ዓመታዊው የዓጋዕዝተ ዓለም ሥላሴ ክብረ በዓል በድምቀት ተከበረ
በየዓመቱ ሐምሌ 7 ቀን በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ የሚከበረው ዓመታዊው የሥላሴ ክብረ በዓል በዚህ ዓመትም በመንበረ ጸባዖት ቅድሰት ሥላሴ ካቴድራል ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአኩሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት፣ ብፁአን ሊቃነ ጳጳሳት እንዲሁም በብዙ ሽህ የሚቆጠሩ ምዕመናን በተገኙበት እጅግ ደማቅ በሆነ ሁኔታ በዓሉ ተከብሮ ውልዋል፡፡
በዚሁ ዕለት አጋዕዝተ ዓለም ሥላሴ በአብርሃም ቤት ተገኝተው ቤቱን የባረኩበት፣ የአንድነታቸውንና ሦስትነታቸው ሚስጢር የተገለፀበት ታላቅ በዓል ነው። በዓሉ መከበር የጀመረው ከዋዜማው ከሐምሌ 6 ጀምሮ ሲሆን የካቴድራሉ ካህናትና መዘምራን ከዋዜማው ከቀኑ 3 ሰዓት ጀምሮ ለ30 ሰዓታት ያህል ሌሊትና ቀኑን ሙሉ ያለ ማቋረጥ ስብሃተ እግዚአብሔር ሲያቀርቡ ውለው አድረዋል፡፡
ይህ መንፈሳዊ አገልግሎት ማለትም ስርዓተ ማህሌተ፣ ስርዓተ ቅዳሴ እንዲሁም ሰዓታትና ሰርክ ፀሎት በአጠቃለይ የስርዓተ አምልኮ አፈፃፀም በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ ልዩ በመሆኑ የእምነቱ ተከታዮች ብቻ ሳይሆን ሌሎችንም እጀግ የሚስደንቅ በዓል ነው፡፡
የበአሉን ታሪክ አጠር አድርገን እንደሚከተለው አቅርበነዋል
እግዚአብሔርን የሚፈራና ቸር ጻድቅ የሆነ ስሙ አብርሃም የተባለ ምድያም በሚባል አገር አንድ ሰው ይኖር ነበር የሚስቱም ስም ሣራ ይባላል።እነዚህም ቅዱሳን በሥላሴ ሕግ ተጠብቀው ስደተኛውንና እንግዳውን እየተቀበሉ ያስተናግዱ ነበር።እንግዳ ሳይዙ ወይም ሣይኖር የሰናፍጭ ቅንጣት ስንኳ ያህል ምግብ ምንም ምን አይቀምሱም ነበር።
የበጎ ነገር ጠላት የሆነ ሰይጣንም ይህን በተመለከተ ጊዜ ከጭፍሮቹ አንዱን እንዲህ ሲል ላከው። እንግዶች ሁሉ ወደ አብርሃም ቤት እንዳይሄዱ ሄደህ በምድያም ጎዳና ተቀምጠህ ዕውነቱን በሐሰት ለውጠህ ተናገር።
እነሆ ደምህ በመሬት ላይ እስኪወርድ ድረስ እራስክን በድንጋይ ፈጥፍጠው አለው።ሰይጣኑም ይህን ትእዛዝ ከተቀበለ በኋላ ወደ ምድያም ወረደና ደሙ በምድር ላይ እስኪፈስ ድረስ ራሱን በድንጋይ ገምሶ በጎዳና ዳር ተቀመጠ። በጎዳና የሚያልፉ መንገደኞች ሰዎችም ወደ እርሱ በደረሱ ጊዜ እናንት መንገደኞች ከወዴት መጥታችኋል ወዴትስ ትሄዳላችሁ ሲል ጠየቃቸው።
መንገደኞቹም እኛስ ወደ ደገኛው ወደ አብርሃም ቤት እንሄዳለን አሉት።በውኑ አብርሃም ደግነቱ በክፋት እንደተለወጠና ክፉ ሰው እንደሆነ አልሰማችሁምን።እነሆ እንግዳ ከመጥላቱ የተነሣ ደሜ ከመሬት ላይ እንደ ውሃ እስኪፈስ ድረስ የፈነከተኝን እራሴን መጥታችሁ ተመልከቱ ይልቁንስ በኔ የደረሰ እንዳይደርስባችሁ አትሂዱ አላቸው።እንግዶቹም ያ ቸርና መልካም ሰው የነበረ አብርሃም ምን ነክቶት ክፉ ሰው ሊሆን ቻለ በማለት እርስ በራሳቸው ተወያዩ።ይህንንም ከተባባሉ በኋላ ተመልሰው ወደ ሀገራቸው ሄዱ።በዚችም ዕለት አብርሃም ከቤቱ ወጥቶ በጎዳና እንግዳ ፈልጎ አጣ።ከዚያም ወደ ቤቱ ተመልሶ ገባና ምንም ምን ሳይቀምስ ተኛ።
