“በገድል የተፈተነ ሰማዕት”
ከሊቀ ብርሃናት ኢሳይያስ ወንድምአገኘሁ
“መንፈስ ቅዱስ በእናንተ ላይ በወረደ ጊዜ ኃይልን ትቀበላላችሁ፤ በኢየሩሳሌም፣ በይሁዳም ሁሉ በሰማርያም እስከ ምድር ዳርም ድረስ ምስክሮቼ ትሆናላችሁ” በማለት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለሐዋርያት በተናገረው ቃል መሠረት በሃይማኖት ምክንያት መከራ እየተቀበለና ስለክርስቶስ እየመሰከረ በግፍ የተገደለ ሰው ሰማዕት ተብሎ ይጠራል፡፡ ቃሉ ከግእዝ ወደ አማርኛ ሲተረጎም ሰማዕት ማለት ምስክር ማለት ነው፡፡ ይህ የቅድስናና የክብር ስም የሚገኘውም እንዲሁ በከንቱ ሳይሆን ወርቅ በእሳት እንደሚፈተን ከብዙ ተጋድሎና ፈተና በኋላ ነው፡፡ (የሐ. ሥራ 1÷8፤ 22÷26)
ለዚህ አባባልና ታላቅ ቁምነር መልካም ምሳሌና ማስረጃ የሚሆነን ሚያዝያ 23 ቀን በየዓመቱ የሰባት ዓመት ተጋድሎውና የዕረፍቱ መታሰቢያ በዓል በስሙ በታነፁ አብያተ ክርስቲያት ሁሉ በታላቅ ክብር የሚከበርለት የልዳው ሰማዕት ቅዱስ ጊዮርጊስ ግምባር ቀደም ሆኖ የሚጠስ ነው፡፡
ቅዱስ ጊዮርጊስ ወላጅ አባቱ አንጣስዮስ (ዘሮንቶስ) የሚባል ሲሆን እናቱ ደግሞ ቴዎብስታ በመባል ትታወቃለች፡፡ የአባቱ አገር በዚያን ጊዜው አጠራር “ቀጰዶቅያ” የሚባል ሲሆን የእናቱ አገር ግድሞ ልዳ ተብሎ ይጠራል፡፡ ይህ ቅዱስ ጊዮርጊስ የሰባት ዓመት ተጋድሎውን ፈጽሞ ከዚህ ዓለም በሞተ ሥጋ በተለየና ዘለዓለማዊ ዕረፍትን ባረፈ ጊዜ ሥጋው ያረፈው በዚሁ በልዳ በተሠራች ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ነው፡፡ ስለዚህም ቅዱስ ጊዮርጊስ “የልዳው ፀሐይ፣ የልዳው የምሥራቅ ኮከብ” እየተባለ ይጠራል፡፡ በዚሁ ሰማዕት ስም የሚጠራውና አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ በመባል የሚታወቀው ኢትዮጵያዊው ሊቅና መንፈሳዊ አባት ሰዓታት በተባለው መንፈሳዊ ድርሰቱ “ፀሐይ ዘልዳ፣ ኮከብ ዘልዳ፣ ዘልዳ ንጉሥ ነዓ ጊዮርጊስ” በማለት የዘመረለትና ታላቅ ምስጋናም ያቀረበለት ይህንኑ መነሻ በማድረግ ነው፡፡ ይህም ከግዕዝ ወደ አማርኛ ሲተረጎም “የልዳው ፀሐይ፤ የልዳው ኮከብ ቅዱስ ጊዮርጊስ ሆይ ና” ማለት ነው፡፡
ታላቁ ሰማዕት ቅዱስ ጊዮርጊስ የተወደለበት ዘመን ዘመነ ሰማዕታት ሲሆን ያ ዘመን ብዙ ክርስቲያኖች በመከራ የተፈተኑበትና ስለክርስትና ሃይማኖት ብዙ ዋጋ እየከፈሉ ሕይወታቸውን ለሞት የሰጡበት ዘመን ነበር፡፡ በዚያም ዘመን ያንን አገር የሚመራውና የሚያስተዳድረው “ዱድያኖስ” የሚባል ከሐዲና ጣዖት አምላኪ የሆነ ንጉሥ ነበር፡፡ የቅዱስ ጊዮርጊስ አባት ዞሮንቶስ በዱድያኖስ ቤተ መንግሥት ታላቅ ሹመት ተሰጥቶት ሲያገለግል ከቆየ በኋላ ከዚህ ዓለም በሞት ስተለየና