ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት የ2006 ዓ.ም የልደት በዓልን አስመልክተው መልእክት አስተላለፉ

0908

ቃለ በረከት ዘብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳስት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት በእንተ ልደቱ ለእግዚእነ ወአምላክነ ወመድኃኒነ ኢየሱስ ክርስቶስ
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን
–    በሀገራችን በኢትዮጵያ በገጠርና በከተማ የምትኖሩ፣
–    ከሀገር ውጭ በተለያዩ አህጉር የምትኖሩ፣
–    የሀገራችንን ዳር ድንበር ለመጠበቅና ለማስከበር በየጠረፉ የቆማችሁ፣
–    በሕመም ምክንያት በየሆስፒታሉ ያላችሁ፣
–    እንዲሁም የህግ ታራሚዎች ሆናችሁ በየማረሚያ ቤቱ የምትገኙ ኢትዮጵያውያት በሙሉ፣
 ወልድ ተብሎ ውሉድ እንድንባል ላበቃን ለጌታችን ለአምላካችንና ለመድኃኒታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ በዓለ ልደት እንኳን በሰላም አደረሳችሁ!!
“ወናሁ ትፀንሲ ወትወልዲ ወልደ ወትሰምዩዮ ስሞ ኢየሱስ ዘውእቱ ያድኅኖሙ ለሕዝቡ እምኃፂአቶሙ፤ እነሆ ትፀንሻለሽ ወንድ ልጅንም ትወልጃለሽ፣ ሕዝቡን ከኃጢአታቸው ያድናቸዋልና”፣ ስሙንም ኢየሱስ ትይዋለሽ” (ሉቃ 1፡31፣ ማቴ. 1፡21)፡፡
ሁላችንም እንደምናውቀው ዘላለማዊና ቀዳማዊ የሆነ የእግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ፣ ሰው ሆኖ እንዲወለድ ምክንያት የሆነው፣ የሰው ኃጢአት ነው፡፡
    ሰው በኃጢአት ምክንያት ከእግዚአብሔር ተለይቶ ክብሩን ካጣ በኋላ፣ በነፍሱም ሆነ በሥጋው፣ ለአጠቃላይ ውድቀት ተዳረገ፤ ንፁሕ የነበረ ባህርዩ እንደ ሰኔና እንደ ሐምሌ ጎርፍ ደፈረሰ፤ የኃጢአት ድፍርሱም እየባሰና እየከፋ ከመሄድ በቀር፣ መሻሻል አላሳየም፣ ይሁንና የክብር አምላክ የሆነ እግዚአብሔር አምላካችን፣ ለክብር በክብር የፈጠረውን የሰው ልጅ፣ እንደ ወደቀ ሊቀር አልፈለገምና፣ የመዳኛ ዘዴ አበጀለት፡፡
አምላካችን እግዚአብሔር፣ ሰውን የማዳን ሥራው፡-
መቼ?በማን?የት?እንዴት እንደሚከናወን፣ አምስት ሺህ አምስት መቶ ዘመን ሙሉ በትንቢት፣ በምሳሌ፣ በራዕይና በቀመረ ሱባኤ፣ በቅዱሳን ነቢያቱ አማካኝነት፣ ለዓለም ሲገለጽ ቆየ፡፡
