በኢ/ ኦ/ተ/ቤ/ ክ/የመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል
  • ቀዳሚ ገጽ
  • መ/ጸ/ቅ/ሥ/ካቴድራል
    • የአስተዳዳሪው መልእክት
    • ታሪክ
    • አስተዳደራዊ መዋቅር
    • የልማት እንቅስቃሴዎች
    • መንፈሳዊ አገልግሎቶች
    • ፎቶዎች
  • ቤተ መዘክር
    • የቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ቤተ መዘክር
    • ፎቶዎች
  • ት/ ቤት
    • መግቢያ
    • መሰናዶ እና 2ኛ ደረጃ
    • 2ኛ ደረጃ ት/ቤት ወርሐዊ ክፍያ
    • 1ኛ ድረጃ ት/ቤት ወርሐዊ ክፍያ
    • ፎቶዎች
  • ሰንበት ት/ቤት
    • መግቢያ
    • አውደ ወራዙት
    • ፎቶዎች
  • አገልግሎቶች
    • መግቢያ
    • ፎቶዎች
  • ስብከተ ወንጌል
    • መግቢያ
    • ታሪክ
    • ፎቶዎች
  • Menu Menu

“ሰሙነ ሕማማት”

April 24, 2016

“ነሥአ ደዌነ መጾረ ሕማመነ በእውነት ደዌያችንን ተቀበለ፣ ሕማማችንን ተሸከመ፣ ስለመተላለፋችን ቆሰለ፣ በእርሱም ቍስል እኛ ተፈወስን” (ኢሳ. 53÷4-6) በማለት ነቢዩ ኢሳይያስ የተነበየው ትንቢት ይፈጸም ዘንድ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እኛን ከፍዳና ከዘለዓለማዊ ሞት ለማዳንና ከዲያብሎስም ቁራኝነት ነፃ ለመውጣት ሲል 13ቱን ሕማማተ መስቀልና ሌሎቹንም ጸዋትወ መከራዎች የተቀበለበት ሳምንት “ሰሙነ ሕማማት” በመባል ይታወቃል፡፡ ትርጓሜውም የመከራ ሳምንት ማለት ነው፡፡
ከፋሲካ በፊት በጸሎትና በጾም፣ በብዙ ስግደት የክርስቶስ አዳኝነትና ቤዛነት የሚታሰብበት ይህ ሳምንት በልዩ ልዩ አብያተ ክርስቲያናት በተለያዩ ስሞች የሚጠራ ሲሆን እንደኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን አጠራር ግን “ሕማማት” በሚል ስያሜ ይጠራል፡፡ እስከ 4ኛው ምእተ ዓመት ድረስ ጌታችን ከጾመው 40 ጾም ጋር ሳይሆን ለብቻው ይታሰብ እንደነበረ ከቤተ ክርስቲያን ታሪክ መረዳት ይቻላል፡፡ ምክንያቱም ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በእሱ ላይ የደረሱትን ጸሞትወ መከራዎች ሁሉ በትዕግሥት ተቀብሎና በመስቀል ላይ ተሰቅሎ የሞተው 40ውን ጾም ከፈጸመ በኋላ ወዲያውኑ ሳይሆን ከሦስት ዓመታት በላይ ከአስተማረና ቤተ ክርስቲያንን ካደራጀ በኋላ ስለሆነ ነው፡፡
በ4ኛው ምእት ዓመት ግን በምሥራቅ አብያተ ክርስቲያናት ክርስቶስ ከጾመው 40 ጾም ቀጥሎ ከትንሣኤ በፊት ባለው ሳምንት “ሰሙነ ሕማማት” እንዲታሰብ ተደርጓል፡፡ በዚህም ምክንያት የጾሙ ጊዜ ከ6 ወደ 7 ሳምንታት ከፍ ብሎአል፡፡ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ግን ከ40 ጾም በፊት ባለው መጀመሪያ ሳምንት ጾመ ሕርቃል ተጨምሮ እንዲጾምና ከ40ው ጾም በኋላም “ሰሙነ ሕማማት” በጾም፣ በጸሎትና በስግደት እንዲታሰብ በመደረጉ የጾሙ ጊዜ 55 ቀናት ወይም 8 ሳምንታት ስለሆነ የነዚህ ድምር ውጤት ጾሙን ዐቢይ ጾም ሊያሰኘው ችሏል፡፡ ዐቢይ ጾም ማለትም ታላቁ ጾም ማለት ነው፡፡ የዚህ የሰሙነ ሕማማት መታሰቢያ ጾም መጨረሻው የዓቢይ ጾምም መጨረሻ ስለሆነ ጾሙ በአክፍሎት ይደመደምና ከእሁድ መንፈቀ ሌሊት ጀምሮ በዓለ ትንሣኤው ይከበራል፡፡ የምዕራብ ቤተክርስቲያን ደግሞ በኒቆዲሞስ የሰሙነ ሕማማትን መታሰቢያ ታደርግና በሆሳዕና ዕለት የትንሣኤን በዓል ታከብራለች፡፡
በሰሙነ ሕማማት መጀመሪያ በሆሣዕና ዕለት የሚፈጸሙት አስደሳች ሥርዓቶች በኋላ በ6ኛው ምእት ዓመት እንደተጀመሩ ከቤተክርስቲያን ታሪክ መረዳት ይቻላል፡፡
ለምሳሌ ያህል የዘንባባ ዝንጣፊ ባርኮ ለምእመናን ማደል፣ የዘንባባውን ዝንጣፊ በእጅ ይዞ መዘመርና በቤተክርስቲያን ዙሪያ ዑደት ማድረግ፣ በቤተክርስቲያኑ በሮችና ማዕዘኖች የዳዊት መዝሙራትን እየዘመሩ ወንጌልን ማንበብ፣ ሌሎችንም በዓሉን የሚመለከቱ ሥርዓተ ቤተክርስቲያን መፈጸም የተጀመረው በዚሁ በ6ኛው ምእት ዓመት ሲሆን ይህም አስደሳች ሥርዓት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን እስከዛሬ ድረስ እየተፈጸመ ይገኛል፤ ወደፊትም ይቀጥላል፡፡ ዘንባባ የክብርና የድል ምልክት ከመሆኑም በላይ ድርጊቱና አፈጻጸሙ ደግሞ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በድል አድራጊነት ወደ ኢየሩሳሌም በገባበት ጊዜ የተደረገለትን የክብር አቀባበል የሚያመለክት ነው፡፡
በጸሎተ ሐሙስ ዕለትም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጌታና መምህር ሲሆን በትኅትና ራሱን ዝቅ አድርጎ የደቀ መዛሙርቱን እግር ያጠበ መሆኑን ለማስታወስና ምሳሌውን ለመከተል ሲባል በፓትርያርክ፤ በሊቃነ ጳጳሳትና በሊቃነ ካህናት የካህናትንና የምእመናንን እግር የማጠብ ሥርዓትም በዚሁ በ6ኛው ምእት ዓመት ተጀምሮአል፡፡
በሰሙነ ሕማማት የተፈጸሙ ታላላቅ ድርጊቶች:-
እሁድ የሆሣዕና ዕለት፡ – ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በድል አድራጊነት ወደ ኢየሩሳሌም በገባ ጊዜ ሕፃናትና ሽማግሌዎች፣ በጠቅላላ ሕዝቡ ሁሉ ልብሳቸውን እያነጠፉና ቅጠል እየጎዘገዙ፣ በእጃቸውም የድል አድራጊነት ምልክት የሆነውን የዘንባባ ዝንጣፊ እያያዙ በዝማሬና በታላቅ ክብር ተቀብለውታል፡፡
ሰኞ፡-በቤተ መቅደሱ ውስጥና በዙሪያው ይሸጡና ይገዙ የነበሩትን ከቤተ መቅደስ ያስወጣቸው፤ የገንዘብ ለመዋጮች ገበታዎችንና የርግብ ሽያጮችን ወንበሮች ገልብጦ ሁሉንም ከቤተ መቅደሱ በጅራፍ ያባረራቸው፣ ፍሬ አልባ የሆንችውን በለስ የረገማት በዚሁ ዕለታተ ሰኑይ ነው፡፡ በበለስም አንፃር ኃጢአትን እንደረገመ ሊቃውንት ያትታሉ፡፡
