በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ሰንበት ትምህርት ቤት ምልአተ ጉባኤ ተካሄደ

የካቲት 23 ቀን 2011 ዓ.ም በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ሰንበት ትምህርት ቤት አባላት መካከል የፍቅር አገልግሎት እንዲዳብር ለመወያየት ታስቦ ምልአ ተጉባኤ ተካሂዷል፡፡

አስደናቂውና ታሪካዊው የካቴድራሉ ሕንፃ (ፍቶ ፋይል)

ጉባኤው የተጠራበት ዓላማ በተሰጣቸው እውቀት፣ ጊዜና ገንዘብ ውብና ማራኪ የሆነ አገልግሎት እያበረከቱ ያሉ የሰንበት ትምህርት ቤታችን አባላትን አንድነት አስጠብቆ የነበረውና ያለውን አገልግሎት አጠናክሮ ለማስቀጠል ነው፡፡

በጉባኤው ከመንበረ ፓትርያርክ የሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ መምሪያ እና ከሰበካ ጉባኤ ጽ/ቤቱ የተላኩ ደብዳቤዎች ተነበው የሰንበት ትምህርት ቤቱ ወቅታዊ ሁኔታ ከተብራራ በኋላ  በተቀመጠው የውይይት መርሃ ግብር መሰረት፡-

ምልአተ ጉባኤው በስፋትና በጥልቀት ከተወያየ በኋላ ሰንበት ትምህርት ቤቱ በዘመናት ብዙ ፈተናዎችን ተወጥቶ ብዙ ውጣውረዶችን አልፎ አሁን ያለበት ደረጃ የደረሰ፣ ብዙ ባለ ትሩፋት አባላትን ያፈራ እና የራሱ የሆኑ አወንታዊ መገለጫ ባሕርያት ያለው ቀዳማዊ  ሰንበት መሆኑ ተገልጾ  የሚከተሉት የመፍትሔ ሃሳቦች በጋራ ተቀምጠዋል፡፡

  1. አገልግሎት ድርድር የማያስፈልገው  የሰንበት ትምህርት ቤታችን መንፈሳዊ ግዴታ ስለሆነ ተጠናክሮ እንዲቀጥል፣
  2. ከማደራጃ መምሪያው እና ከካቴድራሉ በመጡ ደብዳቤዎች ላይ ምልዓተ ጉባኤው መስማቱ እንዳለ  ሆኖ  በጊዜአዊ አመራሩ በኩል ጥያቄ ከሚያነሱ ወንድሞች ጋር  ውይይት እንዲያደረግ፣
  3. ለብዙ ዘመናት  የዳበረው የእርስ በርስ ግንኙነት በወቅታዊ ሁኔታዎች መሸርሸር ስለሌለበት የነበረውን እና ያለውን የእርስ በርስ ግንኙነት አጠናክሮ ማስቀጠል ተገቢ ነውና ጊዜያዊ አመራሩ የእርስ በርስ ግንኙነት  ላይ ጠንከር ያለ ሥራ ቢሠራ፣
  4. ቃለ ዓዋዲው ስለሰንበት  ትምህርት ቤትእንቅስቃሴ ምን እንደሚል ተብራርቶ አማራጭ በሆነው የማስተማርያ መንገድ ትምህርት ቢሰጥ የሚሉ ነበር፡፡
የካቴድራሌ ሰንበት ት/ቤት በአገልግሎት ላይ (ፍቶ ፋይል)

በአጠቃላይ ውይይቱ የተያዘለትን ዓላማ እና ግብ የመታ እና የብዙሃኑን ሃሳብ የሰበሰበ፣ በአካል ያልተገኙ በተለይም ከሀገር ውጭ ያሉ አባላት ደስታቸውን እና ገንቢ አስተያታቸውን የሰጡበት እና አባላቱ ለአገልግሎት ያላቸውን ተቆርቋሪነት ያሳዩበት ነበር፡፡

ልዑል እግዚአብሔር ሰንበት ትምህርት ቤታችን እና አባላቱን ሁሉ በዘለዓለማዊ አባትነቱ፣ በማያልቅ ቸርነቱ እና በመለኮታዊ ጥበቃው ይጠብቅልን፡፡