    በእርሱ የተያዘው ቀጠሮ ሲደርስ፣ በፊቱ የሚቆመውን መልአኩ ቅዱስ ገብርኤልን፣ ወደ ድንግል ማርያም ላከ፡፡ ቅዱስ ገብርኤልም ከእግዚአብሔር ንገር ተብሎ የተላከበትን መልእክት ይዞ፣ ወደ ድንግል ማርያም መጣ፤ እንዲህም አላት “እነሆ ትፀንሻለሽ፣ ወንድ ልጅንም ትወልጃለሽ፤ ሕዝቡን ከኃጢአታቸው ያድናቸዋልና፤ ስሙንም ኢየሱስ ትይዋለሽ፤ እርሱ የልዑል እግዚአብሔር ልጅ ይባላል፤ አላት”  ከዚህ አገላለጽ በመነሣት፣ ፍሬ ነገሩን ስናስተውል፤ ከቅድስት ድንግል ማርያም የሚወለደው ህጻን፡- ዕሩቅ ብእሲ (ተራ ሰው) ሳይሆን የእግዚአብሔር ልጅ እግዚአብሔር መሆኑን፣ የስሙ ትርጓሜም መድኃኒት ማለት መሆኑን፣ መድኃኒትነቱም ለሕዝቡ ሁሉ መሆኑን፣ ሕዝቡን የሚያድናቸውም ከኃጢአታቸው መሆኑን፣ በማያሻማ ሁኔታ ማወቅ ይቻላል፡፡
                             የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቼ ምእመናንና ምእመናት
የጌታችን መድኃኒትነት ድንበር የለሽና፣ በሁሉም በሽታዎች ላይ የሚሠራ ቢሆንም፣ በዋናነት ግን በትልቁ የኃጢአት በሽታ ላይ ያነጣጠረ መድኃኒት መሆኑን፣ በተጠቀሰው ኃይለ ቃል መረዳት ይቻላል፡፡ ምክንያቱም በዓለም ላይ የሚታየውን ክፉ በሽታ ሁሉ፣ ሰበብ በመሆን ጎትቶ ያመጣብን ይህ ኃጢአት ነውና፤ ጌታችን በዋናነት እርሱን ለመደምሰስ መምጣቱን ለማሳየት፣ ከኃጢአታቸው ያድናቸዋል ተብሎ በግልጽ ተለይቶ ተነገረ፤ በሽታው ትልቅ መሆኑን የምንረዳውም፣ ትልቅ ዋጋ ያለው መድኃኒት፤ ያውም የእግዚአብሔር ልጅን ያህል፤ ለመሥዋዕትነት ያስፈልገው በመሆኑ ነው፡፡
    ለመሆኑ የኃጢአት በሽታ የሚያስከትለው ጉዳት ምንድን ነው ? ያልን እንደሆነ፤ ሰውን ከእግዚአብሔር በማራቅና እግዚአብሔርን በማሳጣት፣ ሰውን ማዋረድ፣ ማጎሳቆልና መግደል ነው፡፡ ሰው እግዚአብሔርን ካጣ፣ ሁሉንም ያጣል፣ አዳም አባታችንና ሔዋን እናታችን ያጡትም ይህንን ታላቅ ሀብት ነበር፤ እግዚአብሔርን ሲያጡ፤ ሁሉንም አጡ፣ ኃጢአተኛ ማለት ያጣ፣ የነጣ ማለት ነው፤ ምንን ያጣ? እግዚአብሔርንና የእግዚአብሔር የሆነውን ሁሉ ያጣ ማለት ነው፤
ሰው ከእግዚአብሔር ከተለየ፡-  ሕይወት የለም፣ ሰላምም የለም፣ ክብርም የለም፣
በአጠቃላይ መልካም የሆነ ነገር ሁሉ የለም፣ ሊኖር የሚችለው ተቃራኒው ነው፤ እርሱም፡-
    ሞት፣ በሽታ፣ ድህነት፣ ጠብ፣ መለያየት፣ ውርደት የመሳሰለው ክፉ ነገር ሁሉ ነው ሊኖር የሚችለው፤
ከዚህ አንጻር ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፣ ሕዝቡን ከኃጢአታቸው ያድናቸዋል ሲባል፣ በዋነኛነት እግዚአብሔርንና የእግዚአብሔር የሆነውን ሁሉ ከማጣት ያድናቸዋል ማለት ነው፤
    ይህንም በራሱ መሥዋዕትነት፣ ሰውን ከእግዚአብሔር ጋር ስላስታረቀና ስላገናኘ፣ ድኅነታችንን በዚህ አረጋግጦልናል፤ ፈጽሞልናልም፤ (1 ቆሮ. 5፡19)፡፡
ዛሬ፣ እግዚአብሔርንና የእርሱ የሆነውን የምናጣበት የኃጢአት በሽታ፣ በጌታችን ተወግዷል፡፡
አሁን በፊታችን ቆሞ እየጠበቀን ያለው ኃጢአት ሳይሆን፣ በኢየሱስ ክርስቶስ የተገኘው ጽድቅ ነው፤
ጽድቁን ተከትሎ ደግሞ፣ እግዚአብሔርና የእርሱ የሆነው መልካመ ነገር ሁሉ ማለትም መንግሥተ ሰማያት፣ ዘላለማዊ ሕይወትና ዘላለማዊ ክብር፣ በፊታችን ቆመው እየጠበቁን ነው፤
እነኝህም፣ ጌታችን ዳግመኛ ወደዚህ ዓለም ሲመጣ፣ እውን የሚሆኑ ናቸው (1 ጴጥ. 1፡5-7)
                                      የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቼ ምእመናንና ምእመናት!!
ዛሬ፣ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስን በዓለ ልደት በታላቅ ድምቀት የምናከብርበት ዋናው ምክንያት፣ በኃጢአታችን ምክንያት ያጣናቸውን እግዚአብሔርና የእርሱ ሀብታት ሁሉ፣ በእርሱ ፍጹም ምሕረትና ፍቅር፣ እንደገና ያገኘናቸው መሆናችን፣ በቤተልሔም በግልጽ የታየበት ዕለት ስለሆነ ነው፡፡
የጌታችን፣ ሥጋችንን ተዋሕዶ መገለጥ፣ የመላእክት የደስታ ዝማሬ፣ የእረኞችና የሰብአ ሰገል ተአምራዊ ጉዞ፣ የኅብረታችን መመለስን ይገልጻሉ፡፡
የእኛ አካል ሥጋና፣ የእርሱ አካለ መለኮት፣ በተዋህዶ አንድ አካል ሆኖ በቤተልሔም መወለዱ፣ ሰው አጥቶት የነበረውን የእግዚአብሔር ኅብረት ማግኘቱ ብቻ ሳይሆን፣ በአካል ቃል ርስትነት፣ አምላክ ለመሆን በመብቃቱ የኃጢአት ግንብ መደርመሱ እርግጥ ሆነ፣ የተፈለገው ትልቅና ወሳኝ መድኃኒትም ይሄ ነው፤ እግዚአብሔር ይህን ያህል ከወደደን፣ ማለትም ከመለኮት ጋር ለመዋሀድና፣ የመለኮት የሆነውን ሁሉ ባለቤት ለመሆን ካበቃን፣ ይህን ላደረገልን አምላክ ምን ውለታ መክፈል እንችላለን?
