ለአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሠራተኞች የቁጥጥርና የሥራ አመራር ሥልጠና ተሰጠ
ለአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ጽ/ቤት እና በሥሩ ላሉ 7 ክፍላተ ከተማ ቤተ ክህነት ጽ/ቤቶች የሥራ ኃላፊዎች እና አጠቃላይ ሠራተኞች ከነሐሴ 22 -23 ቀን 2005 ዓ.ም. ለሁለት ቀናት የተዘጋጀ የአቅም ግንባታና ማሻሻያ ሥልጠና መርሐ ግብር ተሰጥቷል፡፡ አዲስ አበባ ሀገረ ስብከት በ7 ክፍላተ ከተማ ቤተ ክህነት ጽ/ቤቶች ማለትም
1. አራዳ ጉለሌ ክ/ከተማ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት
2. የካ ክ/ከተማ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት
3. ቦሌ ክ/ከተማ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት
4. ኮልፌ ቀራንዮ ክ/ከተማ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት
5. ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክ/ከተማ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት
6. ልደታ ቂርቆስ አዲስ ከ/ክፍለ ከተማ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት
7. አቃቂ ቃሊቲ ክ/ከተማ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት በሚል በአዲስ መልክ መደራጀቱንና መዋቀሩን ተከትሉ ቀደም ሲል በሐምሌ /2005 ዓ.ም መልካም አስተዳደር ለዘላቂና ሁለንተናዊ የቤተ ክርስቲያን እድገት በሚል ርዕስ ለ5 ቀናት ያህል ለሀገረ ሰብከት ሠራተኞች፣ለአዲስ አበባ ገዳማትና አድባራት አስተዳዳሪዎችና ፀሐፊዎች፣ለአዲስ አበባ ገዳማትና አድባራት የሰበካ ጉባኤ ምክትል ሊቃነ መናብርት፣ ለአዲስ አበባ ገዳማትና አድባራት የክፍል ኃላፊች፣ ለአዲስ አበባ ገዳማትና አድባራት የሰንበት ት/ቤት ተወካዮች ሙሉ ሥልጠና መስጠቱ ይታወቃል፡፡
እንደዚሁም ሀገረ ስብከቱ ከሐምሌ ወር 2005 ዓ.ም ጀምሮ ለ3 ወራት ያህል የሚገለግል ጊዚያዊ የሥራ አደረጃት በባለሞያዎች አዘጋጅቶና በቅዱስ ሲኖዶስ አፀድቆ ሥራ ላይ እንዲውል ያደረገ ሲሆን 2ኛው ሙሉ መዋቅርና አደረጃጀት ደግሞ ሥራውን ሙሉ ቡሙሉ በመጠናቀቅ ላይ የሚገኝ ሲሆን ከጥቅምት 30/2006 ዓ.ም ጀምሮ ሥራ ላይ ይውላል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን ይህም ለሀገረ ስብከቱ በታሪከ የመጀመሪያ ጊዜ ነው፡፡
ይህን ተከትሎም ለ2ኛ ጊዜ ከነሐሴ 22-23/05 ዓ.ም የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠና ተሰጥቷል በዚሁ በሥልጠና ላይ የተገኙ ባለሥልጣናትና ተሳታፊዎች 1. ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአኵስም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት 2. ብፁዕ አቡነ ማቴዎስ የጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት ዋና ሥራ አስኪያጅ፣ የወላይታ ዳውሮና ኮንታ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ 3. ብፁዕ አቡነ ሉቃስ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ፣ የሰቲት ሑመራ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ 4. ብፁዕ አቡነ እስጢፋኖስ በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የብፁዕ ወቅዱስ ፓትያርክ ረዳት ሊቀ ጳጳስ እና የጅማ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ 5. የሀገረ ሰብከቱ ዋና ሥራ አሥኪያጅ፣ የየክፍላተ ከተሞቹ ቤተ ክህነት ጽ/ቤቶች ሥራ አሥኪያጆች፣ ልዩ ልዩ የሥራ ዘርፍ ኃላፊዎች እና ሠራተኞች የሥልጠናው መርሐ ግብር በቅዱስነታቸው ጸሎትና ቡራኬ ተከፍቷል፡፡ በመቀጠል ብፁዕ አቡነ እስጢፋኖስ በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የብፁዕ ወቅዱስ ፓትያርክ ረዳት ሊቀ ጳጳስ እና የጅማ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ሥልጠናውን አስመልክቶ “ነገርን ሁሉ በጊዜው ውብ አድርጎ ሠራው” በሚል ርዕስ የመግቢያ ንግግር አድርገዋል፡፡
ብፁዕነታቸው በመግቢያ ንግግራቸው፤ ቅዱስ ሲኖዶስ ለአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ይበጃል ይሆናል ያለውን ሲወስን ቆይቶ በግንቦት 2005 ዓ.ም የርክበ ካህናት ጉባዔ በወሰነው መሠረት፤ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት በአንድ ሀገረ ስብከት እና በሰባት ክፍላተ ከተማ ቤተ ክህነት ጽ/ቤቶች ተደራጅቶ ላለፉት ሦስት ወራት የአድባራት እና የገዳማት ጥያቄዎችን በፍጥነትና በተቀላጠፈ መልኩ አገልግሎት እንዲያገኝ ብርቱ ጥረት ማድረጉን በማውሳት፤ ይህን የበለጠ ለማጠናከር በሥልጠና መታገዝ አስፈላጊ መሆኑን በመረዳት በሀገረ ስብከቱና በሥሩ ለሚገኙ የክፍለ ከተማ ቤተ ክህነት ጽ/ቤቶች ይህ የአቅም ግንባታ ሥልጠና መዘጋጀቱን ገልጸዋል፡፡ በመቀጠል ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት የሥልጠናውን መጀመር በይፋ አብሥረው ባስተላለፉት ቃለ ምዕዳን እና የሥራ መመሪያ በቤተ ክርስቲያን ከላይ እስከ ታች ባለው የሥራ ኃላፊነት ላይም ሆነ በተለያየ የሥራ ዘርፍ የምንገኝ አጠቃላይ ሠራተኞች /አገልጋዮች/ ሁሉ እስከ አሁን ድረስ የቤተ ክርስቲያናችንን ስም ያስጠፋውንና መልካም ስማችንን እያጎደፈ ባለው የመልካም አስተዳደር እጦት፣ የሥነ ምግባር ጉድለት፣ ዘረኝነትና የጎጠኝነት መንፈስ ከሥር መሠረቱ ነቅለን በማስወገድ ሁላችንም ታማኞች ሆነን ግልጽነትና ተጠያቂነት ያለው፣ ዘመኑን የዋጀ አሠራርን መከተል እንደሚገባን ከገለጹ በኋላ የተቀመጥንበት ወንበር ትልቅ ኃላፊነት ያለበት በመሆኑ በሥራችን ቸልተኛ መሆን የለብንም ብለዋል፡፡
