በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል መሰናዶ እና 2ኛ ደረጃ ት/ቤት ከወላጆች ጋር በመማር መስተማር ሄደት ላይ ውይይት ተካሄደ
በመ/ር ዘሩ ብርሃኔ
የመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል 1ኛና 2ኛ ደረጃ ዘመናዊ ት/ቤት ከመዋዕለ ህጻናት እስከ የ2ኛ ደረጃ እና መሰናዶ ት/ቤት ደረጃ ያለውን ት/ቤት አቋቁሞ ተማሪዎች መንፈሳዊና ሥጋዊ ጥበብ እንዲማሩ በማደረግ ላይ ነው፡፡ ሥጋዊ ጥበብ የሚባለውም በቀደሙት አባቶቻችን አባባል ቀለም በጥብጦ፣ ብራና ፍቆ፣ ብዕርን ቀርፆ፣ መፃህፍትን መፃፍ፣ መጠረዝና መደጎስ እንዲሁም እርሻ ማረስ፣ ንግድ መነገድና የመሳሰለ ሲሆን እንደ ዘመኑ አባባል ደግሞ የቀለም ት/ቤቶችን አቋቁሞ /ከፍቶ በዘመኑ ቴክኖሎጂ በመታገዝ እስከ ዮኒቨርሲቲ ያለውን ትምህርት መስጠት ማለት ነው፡፡ በመሆኑም የመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል 1ኛና 2ኛ ደረጃ ዘመናዊ ት/ቤት መስከረም 14 ቀን 1955 ዓ.ም. ተቋቋሞ የማስተማር ሥራውን የጀመረው የመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ት/ቤት በወቅቱ የህብረተ ሰቡ የመማር ፍላጎትና የተማሪዎች ቁጥር እየጨመረ በመሄዱ መጠነኛ የሆነ ክፍያ እንዲከፍሉና የተሻለ የትምህርት አገለግሎት እንዲያገኙ ከህብረተሰቡ ጥያቄው በመቅረቡ በ1962 ዓ.ም. መጠነኛ ክፍያእንዲከፈል ተወስኖ ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ትምህርት ቤቱ በክፍያ ማስተማር የጀመረ ሲሆን የት/ቤቱ ፈላጊ ሕብረተሰብ ከጊዜ ወደ ጊዜ ቁጥሩ እየጨመረ በመሄዱና ማስተናገድ ከሚችለው በላይ በመሆኑ የተማሪ ቅበላ የሚከናወነው በየዓመቱ ኮሚቴ እየተቋቋመ ኮሚቴው በሚያወጣው የመቀበያ መስፈርት አማካይኝነት እንደ ነበረ የታሪክ መዛግብት ያስረዳሉ፡፡ በወቅቱ የተማሪ ቁጥር እያደገ ሲሄድ አሁን 1ኛ ደረጃ ት/ቤት ያለበትን ቦታ ይዞ ከ1962 ዓ.ም. ጀምሮ 12ኛ ክፍል በዚሁ ት/ቤት የብሔራዊ ፈተና ማስፈተን የጀመረ ሲሆን አሁንም ከመቸውም በተጠናከረ መልኩ በቴክኖሎጂ እና ብቁ በሆነ የሰው ኃይል በመታገዘ የመማር ማስተማሩ ሂደት ቀጥሎ በየዓመቱ ተማሪዎችን ተቀብሎ በማስፈተን በከፍተኛ ውጤት ወደ ዩኒቨርሲቲ እንዲገቡ በመድረግ ላይ ላይ ይገኛል፡፡ በመሆኑም ዛሬ የመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ት/ቤት በሦስት የትምህርት ዕርከኖች ወይም ደረጃዎች ተደራጅቶ በርካታ ወጣቶችን እያስተማረ ይገኛል፡፡ እነዚህም ት/ቤቶች፡- 1. አፀደ ህፃናት 2. የ1ኛ ደጃ ት/ቤት 3. የ2ኛ ደረጃ እና መሰናዶ ት/ቤቶች ናቸው፡፡ በአሁኑ ሰዓት በ1996 ዓ.ም. አዲስ ባሠራው ህንፃ የ2ኛ ደረጃና ኮሌጅ መሰናዶ ተማሪዎችን ተቀብሎ እያስተናገደ ይገኛል፡፡ት/ቤቱ ትምህርት ሚኒስተር ያወጣውን ሥርዓተ ትምህርት በመከተልና ባለ 3 ፎቅ የራሱ ህንፃ ገንብቶ ት/ቤቱን ከ2ኛ ደረጃ ት/ቤት ወደ ተሻለ ደረጃ ላይ እንዲደርስ ከፍተኛ ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛል ፡፡በመሆኑም ት/ቤቱ በአሁኑ ሰዓት ከመዋዕለ ሕጻናት እስከ ኮሌጅ መሰናዶ ድረስ ከ2,500 ያላነሱ ተማሪዎችን እየተቀበለ ጥራቱን የጠበቀ ትምህርት በመስጠት ላይገኛል፡፡
