ወርሐዊ የአጋዕዝተ ዓለም ሥላሴ ክብረ በዓል ባማረ ሁኔታ ተከበረ
በወጣት ኢዮብ በላቸው
ዛሬ ሰኔ 7 ቀን 2012 ዓ.ም በተከበረው ወርሐዊ የአጋዕዝተ ዓለም ሥላሴ ክብረ በዓል ባማረ ሁኔታ ተከብሮ ውሏል። በዓሉ ባማረ ሁኔታ እንዲከበር የካቴድራሉ ሰ/ት/ቤት አባላት ፣ የአካባቢ ወጣቶች፣ የሃሌ ሉያ ከፍተኛ ክሊኒክ የጤና ባለሙያዎችና የካቴድራሉ የጤና አጠባበቅ ኮሚቴ በጋር በመሆን ጠንካራ የማስተባበር ሥራ በመሥራታቸው በዓሉ እጅግ ባማረ ሁኔታ ተከብሯል።
ለሕዝቡ ደህንነት ሲባል ሕዝበ ክርስቲያኑ በሙቀት መለኪያ ማሽን በመለካት፣ በአካባቢው ወጣቶች የእጅ ሳኒታይዘር እየተደረገላቸውና የአፍና የአፍንጫ ጭንብል ማድረጋቸውን በመቆጣጠር ምዕመናን በተዘጋጀላቸው ወንበር ርቀታቸውን ጠብቀው እንዲቆሙ በማድረግ የካቴድራሉ የሰ/ት/ቤት አባላት ፣ የአካባቢ ወጣቶች፣ የሃሌ ሉያ ከፍተኛ ክሊኒክ የጤና ባለሙያዎችና የካቴድራሉ የጤና አጠባበቅ ኮሚቴ ከፍተኛ አገልግሎት ሰጥተዋል።
በተለይም ከዚህ በፊት በግቢው ውስጥ ይፈጠር የነበረውን የመኪና መጨናነቅ ቦታ በመለየት፣ መግቢያና መውጫው ምዕመናኑ በአግባቡ እንዲገለገሉ አድርገዋል ።
በትላንትናው ዕለት ሰኔ 6/2012 ዓ.ም በካቴድራሉ አስተዳደር አማካኝነት የተለያዩ የኮረና በሽታ ቅድመ መከላከያ የሚያገለግሉ 3 የሙቀት መለኪያ፣ 54 ሌትር ሳኒታይዘር፣ 30 የአካባቢው ወጣቶች የሚያስተናግዱበት መለያ ልብስ ተገዝቶ ለአገልግሎት መዘጋጀቱና የጸረ ተዋህስያን ኬሚካል በሃሌሉያ ከፍተኛ ክሊኒክ የጤና ባለሙያዎች አማካኝነት በካቴድራሉ ቅጽረ ግቢ መርጨቱ መዘገባችን ይታወሳል።