በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል በክቡር ቢተወደድ ባሕሩ አብርሐም G+2 የአብነት ት/ቤት የመሠረት ድንጋይ ተቀመጠ

ኅዳር 11/2012 ዓ.ም ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት፣ብጹዕ አቡነ መልከጼዴቅ የጉራጌ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣ብፁዕ አቡነ ፊሊጶስ የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ የበላይ ኃላፊና የደቡብ ኦሞ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣ብጹዕ አቡነ እንድርያስ፣ክቡር ቢተወደድ ባሕሩ አብርሐም እና ቤተ ሰዎቻቸው ፣የካቴድራሉ አስተዳር ሠራተኞች እና ልማት ኮሚቴ አባላት፣የካቴድራሉ ማኅበረ ካህናት፣የካቴድራሉ ሰንበት ት/ቤት አባላትና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት የመሠረት ድንጋይ ተቀምጧል፡፡

ይህ መሠረት ድንጋይ የተቀመጠበት የአብነት ት/ቤት ቀደም ሲል እውቁ የመጽሐፍ መምህር የነበሩት መጋቤ ሚስጢር ልሣኑ ብሩ ለዘመናት መጽሐፍ ሲያስተምሩበት የነበረና ብዙ ሊቃውንት የተማሩበት ቦታ ነው፡፡

በካቴድራሉ 6 የአብነት መምህራን ቢኖሩም የሚያሰተምሩበት ምቹ የሆነ ቦታ ባለመኖሩ ለዘመናት ሲቸገሩ መኖራቸው ሊቃውንቱ፣የሊቃውንቱ ደቀ መዛሙርትና የካቴድራሉ ማኅበረ ካህናት የሚያወቁት ሀቅ ነው፡፡ እነሆ ዛሬ የሊቃውንቱን ጸሎት በሥላሴ ፊት ደርሶ በአንድ በጎ አድራጊ ባለፀጋ በቢተወደድ ባሕሩ አብርሐም በካቴድራሉ ግቢ ውስጥ ሊሠራ ለታሰበው ዘመናዊ G+2 የአብነት ት/ቤት በብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት የመሠረት ድንጋይ ተጥሏል፡፡

የአብነት ት/ቤቱ እንዲሠራ ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ለልዩ ሀገረ ስብከታቸው ለአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት በሰጡት አባታዊ መመሪያ መሠረት ነው የመሠረት ድንጋዩ የተጣለው፡፡

ቅዱስነታቸው በመርሃ ግብር ግቡ ላይ ተገኝተው ባስተላለፉት መልእክት ይህን የመሰለ ሊቃውንት የሚያፈራ የአብነት ት/ቤት መሥራት ቤተ ክርስቲያኒቱ ለምትሰጠው ሁለንተናዊ አገልግሎት የላቀ አስተዋፅኦ ስላለው ሌሎች በጎ አድራጊዎችም እንደ ቢተወደድ ባሕሩ አብርሐም በቤተ ክርስቲያን የማይጠፋ አሻራቸው ሊያስቀምጡ ይገባል ብለዋል፡፡

የአብነት ት/ቤቱ እጅግ ዘመናዊ የሆነ ሁለገብ G+2 ሕንፃ ሲሆን ከ15 እስከ 16 ሚሊዮን ብር እንደሚፈጅ ክቡር ቢተወደድ ባሕሩ አብርሐም ተናግረዋል፡፡
ሙሉ ሪፖርቱን እንደ ደረሰን እናቀርባለን፡፡