በዚያን ዘመንም አባት ሲሞት ልጁ በሥራው የመተካት መብት ስለነበረው የ20 ዓመት ዕድሜ የነበረው ወጣቱ ሰማዕት ቅዱስ ጊዮርጊስም በአባቱ ሹመት ተተክቶ ለመሥራት ወደ ንጉሡ በሔደ ጊዜ ንጉሥ ዱድያኖስ በቤተ መንግሥቱ ጣዖት አቁሞ ለጣዖት ሲሰግድና ሕዝቡንም ሁሉ እያስገደደ ለጣዖት እንዲሰግዱና ጣዖት እንዲያመልኩ ሲያደርግ በማግኘቱ ይህንን እኩይ ተግባር በመቃወም ገና በ20 ዓመት ዕድሜው የሰማዕትነት ተጋድሎውን ጀመረ፡፡ በመንፈስ ቅዱስ አነሳሽነትና በእግዚአብሔር ላይ ባለው የፀና እምነት መሠረትም የዚህ ዓለም ተድላና ደስታ ከንቱ መሆኑን በመገንዘብ ያለውን ሀብት ሁሉ ለድኆችና ለምስኪኖች በመስጠት ሹመቱንና ሽልማቱን በጠቅላላ የዚህን ዓለም ክብር ሁሉ በመናቅ ከንጉሡ ከዱድያኖስና ሰባ ነገሥት በመባል ከሚታወቁት ኃያላን ጋር ተጋድሎውን ቀጠለ፡፡ “ምንት ይበቁዖ ለሰብእ ለእመ ኵሎ ዓለመ ረብሐ ወነፍሶ ሀጉለ” (ማቴ 16÷25) የሚለውም የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ቃለ ወንጌል መመሪያው ስለነበረ የዚህ ዓለም ከንቱ ነገር ሁሉ በእሱ ዘንድ ፈጽሞ የተናቀና የተጠላ ከመሆኑ የተነሣ ለሥጋዊ ሕይወቱም ሳይሳሳና ሳይፈራ በንጉሡ ፊት ቆሞ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ የሚያምን እውነተኛ ክርስቲያን መሆኑን እየገለጠና እየተናገረ ስለእውነተኛው አምላክ መመስከርና ማስተማር ጀመረ፡፡
ንጉሡና የእሱ ተከታዮች የሚሰግዱለት ጣዖትም ምንም ምን ማድረግ የማይችል ደካማ ፍጡር መሆኑን በሚገባ ከአስረዳ በኋላ ሰማይና ምድርን፣ የሚታየውንና የማይታየውን ሁሉ የፈጠረውን እውነተኛውን አምላክ እንዲያመልኩና ለእሱም እንዲሰግዱ እያስተማረ የንጉሡን ሚስት ንግሥቲቱን ሳይቀር ሕዝቡን ሁሉ በማሳመን የሰማዕትነት ተግባሩን ቀጠለ፡፡ ንጉሡ ዱድያኖስ ግን በፍቅረ ጣዖት የተለከፈና ፈጽሞም የተመረዘ ስለነበረ የቅዱስ ጊዮርጊስን ቃል ሰምቶ ከአምልኮ ጣዖት ተመልሶ በእውነተኛው አምላክ በእግዚአብሔር ማመን አልቻለም፡፡ እንዲያውም ንግሥቲቱ እለእስከንድርያ የቅዱስ ጊዮርጊስን ትምህርት ሰምታ በኢየሱስ ክርስቶስ በማመኗ ምክንያት በመጋዝ ስንጥቀው እንዲገድሏትና መቀጣጫም እንድትሆን አድርጓል፡፡ እሷ ግን በኢየሱስ ክርስቶስ አምና ከቅዱስ ጊዮርጊስ በተማረችውንና በተረዳችው መሠረት በእውነተኛው ሃይማኖት ፀንታ በመሞቷ የሰማዕትነትን ክብር አግኝታለች፡፡
ከሐዲውና ጣዖት አምላኪው ዱድያኖስ በአምልኮ ጣዖት የፀና፣ እውነተኛውን አምላክ እግዚአብሔርንም የካደ ከመሆኑ የተነሣ እሱ ቃሉን ሰምቶ በእውነተኛው አምላክ ማመን ሲገባው በተቃራኒው ቅዱስ ጊዮርጊስ እሱ ለሚያመልከው ጣዖት ቢሰግድና በእሱም ጣዖት ቢያመልክ ከአባቱ የበለጠ ሹመትና ክብር እንደሚሰጠውና ከእሱም ቀጥሎ ባለው የመንግሥት ሥልጣን ላይ እንደሚያስቀምጠው ደጋግሞ ቃል በመግባት ያባብለው እንደነበር ስለቅዱስ ጊዮርጊስ ተጋድሎ በተጻፈው መጽሐፈ ገድል በሰፊው ተጽፎ ይገኛል፡፡