ቅዱስነታቸው አያይዘውም ለአዲሱ አደረጃጀት የለውጥ ሐዋርያነት ግንባር ቀደም ሆነን የቤተ ክርስቲያኒቱን ታሪካዊነት፣ ጥንታዊነትና ሉዐላዊነት አስከብረን የቀደመ ስሟን አስመልሰን ሀብቷንና ንብረቷን በሕጋዊ አሠራር ተቆጣጥረን በአግባቡ በሥራ ላይ ለማዋል ይቻል ዘንድ በየደረጃው ያለን ሁላችንም አገልጋዮች የለውጥ ሰው ለመሆን፣ ለውጡን አምኖ ለመቀበል ሥልጠና በእጅጉ አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በዋናነት ይህን ዓላማ ከማስተግበር አንጻርም የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ለለውጡ አመራር ራሳቸውን በማስቀደም ከዚህ በፊትም ለመላው የአዲስ አበባ ገዳማትና አድባራት ሠራተኞች ሥልጠና እንዲሰጥ ማድረጋቸውን አስታውሰው፤ የዛሬውም ከዚያ ጋር ተያያዥነት ያለው ሆኖ በሀገረ ስብከቱ ጽ/ቤት እና ለተመደቡት አገልጋዮች በየደረጃቸው የተዘጋጀ ሥልጠና በመሆኑ ተሳታፊዎችም በሥልጠናው ንቁ ተሳትፎ ማድረግ እንደሚገባቸው አስምረውበታል፡፡
ቅዱስነታቸው በቃለ ምዕዳናቸው ብጹዕ ረዳት ሊቀ ጳጳሱም ሆኑ ከክቡር ሥራ አስኪያጁ ጀምሮ በአጠቃላይ የሀገረ ስብከቱ ጽ/ቤት ሠራተኞች እስከ አሁን ላደረጉት የሥራ እንቅስቃሴ እና ላዘጋጁት የሥልጠና መርሐ ግብር ከፍተኛ ምሥጋና አቅርበው፤ ወደ ፊትም እንዲህ ዓይነቱ መርሐ ግብር ተጠናክሮ እንዲቀጥል ከአደራ ጭምር ለሥልጠናው ተሳታፊ አባታዊ መመሪያ ሰጥተዋል፡፡ የዕለቱ መርሐ ግብር መሪ ክቡር ዋና ሥራ አስኪያጁ መጋቤ ሀዲስ ይልማ ቸርነት የሁለቱን ቀን መርሐ ግብር አስተዋውቀው ወደ ሥልጠና ተገብቷል፡፡ የሥልጠና ርዕሶችም “የለውጥ ሥራ አመራር ሥልጠና፣ የኦዲትና ኢንስቴክሽን /ክትትልና ቁጥጥር/ ሥርዓትና ሥልጠና እንዲሁም የሒሳብ አያያዝ ሥልጠና” በሚሉ አርዕስት ሲሆን፤ ሥልጠናውም የጉባዔውን በውይይት ባሳተፈ መልኩ የሚከተሉት ነጥቦችን ዳስሷል፡-
- ለውጥ በማንኛውም ተቋም ሊኖር የሚችል ክስተት መሆኑን
- በለውጥ ሂደት እንቅፋቶች ለኖሩ እንደሚችሉ
- ለውጥ ለአንድ ተቋም ስኬት እንደ አንድ መልካም አጋጣሚ የሚታይ መሆኑን እና ሌሎችም ነጥቦች በአቶ ታደሰ አሰፋ እና በአቶ ካሳ አወቀ
- አንድ ኦዲተር ሊኖረው ስለሚገባ ሙያዊ ክህሎት
- መሠረታዊ የኦዲትና ኢንስቴክሽን መርሆች
- ስለ ኦዲት እና ኢንስፔክሽን ዓይነቶች እና የኦዲት ባለሙያ ስለሚያቀርበው የሪፖርት ቅርጽ በዲ/ን ንጋቱ ባልቻ እና ዲ/ን ተመስገን ወርቁ
- ስለ መሠረታዊ የሂሳብ አሠራር መቅላላ ሂሳብ ሥራ መነሻ እና መድረሻ አስመልክቶ በአቶ ሞሐባ በስፋትና በጥልቀት በታዘዘላቸው ሰዓት ጊዜ ሰጥ በተሳታፊዎች የቡድን ውይይት እንዲሁም በጥያቄና መልስ ንቁ ተሳትፎ በማድግ ሥልጠናው እንዲሰርጽ አድርገዋል፡፡
- ከሥልጠናው የሚገኝ ግብዓት በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ከዋና ጽ/ቤቱ ጀምሮ እስከ አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት አድባራትና ገዳማት ያለውን የመልካም አስተዳደር እጦት፣ የገንዘብ እና የንብረት ብክነት፣ ያለማቋረጥ የሚታየውን የሰዎች አቤቱታ በአፋጣኝ ምላሽ ለመስጠት እየተደረገ ያለው የመዋቅር ማስተካከያና ተከታታይ ሥልጠና ይበል የሚያሰኝ መልካም ጅምር ነው፡፡ ለተግባራዊነቱም በቅድሚያ በሀገረ ስብከቱና በየክፍላተ ከተሞች የምንገኝ ኃላፊዎችና ሠራተኞች በቁርጠኝነት በመነሣት፤ የነበረውን የተሳሳተ አመለካከት በፍጥነት ለመቅረፍ በእጅጉ ይረዳል ተብሎ ይታመናል፡፡ ለተግባራዊነቱም የሥልጠናው ተሳታፊዎች አዎንታዊ ምላሽ በመስጠት በተደረገው ውይይት አረጋግጠዋል፡፡ ተሳታፊውም ይህን ዓይነቱ ሥልጠና በሥራው ላይ ያለው አዎንታዊ ተጽእኖ መልካም ስለሆነ ወደ ፊትም እንዲቀጥል እየገለጸ የሚከተለውን የጋራ አቋም መግለጫ አውጥቷል፡፡
