ቀስረው በቤተ ክርስቲያን ላይ እንዳሾሉ ይኖራሉ የሚለውን ጥያቄ የሁሉም የቤተ ክርስቲያን ተቆርቋሪ ሊሆን ይገባል፡፡ ምንም እንኳ የቤተ ክርስቲያናችን ሥርዓት የሚፈቀደው ባይሆንም እንደነዚህ ያሉትን በቤተ ክርስቲያንና በመሪዎቿ ላይ ለሚነግዱ ኢሎፍላውያን ግን የቤተ ክርስቲያኗ ምሁራን ብዕራቸውን ሊያሱ ይገባል እንላለን፡፡

ምንጭ፡-ሰንደቅ ጋዜጣ፤  ረቡዕ፣ ሐምሌ 19 ቀን 2009 ዓ.ም. 

{flike}{plusone}