በሰሜን አዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የስብከተ ወንጌል ማስፋፊያ የአንድነት ጉባኤ መርሃ ግብር ተጀመረ
በመ/ር ዘሩ ብርሃኔ
መጋቢት 8/005 ዓ.ም በአዲስ አበባ አህጉረ ስብከት መሰብሰቢያ አዳራሽ ከጠዋቱ 3.00 ሰዓት ጀምሮ በስብከተ ወንጌል ማስፋፊያ መርሃ ግብር ላይ ስብሰባ የተካሄደ ሲሆን በመርሀ ግብሩ ላይ ብፁዕ አቡነ ዳንኤል የሰሜን እና የምስራቅ አዲስ አበባ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ፤ክቡር መልአከ ሰላም ዳዊት ያሬድ የሰሜን አዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅን ጨምሮ ሁሉም የሀገረ ስብከቱ የክፍል ሃላፊዎቹና ሠራተኞች እንዲሁም የገዳማትና አድባራት አስተዳዳሪዎች ፣ የደብር ፀሀፊዎች፣ ቁጥጥሮች፣ ሂሣብ ሹሞችና ሰባኪያነ ወንጌል በስብሰባው ላይ ተገኝተዋል፡፡
ስብሰባው በብፁእነታቸው በፀሎት ከተከፈተ በኋላ የመግቢያ ንግግር በብፁዕ አቡነ ዳንኤል የሰሜን እና የምስራቅ አዲስ አበባ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ አማካኝነት የተደረገ ሲሆን በመቀጠልም በክቡር መልአከ ሰላም ዳዊት ያሬድ የሰሜን አዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ አማካኝነት ስለአንድነት ጉባኤው ጠቀሜታ ሰፋ ያለ ማብራሪያ ሰጥተዋል ፡፡
በጉባኤው ላይ በሰሜን አዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሥር ለሜገኙ ገዳማት እና አድባራት የሚከተለው ይዘት ያለው ሴኩላር ደብዳቤ ተበትኗል፡፡
ቀደም ሲል በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሥር የሚገኙት ገዳማት እና አድባራት እንደየ አቅራቢያቸው ተመድበው የአንድነት ጉባኤው በሚካሄድበት ወቅት ካህናትን እና ምዕመናንን ያቀራረበና ለስብከተ ወንጌል መስፋፋት መነቃቃትን የፈጠረ ጉባኤ እንደነበረ ይታወቅል፡፡
ይሁን እንጂ በሀገራችን አንዱ የጀመረውን መልካም ሥራ ተተኪው የማስቀጠል ልምድ ባለመኖሩ የአንድነት ጉባኤው ተቋርጦ ቆይቶ ነበር፡፡ ነገር ግን የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ለ4 አህጉረ ስብከት ከተከፈለ በኋላ የሰሜን አዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ጽ/ቤት የአንድት ጉባኤው ለስብከተ ወንጌል መስፋፋት ካህናቱን እና ምዕመናንን ለማቀራረብና በሃይማኖታቸው ፀንተው እንዲኖሩ አስፈላጊ በመሆኑ የካትት 13 ቀን 2ዐዐ5 ዓ/ም በሀገረ ስብከቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ ሰብሳቢነት በተደረገው የሰባክያነ ወንጌል ጥምር ስብሰባ የአንድት ጉባኤው ጠንካራ ጎን እና ደካማ ጎን በስፋት ውይይት ከተደረገበት በኋላ የአንድነት ጉባኤው ለስብከተ ወንጌል መስፋፋት ጠቃሚ መሆኑ ስለታመነበት በሀገረ ስብከቱ የስብከተ ወንጌል መምሪያ ኃላፊ የሚመራ 7 አባላት ያሉት የስብከተ ወንጌል መስፋፋት አጋዥ ኰሚቴ ተመርጦ ሥራ በመጀመር የአንድነት ጉባኤው እንዲጀመር ገዳማት እና አድባራትን እንደየ አቅራቢያቸው መድቦአል፡፡
በመሆኑም የገዳሙ /የካቴድራሉ/ የደብሩ ሰበካከ ጉባኤ ጽ/ቤት የአንድነት ጉባኤው መጀመሩን አውቆ ለሰብከተ ወንጌል መስፋፋት ቅድመ ዝግጅት በማድረግ አስፈላጊውን ወጪ እንዲመድብ እናስታውቃለን የሚል ነው፡፡ በዚሁም መነሻነት የሰሜን አዲስ አበባ ገዳማትና አድባራት በ6 ምድብ ተመድበው/ተከፍለው በየተራ የአንድነት ጉባኤውን ሊያካሂዱ እንደሚችሉ ሁሉም በደስታ ተቀብለውታል፡፡
ምድብ 1
1. መንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል
2. ታዕካ ነገስት በዓታ ለማርያም ገዳም
3. መንበረ መንግስት ቅዱስ ገብርኤል ገዳም
4. ቀበና ምሥራቀ ፀሐይ መድኃኔ ዓለም ቤ/ክ
5. ቀበና ቤዛዊት ዓለም ኪዳነ ምህረት ቤ.ክ 6. ደብረ ዕንቁ ልደታ ለማርያም ቤ/ክ
ምድብ 2
1. መንበረ ፓትርያርክ ቅ/ቅ/ማርያም ገዳም
2. መንበረ ልዑል ቅ/ማርቆስ ቤ/ክ
3. ምስካየ ኅዙናን መድኃኔ ዓለም ገዳም
ምድብ 3
1. ገነት ጽጌ ቅ/ጊዮርጊስ ቤ/ክ
2. ደብረ ሰላም ቀጨኔ መድኃኔ ዓለም ቤ/ክ
3. ደበረ ነጎድጓድ ቅ/ዮሐንስ ቤ/ክ
ምድብ 4
1. ደብረ ሲና ቅ/እግዚአብሔር አብ ቤ/ክ
2. መንበረ ክብር ደብረ ታቦር ቅዱስ ሚካኤል ገዳም
3. ደብረ ጎልጎታ ድል በር መድኃኔ ዓለም ቤ/ክ
ምድብ 5
1. እንጦጦ መንበረ ንግስት ቁስቋም ቤ/ክ
2. እንጦጦ መንበረ ስብሐት ቅ/ሥላሴ ቤ/ክ
3. እንጦጦ ሐመረ ኖኅ ኪዳነ ምህረት ገዳም
ምድብ 6
1. ገነተ ኢየሱስ ወገነተ ማርያም ቤ/ክ
2. መካነ ሕይወት አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ቤ/ክ
3. አንቀጸ ምህረት ቅ/ሚካኤል ቤ/ክ
4. ደብረ ፀሐይ ፈረንሳይ ቅ/ጊዮርጊስ ቤ/ክ
5. ምስራቀ ፀሐይ ጉራራ ኪዳነ ምህረት
በቀጣይ የዚህ ዓይነት የአንድነት ጉባኤ መርሃ ግብር በሁሉም የአዲስ አበባ አህጉረ ስብከት ገዳማትና አድባራት ሊካሄድ እንደሚችል ለማወቅ የተቻለ ሲሆን እኛም በሰዓቱና በወቅቱ እየተገኘን ስለ አንድነት ጉባኤው የትና መቼ እንዲሁም እንዴት ተከበረ የሚለውን በጽሁፍ፤በድምፅና በምስል በሰፊው የምንዘግብ መሆኑን ከወዲሁ ለመግለጽ እንወዳለን፡፡
ቸር ያቆየን::