የርክበ ካህናት የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ስብሰባ ተጠናቀቀ

00001

ከግንቦት 21 ቀን ጀምሮ እስከ ግንቦት 30/ 2005 ዓ.ም. ድረስ ሲካሔድ የሰነበተው የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ለቤተ ክርስቲያኗ አስፈላጊ ናቸው ያላቸውን ውሳኔዎች በማሳለፍ ተጠናቀቀ፡፡

 

 

 

 

 

 

በዚህም መሠረት የሚከተሉትን ጠቅለል ያሉ ውሣኔዎች ተላልፈዋል፡፡

 የቅዱስ ሲኖዶስ ሙሉ መግለጫ

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!

በፍትሕ መንፈሳዊ አንቀጽ 5 ቁጥር 164 ላይ ከበዐለ ትንሣኤ በኋላ በሃያ አምስተኛው ቀን የቅዱስ ሲኖዳስ ጉባኤ እንዲካሔድ በተደነገገው ቀኖና ክርስቲያን መሠረት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ከግንቦት 21-30 ቀን 2005 ዓ.ም ተካሒዷል፡፡

ይህ ጉባኤ የርክብ ካህናት ጉባኤ ተብሎ የሚታወቅ ሲሆን ከላይ በተጠቀሰው ቀኖና ቤተ ክርስቲያን እንደተገለው ብፁዓን ሊቃነ ጰጳሳት በቤተ ክርሲቲያን ያለውን አጠቃላይ መንፈሳዊ ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኀበራዊ ጉዳዮችን በማየት በመንፈስ ቅዱስ መሪነት ታላላቅ ውሳኔዎችን የሚወስኑበት ዓቢይ ጉባኤ ነው፡፡

ቅዱስ ሲኖዶስ በቤተ ክርስቲያናቸን ውስጥ ያሉትን ወቅታዊና ነባራዊ ጉዳችን ለመመርመርና ለመገምገም ባለው ሐዋርያዊ ኃላፊነት ለቤተክርስቲያን መንፈሳዊ ተልዕኮ አፈጻጸም እንቅፋት ናቸው ብሎ ያመነባቸውን ጉዳዮች በአጀንዳ ቀርጾ፣በስፋትና በጥልቀት ተወያይቶ ውሳኔ ሰጥቶባቸዋል፡፡ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን በምድር ላይ ያለች የእግዚአብሔር መንግሥት ማዕከል፣በባሕርይዋም ንጽሕትና ቅድስት ብትሆንም ኃጢአትና ስሕተት በነገሠበት ዓለም ያለች በመሆንዋ ከእርስዎ መሠረታዊ ባሕርይ ጋር የማይስማሙ ተግባራት እንዳይጋቡባት የመጀመሪያው ጥበቃ በብፁዓን ሊቀነ ጰጳሳት ላይ ያረፈ ነው፡፡ በተለይም የአሁኑ ዓላማችን ጥበብ ባፈራው የአሠራር ዕውቀት በየቀኑ በለውጥ ጎዳና በሚራመድበት ጊዜ ቤተ ክርስቲያናችንም ከዓለሙ በተሻለና በበለጠ በመንፈሳዊ በአእምሮአዊ ጥበብ ሕዝበ ክርስቲያኑን መምራት፣ማስተማርና ማገልገል ይጠበቅባታል፡፡ በቤተ ክርስቲያናችን እነዚህ የተቀደሱ ተግባራት በሥራ ለመተርጎም ወቅታዊ እንቅፋት ሊሆኑ የሚችሉ ነገሮች ምን ምን ናቸው?በማለት ቅዱስ ሲኖዶስ በጥልቀት ተመልክቶአል፡፡ በዚህ መሠረት ጉባኤው ብዙ ውይይት ካደረገ በኋላ የሚከተሉትን ዓበይት ውሳኔዎች አሳልፎል፡፡

1. በየሥራ ዘርፉ እየተከሠተ ያለው የመልካም አስተዳደርን ችግር በተለይም ብልሹ አስተዳደርና አሠራር፣ዘመኑን ያልዋጀና ጥራት የጎደለው የፋይናስ አያያዝ፣እንዲሁም ለሙስናና ለብክነት የተጋለጡ አሠራሮች ሁሉ ወሳኝ በሆነ መልኩ ለመቅረፍና ለማድረቅ፣ከዚህም ጋር ቤተ ክርስቲያናችን በመሪ እቅድ መሥራት የምትችልበትን አሠራር ለመቀየስ፣ ቅዱስ ሲኖዶስ፡- ብፁዓን ሊቃናት ጳጰሳት፣ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን፣ምሁራን ምእመናን የሚገኙበት ዓቢይ ኮሚቴ ተቋቁሞ ጉዳዩን ለማጣርትና ሥራውን እንዲቀጥል ተስማምቶ በአንድ ድምጽ ወስኖል፡፡

2. የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ለሌሎች አህጉረ ስብከት በመልካም አስተዳደርና በፋይናስ አያያዝ፣እንዲሁም በስብከተ ወንጌልና በአገልግሎት አሰጣጥ ለሌሎች አሁጉረ ስብከት በሞዴልነት የሚጠቀስ ሀገረ ስብከት መሆን ስለሚገባው በአንድ ሀገረ ስብከት፣ በአንድ የቅዱስ ፓትርያርክ ረዳት ሊቀ ጳጰስ እንዲመራ፣ እንደዚሁም በመልካም አስተዳደር ፣በፋይናንስ፣ አያያዝና በሰው ኃይል አመዳደብ የሕግ የበላይትን አክብሮ እንዲሠራ አስፈፈላጊውን ክትትል ሁሉ በቋሚ ሲኖዶስ በመንበረ ፓትርያርኩ ጥልቅ ክትትል እንዲደረግ ፣ 3. የቤተ ክርስቲያናችን የሕይወት ምንጭ የሆነውን ስብከተ ወንጌል ትምህርት በሰው ኃይል ፣በሚዲያም ጭምር እየታገዘ በመላው ዓለም ላሉ የቤተ ክርስቲያናችን ተከታዮች ትምህርቱን በጥራትና በጥልቀት ይሰጥ ዘንድ አስፈጻሚው አካል ጠንከር ያለ ሥራ እንዲሠራ ቅዱስ ሲኖዶሱ በሙሉ ድምጽ ወስኗል፡፡ የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት ዋና ሥራ አስኪያጅና የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ፀሐፊ ምርጫ በየ3 ዓመቱ እንዲካሄድ ቤተ ክርስቲያን ባስቀመጠው ድንጋጌ መሠረት ብፁዕ አቡነ ማቴዎስ፤ የወላይታ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጰስ፤የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት ዋና ሥራ አስኪጅ ፤ብፁዕ አቡነ ሉቃስ፤ የሰቲት ሑመራ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጰስ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ አድርጎ ሲኖዶሱ መርጦአቸዋል፡፡

4. ብፁዕ አቡነ እስጢፋኖስ የጅማ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጰስ በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ ረዳት ሊቀ ጳጳስ ሆነው እንዲሠሩ፣እንደዚሁም የምስራቅና ሰሜን አዲስ አበባ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጰስ ብፁዕ አቡነ ዳንኤል በኢሩሳሌም የኢትዮጵያ ገዳማት ሊቀ ጳጰስ ሆነው እንዲሰሩ ቅዱስ ሲኖዶስ ወስኖአል፡፡

5. በመካከለኛው ምስራቅና በሎሎች የዓለም ክፍሎች ለሥራ ፍለጋ በሕገ ወጥ መንገድ በሚሄዱ ልጆቻችንና ወገኖቻችን ላይ እየደረሰ ያለውን ዘግናኝ ድርጊት ለማስቆም መንግሰት እያደረገ ያለው ጥረት ቤተ ክርስቲያናችን በሙሉ ልብ እንደምትደግፈውና ለስኬቱም የበኩሏን እንደምትወጣ፣ለዚህም በየደረጃው ያሉ መምህራን ፣ካህናትና ሰባኪያን ሁሉ የዚህን ጎጂነት ደጋግመው በማስረዳትና በማስተማር ሕዝቡ ግንዛቤ እንዲኖረው ጠንክረው እንዲስተምሩ ቅዱስ ሲኖዶስ መመሪያ ሰጥቷል፡፡

6. የሀገራችን ሕዝቦች ከድህነትና ከኋላ ቀርነት ተላቀው መካከለኛ ገቢ ካለቸው ሀገሮች እኩል ለማስለፍ በሚደረገው ሁለንተናዊ የልማት ተግባር ቤተ ክርስቲያናችን ከሕዝቡና ከመንግስት ጎን በመሆን የሚጠበቅባትን ሁሉ እንደምታደርግ ቅዱስ ሲኖዶስ አረጋግጧል፡፡

7. ኢትዮጵያ ሀገራችን በሀገር ውስጥ፣ በምስራቅ አፍሪካ፣ በመላ አፍሪካ ከዚያም በመላው ዓለም ሰላም እንዲሰፍን፣ የሰው ልጅ እኩልነትና መብት እንዲከበር ፣ፍትሐዊ የሆነ የሀብት አጠቃም እንዲኖር ፣የአየር መዛባትን ለመቋቋም የአረንጓዴ ልማት ሀብት እንዲስፋፋ የምታደርገው ያላሳለሰ ጥረት ቅዱስ ሲኖዶስ በእጅጉ እያደነቀ የሀገሪቱን መልካም ዝናና በጎ ገጽታ ለመጠበቅ የበኩሉን ጠንክሮ እንዲሰራ አረጋግጦአል፡፡