ማክሰኞ፡-ሰኞ የረገማት በለስ ማክሰኞ ደርቃ ተገኝታለች፡፡ የበለሲቱ መረገምና መድረቅ ቀድሞ በአዳም በኩል የመጣውና ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲተላለፍ የኖረው ኃጢአትና መርገም በክርስቶስ ሞት መወገዱን ያመለክታል፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዚሁ በማክሰኞ ቀን ስለግብር አከፋፈል፣ ስለትንሣኤ ሙታንና የዳዊት ልጅ የሚባል ማን እንደሆነ በመግለጥ መጻሕፍትን እየጠቀሰ ከፈሪሳውያን ጋር ይከራከር የነበረው በዚሁ ማክሰኞ በሚባለው ዕለተ ሠሉስ ነው፡፡ እንዲያውም ጸሐፍትና ፈሪሳውያንን በታላቅ ተግሣጽ ገሥጾአቸዋል (ማቴ. 23÷1-39)፣ በለምፃሙ፣ በስምዖን ቤት ማርያም እንተ እፍረት ሽቶ የቀባችው፤ የአስቆርቱ ይሁዳ ጌታውን ለማስያዝ ከአይሁድ ጋር በድብቅ የተነጋገረው በዚሁ በዕለተ ማክሰኞ ነው፡፡
ረቡዕ፡-አይሁድ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንዲያዝና እንዲገደል ለማድረግ ውሳኔ የወሰኑበት እና ምክር የፈጸሙበት ቀን ነው፡፡ እንዴት እንደሚይዙት ማን እንደሚያስይዛቸውና መቼ እንደሚይዙት በዚሁ ዕለት ወስነዋል፡፡ ለክፉ ሥራቸው ተባባሪ ያደረጉትም ከአሥራ ሁለቱ ደቀ መዛሙርት መካከል የጥፋት ልጅ የሆነውን የአስቆርቱ ይሁዳን ነበር ስለዚህ ዕለተ ረቡዕ ምክር የተፈጸመበትና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተይዞ እንዲገደል ውሳኔ የተላለፈበት ቀን በመሆኑና ውሳኔውም ተግባራዊ ሆኖ ጌታችን የተሰቀለውና የሞተው በዕለተ ዓርብ በመሆኑ የክርስቶስን መከራና የሰውን ልጅ ድኅነት ለማስታወስ ሲባል ከትንሣኤው በኋላ በአሉት 50 ቀናት ካልሆነ በቀር በየሳምንቱ ረቡዕና ዓርብ ጾመ ድኅነት በሚል ስያሜ እንዲጾም ተደርጎአል፡፡
ሐሙስ፡-በዚህ ዕለት ጧት የፋሲካን በዓልና ዝግጅት እንዲያዘጋጁ ደቀ መዛሙርቱን ወደ ከተማ የላከ ሲሆን ሐሙስ ማታ ለመጨረሻ ጊዜ የፋሲካን በዓል ከደቀ መዛሙርቱ ጋር አክብሮአል፡፡ በዚሁ ዕለት የኦሪቱን ሥርዓት ለውጦ አዲስ ሥርዓተ ቁርባን ሠርቶአል (ማቴ. 26÷26-27)፡፡
በጌቴ ሴማኒ እየጸለየ ጸሎት ከችግርና ከፈተና እንደሚያድንም ለማስረዳት “ወደፈተና እንዳትገቡ ጸልዩ” በማለት ለደቀ መዛሙርቱ መመሪያና ትምህርት ሰጠ (ማቴ. 26÷40)፡፡ ይሁዳም የአይሁድን ጭፍሮች እየመራ ወደ ጌታውና መምህሩ በመቅረብ “ሰላም ለአንተ ይሁን ብሎ ጫማውን በመሳም ለጭፍሮቹ አሳልፎ የሰጠው በዚሁ በዕለተ ሐሙስ ማታ ነው፡፡ የደቀ መዛሙርቱን እግር በማጠብ” እኔ ጌታና መምህር ስሆን እግራችሁን ከአጠብኩ እናንተ ደግሞ እርስ በርሳችሁ እግራችሁን ትተጣጠቡ ዘንድ ይገባችኋል፤ እኔ ለእናንተ እንዳደረግሁ እናንተ ደግሞ እንዲሁ ታደርጉ ዘንድ ምሳሌ ሰጥቻችኋለሁ” (ዮሐ. 13÷13-15) በማለት ትኅትናን በተግባር እየተረጎመና በድርጊት እያሳየ ለቀደ መዛሙርቱ ያስተማረው በዚሁ ዕለት ነው፡፡ ይህ ቀን ጌታችን በመከራው ጊዜ በተዋሐደው ሥጋ ተገብቶ ወደ ባሕርይ አባቱ የጸለየበትና ስለጸሎትም ያስተማረበት በመሆኑ ዕለቱ ጸሎተ ሐሙስ በመባል ይታወቃል፡፡