ከትምህርቱ ጥራትም የተነሳ ተማሪዎች በሁሉም ብሔራዊ ፈተናዎች ከፍተኛ ውጤት እያመጡ ከደረጃ ወደ ደረጃ እያለፉ ስለመጡ የመንበረ ጸበዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ት/ቤት በተገልጋዩ ህብረተሰብ ዘንድ በአዲሰ አበባ ከሚገኙ እውቅ ት/ቤቶች አንዱ ለመሆን በቅቷል፡፡በዚህም ምክንያት ት/ቤቱ በአሁኑ ጊዜ ለህብረተሰቡ እየሰጠ ያለው ት/ት ካቴድራሉን ብቻ ሳይሆን የኢ.ኦ.ተ.ቤ.ክርስቲያንም የሚያኮራና የሚያስመሰግን ት/ቤት እየሆነ መጥቷል፡፡ በመሆኑም የመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል መሰናዶ እና 2ኛ ደረጃ ት/ቤት እንደ ቀድሞው ሁሉ ደረጃውን ጠብቆ የተሻለ ሥራ ለመስራት ታስቦ በ15/07/05 ዓ.ም ከተማሪ ወላጆች ጋር ለ3ኛ ጊዜ ውይይት የተደረገ/ያካሄደ ሲሆን ስብሰባውን የመሩት ክቡር ሊቀ ሥልጣናት አባ ገ/ሥላሴ በላይ የመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ዋና አስተዳዳሪ ሲሆኑ የካቴድራሉ ትምህርት ቤት ዋና ርዕሰ መምህርና ምክትል ርዕስ መምህር በስብሰባው ላይ ተገኝተዋል፡፡በአጠቃላይ ከ1000 በላይ የሚሆኑ የተማሪ ወላጅ በስብሰባው ላይ የተገኙ ሲሆን በመማር መስተማሩ ሂደት ላይ ሰፋ ያለ ውይይት ተካሂዷል፡፡ ክቡር ሊቀ ሥልጣናት አባ ገ/ሥላሴ በላይ እንደ ገለፁት ተማሪዎች የተወሰነ የማርፈድና ከክላስ የመቅረት ችግር አልፎ አልፎ እንደ ሚታይ ጠቁመው ይህ ሊስተካከል የሚችለው ደግሞ ት/ቤቱ እና ወላጆች ባላቸው ኃላፊነት የበኩላቸውን ግዴታ ሲወጡ ብቻ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ በአሁኑ ሰዓት ት/ቤቱ ከመቸውም በላይ ከወላጆች ጋር እየተመካከረ እየሰራ መሆኑን ገልፀው ወላጆች ልጆቻቸውን በአግባቡ ሊከታተሉና ሊቆጣተሩ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡ቅዳሜ በሚሰጠው የማጠናከሪያ ት/ት ላይ ተማሪዎች ዩኒፎርም ሳይለብሱ እየመጡ በተወሰኑ ተማሪዎች ላይ የተወሰነ ችግር እንደነበር ገልፀው ቀደም ሲል ከወላጆች ጋር በተደረገው ስምምነት ሁሉም ተማሪዎች ቅዳሜ ለማጠናከሪያ ትምህርት ሲመጡ ዩኒፎርማቸውን እንዲለብሱ በመደረጉ ሙሉ በሙሉ ችግሩ መቀረፉን ጨምረው ገልፀዋል፡፡ ከዚህ ስብሰባ በኃላም የማርፈዱ ችግር ሙሉ ለሙሉ እንደሚቀረፍ እምነታቸው መሆኑን ተናግረዋል፡፡በቀጣይም በተመሳሳይ ሁኔታ እንደተለመደው ከወላጆች ጋር ስብሰባ ሊኖር እንደሚችል ጠቁመው የካቴድራሉ ት/ቤት ለሚያደርገው ጥሪ ተባባሪ እንዲሆኑ አሳስበዋል