ቅዱስ ጊዮርጊስ ግን የእግዚአብሔርን እውነተኛ አምላክነት፣ ከሀላፊነቱንና ኃያልነቱን በሚገባ ያወቀ ከመሆኑም በላይ የዚህን ዓለም ከንቱነት ከልብ የተረዳ ስለሆነ የንጉሡ የዱድያኖስ ቃል አለታለለውም፣ ጊዜያዊ ሹመትና ሽልማትም አልማረከውም፡፡ እንዲያውም ሰባት ዓመት ሙሉ ተጋድሎውን በመቀጠል እጅግ አሰቃቂና ዘግናኝ የሆኑ ፀዋትወ መከራዎችን በመቀበል የኢየሱስ ክርስቶስ እውነተኛ ምስከር ሆኖአል፡፡ ብዙ አስደናቂ ተአምራትንም በማድረግ ብዙ አሕዛብን በኢየሱስ ክርስቶስ እንዲያምኑ አድርጓል፡፡
በንጉሥ ዱድያኖስ ትእዛዝ በቅዱስ ጊዮርጊስ ላይ የደረሱና የተፈጸሙ አሰቃቂና ዘግናኝ የሆኑ መከራዎችና ሰቃዮች እጅግ ብዙዎች ሲሆኑ ከነዚህ ውስጥ ጥቂቶቹ የሚከተሉት ናቸው፡፡
1.በንጉሡ ትእዛዝ አትናትዮስ በተባለ መሠሪይ (ጠንቋይ) የተዘጋጀና የተቀመመ ወዲያውኑ የሚገድል መርዝ እንዲጠጣ ተደርጓል፡፡ ግን “በእኔ የሚያምኑ እና የእኔ ደቀ መዛሙርት የሆኑ እባብ ቢይዙ፤ የሚገድል መርዝም ቢጠጡ አይጎዳቸውም” ብሎ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለሐዋርያት እንደተገናገረው ምንም ጉዳት አልደረሰበትም (ማር. 16÷18)፡፡
2.የጠጣው መርዝ ጉዳት ሳያደርስበት በመቅረቱ ይኸው ዓላዊ ንጉሥ ተናዶ ትልቅ መጋዝ በማሰራት ሥጋውን እንዲቆራርጡትና እንዲከትፉት ከአደረገ በኋላ አጥንቱን አስፈጭቶና አቃጥሎ አመዱን ይድራስ በተባለ ተራራ ላይ በነፋስ እንዲበተን አድርጓል፡፡ በዚህም ጉዳት አልደረሰበትም ይልቁንም በተራራው ላይ ያሉ እንጨቶችና ቅጠሎች “ጊዮርጊስ ሆይ ጽና፤ በርታ” እያሉ ተአምራታዊ ድምጽ ያሰሙት ነበር፡፡ ከዚህም ሁሉ ስቃይና መከራ በኋላ ከሞት ተነሥቶ ተጋድሎውን ቀጥሏል፡፡ በዚህም ምክንያት “ዘሐረፀከ ዱድያኖስ፤ ወወገረከ ደብረ ይድራስ፤ ዘዘረወከ በነፋስ፤ ሰላም ለከ ጊዮርጊስ” በማለት አሁንም ታላቁ ሊቅ አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ የዘመረለትን ስብሀተ ፍቁር ዛሬም ካህናት እዘመሩለት ይገኛሉ፡፡
3.በጅራፍ ገርፈውታል፤ በመንኮራኩርም አበራይተው ገድለው ከከተማ ውጭ ጥለውታል፡፡ ጌታችንም ከሞት አሥነሥቶታል፡፡
4.ንጉሥ ዱድያኖስ ለአቆመው ጣዖት ባለመስገዱና እሱንም ባለማምለኩ፤ ይልቁንም ንጉሡን፣ መኳንንቱንና ሕዝቡን ለጣዖት አትስገዱ እሱንም አታምልኩ እውተናውን አምላክ ኢየሱስ ክርስቶስን ብቻ እመኑ፡፡ ለእርሱም ሰገዱ እያለ በድፍረት በማስተማሩና ስለእሱም በመመስከሩ ቆዳው ተገፎ በሰውነቱ ላይ ጨው ተነስንሶበት በብረት ምጣድ ላይ እንዲጠበስና በእስትም እንዲተኮስ ተደርጓል፡፡ በዚህም ጉዳት ሳይደርስበት ከሞት ድኖአል፡፡