ዐርብ፡-ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለአይሁድ ተላልፎ ከተሰጠበት ጊዜ ጀምሮ ሌሊቱን በሙሉ ከአንዱ ገዥ ወደ ሌላው ገዥ፤ ከአንዱም ሊቀ ካህናት ወደ ሌላው ሊቀ ካህናት እያመላለሱት በሐሰት ሲከሱትና ሲያስመሰክሩበት፤ ሲኮንኑትና ሲወነጅሉት አድረው ዐርብ ጧት ወደ ገዥው ወደ ጲላጦስ ዘንድ ቀርቦ ሞት የማይገባው አምላክ በግርግር፣ በተድእኖና በጩኸት ብዛት በመስቀል ላይ ተሰቅሎ እንዲሞት የተወሰነበት በመሆኑ በዚሁ በዕለተ ዓርብ በቀትር ጊዜ ስድሰት ሰዓት ሲሆን በግራና በቀኝ ሁለት ወንጀለኞች፣ ምንም ወንጀልና በደል የሌለበት ንጹሐ ባሕርይ ክርስቶስ ያላንዳች ጥፋት እንደወንጀለኛ ተቆጥሮ በወንበዴዎች መካከል በመስቀል ላይ ተሰቅሏል፡፡ ከ6 -9 ሰዓትም በመስቀል ላይ ሆኖ ብዙ ተአምራትን ሲፈጽምና ለሰው ሁሉ ትምህርት ሰጭ የሆኑ ቃላትን ሲናገር ከቆየ በኋላ በ9 ሰዓት ተጠማሁ ሲላቸው ያቀረቡለትን መራራ ሐሞትና ከርቤ ከቀመሰ በኋላ ተፈጸመ የሚለውን የመጨረሻ ቃል ተናግሮ ቅድስት ነፍሱን ከቅዱስ ሥጋው ለይቶ በራሱ ፈቃድ የመጣበትን የማዳን ሥራ ፈጽሞአል፡፡
ክርስቶስ በሰሙነ ሕማማቱና በዕለተ ስቅለቱ የተቀበላቸው ፀዋትወመከራዎች እጅግ በጣም ብዙዎች እንደሆኑ ከቅዱሳት መጻሕፍት መረዳት የሚቻል ሲሆን በተለይ በግብረ ሕማማቱና ድርሳነ ማሕየዊ በተሰኙ መጻሕፍት በዝርዝር ተገልጠው ይገኛሉ፡፡ ከነዚህም ውስጥ 13ቱ ሕማማተ መስቀል የተሰኙት ጥቂቆቹ ናቸው እነሱም ተአስሮ ድኅሪት፤ ተስሕቦ በሐብል፤ ወዲቅ ውስተ ምድር፤ ተከይዶ በእግረ አይሁድ፤ ተገፍዖ ማዕከለ ዓምድ፤ ተጸፍኦ መልታሕት፤ ተቀስፎ ዘባን፤ ተኮርዖተ ርእስ፤ አክሊለ ሶክ፤ ፀዊረ መስቀል፤ ተቀንዎ በቅንዋት፤ ተሰቅሎ በዕፅና ሰሪበ ሐሞት ናቸው፡፡
መድኃኒታችን በዕፀ መስቀል ላይ እያለ ዐርብ ከ6 እስከ 9 ሰዓት ባለው ጊዜ 7 ተአምራት ተደርገዋል፡፡
1.ፀሐይ ጨልሞአል፤
2.ጨረቃ ደም ሆኖአል፤
3.ከዋክት ረግፈዋል፤
4.አለቶች (ድንጋዮች) ተፈረካክሰዋል፤
5.መቃብራት ተከፍተዋል፤
6.ሙታን ተነሥተዋል፤
7.የቤተ መቅደሱ መጋረጃ ማንም ሳይነካው ራሱ ተቀዷል፡፡
ቅዳሜ፡-ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በአካለ ሥጋ በመቃብር ውስጥ ነበር፤ መቃብሩም በዘብ ይጠበቅ ነበር፡፡ ክርስቶስ በአካለ ሥጋ ከዐርብ 11 ሰዓት እስከ እሁድ መንፈቀ ሌሊት ድረስ በመቃብር ውስጥ የነበረ ሲሆን በአካለ ነፍስ ደግሞ ወደ ሲዖል ወርዶ ከአዳም ጀምሮ በሲዖል ውስጥ ለነበሩ ነፍሳት ነፃነትን ሰብኮላቸዋል፡፡ ከሲዖል ወጥተው ወደገነት እንዲገቡ አድርጓቸዋል፡፡ በአጠቃላይ እስከ ክርስቶስ ሞት ድረስ በፍርድ ግዞት ውስጥ ያሉትን ሁሉ በመከራውና በሞቱ ድል አጎናጽፎአቸዋል፡፡ በኃጢአት ባርነት ውስጥ የነበሩት ሁሉ ሙሉ ነፃነትን አግኝተው የእግዚአብሔርን መንግስት የመውረስ ዕድልን አግኝተዋል፡፡
                                (በሊቀ ብርሃናት ኢሳይያስ ወንድምአገኘሁ)