በማግስቱም አምስት ሰዎች ወደ አብርሃም ቤት ሲሄዱ ያ ተንኰለኛ ሰይጣን አገኛቸውና እንደቀድሞው እናንተ ሰዎች ወዴት ትሄዳላችሁ ሲል ጠየቃቸው።
እነሱም ወደ አብርሃም ቤት እንሄዳለን አሉት።ሰይጣኑም መልሶ ወንድሞቼ ሆይ አብርሃም እራሴን ፈንክቶኝ ከማህል ራሴ የሚወርደውን ደሜን ኑ ተመልከቱ አላቸው።እነሆ አሁንም እንደኔ እንዳትሆኑ በሰላም ወደ ሀገራችሁ ተመለሱ አላቸው።በዚህን ጊዜ እነዚያ እንግዶች እርስ በራሳቸው አብርሃም ከሚገድለንስ ወደ ሀገራችን ብንመለስ ይሻላል ተባባሉ።
ዳግመኛም እንደ ልማዱ አብርሃም ወደ ጎዳና ወጥቶ ፀሐይ እስኪጠልቅ ድረስ ሲጠብቅ ውሎ ምንም እንግዳ ሳያገኝ ቀረ።ከዚያም ወደ ቤት ተመልሶ ምንም ምን ሳይቀምስ ተኝቶ አደረ።
በሦስተኛውም ቀን አጋዕዝተ ዓለም ሥላሴ የአብርሃምን የልቡን ቆራጥነትና የሰይጣንን ተንኰል ተመልክተው ወደ አብርሃም ቤት ሄዱ።በዚህ ጊዜ የሰይጣን ምክሩን ሁሉ ተሻረ ይዘውም ወደ መጨረሻይቱ የሲኦል ረግረግ ጣሉት።እሊህ ሥላሴም በእንግዳ ደንብ በአብርሃም በቤቱ ደጃፍ ተቀመጡ። አብርሃምም በደጁ እንደተቀመጡ በተመለከተ ጊዜ ወደ ቤቱ ሮጦ ገብቶ ለሚስቱ እንዲህ ሲል ነገራት።
እኅቴ ሣራ ሆይ እነሆ የከበሩ አረጋውያን ሦስት እንግዶች መጥተውልናል።
እንግዲህ አንቺ ፈጥነሽ እንጀራና ወጡን ጥሩውን ጠላና መልካሙን ጠጅ አዘጋጂ እኔም የወይፈን ፍሪዳ አርዳለሁ አላት።ሣራ ሚስቱም እሺ ጌታየ እንዳልከኝ አደርጋለሁ አለች።ዳግመኛም ዕርጎውን ማሩን እንድታዘጋጅና ለእግራቸው መታጠቢያም ውሀ በምንቸት ታሞቅላቸው ዘንድ አዘዛት።ከዚያም በኋላ ለእያንዳንዳቸው ለየራሳቸው ፤ ሦስት ታላላቅ ዳቦ ትጋግር ዘንድ አዘዛት።
አብርሃምም ይህን ከተናገረ በኋላ ወይፈኑን አርዶ ሥጋውን በየብልቱ አወጣው።ከዚያም የታረደውን የወይፈን ሥጋ በትከሻው ተሸክሞ ወደ ቤቱ ይዞ ከገባ በኋላ ለሚስቱ ሰጣትና እኔ እግራቸውን እስካጥብ ድረስ ይህን ሥጋ ቅባቱን በዛ አድርገሽ በጨውና በቅመም አጣፍጠሽ ስሪው አላት።እሷም እሺ በጄ አለችው። አብርሃምም ከቤቱ መድረክ በስተውጭ ሥላሴን ባገኛቸው ቦታ ላይ ልብሱን አነጠፈና ጌቶቼ እግራችሁን አጥባችሁ ዘንድ ወደ ወንድማችሁ ቤት ዝለቁ ግቡ አላቸው።
ከዚህ በኋላ ተነሥተው ወደ ድንኳኑ ወይም አዳራሹ ገቡና ባነጠፈላቸው ምንጣፍ ላይ ተቀመጡ። በዚህን ጊዜ የአብን እግር ማጠብ ጀመረና አብን ካጠበ በኋላ ወልድና መንፈስ ቅዱስም ታጥበው አገኛቸው ያለመለየት አንድ ናቸውና።በዚህ ጊዜ ማዕዱን በገበታ ሠርቶ ወይኑንም በማድጋ ቀድቶ አቀረበላቸውና እስኪጠግቡ ድረስ በሉ ጠጡ።ማዕዱ ከተነሣ በኋላ ለእንግዶቹ እራት የታረደውን ወይፈን በቤቱ በራፍ ፊት ለፊት ከውጭ በኩል ቆሞ አየው።አብርሃምም ይህን ወይፈን ባየ ጊዜ ፈጽሞ ፈራ ተንቀጠቀጠ።በዚህ ጊዜ ሥላሴ አብርሃም ሆይ ሰይጣን እንዳይቀናብህ ጠንቅቀህ ዕወቅ።እንግዳ በመጣልህ ጊዜ በብሩህ ልቡና እና በንቁህ ኅሊና ሆነህ ተቀበለው።ነገር ግን እንግዳ ካልመጣ እራትህን በጊዜው ብላ መጠጥህንም ጠጣ እንጂ ጦምህን አትደር አሉት።ይህንንም ተናግረው እኒህ በአምሣልና በህልውና ትክክል የሆኑ ሥላሴ ወደ ሰማይ ዐረጉ።
የምድያም ሰዎችም ስለዚህ ለምግብ ከተዘጋጀ በኋላ ሥላሴ ስላስነሡት ወይፈን እንዲሁም በሥላሴ ዘንድ በተደረጉት ድንቅ ድንቅ ሥራዎች ሁሉ ፈጽመው ተደነቁ።