5.በመጨረሻም ሚያዝያ 23 ቀን አንገቱን በሰይፍ ተሰይፎ (ተቆርጦ) የመጨረሻውን ዕረፍተ ሞት አርፎአል፡፡ አንገቱን በቆረጡትም ጊዜ ከአንገቱ ደም፣ ውኃ፣ ወተትና ማር እንደፈለቀ መጽሐፈ ገድሉ ይተርካል፡፡ ሊቃውንተ ቤተክርስቲያን “ቅዱስ ጊዮርጊስ ሶበ ተከለለ፣ ደም ወማይ ወሀሊብ እምነ ክስዱ ፈልፈለ” እያሉ በዕለተ ዕረፍቱ የሚዘምሩትም ይህንኑ በማስመልከት ነው፡፡ ይህንንም የዕለተ ዕረፍቱን ታሪክ ሚያዝያ 23 ቀን የሚነበበው ስንክሳር የተባለው መጽሐፍ ሲገልጥ “ከዚህ በኋላ ራሱን ዘንበል አድርጎ በሰይፍ ቆረጡት፡፡ በመንግሥተ ሰማያትም አክሊላትን ተቀበለ፡፡ ከአገልጋዮቹም የቀሩት ሥጋውን ወስደው በልብስ ጠቀለሉት፡፡ ወደ ሀገሩ ልዳም ወሰዱት ቤተ ክርስቲያንም ሠርተው በውስጧ አኖሩት ከእርሱም ቁጥር የሌላቸው ብዙዎች ድንቆች ተአምራት ተገለጡ” በማለት ታሪኩን ያጠቃልላል፡፡
ይህ ቅዱስ ሰማዕት በሕይወተ ሥጋ እያለ በሰባት ዓመት ተጋድሎ ጊዜው ውስጥ ብዙ ተአምራትን እንደ አደረገና ተአምራቱን የተመለከቱ እጅግ ብዙ የሆኑ አሕዛብም በአዩአቸው ተአምራት ተመስጠው ከጣዖት አምልኮ ወደ እውነተኛው አምላክ ወደ እግዚአብሔር ተመልሰው የእውነተኛይቱ ቤተ ክርስቲያን አባላት ለመሆን ችለዋል፡፡ የአደረጋቸው ገቢረ ተአምራት እጅግ ብዙዎች ሲሆኑ ጥቂቆቹን ቀጥለን እንመለከታቸዋለን፡፡
1) በአንዲት መበለት ቤት የደረቀውን ምሰሶ አለምልሞ ትልቅ ዛፍ አስለደረገው “የክርስቲያን አምላካቸው ሰው መስሎ ወደ እኔ መጣ” እያለች መበለቷ በአድናቆት ስትናገር ቅዱስ ጊዮርጊስ “እኔ የአምላክ አገልጋይ ሆኜ የመጣሁ ነኝ እንጂ አምላክ አይደለሁም” በማለት ራሱን ዝቅ ክርስቶስን ግን ከፍ አድርጎ እየተናገረ ስለእውነተኛው የክርስትና ሃይማኖት በመመስከሩ ብዙዎችን አሳምኖአል፡፡
2) በንጉሡ በዱድያኖስና በሰባ ነገሥታት ፊት ፍርድ ለመቀበል ቆሞ ሳለ እነሱ የተቀመጡባቸውን ደረቅ የእንጨት ወንበሮች አለምልሞ ምልክት እንዲያሳያቸው በጠየቁት ጊዜ በጸሎቱ እንዚያ ደረቅ ወንበሮች ወዲያውኑ ለምልመው አብበውና አፍርተው እንዲታዩ አድርጓቸዋል፡፡ ይህንንም ድንቅ ተአምር በማየት ቁጥር የሌላቸው ብዙ አሕዛብ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ አምነዋል፡፡
3) ቤይሩት በምትባል አገር የሚኖሩ ሰዎች በየተራ አንዳንድ ልጅ ለዘንዶ እየገበሩ ዘንዶውን ያመልኩ ስለነበር ከዕለታት አንድ ቀን አንዲት ቤይሩታዊት ቆንጆ ልጃገረድ ለዘንዶው ግብር ልትሰጥ ወላጆቿ ወስደው ከዛፍ ላይ አኑረዋት ሳለች ቅ/ጊዮርጊስ በዚያ አልፎ በሚሄድበት ጊዜ በዛፉ ላይ ሆና ስላያት ለምንድነው በዚህ ዛፍ ላይ የተቀመጥሺው ብሎ ሲጠይቃት ለዘንዶ ግብረ ልሰጥ ነው አለችው፡፡ እሱም አይዞሽ በማለት እያረጋጋት ሳለ ሰዓቱ ሲደርስ ዘንዶው እንደለመደ መጥቶ ግብሩን ተቀብሎ ብላቴናይቱን ሊበላ ሲል ቅዱስ ጊዮርጊስ በክርስቶስ ስም ሲያማትብበት ባለበት ፈዞ ቆመ፡፡ በዚህ ጊዜ በያዘው ጦር ከገደለው በኋላ አንገቱን አሥሮ ያችን ቤይሩታዊት ልጃገረድ እያስጎተ ወደ ከተማ ወስዶ ለሕዝቡ በማሳየት “እናንተ ስታመልኩበትና ልጆቻችሁን ስትገብሩለት የነበረው ይህ አውሬ ራሱን እንኳን ማዳን የማይችል ነው” እያለ በማስተማሩና ብዙ ተአምራትንም በማሳያቱ ብዙ አሕዛብ በክርስቶስ እንዲያምን አድርጓል፡፡
4) ከላይ እንደተገለጠው አትናትዮስ የተባለው ጠንቋይ (መተተኛ) በንጉሡ ትእዛዝ ወዲያውኑ የሚገድል መርዝ ቀምሞና በጥብጦ ቢያጠጣው መርዙ ጉዳት አላደሰበትም፡፡ አትናትዮስ የተባለው ይህ ጠንቋይም በቅዱስ ጊዮርጊስ የተደረገውን ተአምር ከአየ በኋላ በቅዱስ ጊዮርጊስ አምላክ አምኖ ከመጠመቁም በላይ ወንጌላዊ ሐዋርያ ለመሆን በቅቶአል፡፡
5) ይህ ቅዱስ ሰማዕት የእግዚአብሔር መንፈስ ስላደረበት ከደረቅ ምድር ውኃ አፍልቋል፤ ሙታንን አሥነሥቷል፤ የዕውራንን ዓይን አብርቶአል፤ ለምፅን አንጽቶአል አጋንንት የያዛቸውን ሕሙማን ሁሉ ፈውሶአል፡፡
6) በተለያዩ ጊዜያት ከደረሰበት አሰቃቂ መከራ የተሣ ከአጋጠመው የሞት አደጋ ድኖ በሕይወት በመገኘቱና ከሞት በመነሣቱ በእግዚአብሐየር የማያምኑ ብዙ አሕዛብን የማሳመን ችሎአል፡፡
ወደ ዜና ዕረፍቱ እንመለስና ቅዱስ ጊዮርጊስ ወደሚገደልበት ቦታ በተወሰደ ጊዜ ገዳዮቹ ጥቂት የጸሎት ጊዜ እንዲሰጡት ጠይቆ በገዳዮቹ ፊት እጆቹን ወደ ሰማይ ዘርግቶ እየደለየ ሳለ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተገልጦ “ድካምህን ሁሉ ተቀብያሃለሁ፣ ክብርህንም እንደወዳጆቼ ሐዋርያት አድርጌልሃለሁ፤ ስምህን ጠርቶ የሚለምነኝን ሁሉ ጸሎቱን ፈጥኜ እሰማዋለሁ፤ ዝክርህን የሚዘክረውን፤ በስምህ ወደታነፁ አብያተ ክርስቲያናት የሚመጣውንና የሚጸልየውን ሁሉ አንተ ከገባህበት መንግሥተ ሰማያት እንዲገባ አደርገዋለሁ፡፡
ወዳጄ ጊዮርጊስ ሆይ ሰባት ዓመታት ሙሉ የወንጌልን ቃል በማስተማር ልዩ ልዩ ጸዋትወ መከራን ስልተቀበልክ ሰባት አክሊላተ ክብር እሰጥሃለሁ፡፡ እስከዛሬ የተጋደልከው ገድለና የተቀበልከው መከራ ይበቃሃል፡፡ እንግዲህ ነፍስህ ከሥጋህ ተለይታ አስቀድሜ ወደአዝጋጀሁላት የክብር ማረፊያ ትሄዳለት፤ መላእክተ ብርሃንም በክብር ያሳርጓታልና በዚህ ደስ ይበልህ በማለት” ባርኮት ተሠውሮአል፡፡
ስለዚህ ቤተክርስቲያን ለዚህ ሰማዕት “ቅዱስ” የሚለውን የቅድስና ስም ከማስጠቷም በላይ በስሙ ጽላት ቀርፃና አብያተ ክርስቲያናትንም እያነፀች በዓላቱን በየጊዜው ስታከብር ኖራለች ወደፊትም እስከ ዕለተ ምፅአት ትቀጥላለች፡፡
“ወስብሐት ለእግዚአብሔር”