የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ 6ኛ ዓመት በዓለ ሢመት በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል በድምቀት ተከበረ
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ፬ኛ ፓትርያርክ፣ ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት ዋና ሥራ አስኪያጅ፣ ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ፣ ከ34 በላይ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፣ የእስልምና ዋና ሐላፊ ሸክ አህመድ፣ የቤተክህነት ሠራቶኞች፣ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን፣ በርከት ያሉ ምእመናንና እንግዶች በተገኙበት በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀጳጳስ ዘአክሱም፣ ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት በደማቅ መልኩ የ6ኛ ዓመት በዓለ ሢመት በዓል ተከብሯል። በዕለቱ የመርካቶ ቅዱስ ራጉኤል ሊቃውንት “ብፅዕት ከርስ እንተፆረተከ፣ ወብፁዓት አጥባት እንተኃጸናከ፣ ወበእንተዝ ቅዱስ ማትያስ ፓትርያርክ አብያተ ክርስቲያናት አፍቀራከ…እያሉ ያሬዳዊ ዝማሬ ሲያቀርቡ፣ የሰንበት ት/ት ቤት መዘምራንም “ ብፁዕ ወቅዱስ ማትያስ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ፣ ሊቀጳጳስ ዘአክሱም፣ ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ጸሎትከ ትኩነነ… የሚል መዝሙር አቅርበዋል።
በመቀጠልም የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት ዋና ሥራ አስኪያጅ፣በክልል ትግራይ ደቡባዊ ዞን ማይጨውና ደቡባዊ ምሥራቅ ትግራይ አህጉረ ስብከት ሊቀጳጳስ ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ በዓሉን አስመክተው ንግግር አድርገዋል። ለብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ እንኳን ለዚህች 6ኛ ዓመት በዓለ ሢመትዎ በሰላም አደረሶት በማለት፣ ከሁሉም ቀድማ የነበረች ቤተክርስቲያናችን፣ የራስዋ ጳጳስና ፓትርያርክ ባልነበረባት ጊዜ በትግል ቆይታ እነሆ በእግዚአብሔር ፈቃድ በራሷ ጳጳሳት መተዳደር ከጀመረች ከአምሳ ዓመታት በላይ አስቆጥራለች። በቅርቡ የተደረገው የእርቅና የአንድነት ጉባኤም ደስ የሚያሰኝ ነው፤ አሁንም አጠናክረን በመቀጠል ቤተክርስቲያናችን በአንድነትና በፍቅር መያዝ አለብን ብለዋል።
በመጨረሻም፡ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ፣ በዋና ሥራ አስኪያጅ ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ ጋብዥነት፣ የካህናት አለቃ የምእመናን ወዳጅ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለዚህ በዓል ያደረሰን ከሁሉ በፊት እርሱ ይክበር ይመስገን ብለው እናንተም እዚህ የተገኛችሁ እግዚአብሔር ይባርካችሁ ብለዋል። በዛም ሰፋ ያለ አጥንትን ሰርስሮ የሚገባ ት/ት ሰጥተዋል፤ በተለይም የቤተክርስቲያን የወደፊት ዓላማ ምን መሆንና ምን መምሰል እንዳለባት፤ ወደኋላ መለስ ብለን አይተን፣ አሁን የት እንዳለን ተገንዝበን ለወደፊት ምን መሥራት እንዳለብን ራእይን የሚያሰንቅ መልእክት አስተላልፈዋል። ፍልሰተ ምእመናን አንገብጋቢ ጉዳይ መሆኑ ላይ ያተኮረው ንግግራቸው፣ ክስተቱን ለመቀልበስ ቅዱስ ሲኖዶስ መሠረታዊ የሆነ የአስተዳደር፣ የሐዋርያዊ ተልኮ መርሐ ግብር፣ የፋይናንስና የንብረት አያያዝ ሲስተም ዘርግቶ፣ የሰው ኃይል አስተዳደር አዘምኖ፣ሙሉ የምእመናን ጥያቄ የሚመልስ መሠረታዊ የመልካም አስተዳደር ለውጥ ለማምጣት በቆራጥነት መሥራት አለበት። ይህንም የመሰለ ለውጥ እውን ለማድረግም የቤተክርድቲያኒቱን ምሁራን በሚገባ ማሳተፍና መጠቀም አለበት። የሃይማኖታቸው ፍቅር እንደ እሳት እያቃጠላቸው ስሕተቶች እንዲታረሙ ሐሳብና አስተያየት ለሚያቀርቡ፣ ቤተክርስቲያንን እንርዳ እናግዝ፣ እናገልግል የሚሉት ምሁራንና ሊቃውንትም ገንቢ ሐሳባቸውንና ዕውቀታቸውን ተቀብለን እናስተናግዳቸው ካሉ በኋላ በዚህ መንፈስ መግባባት ከተፈጠረ እየበዙ የመጡ ጩኸቶች ወደ ዝማሬ የማንለውጥበት ምክንያት አይኖርም በማለት አባታዊ ምክራቸውናን ለየት ያለ የወደፊቱ ራእያቸውን የሚያንጸባርቅ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።