{flike}{plusone}

Share this entry
  • Share on Facebook
  • Share on X
  • Share on Pinterest
  • Share on LinkedIn
  • Share on Tumblr
  • Share on Vk
  • Share on Reddit
  • Share by Mail
https://eotc-htc.org/a/wp-content/uploads/logo_am2.png 0 0 tc https://eotc-htc.org/a/wp-content/uploads/logo_am2.png tc2016-04-24 14:51:022016-04-24 14:51:02“ሰሙነ ሕማማት”

መፈለጊያ

Search Search

በቅርብ የተለቀቁ

  • የአርባዕቱ እንስሳ (ኪሩቤል) የንግሥ በዓል በመካነ ሥላሴ ቅዱስ በዓለ ወልድ ቤ/ክ በድምቀት ተከበረ። 
  • ⛪️ከቅዱስ ሲኖዶስ መግለጫ የተቀነጨበ
  • የቅዱስ ሲኖዶስ መግለጫ
  • ቅዱስ ፓትርያርኩ በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል በመገኘት የካቴድራሉ እድሳት የሚገኝበት ደረጃ ጉብኝት አድርገዋል። (መስከረም 2017 ዓ.ም)
  • ከእዚህ በላይ ደስታ ምን አለ፤ እንኳን ደስ አላችሁ፤
  • “ቤተ መቅድሳችንን እናድስ ለቀጣዩም ትውልድ እናድርስ ፣ ኃላፊነታችንንም እንወጣ!” መሪ ቃል
  • ሁላችንም የኢትዮዽያ ልጆች ከከተማ እስከ ገጠር ያለን የመ/ጸ/ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ጠባቂዎች እና ደጋፊዎች ነን‼️
  • ሚያዚያ 10 ቀን 2016 ዓ.ም የመ/ጸ/ቅ/ሥላሴ ካቴድራል ህንጻ ዕድሳትን አስመልክቶ መግለጫ ተሰጠ፤
  • የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ፲፩ኛ ዓመት በዓለ ሢመተ ፕትርክና የካቲት ፳፬/፳፻፲፮ ዓ/ም በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ይከበራል።
  • የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ የጾመ ነነዌ መልዕክት

አስተያየቶች

    © Holy Trinity Cathedral | Website by atbiya.com
      Link to: በመንበረ ጸባዖት ቅ/ሥላሴ ካቴድራል የካህናት ሙያ ማሻሻያ ሥልጠና ተካሄደ Link to: በመንበረ ጸባዖት ቅ/ሥላሴ ካቴድራል የካህናት ሙያ ማሻሻያ ሥልጠና ተካሄደ በመንበረ ጸባዖት ቅ/ሥላሴ ካቴድራል የካህናት... Link to: ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ተገኝተው የጸሎተ ሐሙስን በዓል አከበሩ Link to: ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ተገኝተው የጸሎተ ሐሙስን በዓል አከበሩ ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ በመንበረ ጸባዖት ቅድስት...
      Scroll to top Scroll to top Scroll to top