የጥቅምት 2011 ዓ.ም ቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ባለ 15 ነጥቦች መግለጫ በማወጣት ተጠናቀቀ

18

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን

ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ የተሰጠ መግለጫ

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ በዓመት ሁለት ጊዜያት እንዲሆን በፍትሕ መንፈሳዊ አንቀጽ 5 ቁጥር 164 በተደነገገው መሠረት ምልዓተ ጉባኤው የመክፈቻው ሥርዓተ ጸሎት ከተፈጸመበት ከጥቅምት 11 ቀን 2011 ዓ.ም ጀምሮ እስከ ጥቅምት 21 ቀን 2011 ዓ.ም ድረስ የተለመደውን ዓመታዊ መደበኛ ስብሰባ ሲያካሒድ ሰንብቶ ማህበራዊና መንፈሳዊ ለቤተ ክርስቲያናችንና ለሀገራችን የሚበጁ ውሳኔዎችን አሳልፎአል ፡፡

በዚሁ መሠረት፤

1. ለቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ በቀረበው አጀንዳ ተራ ቁጥር አንድ ላይ በተገለፀው የጉባኤ መክፈቻ ንግግር የተመዘገበው ፍሬ ሐሳብ የበጀት ዓመቱ መመሪያ ሆኖ ያገልግል ዘንድ ምልዓተ ጉባኤው ተቀብሎታል፤

2.የብፁዓን አባቶች የሥራ ምደባና ዝውውር በማስፈለጉ ቅዱስ ሲኖዶስ ያለውን ሁኔታ ከመረመረ በኋላ ዝውውሩን አከናውኗል፤ አዲስ የሥራ ምደባም ተካሒዷል ፡፡

3. በሀገራችን ኢትዮጵያ በአንዳንድ ክልሎችና ዞኖች ተከስቶ የነበረው ሕልፈተ ሕይወት፣ የአብያተ ክርስቲያናት መቃጠልና የንብረት መውደም የዜጎች መፈናቀል ይገታ ዘንድ በመደጋገም የተላለፈው ጥያቄ በኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፑብሊክ መንግሥት በኩል ተቀባይነትን ያገኘ ቢሆንም፤ አሁንም በሀገሪቱ አንዳንድ ችግሮች እንዳሉ እየተሰማ ነው ፡፡ ስለዚህ ከየአቅጣጫው እየተሰማ ላለው ችግር አስቸኳይ መፍትሔ ተፈልጎ እንዲገታ ካልተደረገ እየሰፋና እያደገ ሊሔድ ስለሚችል መንግሥት ከአቅም በላይ እየሆነ ለሚታየው ችግር አጽንዖት ሰጥቶ አስፈላጊውን ሕጋዊ መፍትሔ እንዲገኝ በማድረግ ተገቢውን እንዲፈጸም የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ በድጋሚ ያሳስባል ፡፡

4. የዘንድሮውን የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ልዩ ታሪካዊ ጉባኤ ከሚያደርጉት መካከል፣ የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ዐራተኛ ፓትርያርክ፣ አብረዋቸው ከነበሩት አባቶች ጋር ወደ እናት ሀገራቸው ኢትዮጵያ የመመለሳቸው ጉዳይ አንዱ እንደሆነ አያጠያይቅም፤

5. ለኢትዮጵያ ምእመናን ከኤርትራ ምእመናን፤ ለኤርትራ ቤተ ክርስቲያን ከኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን፣ ለኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያንም የኤርትራ ቤተ ክርስቲያን የመፈቃቀርና የአንድነት እንዲሁም የበለጠ የክፉ ቀን ደራሽ ይኖራል ተብሎ አይገመትም ፡፡ ስለዚህ በሁሉም መንፈሳዊና ማኅበራዊ አገልግሎት ዘርፍ ተቀራርቦ እየሠሩ መረዳዳት ይቻል ዘንድ ከወዲሁ ሁኔታዎችን የሚያመቻች የጋራ ኮሚቴ እንዲቋቋም ምልዓተ ጉባኤው ተስማምቷል ፡፡

6. በቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ የጸደቀው ሠላሳ ሰባተኛው የመንበረ ፓትርያርክ አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ የጋራ መግለጫ በአፈጻጸም ዙሪያ የሚከሰት ችግር ካጋጠመው በቋሚ ሲኖዶስ እየተመረመረ ለውጤት ይበቃ ዘንድ ቅዱስ ሲኖዶስ ተስማምቶ መመሪያ አስተላልፏል፤