የአቋም መግለጫ
1. እኛ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት እና የክፍለ ከተማ ጽ/ቤት ሠራተኞች ሀገረ ስብከቱ የጀመረውን የለውጥ ሥራ አመራር ሂደት ሙሉ በሙሉ በመደገፍ አዲሱን አደረጃጀት ለመተግበር ቃል እንገባለን፡፡
2. እኛ የዚህ ሥልጠና ተሳታፊዎች ለዚህ የለውጥ እንቅፋት የሚሆኑ ማንኛውም አካላትን በጽኑ በመቃወም እና በመታገል ለመልካም አሠራር ሂደት አፈጻጸም እንተጋለን፡፡
3. የክትትልና ቁጥጥር ሥራ ለአንድ ተቋም ያለው ፋይዳ ከፍተኛ መሆኑን ተረድተን ሕግን የተከተለ የቁጥጥርና የክትትል ሥራ እንዲተገበር እንተጋለን፡፡
4. በቤተ ክርስቲያናችን ዘመናዊ የፋይናንስ ሥርዓት እንዲተገበር የበኩላችንን ሥራ እሰራለን፡፡
5. በቤተ ክርስቲያናችን ግልጽነትና ተጠያቂነት ያለው አሠራር እንዲሰፍን ባለንበት የሥራ ኃላፊነት ላይ ጠንክረን በመሥራት የቤተ ክርስቲያናችንን ክብር እናስጠብቃለን፡፡
6. በሀገረ ስብከቱና በክፍላተ ከተማ መልካም አስተዳደር እንዲሰፍን ያለመሰልቸት እንሠራለን፡፡
7. የቤተ ክርስቲያናችንን ክብርና ስም የሚያጎድፍ ብልሹ አሠራር አስወግደን በዓለም ዓቀፍ ደረጃ ያላትን ጥንታዊነት፣ ታሪካዊነትና ሐዋርያዊነት ለማስጠበቅ ከመቼውም ጊዜ በላቀ ሁኔታ በታማኝነት ለማገልገል ቃል እንገባለን፡፡
8. ጊዜው በሚጠይቀው መሠረት የሥራ አመራር ለውጥ ለቤተ ክርስቲያችን ተልዕኮ መሳካት የሚሰጠውን ጥቅም በመረዳት ጠንክረን እንሠራለን፡፡
9. የኦዲትና ኢንስፔክሽን አገልግሎት ከማንኛውም አስተዳደራዊ ተጽዕኖ ነጻ ሆኖ ሙያዊ ተግባሩን እንዲያከናውን እንደግፋለን፡፡
10. በሂሳብ አያያዝ ሥራ በኩል ያለውን ክፍተት በማረም በተሰጠን ሥልጠና መሠረት ዘመኑ በሚጠይቀው የፋይናንስ ሥርዓት ለማስተካከል እና ለመሥራት ጥረት እንናደርጋለን፡፡
ማጠቃለያ በተለይ ብፁዕ አቡነ እስጢፋኖስ በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የብፁዕ ወቅዱስ ፓትያርክ ረዳት ሊቀ ጳጳስ እና የጅማ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ሥልጠናው ከተጀመረበት ደቂቃና ሰዓት ጀምሮ በቦታው ከተሳታፊዎች ቀድመው በመገኘት ለሁሉም ሠራተኞች የአባትነት አርአያነታቸውን ያሳዩን በመሆናቸው እጅግ ምሥጋናችን የላቀ ነው፡፡
እኛም የሀገረ ስብከትና የክፍለ ከተማ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት ሠራተኞች የብፁዕነታቸውን ፈለግ በመከተል በየተመደብንበት የሥራና የአገልግሎት ክፍል በርትተን ለመሥራት ከብፁዕነታቸው በተግባር የተተረጎመ ትልቅ የሥራ መመሪያ አግኝተናል፡፡
ብፁዕ አባታችን! እኛ ልጆችዎት ሌሊት ከቀን እየደከሙበት ያለውን የሥራ አመራር ለውጥ እና መዋቅር ተግባራዊ እንዲሆን ከልብ እንሠራለን፡፡
“አንትሙ ውእቱ ብርሃኑ ለዓለም ከማሁኬ ይብራህ ብርሃንክሙ በቅድመ ሰብእ ከመ ይርአዩ ምግባሪክሙ ሰናየ ወይሰብህዎ ለአቡክሙ ዘበሰማያት፤
የዓለም ብርሃን እናንተ ናችሁ እንዲሁ ብርሃናችሁ በሰው ፊት ይብራ በጎ ሥራችሁን አይተው በሰማያት ያለውን አባታችሁን ያመሰግኑ ዘንድ” ማቴ. 5፡12
እኵት እግዚአብሔር አምላከ አበዊነ ዘዘልፈ የአቅበነ ዘአውትሮ የሚጠብቀን የአባቶቻችን አምላክ ይመስገን አሜን!!