የካቴድራሉ ዋና አስተዳዳሪ ሊቀ ሥልጣናት አባ ገ/ዋህድ ገ/ኪዳን ያቀረቡትን ሙሉ ሪፖርት እንደሚከተለው ቀርቧል፡

ኅዳር 11 ቀን 2012 ዓ.ም

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን፡፡


ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአኵሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት፣ ብፁዕ አቡነ መልከ ጼዴቅ በአዲስ አበባ ሀ/ስብከት የብፁዕ ወቅዱስ ረዳት ሊቀ ጳጳስ እና የጉራጌ ሀ/ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣ ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት፣ የተከበሩ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና አስኪያጅ መ/ር አባ ሞገስ ኃ/ማርያም፣ የተከበራችሁ የጠቅላይ ቤተ ክሕነት፣ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት፣ የአራዳና ጉለሌ ቤተ ክሕነት ክ/ከተማ የመምሪያ ኃላፊዎች፣ ክቡር ቢትወደድ ባህሩ አብርሃም፣ ክቡራን የካቴድራሉ የሰበካ ጉባዔ እና የልማት ኮሚቴ አባላት፣ የአስተዳደር ኃላፊዎች፣ ማኅበረ ካሕናት፣ የሰንበት ት/ቤት አባላትና ልዩ ልዩ ሠራተኞች ፣ የተከበራችሁ እንግዶች፣ ብፁዕ ወቅዱስ አባታችን በዛሬዋ ዕለት በዚህ ታላቅ ካቴድራል በበጎ አድራጊው ክቡር ቢትወደድ ባህሩ አብርሃም አማካይነት ሊሠራ ለታሰበው የአብነት ትምህርት ቤት ሕንፃ ግንባታ የመሠረት ድንጋይ ለማስቀመጥና አባታዊ ቡራኬና መመሪያ ለመስጠት ስለተገኙልን በካቴድራሉ ሰበካ ጉባዔ ጽ/ቤት ስም ከፍተኛ ምስጋናናችንን እናቀርባለን፡፡
“ግበር ለገብርከ በከመ ምሕረትከ ወምህረኒ ኵነኔከ ገብርከ አነ አለብወኒ ወአእምር ስምዓከ ጊዜ ገቢር ለእግዚአብሔር ” መዝ ፻፲፰÷፻፳፬-፻፳፮ “ለባሪያህ እንደ ምሕረትህ አድርግ ሥርዓትህን አስተምረኝ እኔ ባርያህ ነኝ እንዳስተውል አድርገኝ ምስክርህንም አውቃለሁ ለእግዚአብሔር የሥራ ጊዜ አለው” መዝ ፻፲፰÷፻፳፬-፻፳፮


በዛሬው ዕለት የመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ሰበካ ጉባኤ ጽ/ቤት ለብዙ ዓመታት በካቴድራሉ ቅጽረ ግቢ ውስጥ የአብነት ትምህርት ቤት ሕንፃ ግንባታ ለማስገንባት በከፍተኛ ሁኔታ እየተንቀሳቀሰ ባለበት ጊዜ መዝሙረኛው ቅዱስ ዳዊት “ለእግዚአብሔር የሥራ ጊዜ አለው” እንዳለው በተለያዩ አድባራትና ገዳማት በተለይም በጉራጌ ሀገረ ስብከትና በተለያዩ ሀገረ ስብከት በገንዘባቸው በከተማና በገጠር ያሉ ታላላቅ አብያተ ክርስቲያናትን በማሳነጽና የአብነት ትምህርት ቤት ሕንጻዎችን በማስገንባት እንዲሁም በገንዘባቸው መምህራንን በመቅጠር ብዙ ደቀመዛሙርትን ለቤተ ክርስቲያኒቱ በማፍራት ላይ የሚገኙት የቤተ ክርስቲያኒቷ የቁርጥ ቀን ልጅ የሆኑት ክቡር ቢትወደድ ባህሩ አብርሃም “እግዚአብሔር ሆይ ከታናሽነቴ ጀምረህ መታመኛዬ ነህና ከማሕፀን ጀምሮ በአንተ ተደገፍሁ ከእናቴም ሆድ ጀምሮ አንተ መሸሸጊያዬ ነህ ሁልጊዜም ዝማሬዬ ለአንተ ነው” መዝ ፸÷፭-፯ የሚለውን የመጽሐፍ ቃል መሠረት በማድረግ ሃይማኖታዊና ሀገራዊ ኃላፊነታቸውን ለመወጣት በማሰብ በዚሁ ታላቅ ካቴድራል አሁን በህይወተ ሥጋ የሌሉ የወንድማቸውን የክቡር በኩረ ትጉሃን ከበደ ተካልኝን አርዓያ በመከተል በካቴድራሉ ቅጽረ ግቢ ውስጥ ደረጃውን በጠበቀ መልኩ የሙዝየም አገልግሎት የሚሰጥ ሕንፃ ገንብተው ለካቴድራሉ እንዳስረከቡት ሁሉ እርሳቸውም ለቤተ ክርስቲያኗ እጅግ አስፈላጊ የሆነውን እና የካቴድራሉ ሰበካ ጉባዔና ልማት ኮሚቴ ሲጨነቅበት የነበረውን የአብነት ት/ቤት ሕንፃ ግንባታ በአጋዕዝተ ዓለም ሥላሴ መልካም ፈቃድ በራሳቸው ሙሉ ወጪ B+G+2 ለማሳነጽ ቃል በገቡልን መሠረት እና ቅዱስነትዎም ይህንን በጎ ተግባር በመደገፍ በሀገረ ስብከቱ በኩል ፈቃድ እንዲሰጥ በሰጡት መመሪያ መሠረት በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት በኩል የአብነት ት/ቤቱ እንዲሠራ በመፈቀዱ እነሆ በዛሬዋ ዕለት በቅዱስነትዎ የአብነት ት/ቤት ሕንፃ ግንባታ የመሠረት ድንጋይ ለማኖር በካቴድራሉ ስለተገኙልን ቅዱስነትዎን በሰበካ ጉባዔው ጽ/ቤት ስም እጅግ እጅግ አድርገን እናመሰግናለን፡፡

የቅዱስነትዎ ቡራኬ ይድረሰን፡፡