የጠ/ሚ መለስ ዜናዊ ሥርዓተ ቀብር በቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ተፈፀመ
ነሐሴ 27ቀን 2004 ዓ.ም
በመ/ር ዘሩ ብርሃኔ
የጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ የቀብር ስነስርዓት በቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ነሐሴ 27 ቀን 2004 ዓ.ም ከቀኑ 10 ሰዓት ተፈጽሟል፡፡
የጠቅላይ ሚኒስትሩን የቀብር ስነ ስርዓት በተመለከተ ከንጋቱ 11 ሰዓት በታለቁ ቤተ መንግስት ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት፣ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት፣የአዲስ አበባ ሃገረ ስብከት ስራአስከያጅ፣6 የአድባራትና ገዳማት አስተዳዳሪዎችና የመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ካህናት ጋር በህብረት ሙሉ ፀሎተ ፍትሐት አድርሰዋል በአጠቃላይ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤ/ክ ከ15/2004 ዓ.ም መሐራ እግዚኦ ለነፍሰ መራሔ መንግሥትን ገ/ማርያም፤ አቤቱ የመራሔ መንግሥታችን የገብረ ማርያምን ነፍስ ማር” በማለት ጸሎትዋን አድርሳለች በማድረስ ላይም ትገኛለች፡፡በተለይም በ26/2004 ለ27 አጥቢያ በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ከ600 በላይ የሚሆኑ የአዲስ አበባ ካህናትና መዘምራን በህብረት ከምሽቱ 2 ሰዓት ጀምሮ ሙሉ ሌሊቱን ፀሎተ ፍትሐት ሲያደርሱ አድረዋል፡፡
በታላቁ ቤተ መንግስት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ፣ የህዝብ ተወካዮች ም/ቤት አፈ ጉባኤ አባዱላ ገመዳ፣ የክልል ርዕሰ መስተዳድሮች፣ ሚኒስትሮች፣ ከፍተኛ ባለስልጣናት፣ አምባሳደሮች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የመከላከያና የፖሊስ አባላት፣ ቤተሰቦቻቸውን ጨምሮ በርካታ ሰዎች ተገኝተዋል፡፡
በመስቀል አደባባይም ከ25 በላይ የሀገራት መሪዎችና ርዕሳነ ብሔራት እንዲሁም በርካታ የአህጉራዊና አለም አቀፍ ተቋማት ተወካዮች፣ የመከላከያና ፌደራል ፖሊስ ሰራዊት፣ የመንግስት ሰራተኞችና እንግዶች አስከሬኑን ለመቀበል በስፍራው ተገኝተዋል፡፡
ክብርት ባለቤታቸው ቀዳማዊት እመቤት ወ/ሮ አዜብ መስፍን እንዳሉት መለስን ከልጅነቱ ጀምሮ ነው የማወቀው፡፡ ዱሮም ጀምሮ ህልሙ የነበረው በኢትዮጵያ ፍትህ፣ ሰላምና እድገትን ማስመዝገብ ነበር፡፡ ሁሌም ያልም የነበረው ድህነትን ስለመታገል ነበር፡፡ ጊዜውን ሁሉ ይሰጥ የነበረው ህልሙን ለማሳካት ነበር፡፡ ልጆቼም የሚፈልገውን ጊዜ አልነፈጉትም፡፡ መለስ ለፍትህ፣ ለሰላምና ለፍቅር የቆመ ነበር፡፡ ይህንንም የኢትዮጵያ ህዝብ በማረጋገጡ በጣም አመሰግናለሁ ፡፡
እኔም ከኢትዮጵያ ህዝብ ጎን ሆኜ እሱ የጀመራቸውን የልማት ተግባራት ለማስቀጠል የበኩሌን አስተዋፅኦ አበረክታለሁ ብለዋል፡፡
8 ሰዓት ከ25 ደቂቃ ላይ የጠቅላይ ሚኒስትሩ አስከሬን ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል የደረሰ ሲሆን፡፡ በቅድስት ሥላሴ ካቴድራልም ለ30 ደቂቃ ያህል ደውል የተደወለ ሲሆን አስከሬኑም ከሰረገላው ወርዶ ወደተዘጋጀለት ልዩ የፀሎት ቦታ አርፏል፡፡ በካቴድራሉ ካህናትና መዘምራንም ስርዓተ ፀሎት ተካሂዷል፡፡
ከ9 ሰዓት ከ10 ደቂቃ ላይ የፀሎት ስነ ስርዓት እንደተፈፀመ አስከሬኑ ቤተ ክርስቲያኑን በቀኝ በመዞር 9 ሰዓት ከ25 ደቂቃ ላይ የጠቅላይ ሚኒስትሩ አስከሬን ወደተዘጋጀለት የቀብር ቦታ ያረፈ ሲሆን፤የጠቅላይ ሚኒስትሩ የቀብር ስነ ስርዓት መጠናቀቁን በማስመልከት 21 ግዜ መድፍ ተተኩሷል፡፡
የጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ አጭር የህይወት ታሪክ
ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ግንቦት 1 ቀን 1947 ዓ.ም ነው በትግራይ አድዋ ከተማ ከአባታቸው ከአቶ ዜናዊ አስረስ እና ከእናታቸው ወይዘሮ አለምነሽ ገብረልዑል የተወለዱት፡፡
ለቤተሰባቸው ሶስተኛ ልጅ የሆኑት አቶ መለስ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን በአድዋ ንግስተ ሳባ ትምህርት ቤት የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ደግሞ ባሳዩት ከፍተኛ የትምህርት ብልጫ ከመላው ሀገሪቱ ከተመረጡ ተማሪዎች መካከል አንዱ በመሆን በአዲስ አበባ ጄነራል ዊንጌት ትምህርት ቤት ተከታትለዋል፡፡
በ1965 የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲን በመቀላቀል ለሁለት አመታት በህክምና ፋካሊቲ ትምህርታቸውን ሲከታተሉ ቢቆዩም በወቅቱ የነበረውን ብሄራዊ ጭቆናን ለመታገል ህዝባዊ ወያነ ሃርነት ትግራይን በመቀላቀል በርሃ ገቡ፡፡
አቶ መለስ በ1967 የተመሰረተው ህወሃትን ከተቀላቀሉ አንስቶ ከታጋይነት እስከ አመራርነት ለህዝቦች እኩልነትና ለኢትዮጵያ ጉስቁልናና ድህነት መወገድ ሲታገሉና ሲያታግሉ ቆይተዋል፡፡
በህዝቦች መሪር ትግልና መስዋዕትነት ደረግ መወገዱን ተከትሎ አቶ መለሰ ዜናዊ በፕሬዚዳንትነት የመሩት የኢትዮጵያ የሽግግር መንግስት ሁሉንም የፖለቲካ ሃይሎች ያሳተፈ መንግስት ለመመስረት የላቀ አስተዋፅኦ አድርጓል፡፡
አቶ መለስ ዜናዊ የሚመሩት የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር ኢህአዴግ ኢትዮጵያ ላለፉት 21 አመታት በሰላም፣ በልማትና በዴሞክራሲ እድገት እንድትጓዝ ጠንካራ አመራር ሰጥቷል፡፡
የኢትዮጵያን ህዝቦች ነባራዊ ሁኔታና የለም አቀፉን እንቅስቃሴ ያጤኑ ጠንካራ የልማት ፖሊሲዎችና ስትራተጂዎችን በመቅረፅና ስራ ላይ በማዋል ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ የሚመሩት የኢፌዴሪ መንግስት ኢትዮጵያ በልማት እንድትጓዝ አድርጓል፡፡
የህዝቦች ኑሮ ለዘመናት ከነበረበት ጉስቁልና ተነስቶ በብሩህና በህዳሴ ጎዳና መራመድ የጀመረውም በዚሁ ወቅት ነው፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ኢትዮጵያ በአፍሪካ አጀንዳዎች ላይ የመሪነት ሚና እንድትወጣ የኢትዮጵያና የአፍሪካ ድምፅ በአለም መድረኮች እንዲያስተጋባ ያደረጉት አስተዋፅኦ የላቀ ነበር፡፡
ባለፉት 21 አመታት የተመዘገቡ ተጨባጭ የሰላም የልማትና የዲሞክራሲ ውጤቶች እንዲጠናከሩና ኢትዮጵያ ወደ ከፍታ ማማ እንድትወጣ በመላ ኢትዮጵያውያን የታየውን ፅኑ ፍላጎት እውን ለማድረግ በጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ሃሳብ አፍላቂነት ይፋ የሆነው የእድገትና የትራንስፎርሜሽን እቅድ የኢትዮጵያን ህዳሴ በማረጋገጥ ላለፉት ሁለት አመታት ስኬት አስመዝግቧል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ከትግል አጋራቸው ወይዘሮ አዜብ መስፍን ጋር በትዳር ከ25 አመታት በላይ ተጣምረዋል፡፡ በትዳራቸውም ሶስት ልጆች አፍርተዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ባደረባቸው ሕመም በውጭ አገር ሕክምና ሲከታተሉ ከቆዩ በኋላ ሰኞ ነሃሴ 14 ቀን 2004 ዓ.ም. በ57 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት መለየታቸው ይታወቃል፡፡