7. በአሁኑ ጊዜ በሀገራችን ኢትዮጵያ በአንዳንድ አካባቢዎች እየታየ ያለው የሰላም እጦት ችግር በቀላሉ የሚገታ ሆኖ ካልተገኘ ወደፊት አስቸጋሪ ሁኔታዎች ሊከሰቱ ይችላሉ የሚል ሥጋት አለ፤ ስለዚህ እንደ ቤተ ክርስቲያናችን ቀኖናዊ ሥርዓት የወንጌል ስምሪት ተዘጋጅቶ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ትምህርተ ወንጌል ተጠናክሮ እንዲሰጥ ሆኖ ከዚህም ጋር ከኅዳር 1 እስከ ኅዳር 7 ቀን 2011 ዓ.ም. ድረስ በመላው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ አብያተ ክርስቲያናት ጸሎተ ምሕላ እንዲደረግ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ መመሪያውን አስተላልፎአል፤

8. በተቀረፀው አጀንዳ መሠረት አቤቱታ የቀረበባቸውን አህጉረ ስብከቶች በተመለከተ መርምሮና አጣርቶ መፍትሔን የሰጠ ሲሆን በአንጻሩ ከቅን አስተዳደር የሚጠበቅ ድርሻ ስለሆነ አስተዳደራዊ ችግር ያጋጠማቸው አህጉረ ስብከት ተመርምረው ውጤታቸው ተፋጥኖ ይቀርብ ዘንድ ቅዱስ ሲኖዶስ መመሪያን ሰጥቷል ፡፡

9. በበጀትና ሒሳብ መምሪያ በኩል የቀረበው የዘመኑ ገቢና ወጭ ሒሳብ ሪፖርት ከተሰማ በኋላ ገቢው በትክክል እንዲመዘገብ ሆኖ፤ የወጭው አርእስት ተጠብቆ በበጀት ዓመቱ እንዲሠራበት ቅዱስ ሲኖዶስ መመሪያን ሰጥቷል፡፡

10. በጥንታዊት ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያናችን በመንፈሳዊውም ሆነ በማህበራዊው ረገድ ከፍተኛ ሥራ መሠራቱን ቅዱስ ሲኖዶስ ገምግሟል፡፡ በቀጣይም የቤተ ክርስቲያኒቱን ተልዕኮ ለማስፋት በቤተ ክርስቲያኒቱ ከላይ እስከታች የሚተገበር የቤተ ክርስቲያን ሁለንተናዊ ችግርና መሪ እቅድ ተዘጋጅቶ የቀረበ በመሆኑ ለዚሁ ተግባር በተከፈተው ጽ/ቤት ሥራው እንዲቀጥል፣ በውጭ አገር ለምትገኘውም ቤተ ክርስቲያናችን የየአገሮቹን ሕገ መንግሥት ባገናዘበ መልኩ ቃለ ዓዋዲ እንዲዘጋጅና ሁሉም አብያተ ክርስቲያናት በመዋቅራዊ አስተዳደር እንዲመራ ተወስኖአል፡፡

11. አሁን በቤተ ክርስቲያናችን ቅዱስ ሲኖዶስ መካከል የተፈጠረው አንድነት ለቀጣይ መንፈሳዊና ማህበራዊ ሥራችን መቃናት በር ከፋች በመሆኑ ከአሁን በኋላ በአገር ውስጥም ሆነ በውጭው ዓለም ያለችው ቤተ ክርስቲያን በአንዲት ቀኖናዊት ቤተ ክርስቲያን በማዕከል እንድትመራ ወስኗል፡፡

12. ከሐምሌ ወር በዋሽንግተን ዱሲ የሁለቱ ሲኖዶስ ልዑካን የስምምነቱን ሠነድ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ተቀበሎ በማጽደቅ በሠነድነት እንዲቀመጥ ወስኗል፡፡