8. በሀገራችን የዕድገት ሒደት ክፍተኛ ሚና ይጫወታል ተብሎ በመገንባት የሚገኘው ታላቁ የህዳሴ ግድብ ሥራው ተጠናቆ ጥቅም ላይ እስኪውል ድረስ ቤተ ክርስቲያናችን አስፈላጊውን ድጋፍ ሁሉ እንደማታቋርጥ ቅዱስ ሲኖዶስ ያረጋግጣል፡፡

9. ሀገራችን ኢትዮጵያ በጤናው ዘርፍ የኅብረተ ሰቡን ጤንት ለመጠበቅ በተለይም በሀገር አቀፍ ደረጃ ለእናቶችና ለህፃናት እየተደረገ ያለው ልዩ የጤና እንክብካቤ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ቤተ ክርስቲያናችን ኀብረተሰቡን ከማስተማርና የጉዳዩን ጠቃሚነት ከማስረዳት ባሻገር ለመርሐ ግብሩ መሳካት አስፈላጊውን ድጋፍ እንደምታደርግ ቅዱስ ሲኖዶስ ይገላፃል፡፡

10. ከሀገር ውጪ ከሚገኙ የቤተ ክርስቲያን አባቶች ጋር የተጀመረው የሰላም ውይይት በተለያዩ ምክንያቶች እስካሁን የሚፈለገውን የአንድነት ውጤት ባያስገኝም የቤተ ክርስቲያኛችን አንድነትና ሰላም ለቤተ ክርስቲያናችንም ሆነ ለሀገራችን እንዲሁም ለሕዝባችን ያለው ትርጉም የላቀ መሆኑን ቅዱስ ሲኖዶስ ስለሚገነዘብ ሁኔታዎች ተመቻችተው የሰላም ውይይት እንዲቀጥል ቅዱስ ሲኖዶስ ወስኗል፡፡

11. ቅዱስ ሲኖዳስ የቤተክርስቲያኒቱን መንፈሳዊ፣ኢኮኖሚያዊና ማኀበራዊ ተልእኮ ዘመኑ በሚጠይቀው ጥበብና ዕውቀት እየቃኘ ለሃይማኖት ፣ለሀገርና ለሕዝበ ክርስቲያኑ ማበርከት የሚገባውን ሁሉ በብቃት ለመሥራት ከምንም ጊዜ በላይ የተዘጋጀ መሆኑን ሕዝበ ክርስቲያኑ ተገንዝቦ እርሱም የበኩሉን ሥራ በቅን መንፈስ እንዲወጣ አበክሮ አሳስቧል፡፡

የቤተ ክርስቲያናችን የመጨረሻ ውሳኔ ሰጪ የሆነው ቅዱስ ሲኖዶስ በየጊዜው የሚያስተላልፋቸው ውሳኔዎችና መመሪያዎች ሁሉ ተፈጻሚነት ኖሮአቸው ጥሩ ውጤት ሊያስገኙ የሚችሉት በሁሉም ደረጃና አካባቢ የሚገኙ ቤተ ክርስቲያናችን ካህናትና ምእመናን ለቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ ተግባራዊነት በሙሉ ልባቸው ሲሰለፉ እንደሆነ የቅዱስ ሲኖዶስ እምነት ነው፡፡ስለሆነም ለእናት ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ክብርና ሉዓላዊነት መጠበቅ፣ለሕልውናዋ መቀጠልና ለዕድገትዋ መስፋፋት የሚቆረቆሩ የቤተ ክርስቲያናችን አገልጋዮችና ተከታዮች በሙሉ ቅዱስ ሲኖዶስ የሚያሳልፋቸውን ውሳኔዎችና መመሪያዎች ለመተግበር አስፈላጊውን ትብብር ሁሉ እንዲያደርጉ በአጽንዖት በማሳሰብ ለዐሥር ቀናት ያህል ሲካሄድ የሰነበተውን ጉባኤ ዛሬ ግንቦት 30 ቀን 2005 ዓ.ም. በጸሎት አጠናቅቆአል፡፡

እግዚአብሔር ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችንንና ሀገራችን ኢትዮጵያን ይባርክ፣ይቀድስ ፣አሜን!!!

አባ ማቲያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአኲስም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ግንቦት 30 ቀን 2005 ዓ.ም.

{flike}{plusone}