ነሐሴ 23 ቀን 2003 ዓ.ም አዲስ አበባ
በመጨረሻም ለአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ጽ/ቤት እና በሥሩ ለሉ 7 ክፍላተ ከተማ ቤተ ክህነት የሥራ ኃላፊዎች እና ሠራተኞች ሥልጠና ተሰጠ በመዝጊያ ፕሮግራሙ ላይ የተገኙት ብፁዕ አቡነ ሉቃስ የቅዱስ ሲኖዶስ ፀሐፊ ንግግር ያደረጉ ሲሆን ሥልጠናው ወደ ቀደመው ታሪካችን የሚወስድ ታሪካዊ ጉባኤ ነው ብለውታል የመጀመሪያ መሪ አባት በመሆንዎ ደስ ሊሎት ይገባል በማለት ብፁዕ አቡነ እስጢፋኖስ በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የብፁዕ ወቅዱስ ፓትያርክ ረዳት ሊቀ ጳጳስ እና የጅማ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስን አመስግነዋቸዋል፡፡
የሐዋሪያት ቁልፍ የተረከብነው እኛ በመሆናችን ታሪካችን በአግባቡ ልንጠብቅ ይገባል ብለዋል፡፡ በመቀጠል ብፁዕ አቡነ እስጢፋኖስ የመጨረሻ የመዝጊያ ንግግር እንዲያደረጉ፤ቃለ ምዕዳንና መመሪያ እንዲሰጡ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአኵስም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት የጋበዙ ሲሆን ቅዱስነታቸውም ቅዱስ ዮሐንስ አባጣ ጎርባጣውን አቅኑ እንዳለው ሁሉ እናንተም ይህን ልታቀኑ ይገባችኋል ብለዋል፡፡
ችግር ወጥቶ ካልተነገረ መፍትሔ አይመጣም እኛ ለመደበቅ ብንሞክርም ሊሆን አይችልም እናንተም በዚሁ ቆይታችሁ ብዙ እንደተወያያችሁ ይገባኛል፡፡አባቶቻችን በየዘመናቱ በሚችሉት ሲጠቀሙ ቆይተው አሁን ያለንበት ዘመን ላይ ደርሰናል ዘመኑም የኮምፒውተር እና የቴክኖሎጂ ዘመን በመሆኑ እኛም ዓለም እየተጠቀመበት ያለውን ቴክኖሎጂ በአግባቡ ልንጠቀምበት ይገባል፤ከዘመኑ ጋር ልንራመድ እና አሠራራችን ኮምፒውተራይዝድ ሊሆን ይገባል በማለት ሰፋ ያለ ንግግር እና ቃለ ምዕዳን የሰጡ ሲሆን በመጨረሻም ለ2 ቀን ሲካሄ የቆየውን ጉባኤው በፀሎት ዘግተዋል፡፡
ለተጨማሪ ንባብ እዚህ ላይ ይጫኑ (‹‹የለውጥ ሥራ አመራር ሥልጠና››)
ለተጨማሪ ንባብ እዚህ ላይ ይጫኑ (‹‹የኦዲት እና ኢንስፔክሽን አገልግሎት››)
{flike}{plusone}