13. በቅድስት ሀገር ኢየሩሳሌም በዴር ሡልጣን ገዳማችን ይዞታ ላይ እየታየ ያለው ችግር ከጊዜ ወደጊዜ እየጨመረ ከመሔዱ የተነሣ ችግሩ ይፈታ ዘንድ ቅዱስ ሲኖዶስ በጽሑፍም ሆነ በቃል ለሚመለከተው ሁሉ በአካል ቀርቦ ከማመልከት የተገታበት ጊዜ እንደሌለ ይታወቃል፤ ታሪካዊ እውነትን ለመሻር በማይገባ ሁኔታ የኮፕቲክ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን በሌላት ርስትና መብት የዴርሡልጣን ገዳማችን ባለቤትነታችንን ለማሳጣት ብዙ የፈጠራ ወሬዎችን በመንዛት የተሰማሩት ግብጻውያን ኮፕቲኮች ሊያውቁት የሚገባ ትልቁ ጉዳይ በማን ርስት ማን ያዝዛል? ኢትዮጵያውያን ለዘመናት ሕይወታቸውን ሳይቀር መስዋዕት በማድረግ ሃይማኖታቸውንና ጥንታዊ ታሪካቸውን ጠብቀው ለእኛ አስረክበውናል፤ እኛም ጠብቀን ለትውልዱ የማስረከብ ኃላፊነታችንን እንወጣለን፡፡ የግብጽ ኮፕቲክ ኦርቶዶክስ በይዞታችን ላይ አግባብነት የሌለው ሥራን የማደናቀፍና በታሪክም ሆነ በማንኛውም የሠነድ መረጃ የሌለው የባለቤትነት ጥያቄ በማንሳት እየተፈጠረ ያለውን አላስፈላጊ ሁከትና ብጥብጥ ማቆም አለባቸው፤ ዴርሡልጣን ትናትም ዛሬም ነገም የኢትዮጵያ ገዳም ነው፡፡ ዳሩ ግን መፍትሔውን ከማስገኘት ይልቅ እየደረሰ ያለው ተፅዕኖ እየሰፋና እየከበደ መጥቶ በአሁኑ ወቅት ገዳሙን በሚጠብቁና በሚቆጣጠሩ መነኮሳት ላይ በኮፕቲክ ቤተ ክርስቲያን አማካኝነት ያልተጠበቀ ከፍተኛ ችግር እየደረሰ ስለሆነ የችግሩን አስገዳጅነት አስመልክቶ የኢትዮጵያ መንግሥት የጉዳዩ ባለቤት እንደመሆኑ አስፈላጊውን መፍትሔ እንዲያስገኝልን እንጠይቃለን፡፡

14. የቦታቸው ታላቅነትና የታሪካቸው ስፋት ዓለም አቀፍ ዕውቅናን ባስገኘላቸው በርእሰ አድባራት ወገዳማት አክሱም ጽዮን ቤተ ክርስቲያን እየተገነባ ላለው ሙዝየምና፣ የመሰነጣጠቅ አደጋ ለሚታይበት ለቅዱስ ላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት ለጥገናና ለግንባታ አገልግሎት የሚውል ገንዘብ ተፈቅዶዋል፤

15. አንዳንድ ግለሰዎች በግልና በቡድን በመደራጀት የቤተ ክርስቲያኗ መብትና ቀኖና እየተጋፉ መሆናቸውን ከቀረበው ሪፖርት ጉባኤው ተገንዝቧል፡፡ስለዚህ መንግሥት በዚህ ተግባር ላይ የተሠማሩትን የሕግ ከለላ እንዲያደርግ እንጠይቃለን፡፡

በዚሁ መሠረት፤

1. ለርእሰ አድባራት ወገዳማት አክሱም ጽዮን ቤተ ክርስቲያን ቤተ መጻሕፍት ወመዘክር ሥራ ማከናወኛ ብር 20,000,000.00 /ሃያ ሚሊዮን ብር/

2. ለቅዱስ ላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት ማስጠገኛ ብር 20,000,000.00 /ሃያ ሚሊዮን ብር/ ከመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት ወጭ ሆኖ እንዲሰጥ ተወስኗል፤ ቅዱስ ሲኖዶስ ከዚህ በላይ በተጠቀሱትና በሌሎችም ዓበይት ጉዳዮች ላይ ለ11 ቀናት ያህል በአገር አቀፍና በዓለም አቀፍ ጉዳዮች በስፋትና በጥልቀት ሲወያይ ሰንብቶ ስብሰባውን በጸሎት አጠናቋል ፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር አሜን አባ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት አዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ ጥቅምት 21 ቀን 2011 ዓ.ም.