እርግጥ ነው ለአምላክ የሚሆን ውለታ ላይገኝ ይችላል፤ ነገር ግን፣ ለእርሱ ያለንን ፍቅር ለመግለጽ የሚያስችለን ተጨባጭ የሆነ ግብረ መልስ መስጠት፣ ከሁላችን ይጠበቃል፤ ይህ ለሰው ሁሉ የሚቻል ነው፡፡
እርሱ፣ ሥጋችንን ከአፈር አንስቶ፣ በተዋሕዶ የራሱ አካል እንዳደረገው፣ እኛም በድህነትና፣ በስደት ምክንያት በሰው ሀገር አሰቃቂ የሆነ እንግልት እየደረሰባቸው የሚገኙ ወጣት ልጆቻችን፣ አካላችን ናቸውና፣ ደግፈን በሁለት እግራቸው እንዲቆሙ ማድረግ ይጠበቅብናል፡፡
ከዚህ አኳያ መንግሥት ከፍ ያለ ገንዘብ በመመደብና አስፈላጊውን የዲፕሎማሲ ሥራ በመሥራት፣ በሰው ሀገር ለከፍተኛ ጉዳት ተጋልጠው የነበሩትን ዜጎች፣ በፍጥነት ወደ ሀገር እንዲመለሱ ያደረገው ተግባር፣ ቤተክርስቲያናችን በከፍተኛ አድናቆት ትመለከተዋለች፡፡
ለወደፊትም እንደዚህ የመሰለውን ወገንን የመታደግ ሥራ ለማከናወን መንግሥት በሚንቀሳቀስበት ሁሉ፣ ቤተክርስቲያናችን የበኩሏን ከማድረግ ወደኋላ እንደማትል በዚህ አጋጣሚ ታረጋግጣለች፡፡
ወጣት ልጆቻችንም፣ ተሰዳችሁ ዋስትና የሌለውን የባዕድ ሀገር ሀብት ከመቋመጥ ይልቅ፣ በሃይማኖታችሁና በሀገራችሁ ሆናችሁ፣ ሥራን ሳትንቁና ሳታማርጡ ሌት ከቀን ጠንክራችሁ ሥሩ፣ ጊዜያችሁን በሥራ ብቻ በማዋል አስተማማኝ ሀብት ማምጣት እንደምትችሉ አምናችሁ፣ ሀገራችሁን አልሙ፣ በሀገራችሁ ክብራችሁን ተደላድላችሁ፣ በክብር የምትኖሩበትን አስተሳሰብ መከተል፣ ቀዳሚ ምርጫችሁ ይሁን፤ እንደዚህ ያለውን ችግር ሁሉ በማስወገድ፣ ዘላቂና መሰረታዊ የሆነ መፍትሔ በሀገራችን ላይ ለማምጣት፡-
   በመንፈስ፣ በኢኮኖሞና በማህበራዊ አገልግሎት ያደገችና የበለፀገች ሀገር እውን ለማድረግ በሚደረገው ርብርቦሽ፣ ሁላችንም በመተባበርና በቀጥታ በመሳተፍ፣ የድህነት ቅነሳ መርሐ ግብሩን፣ በተፋጠነ ሁኔታ ማሳካት ይኖርብናል፡፡
በተለይም በዚህ የደስታና የኅብረት በዓል፣ የእግዚአብሔር ልጆችና ፍጡራን የሆኑ ወገኖቻችን፣ ምግበ ሥጋ እየሸተታቸው፣ በምግብ እጦት ምክንያት ጾም እንዳይውሉና፣ እግዚአብሔር እንዳያዝንብን፣ ከኛ ጋር በማዕዳችን እንዲከፈሉ ማድረግ አለብን፡፡
ለእግዚአብሔር ፍቅር የምንሰጠው ግብረ መልስ ይኸው ነው፤ እግዚአብሔርና ሕዝብ፣ ሕዝብና ሕዝብ፣ አንድ ላይ አገናኝቶ ለሠመረ ሀገራዊ ውጤት የሚያበቃንም እንደዚህ ያለ መተዛዘንና መደጋገፍ፣ መቻቻልና መስማማት፣ መተሳሰብና መከባበር ሲኖር እንደሆነ መዘንጋት የለብንም፡፡
በመሆኑም ሕዝበ ክርስቲያኑ በዓሉን ከተቸገሩ ወገኖቹ ጋር በአንድ ማዕድ እንዲያከብር፣ መልእክታችንን በእግዚአብሔር ስም እናስተላልፋለን፡፡
መልካም የልደት በዓል ያድርግልን፣
እግዚአብሔር ሁላችንንም ይባርከን ይቀድሰን!!
አሜን
አባ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተ/ሃይማኖት
               ታህሳሰስ 29 ቀን 2006 ዓ.ም
                 አዲስ አበባ
                 ኢትዮጵያ

{flike}{plusone}